ሕመምህን ተቋቁመህ መኖር—እንዴት?
ሕመምህን ተቋቁመህ መኖር—እንዴት?
በስሜት ማዕበል መናጥህ ሊያስገርምህ አይገባም። ሕመምህ ወይም በአካልህ ላይ የደረሰው እክል በገሃድ የሚታይ ሐቅ ቢሆንም አእምሮህ በሕመምህ አስገዳጅነት የመጣብህን ለውጥ አይቀበለውም። አንተና ሕመምህ ብርቱ ትግል እንደገጠማችሁ ያህል ነው። በአንድ ወቅት በነበረህ ማንነትና ወደፊት በሚኖርህ ማንነት መካከል የሚካሄድ ውጊያ ነው። በአሁኑ ወቅት ሕመምህ አሸናፊነቱን የጨበጠ ሊመስል ይችላል። ቢሆንም ሁኔታውን መለወጥና በአሸናፊነት መወጣት ትችላለህ። እንዴት?
ዶክተር ኪቲ ስታይን እንደሚሉት “በሕመም ሳቢያ የአካል ጉዳተኛ በምንሆንበት ጊዜ በአብዛኛው ልክ የሞት ያህል ሆኖ ይሰማናል።” ስለዚህ ጤናን የሚያክል ትልቅ ዋጋ ያለው ነገር በምታጣበት ጊዜ አንድ የምትወደው ሰው ሲሞት እንደምታደርገው በቂ ጊዜ ወስደህ ብታዝንና ብታለቅስ ሊያስገርም አይገባም። እንደ እውነቱ ከሆነ ያጣኸው ጤንነትህን ብቻ ላይሆን ይችላል። አንዲት ሴት “ሥራዬን ለመተው ተገደድኩ። . . . ትልቅ ቦታ እሰጠው የነበረውን ነፃነትና ራስን ችሎ የመኖር አጋጣሚ አጣሁ” ብላለች። ቢሆንም ስላጣሃቸው ነገሮች ተገቢ የሆነ አመለካከት ይኑርህ። መልቲፕል ስክለሮሲስ በሚባለው ሰውነትን ሽባ የሚያደርግ በሽታ እየተሰቃዩ የሚኖሩት ዶክተር ስታይን በማከል “ስላጣኸው ነገር ማዘንና ማልቀስ ቢኖርብህም ያላጣሃቸው ነገሮች እንዳሉም መገንዘብ ያስፈልግሃል” ብለዋል። በእርግጥም የመጀመሪያ ሰሞኑን እንባና ሐዘን ታግለህ ካሳለፍክ በኋላ ገና ያልተነኩ ጠቃሚ ነገሮች እንዳሉህ ትገነዘባለህ። በመጀመሪያ ደረጃ ከተፈጠረው አዲስ ሁኔታ ጋር ተለማምደህ የመኖር ችሎታ አለህ።
አንድ ባሕረኛ የባሕሩን ማዕበል መቆጣጠር አይችልም። ይሁን እንጂ የጀልባውን መቅዘፊያ ሸራ በማስተካከል ማዕበሉን መቋቋም ይችላል። በተመሳሳይም ሕይወትህን ልክ እንደ ማዕበል ያናወጠውን ሕመምህን መቆጣጠር አትችል ይሆናል። ይሁን እንጂ “ሸራህን” ማለትም አካላዊ፣ አእምሯዊና ስሜታዊ አቅምህን በማስተካከል መቋቋም ትችላለህ። ሌሎች ከባድ ሕመም ያደረባቸው ሰዎች እንዲህ እንዲያደርጉ የረዳቸው ምንድን ነው?
