የዘመናዊው ጦርነት ባሕርይ
የዘመናዊው ጦርነት ባሕርይ
የስደተኞቹ ሠፈር ከጎረቤት የአፍሪካ አገር በድንገት የጎረፉትን 1, 548 ስደተኞች ለማስፈር ሲባል በችኮላ ተዘጋጅቷል። ሰማያዊና ካኪ ቀለም ያላቸው ድንኳኖች በዘንባባ ዛፎች መካከል ተመንጥሮ በተዘጋጀ ጭቃማ መሬት ላይ ተተክለዋል። ኤሌክትሪክም ሆነ አልጋ የለም። የቧንቧ ውኃም ሆነ የመፀዳጃ ቤት የለም። ከባድ ዝናብ ይዘንባል። ስደተኞቹ ድንኳናቸው በጎርፍ እንዳይጥለቀለቅ በቆረጧቸው እንጨቶች የውኃ መውረጃ ቦይ ይቆፍራሉ። ሁለት ዓለም አቀፍ የእርዳታ ድርጅቶች የስደተኞቹን የኑሮ ሁኔታ ለማሻሻል ይጣደፋሉ።
ስደተኞቹ የመጡት አገራቸውን ለበርካታ ዓመታት ሲያወድም ከቆየው የእርስ በርስ ጦርነት ለማምለጥ ሲሉ በአንዲት ያረጀች የዕቃ መጫኛ ጀልባ ላይ ተሳፍረው ነው። ጦርነቱ የሚካሄደው በታንኮች ወይም በቦምብ ጣይ አውሮፕላኖች አልነበረም። ጦርነቱ የጀመረው 150 የሚያክሉ አውቶማቲክ ጠመንጃ የታጠቁ ወታደሮች ሸፍተው ጫካ በገቡ ጊዜ ነበር። ከዚያ በኋላ በነበሩት ዓመታት ወታደሮቹ በርካታ መንደሮችን እየተቆጣጠሩ ከሰላማዊ ሰዎች ግብር ሲቀበሉ፣ አዳዲስ ተዋጊዎችን ሲመለምሉና የተቃወማቸውን ሁሉ ሲገድሉ ቆይተዋል። ውሎ አድሮም አገሪቱን በሙሉ ተቆጣጠሩ።
በስደተኞቹ ሠፈር ከሚገኙት ስደተኞች መካከል ኤስተር የምትባል ወጣት ሴት ትገኛለች። “በሕይወቴ ከገጠመኝ ሁሉ በጣም የከፋ ሁኔታ የደረሰብኝ ባለቤቴ በተገደለ ጊዜ ነበር” ትላለች። “ተኩሰው ገደሉት። ከፍተኛ የሆነ ፍርሃት ነበር። የጩኸት ድምፅ ስትሰማ ሊገድልህ የመጣ ሰው ያለ ይመስልሃል። ጠመንጃ የያዘ ሰው ባየህ ቁጥር የሚገድልህ ይመስልሃል። ዘና ብዬ ያሳለፍኩትን ጊዜ አላስታውስም። በማታ እንቅልፍ መተኛት የጀመርኩት እዚህ ስደተኞች ሠፈር ውስጥ ነው። አገሬ ሳለሁ መተኛት አልችልም ነበር። እዚህ ግን ድብን ያለ እንቅልፍ ይወስደኛል።”
“በዚህ በዝናብ በራሰ ድንኳን ውስጥ?” ሲል የንቁ! ጸሐፊ ጠየቃት።
ኤስተር ሳቀች። “እዚህ ጭቃ ውስጥ ብተኛ እንኳን ከመጣሁበት ቦታ የተሻለ እንቅልፍ ይወስደኛል።”
የአሥር ዓመቱ አምብሮዝ አብዛኛውን ሕይወቱን ያሳለፈው ከቤተሰቦቹ ጋር ከአንዱ የውጊያ አካባቢ ወደ ሌላው በመሸሽ ነው። “ሰላም የሚሰፍንበትንና እንደገና ትምህርት ቤት የምገባበትን ጊዜ ማየት እፈልጋለሁ። አሁን እኮ ትልቅ ልጅ ሆኛለሁ” ይላል።
ክፓና ዕድሜዋ ዘጠኝ ዓመት ሲሆን የሚያማምሩ ቡናማ ዓይኖች አሏት። ትዝ የሚላት ነገር ምን እንደሆነ ስትጠየቅ ወዲያው “ውጊያ! ጦርነት!” ስትል መለሰች።
