በመጨረሻ መፍትሔ ያገኛል!
በመጨረሻ መፍትሔ ያገኛል!
እያንዳንዱ ሕፃን ተፈላጊ የሚሆንበትንና የሚወደድበትን እንዲሁም እያንዳንዱ ሕፃን ለልጆቻቸው ከሁሉ የተሻለውን መመሪያ ለመስጠት ልባዊ ፍላጎት ያላቸው ወላጆች በማግኘት የሚባረክበትን ዓለም በዓይነ ሕሊናህ ለማየት ሞክር። እያንዳንዱ ሕፃን በአካልም ሆነ በአእምሮ ሙሉ ጤነኛ የሚሆንበትን፣ ጎዳና ተዳዳሪዎች ፈጽሞ የማይገኙበትንና በኢኮኖሚ ችግር ምክንያት የመጫወት እድል ሳያገኙ ላባቸውን አንጠፍጥፈው ለማደር የተገደዱ ሕፃናት የማይኖሩበትን ዓለም በዓይነ ሕሊናህ ለመሳል ሞክር።
በጣም የሚፈለግ ነገር አይደለም? እንዴታ! ግን ይህ ሊሆን የሚችል ነገር ነውን? የይሖዋ ምሥክሮች በሁለት ምክንያቶች የተነሣ አዎን፣ የሚል መልስ ይሰጣሉ።
ወላጆች መፍትሔውን በከፊል ሊያስገኙ ይችላሉ
ትላልቅ ሰዎች አንዳንዶቹን የሕፃናት ችግሮች መፍታት ብሎም በአንዳንድ ሁኔታዎች ጨርሶ ማስወገድ የሚችሉ መሆኑን እንደምታምን ጥርጥር የለውም። እርግጥ ይህ ሊሆን የሚችለው ፈቃደኛ ሆነው እስከተገኙ ድረስ
ብቻ ነው። አዎን፣ ከችግሮች መፍቻ ቁልፎች መካከል አንደኛው የሚገኘው በወላጆች እጅ ነው።ለምሳሌ “ሚስትም ከባልዋ አትለያይ . . . ባልም ሚስቱን አይተዋት” የሚለውን የመጽሐፍ ቅዱስ ምክር መከተል የሚችሉ ሰዎች በፍቺና በመለያየት በፈራረሰ ቤት ውስጥ መኖር የሚያስከትለውን የመከራ ኑሮ የሚገፉ ልጆች አይኖሩአቸውም።—1 ቆሮንቶስ 7:10, 11
“በአገባብ እንመላለስ፤ በዘፈንና በስካር አይሁን” የሚለውን የመጽሐፍ ቅዱስ ምክር ለመከተል ፈቃደኛ የሆኑ ሰዎች የሚሰክሩ ወይም የዕፅ ሱሰኞች የሆኑ ወላጆች የሚያስከትሉባቸውን ጭንቀት ተቋቁመው ለመኖር የሚገደዱ ልጆች አይኖሩአቸውም።—ሮሜ 13:13፤ ኤፌሶን 5:18
“ከዝሙት ሽሹ” የሚለውን የመጽሐፍ ቅዱስ ምክር ለመከተል ፈቃደኛ የሆኑ ሰዎች የማይፈለጉ እንደሆኑ እየተሰማቸው ምናልባትም በአንድ ወላጅ አሳዳሪነት የሚያድጉ ልጆች የማሳደግ እድላቸው በጣም አነስተኛ ነው።—1 ተሰሎንቄ 4:3፤ ማቴዎስ 19:9
“ልባቸው እንዳይዝል ልጆቻችሁን አታበሳጩአቸው” የሚለውን የመጽሐፍ ቅዱስ ምክር ለመከተል ፈቃደኛ የሆኑና “ልጆቻቸውን የሚወዱ” ሰዎች በተለያየ መልኩ ለአካላዊና አእምሮአዊ በደሎች የተጋለጡ ልጆች አይኖሩአቸውም።—ቆላስይስ 3:21፤ ቲቶ 2:4
ለማጠቃለል፣ ትላልቅ ሰዎች በሙሉ ኢየሱስ “ሰዎች ሊያደርጉላችሁ የምትወዱትን ሁሉ እናንተ ደግሞ እንዲሁ አድርጉላቸው” በማለት የሰጠውን የመጽሐፍ ቅዱስ ምክር ለመከተል ፈቃደኛ ቢሆኑ ኖሮ እንዳልተፈለጉ የሚሰማቸው ወይም ፍቅር ያላገኙ በሚልዮን የሚቆጠሩ ሕፃናት ይኖሩ ነበርን?—ማቴዎስ 7:12
ይሁን እንጂ ከላይ የተጠቀሱትን በሙሉ ለማድረግ ፈቃደኛ የሆኑ ብዙ ሰዎች መኖራቸው ደስ ያሰኛል። ሁሉም ሰዎች ፈቃደኛ አለመሆናቸው ደግሞ በእጅጉ ያሳዝናል። ችግሩ እዚህ ላይ ነው። ፈቃደኞች የሆኑትም እንኳን በሰብዓዊ አለፍጽምና እና ከራሳቸው ቁጥጥር ውጭ በሆኑ ምክንያቶች የተነሣ ብዙውን ጊዜ ጥረታቸው ሳይሳካ ይቀራል። ሰዎች በሕፃናት ላይ የሚደርሱትን ችግሮች በከፊል ሊፈቱ ቢችሉም የተሟላ መፍትሔ ግን ሊያስገኙ እንደማይችሉ ግልጽ ነው።
የተሟላ መፍትሔ የሚያስገኝ መለኮታዊ መንግሥት