ስለ ሕመምህ በቂ እውቀት ይኑርህ
ብዙዎች የሕመማቸውን ምንነት ማወቃቸው ያስከተለባቸውን ድንጋጤ ካሳለፉ በኋላ በውል ባልታወቀ ሥጋት ከመኖር ይልቅ መራራ ቢሆንም እውነቱን ማወቅ እንደሚሻላቸው ተገንዝበዋል። ፍርሃትና ሥጋት ምንም ነገር እንዳታደርግ ሲያሽመደምድ ምን እየደረሰብህ እንዳለ ማወቅህ ግን ምን ማድረግ እንደምትችል እንድታውቅ ይረዳሃል። ይህ ራሱ አዎንታዊ ውጤት ይኖረዋል። የስታንፎርድ ዩኒቨርሲቲ ባልደረባ የሆኑት ዶክተር ዴቪድ ስፒገል “አንድ ሲያስጨንቅህ የቆየን ጉዳይ እንዴት እንደምትፈታ እቅድ ካወጣህ በኋላ ምን ያህል ጥሩ ስሜት እንደሚሰማህ ልብ ሳትል አትቀርም” ብለዋል። “ገና ምንም ነገር ከማድረግህ በፊት ስለምታደርገው ነገር እቅድ በማውጣት የሚሰማህን ጭንቀትና መጥፎ ስሜት መቀነስ ትችላለህ።”
ስለሁኔታህ ተጨማሪ እውቀት ማግኘት እንደሚያስፈልግህ ሊሰማህ ይችላል። አንድ የመጽሐፍ ቅዱስ ምሳሌ እንደሚለው “አዋቂም ሰው ኃይሉን ያበዛል።” (ምሳሌ 24:5) “ከአብያተ መጻሕፍት አንዳንድ መጻሕፍት ተዋስ። ስለ ሕመምህ የቻልከውን ያህል ብዙ እውቀት ሰብስብ” ሲል አንድ አልጋ ላይ የዋለ ሰው መክሯል። ምን ዓይነት የሕክምና አማራጮችና ሕመሙን መቋቋም የሚቻልባቸው ዘዴዎች እንዳሉ ስታውቅ ሁኔታህ የፈራኸውን ያህል አስከፊ እንዳልሆነ ትገነዘብ ይሆናል። እንዲያውም ተስፋ የሚያሳድሩ አንዳንድ አሳማኝ መረጃዎች ታገኝ ይሆናል።
ይሁን እንጂ የመጨረሻ ግብህ ሕመምህን ምክንያታዊ በሆነ መንገድ ለመረዳት መቻል አይደለም። ዶክተር ስፒገል እንዲህ በማለት ያብራራሉ:- “ይህ መረጃ ለማሰባሰብ የሚደረገው ጥረት ሕመምህን ተቀብለህ አብረህ የመኖር፣ ሕመምህን የመረዳትና ሕመምህን በትክክለኛ አመለካከት የማየት በጣም አስፈላጊ የሆነ ሂደት አንዱ አካል ነው።” በሕይወትህ ላይ ለውጥ እንደደረሰ ግን ሕይወትህ ጨርሶ እንዳላከተመ ተቀብሎ መኖር በጣም አስቸጋሪና ብዙውን ጊዜም በጣም አዝጋሚ የሆነ ሂደት ነው። ይሁን እንጂ ሕመምህን ምክንያታዊ በሆነ መንገድ ከመረዳት አልፈህ ስሜትህ እንዲቀበለው ማድረግ ትችላለህ። እንዴት?
አስቸጋሪ የሆነውን ሚዛን መጠበቅ
ሕመምህን መቀበል የሚለው አነጋገር በሚኖረው ትርጉም ረገድ ያለህን አመለካከት ማስተካከል ሊያስፈልግህ ይችላል። አንድ ባሕረኛ በማዕበል መሐል እንደሚገኝ መቀበሉ ሽንፈት እንደማይሆንበት ሁሉ አንተም ሕመምተኛ መሆንህን መቀበልህ ሽንፈት ሊሆንብህ አይችልም። ይልቁንም ባሕረኛው የባሕሩን ሞገድ እውነትነት መቀበሉ ተገቢውን እርምጃ እንዲወስድ ያነሳሳዋል። በተመሳሳይም ሕመምተኝነትህን መቀበልህ አንዲት ሕመምተኛ ሴት እንዳለችው “በአዲስ አቅጣጫ መጓዝ” እንጂ ሽንፈት ማለት አይሆንም።