እነዚህ ሰዎች ለሽሽት የዳረጋቸው ዓይነት ጦርነት ከቅርብ ዓመታት ወዲህ በጣም የተለመደ ሆኗል። አንድ ምንጭ እንደሚለው ከ1990 ወዲህ ከተካሄዱት 49 የሚያክሉ ዋና ዋና ግጭቶች መካከል 46ቱ የተካሄዱት በቀላል መሣሪያዎች ብቻ ነው። የነፍስ ወከፍ መሣሪያዎችን መጠቀም እንደ ሰይፍ ወይም ጦር ጉልበትና የረቀቀ ችሎታ የማይጠይቅ በመሆኑ መደበኛም ሆኑ መደበኛ ያልሆኑ ተዋጊዎች በጦርነት እንዲሰማሩ አስችለዋል። * አብዛኛውን ጊዜ ሕፃናትና በአሥራዎቹ ዓመታት ዕድሜ ውስጥ የሚገኙ ልጆች ተመልምለው እንዲዘርፉ፣ እንዲያቆስሉና እንዲገድሉ ይገደዳሉ።
ከእነዚህ ግጭቶች አብዛኞቹ የሚካሄዱት በተለያዩ አገሮች መካከል ሳይሆን በአገር ውስጥ ነው። በጦር ሜዳዎች በሰለጠኑ መደበኛ ወታደሮች ሳይሆን አብዛኛውን ጊዜ በከተሞችና በመንደሮች ውስጥ ወታደር ባልነበሩ ሰዎች ነው። አብዛኛው ውጊያ የሚደረገው የውትድርና ሥልጠና ባላገኙ ሰዎች በመሆኑ የተለመዱትን የጦር ሜዳ ሕጎች የመከተል ሐሳብ ወደ አእምሯቸው አይመጣም። በዚህም ምክንያት ባልታጠቁ ወንዶች፣ ሴቶችና ሕፃናት ላይ አሰቃቂ ጥቃት ይፈጸማል። በዛሬዎቹ ጦርነቶች ከሚገደሉት መካከል ከ90 በመቶ በላይ የሚሆኑት ሰላማዊ ሰዎች እንደሆኑ ይታመናል። እንደነዚህ ባሉት ጦርነቶች ዋነኛ ሚና የሚጫወቱት የነፍስ ወከፍና ቀላል መሣሪያዎች ናቸው።
እርግጥ ጠመንጃ ብቻውን የግጭት መንስኤ አይሆንም። የሰው ልጆች ጥይት ከመፈልሰፉ በፊትም ይዋጉ ነበር። ቢሆንም የጠመንጃዎች እንደልብ መገኘት ከድርድር ይልቅ ለውጊያ ይገፋፋል። የጦር መሣሪያዎች ጦርነቶች የሚፈጁትን ጊዜ ያራዝማሉ፣ የሚደርሰውንም እልቂት ያባብሳሉ።
በዛሬዎቹ ጦርነቶች ሥራ ላይ የዋሉት ቀላል መሣሪያዎች ይሁኑ እንጂ የሚያስከትሉት መዘዝ ቀላል አይደለም። እነዚህ መሣሪያዎች በ1990ዎቹ ዓመታት ከአራት ሚልዮን የሚበልጡ ሰዎችን ሕይወት ቀጥፈዋል። ከ40 ሚልዮን የሚበልጡ ደግሞ በእነዚሁ መሣሪያዎች ምክንያት ስደተኞች ሆነዋል ወይም ከቀዬአቸው ተፈናቅለዋል። የነፍስ ወከፍ መሣሪያዎች በጦርነት የፈራረሱ ኅብረተሰቦች ፖለቲካዊ፣ ኅብረተሰባዊ፣ ኢኮኖሚያዊና አካባቢያዊ ቀውስ እንዲደርስባቸው አድርገዋል። ዓለም አቀፉ ማኅበረሰብ ድንገተኛ እርዳታ ለማቅረብ፣ ስደተኞችን ለመርዳት፣ ሰላም ለማስከበርና ለወታደራዊ ጣልቃ ገብነት ያወጣው ወጪ በአሥር ቢልዮን ዶላር የሚቆጠር ሆኗል።
በዘመናዊዎቹ ግጭቶች የነፍስ ወከፍ መሣሪያዎች ይህን የመሰለ ትልቅ ሚና ሊጫወቱ የቻሉት ለምንድን ነው? የሚገኙት ከየት ነው? የሚያስከትሉትንስ አስከፊ ጉዳት ለመገደብ ወይም ለማስወገድ ምን ማድረግ ይቻላል? በሚቀጥሉት ርዕሶች እነዚህን ጥያቄዎች እንመረምራለን።
[የግርጌ ማስታወሻ]
^ አን.9 “የነፍስ ወከፍ መሣሪያዎች” የሚባሉት እንደ ጠመንጃና ሽጉጥ ያሉ አንድ ሰው በቀላሉ ሊይዛቸው የሚችሉ መሣሪያዎች ሲሆኑ “ቀላል መሣሪያዎች” የሚባሉት ደግሞ አንዳንድ ጊዜ ለመሸከም ሁለት ሰው የሚጠይቁትን መትረየሶች፣ ሞርታሮችና ላውንቸሮች ያመለክታል።
[በገጽ 3 ላይ የሚገኝ የሥዕል ምንጭ]
UN PHOTO 186797/J. Isaac