ቀደም ባለው ርዕስ ላይ የተጠቀሱት ጆን ረስኪን “የአንድ መንግሥት ተቀዳሚ ግዴታ በሥሩ የሚወለድ እያንዳንዱ ሕፃን ለአካለ መጠን እስኪደርስ ድረስ በቂ መጠለያ፣ ምግብ፣ ልብስና ትምህርት ማግኘቱን ማረጋገጥ” እንደሆነ በጥብቅ እንደሚያምኑ ጽፈዋል። ይሁን እንጂ “ይህን ለማሳካት መንግሥት ባሁኑ ጊዜ ልናስብ እንኳን በማንችላቸው ሕዝቦች ላይ ሙሉ ሥልጣን ሊኖረው እንደሚገባ” ራስኪን አምነዋል።
ራስኪን የተናገሩለት ዓይነት ተስማሚ ሥልጣን ሊኖረው የሚችለው መለኮታዊ ድጋፍ ያለው መንግሥት ብቻ ነው። እንዲህ ያለ መንግሥት እንደሚመጣ ተስፋ የተሰጠን ሲሆን ይህም በማቴዎስ 6:9, 10 ላይ ኢየሱስ የጠቀሰው መንግሥት ነው። ይህ አምላክ የሚያመጣው መንግሥት የምድርን ጉዳዮች ሙሉ በሙሉ መቆጣጠር ሲጀምር ሕፃናትን ጨምሮ ለዜጎቹ በሙሉ በቂ መጠለያ፣ ልብስ፣ ምግብና ትምህርት በማቅረብ ሥልጣኑን በሁሉም ሕዝቦች ላይ ተግባራዊ ያደርጋል። (ኢሳይያስ 65:17-25) ይሁን እንጂ ይህ ፍጹም የሆነ መንግሥት በዚህ ብቻ አይወሰንም።
የአምላክ መንግሥት የሰው ልጆችን ወደ ፍጽምና በመመለስ ፍጹም ሚዛኑን በጠበቀ መንገድ ልጆች እንዲያሳድጉ ያስችላቸዋል። (ኢዮብ 33:24-26) ሕፃናት የተባበሩት መንግሥታት ድርጅት የሕፃናት መብቶች ድንጋጌ ላይ የተገለጸው ዓይነት ፍጹም የሆነ ሰላምና የወንድማማች መንፈስ በሰፈነበት አካባቢ ያድጋሉ። (መዝሙር 46:8, 9) ከዚያ ወዲያ ዓለም አቀፍ የሕፃናት ዓመት ማወጅ ወይም የሕፃናት መብት ኮንቬንሽን ማርቀቅ አስፈላጊ አይሆንም።
ለወላጆችና የአካል ጉዳተኞች ለሆኑ ሕፃናት ፍጹም ጤንነት ማጎናጸፍ የሰማያዊው መንግሥት ንጉሥ ለሆነው ለክርስቶስ ኢየሱስ በጣም ቀላል ነገር ነው። ምድር ላይ ሳለ የፈጸማቸው ተአምራዊ ፈውሶች ለዚህ ዋስትና ይሰጡናል። (ሉቃስ 6:17-19፤ ዮሐንስ 5:3-9፤ 9:1-7) የሞቱ ሕፃናትንና ወላጆችን እንኳን ማስነሳት ከአቅሙ በላይ አይሆንበትም!—ማቴዎስ 9:18-25
አምላክ ለምድር ሕፃናት የሚበጅ እርምጃ የሚወስድበት ጊዜ ቅርብ መሆኑን ማወቅ ምንኛ ያስደስታል!
[በገጽ 12 ላይ የሚገኝ ሣጥን/ሥዕሎች]
ለልጆች የሚሆን እርዳታ
የይሖዋ ምሥክሮች፣ ልጆች ራሳቸውን ከችግር እንዲጠብቁ ለመርዳትና ሊያስወግዱ የማይችሉትን ችግር እንዴት ሊቋቋሙ እንደሚችሉ ለመጠቆም ልባዊ ፍላጎት አላቸው። በመሆኑም ባለፉት ዓመታት ለትምህርት ካልደረሱ ሕፃናት አንስቶ እስከ አፍላ ጎረምሶች ድረስ ያሉትን ልጆች የሚረዱ በርካታ ጽሑፎች አውጥተዋል። ከእነዚህ መካከል የመጽሐፍ ቅዱስ ታሪኮች መማሪያ መጽሐፌ እና ወጣቶች የሚጠይቋቸው ጥያቄዎችና ተግባራዊ መሆን የሚችሉ መልሶች የተባሉት መጻሕፍት እንዲሁም የወጣቶች ጥያቄ፣ እውነተኛ ወዳጆች ማፍራት የምችለው እንዴት ነው? (የእንግሊዝኛ) የሚለው ቪዲዮ ይገኛሉ። እነዚህን በአካባቢህ ከሚኖሩ የይሖዋ ምሥክሮች ወይም ለዚህ መጽሔት አዘጋጆች በመጻፍ ልታገኝ ትችላለህ።
የይሖዋ ምሥክሮች ራሳቸውም ቢሆኑ ከልጆቻቸው ጋር ዘወትር ስለ ችግሮቻቸው በመወያየት የሚወዷቸውና የሚፈልጓቸው መሆኑን ያሳዩአቸዋል። ወላጆች አብዛኛውን ጊዜ ከላይ የተጠቀሱትን ግሩም ጽሑፎች መሠረት በማድረግ የማይቋረጥና ቀጣይ የሆነ ሥልጠና ይሰጧቸዋል። አንተም ለልጆችህ እንዲሁ ማድረግ ትፈልግ ይሆናል።