አካላዊ አቅምህና ችሎታህ ቢሰናከልም ስሜታዊ፣ አእምሯዊና መንፈሳዊ ባሕርያትህ በዚህ ምክንያት መነካት እንደማይኖርባቸው ለራስህ ማሳሰብ ሊያስፈልግህ ይችላል። ለምሳሌ አሁንም የማስተዋልና የመረዳት እንዲሁም የማደራጀትና የማመዛዘን ችሎታ አለህ? በተጨማሪም ፈገግታ የማሳየት፣ ለሌሎች የማሰብ እንዲሁም ጥሩ አዳማጭና እውነተኛ ወዳጅ የመሆን ችሎታህን ገና አላጣህ ይሆናል። ከሁሉ በላይ ደግሞ በአምላክ ላይ ያለህ እምነት አሁንም እንዳለ ነው።
በተጨማሪም ሁኔታዎችን በሙሉ መለወጥ ባትችልም ለተፈጠሩት ሁኔታዎች የምትሰጠውን ምላሽ መወሰን ትችላለህ። የብሔራዊ ካንሰር ተቋም ባልደረባ የሆኑት አይሪን ፓለን እንዲህ ብለዋል:- “ለሕመምህ የምትሰጠው ምላሽ በአንተ ቁጥጥር ሥር ያለ ነገር ነው። ሕመምህ ምንም ዓይነት አስገዳጅ ሁኔታ ቢያስከትልብህ ይህን ሥልጣን ሊወስድብህ አይችልም።” መልቲፕል ስክለሮሲስ በተባለው በሽታ በመሰቃየት ላይ የሚገኙት ሔለን የተባሉ የ70 ዓመት አረጋዊት “ሚዛንህን ጠብቀህ በመኖር ረገድ ወሳኝ የሆነው የሕመምህ ዓይነት ሳይሆን ለሕመምህ ያለህ አመለካከት ነው” በማለት ገልጸዋል። ለብዙ ዓመታት የአካል ጉዳተኛ ሆኖ የኖረ አንድ ሰው ደግሞ “አዎንታዊ አመለካከት መያዝ ጀልባን ቀጥ አድርጎ እንደሚያቆም መልሕቅ ነው” ብሏል። ምሳሌ 18:14ም “የሰው ነፍስ ሕመሙን ይታገሣል፤ የተቀጠቀጠን መንፈስ ግን ማን ያጠነክረዋል?” ይላል።
ሕይወትህን መቆጣጠር መቻል
ስሜታዊ ሚዛንህን መጠበቅ ስትጀምር ‘ይህ ሁሉ የደረሰብኝ ለምንድን ነው?’ እንደሚለው ያሉ ጥያቄዎች ‘እንዲህ ያለው ሁኔታ ከደረሰብኝ አሁን ማድረግ የምችለው ነገር ምንድን ነው?’ በሚለው ጥያቄ ይተካሉ። እዚህ ደረጃ ላይ ስትደርስ አሁን ካለህበት ሁኔታ ተነስተህ ወደ ሌላ ደረጃ ለመሸጋገር የሚያስችሉ ተጨማሪ እርምጃዎች ለመውሰድ ትመርጥ ይሆናል። ጥቂቶቹን እርምጃዎች እንመልከት።
ያለህበትን ሁኔታ አመዛዝን፣ መለወጥ ስለሚያስፈልግህ ነገር አስብና ሊለወጡ በሚችሉት ነገሮች ላይ ለውጥ ለማድረግ ጣር። ዶክተር ስፒገል “ሕመምህ ሕይወትህን መለስ ብለህ የምትመዝንበት የማንቂያ ደወል እንጂ የሞት ፍርድ አይደለም” ይላሉ። ‘ከመታመሜ በፊት ትልቅ ቦታ እሰጥ የነበረው ለምን ነገር ነበር? ይህስ አሁን የተለወጠው እንዴት ነው?’ ብለህ ራስህን ጠይቅ። እንደነዚህ ያሉትን ጥያቄዎች የምትጠይቀው ማድረግ የማትችለውን ነገር ለማወቅ ሳይሆን ምናልባት ለየት ባለ አሠራር ምን መሥራት እንደምትችል ለማወቅ መሆን አለበት።
ለምሳሌ ቀደም ሲል የጠቀስናትን ሔለንን እንውሰድ።ለ25 ዓመታት በቆየባት የመልቲፕል ስክለሮሲስ ሕመም ጡንቻዎቿ ተዳክመዋል። በመጀመሪያ በምርኩዝ እየተደገፈች ትሄድ ነበር። በኋላም ቀኝ እጅዋን መቆጣጠር ተሳናትና በግራ እጅዋ መገልገል ጀመረች። ከዚያ ቀጥሎ ደግሞ ግራ እጅዋ ከአገልግሎት ውጭ ሆነ። ከስምንት ዓመት በፊት ደግሞ ጭራሽ መሄድ ተሳናት። በአሁኑ ጊዜ ገላዋን የሚያጥብላት፣ ልብሷን የሚያለብሳትና የሚያበላት ሌላ ሰው ነው። ለዚህ ሁኔታ መዳረጓ የሚያሳዝናት ቢሆንም “አሁንም መፈክሬ ‘ከዚህ በፊት ትሠራ የነበረውን ሳይሆን አሁን ማድረግ የምትችለውን አስብ’ የሚል ነው” ትላለች። በባልዋና ሁኔታዋን በሚከታተሉት ነርሶች እርዳታ እንዲሁም የራሷን የፈጠራ ችሎታ በመጠቀም እጅግ የሚያስደስቷትን አንዳንድ ሥራዎች አሁንም መሥራት ችላለች። ለምሳሌ ስለመጪው ሰላም የሰፈነበት አዲስ ዓለም መጽሐፍ ቅዱስ የሚሰጠውን ተስፋ ማብሰር ከ11 ዓመት ዕድሜዋ ጀምሮ ከፍ አድርጋ የምትመለከተው የሕይወቷ ክፍል የሆነ ሥራ ነው። አሁንም ቢሆን ይህን ሥራ በየሳምንቱ ትሠራለች። (ማቴዎስ 28:19, 20) ሔለን ይህን የምታከናውነው እንዴት እንደሆነ ስትገልጽ እንዲህ ብላለች:-
“እንክብካቤ የምታደርግልኝን ነርስ ጋዜጣውን ቀና አድርጋ እንድትይዝልኝ እጠይቃለሁ። የዜና ዕረፍት አምዶችን አብረን እናነብና የተወሰኑትን እንመርጣለን። ከዚያም ለሐዘንተኛው ቤተሰብ የምትጽፈውን ሐሳብ ለነርሷ እነግራትና ነርሷ ደብዳቤውን በታይፕ ትጽፈዋለች። ከደብዳቤው ጋር አጽናኝ ስለሆነው የመጽሐፍ ቅዱስ የትንሣኤ ተስፋ የሚያብራራውን የምትወዱት ሰው ሲሞት * የተባለውን ብሮሹር አንድ ላይ እልካለሁ። ይህን የማደርገው ሁልጊዜ እሁድ ከሰዓት በኋላ ነው። አሁንም የአምላክን መንግሥት ምሥራች ለሰዎች ማካፈል መቻሌ ያስደስተኛል።”
ምክንያታዊ የሆነና ሊደረስበት የሚችል ግብ አውጣ። ሔለን ሊለወጥ የሚችለውን ለመለወጥ የምትጣጣርበት አንዱ ምክንያት ግብ ለማውጣትና ያወጣችው ግብ ላይ ለመድረስ ስለሚያስችላት ነው። ለአንተም ቢሆን እንዲህ ማድረግህ አስፈላጊ ነው። ለምን? ግብ ማውጣትህ አእምሮህ በወደፊቱ ጊዜ ላይ እንዲያተኩር ሲያደርግ ግብህ ላይ መድረስህ ደግሞ አንድ ነገር ማከናወን እንደቻልክ ሆኖ እንዲሰማህ ያደርግሃል። በተጨማሪም በተወሰነ ደረጃም ቢሆን ቀደም ሲል የነበረህን በራስ የመተማመን መንፈስ መልሶ ሊያጎናጽፍህ ይችላል። ይሁን እንጂ የምታወጣው ግብ ግልጽና የተወሰነ መሆኑን አረጋግጥ። ለምሳሌ ‘ዛሬ ከመጽሐፍ ቅዱስ አንድ ምዕራፍ አነባለሁ’ ብለህ ልትወስን ትችላለህ። በተጨማሪም እውን ሊሆን የሚችል ግብ አውጣ። የአንተ አካላዊና ስሜታዊ ተፈጥሮ ዘላቂ በሆነ በሽታ ከተያዙ ሌሎች ገላትያ 6:4
ግለሰቦች የተለየ ስለሚሆን እነርሱ የደረሱበት ግብ ላይ መድረስ አትችል ይሆናል።—በኔዘርላንድ የሚኖረው ሌክስ “አንድ ግብ ምንም ያህል አነስተኛ ቢሆን እዚያ ግብ ላይ መድረስህ ሌላ ተጨማሪ ነገር እንድታደርግ ያነሳሳሃል” ብሏል። ሌክስ ከ20 ከሚበልጡ ዓመታት በፊት በደረሰበት አደጋ ምክንያት ገና በ23 ዓመት ዕድሜው ሽባ ሆነ። በርከት ላሉ ጊዜያት የአካላዊ እንቅስቃሴ ሕክምና (physical therapy) ይከታተል በነበረበት ወቅት ፊቱን በእርጥብ ፎጣ እንደመጥረግ የመሰሉትን ግቦች እንዲያወጣ ማሳሰቢያ ይሰጠው ነበር። ይህን ማድረግ ብዙ ድካም የሚጠይቅበት ቢሆንም ተሳክቶለታል። እዚህ ግብ ላይ መድረስ መቻሉን እንደተገነዘበ ሌላ ግብ በማውጣት የጥርስ ሳሙናውን ክዳን ራሱ ለመክፈትና ለመዝጋት መጣጣር ጀመረ። አሁንም ተሳካለት። “ቀላል ባይሆንም” ይላል ሌክስ “አስብ ከነበረው የበለጠ ብዙ መሥራት እንደምችል ተገነዘብኩ።”
ሌክስ በሚስቱ እርዳታ የበለጡ ግቦች ላይ ለመድረስ ቻለ። ለምሳሌ በተሽከርካሪ ወንበር በመጠቀም ከሚስቱ ከቲኔከ ጋር ከቤት ወደ ቤት እየሄደ የመጽሐፍ ቅዱስን እውቀት ለሌሎች ሰዎች ያካፍላል። በተጨማሪም መጽሐፍ ቅዱስ የሚያስጠናውን ከፍተኛ የአካል ጉዳት የደረሰበት ሰው በየሳምንቱ እየሄደ ያጽናናል። “ሌሎችን መርዳት ትልቅ እርካታ ይሰጠኛል” ይላል ሌክስ። መጽሐፍ ቅዱስም “ከሚቀበል ይልቅ የሚሰጥ ብፁዕ ነው” በማለት ይህን ያረጋግጣል።—ሥራ 20:35
አንተስ ሌሎችን ለመርዳት ግብ ልታወጣ ትችላለህ? ታማሚ ወይም አካላዊ እክል ያለብህ መሆንህ ጥሩ አጽናኝ እንድትሆን ሊረዳህ ይችላል። ምክንያቱም በአንተ ላይ የደረሰው ችግር የሌሎች ሕመምና ችግር ይበልጥ የሚሰማህ ሰው እንድትሆን ያስችልሃል።
ከሰዎች ጋር ተገናኝ። ማኅበራዊ ግንኙነት ማድረግ ለጤናህ ጠቃሚ መሆኑን የሕክምና ጥናቶች ያመለክታሉ። በተቃራኒው ያለው ሁኔታም በእርግጥ ሊከሰት የሚችል ነገር ነው። “በማኅበራዊ መገለልና በሞት መካከል ያለው ዝምድና . . . በማጨስ . . . እና በሞት መካከል ያለውን ዝምድና ያህል ጠንካራ ነው” ይላሉ አንድ ተመራማሪ። በማከልም “ማኅበራዊ ግንኙነቶችህን ማሻሻል ማጨስ የማቆምን ያህል ለጤንነትህ ጠቃሚ ሊሆን ይችላል” ይላሉ። ተመራማሪው ማኅበራዊ ግንኙነቶችን ጠብቆ የማቆየት ችሎታ “ዕድሜ ያራዝማል” ከሚል መደምደሚያ ላይ መድረሳቸው አያስደንቅም!—ምሳሌ 18:1
ይሁን እንጂ ችግሩ በቀደመው ርዕስ ላይ እንደተጠቀሰው አንዳንድ ወዳጆችህ አንተን መጠየቅ አቁመው ይሆናል። ለራስህ ስትል ከብቸኝነት መላቀቅ መቻል ይኖርብሃል። ግን እንዴት? ወዳጆችህ መጥተው እንዲጠይቁህ በመጋበዝ ልትጀምር ትችላለህ።
ሰዎች አንተን በመጠየቅ እንዲደሰቱ አድርግ። * ይህን ማድረግ እንድትችል ጠያቂዎችህ ስለበሽታህ በመስማት እንዳይሰለቹ ስለሚሰማህ ሕመም ብዙ ከማውራት መቆጠብ ይኖርብሃል። አንዲት ሥር የሰደደ በሽታ የያዛት ሴት ከባልዋ ጋር በምታደርገው ውይይት ስለ በሽታዋ ብዙ እንዳትናገር በራስዋ ላይ ገደብ በመጣል ይህን ችግር ፈትታለች። “የግድ መቻል ይኖርብናል” ብላለች። በእርግጥም ሕመማችሁ ከሌሎች ጋር ልትወያዩባቸው የምትችሏቸውን ሌሎች ነገሮች በሙሉ ማዳፈን አይኖርበትም። አንድ ጠያቂ አልጋ ላይ ከዋለ ወዳጁ ጋር ስለ ሥነ ጥበብ፣ ስለ ታሪክና በይሖዋ አምላክ እንዲያምን ስላደረጉት ምክንያቶች ከተወያየ በኋላ “ሕመሙ ስብዕናውን እንዲጋርድበት አልፈቀደም። ከእርሱ ጋር መነጋገር በጣም ያስደስታል” ብሏል።
በተጨማሪም ተጫዋችና ቀልደኛ ለመሆን ብትጣጣር ወዳጆችህ አንተን መጠየቅ ያስደስታቸዋል። ከዚህም በላይ ሳቅ አንተንም ቢሆን ይጠቅማል። ፓርኪንሰንስ የተባለው የሚያንቀጠቅጥ በሽታ የያዘው አንድ ሰው “ተጫዋች መሆን የሚያጋጥሙህን ውጪያዊም ሆነ ውስጣዊ ችግሮች ለመቋቋም ይረዳል” ብሏል። በእርግጥም ሳቅ ጥሩ መድኃኒት ሊሆን ይችላል። ምሳሌ 17:22 “ደስ ያላት ልብ መልካም መድኃኒት ናት” ይላል። የጥቂት ደቂቃዎች ሳቅ እንኳን ብዙ ሊጠቅምህ ይችላል። ከዚህም በላይ ራሳቸው ሥር የሰደደ ሕመም ያለባቸው ደራሲዋ ሱዛን ሚልስትሪ ዌልስ “ሳቅ ልንሞክር ከምንችላቸው አንዳንድ መድኃኒቶች በተለየ ሁኔታ ምንም ዓይነት ጉዳት የማያስከትል፣ መርዝነት የሌለውና የሚያስደስት መድኃኒት ነው። የምናጣው ነገር ቢኖር ትካዜ ብቻ ነው” ብለዋል።
ውጥረትህን የምትቀንስባቸውን መንገዶች ፈልግ። ውጥረት የሕመም ስሜቶችን ሊያባብስ ሲችል ውጥረት መቀነስ ግን የሕመም ስሜቶችን ጋብ እንደሚያደርግ ጥናቶች ያረጋግጣሉ። ስለዚህ በየጊዜው ለራስህ እረፍትና ፋታ መስጠት ይኖርብሃል። (መክብብ 3:1, 4) ነጋ ጠባ ስለ ሕመምህ እያሰብክ በጭንቀት መወጠር የለብህም። እቤት ለመዋል ተገድደህ ከሆነ ለስለስ ያለ ሙዚቃ በማዳመጥ፣ መጽሐፍ በማንበብ፣ ረዘም ላለ ጊዜ መታጠቢያ ገንዳ ውስጥ በመዘፍዘፍ፣ ደብዳቤ ወይም ግጥም በመጻፍ፣ ሥዕል በመሳል፣ የሙዚቃ መሣሪያ በመጫወት፣ ከሚታመን ወዳጅ ጋር በመጨዋወት ወይም እነዚህን የመሰሉ ተግባራትን በማከናወን ስሜትህ የሚያሳድርብህን ጭነት ማቅለል ትችላለህ። እንዲህ ማድረግህ ለችግርህ ዘለቄታ ያለው መፍትሔ ባያስገኝም ጊዜያዊ የሆነ ፋታ ሊያስገኝልህ ይችላል።
መንቀሳቀስ የምትችል ከሆነ የእግር ጉዞ አድርግ፣ ገበያ ውጣ፣ አትክልት ተንከባከብ፣ በመኪና ተጓዝ ወይም ከተቻለ ለዕረፍት ወደ ሌላ አካባቢ በመሄድ ለመዝናናት ሞክር። ረዥም ጉዞ ማድረግ በሕመምህ ምክንያት አስቸጋሪ ሊሆንብህ ቢችልም የቅድሚያ ዝግጅት ካደረግህ እንቅፋቶቹን መወጣት ትችላለህ። ለምሳሌ ቀደም ሲል የጠቀስናቸው ሌክስና ቲኔከ ውጭ አገር ለመሄድ ችለዋል። ሌክስ “መጀመሪያ ላይ ጭንቀት አሳድሮብን ነበር። ቢሆንም በጣም አስደሳች የዕረፍት ጊዜ ልናሳልፍ ችለናል!” ብሏል። በእርግጥም ሕመምህ የሕይወትህ ክፍል ይሁን እንጂ ሕይወትህን ሙሉ በሙሉ መቆጣጠር የለበትም።
ከእምነት ብርታት አግኝ። ከባድ የሆኑ የአካል እክሎችን በተሳካ ሁኔታ የተቋቋሙ እውነተኛ ክርስቲያኖች በይሖዋ አምላክ ላይ ያላቸው እምነትና ከክርስቲያን ጉባኤ ጋር ያላቸው ሕብረት የኃይልና የመጽናኛ ምንጭ እንደሆነላቸው ይናገራሉ። * መጸለይ፣ መጽሐፍ ቅዱስ ማጥናት፣ ስለ ወደፊቱ ጊዜ ማሰላሰልና በመንግሥት አዳራሽ ውስጥ በሚደረጉ ስብሰባዎች ላይ መገኘት ስላለው ጥቅም ከሰጧቸው አስተያየቶች ጥቂቶቹ እነሆ:-
● “አሁንም ቢሆን አልፎ አልፎ በትካዜ እዋጣለሁ። ይህ በሚሆንበት ጊዜ ወደ ይሖዋ እጸልያለሁ። ይሖዋም የምችለውን ሁሉ በማድረግ ለመቀጠል ያደረግኩትን ውሳኔ ያድስልኛል።”—መዝሙር 55:22፤ ሉቃስ 11:13
● “መጽሐፍ ቅዱስ ማንበቤና ባነበብኩት ነገር ላይ ማሰላሰሌ የአእምሮ ሰላም እንዳላጣ በእጅጉ ረድቶኛል።”—መዝሙር 63:6፤ 77:11, 12
● “መጽሐፍ ቅዱስ ማጥናቴ እውነተኛው ሕይወት ገና ወደፊት የሚመጣ እንደሆነና ለዘላለም የአካል ጉዳተኛ ሆኜ እንደማልቀር ያሳስበኛል።”—ኢሳይያስ 35:5, 6፤ ራእይ 21:3, 4
● “መጽሐፍ ቅዱስ በሚሰጠው የወደፊት ጊዜ ተስፋ ላይ ያለኝ እምነት የየቀኑን ችግር በዕለቱ ተቋቁሜ እንዳልፍ የሚያስችል ብርታት ሰጥቶኛል።”—ማቴዎስ 6:33, 34፤ ሮሜ 12:12
● “በመንግሥት አዳራሽ በሚደረጉ ስብሰባዎች ላይ መገኘቴ አእምሮዬ በሕመሜ ላይ ሳይሆን በሚያጽናኑ በጎ ነገሮች ላይ እንዲያተኩር ለማድረግ ረድቶኛል።”—መዝሙር 26:12፤ 27:4
● “ከጉባኤ አባላት ጋር የማሳልፈው አጽናኝ ጊዜ ልቤን በደስታ ይሞላዋል።”—ሥራ 28:15
ናሆም 1:7) ከይሖዋ አምላክ ጋር የጠነከረ ዝምድና መመሥረትና ከክርስቲያን ጉባኤ ጋር መተባበር መጽናኛና ብርታት ያስገኛል።—ሮሜ 1:11, 12፤ 2 ቆሮንቶስ 1:3፤4:7
መጽሐፍ ቅዱስ “እግዚአብሔር መልካም ነው፣ በመከራ ቀንም መሸሸጊያ ነው፤ በእርሱ የሚታመኑትንም ያውቃል” የሚል ዋስትና ይሰጠናል። (ለራስህ በቂ ጊዜ ስጥ
ከባድ ሕመምን ወይም የአካል ጉዳትን ተቋቁሞ መኖር “በአንድ ቀን ጀንበር የሚሳካ ነገር ሳይሆን ረዥም ጊዜ የሚወስድ ነው” ይላሉ ለረዥም ጊዜ የቆየ ሕመም ችግር ያስከተለባቸውን ሰዎች የሚረዱ አንድ የማኅበራዊ ጉዳይ ሠራተኛ። ሌላው ባለሞያ ደግሞ “ፈጽሞ አዲስ የሆነ ክህሎት ማለትም ከባድ ሕመምን ተቋቁሞ የመኖር ችሎታ” በመማር ላይ ስለሆንክ ለራስህ በቂ ጊዜ ስጥ ሲሉ ይመክራሉ። አዎንታዊ አመለካከትና ዝንባሌ ቢኖርህም እንኳ ያደረብህ ሕመም አቅምህን ስለሚያሟጥጥብህ በትካዜ የምትዋጥባቸው ቀናት ወይም ሳምንታት ሊኖሩ ይችላሉ። ይሁን እንጂ ከጊዜ በኋላ መሻሻል ልታይ ትችላለህ። አንዲት ሴት ያጋጠማት ይህን የመሰለ ሁኔታ ነው። “ጨርሶ ስለ ካንሰር ሳላስብ አንድ ሙሉ ቀን እንዳሳለፍኩ ስገነዘብ በጣም ተደሰትኩ። . . . ከጥቂት ጊዜ በፊት እንዲህ ያለ ደረጃ ላይ እደርሳለሁ ብዬ ማሰብ እንኳን አልችልም ነበር” ብላለች።
በእርግጥም የሚቀጥለው ርዕስ እንደሚያሳየው በመጀመሪያ የተሰማህን ፍርሃትና ሥጋት ካሳለፍክ እንዲሁም አዳዲስ ግቦች ካወጣህ በኋላ በተሳካ ሁኔታ ሕመምህን መቋቋም መቻልህን ስታይ ልትገረም ትችላለህ።
[የግርጌ ማስታወሻዎች]
^ አን.17 ኒው ዮርክ በሚገኘው የመጠበቂያ ግንብ መጽሐፍ ቅዱስና ትራክት ማኅበር የታተመ።
^ አን.24 ጠያቂዎችን በምን መንገድ መያዝ እንደሚገባ የተሰጠው ምክር ለትዳር ጓደኛህ፣ ለልጆችህ ወይም ለአስታማሚህ ልታሳየው በሚገባህ ባሕርይ ላይ የበለጠ ተፈጻሚነት ይኖረዋል።
^ አን.28 እምነት ጤንነትንና በጎ የመሆንን ስሜት እንደሚያጎለብት በርካታ የሕክምና ጥናቶች አረጋግጠዋል። በጆርጅታውን ዩኒቨርሲቲ የሕክምና ትምህርት ቤት ባልደረባ የሆኑት ፕሮፌሰር ዴል ማቲውስ “እምነት ፋይዳ እንዳለው ተረጋግጧል” ብለዋል።
[በገጽ 7 ላይ የሚገኝ ሥዕል]
ስለ በሽታህ ማወቅህ ሕመምህ ያስከተለብህን ሁኔታ ተቀብለህ እንድትኖር ሊረዳህ ይችላል
[በገጽ 8 ላይ የሚገኝ ሥዕል]
ሔለን በሌሎች እርዳታ የሚያጽናኑ ደብዳቤዎች ታዘጋጃለች
[በገጽ 8 ላይ የሚገኝ ሥዕል]
“የአምላክን መንግሥት ምሥራች ለሌሎች ማካፈል በጣም ያስደስተኛል”
[በገጽ 8 ላይ የሚገኙ ሥዕሎች]
“ሽባ ብሆንም ካሰብኩት በላይ ብዙ ነገር ማድረግ እንደምችል ተገነዘብኩ”—ሌክስ