ልጆችን ሥርዓታማ አድርጎ ማሳደግ—እንዴት?
ልጆችን ሥርዓታማ አድርጎ ማሳደግ— እንዴት?
“ልጆች ከወላጆቻቸው ፍቅርና ተግሳጽ ካገኙ ለራሳቸው አክብሮት ሊኖራቸውና ራስን የመግዛት ባሕርይ ሊያዳብሩ ይችላሉ” በማለት ሞንትሪያል ካናዳ ውስጥ የሚታተመው ዘ ጋዜት የተባለው ጋዜጣ ሪፖርት አድርጓል። ይህ ምንን ይጨምራል? በሞንትሪያል የክሊኒካዊ ሥነ ልቦና ሐኪም የሆኑት ኮንስታንስ ላሊኔክ እንደሚሉት ከሆነ ልጆች ማሳየት በሚገባቸው ባሕርይ ረገድ ግልጽ የሆነ ገደብ ማበጀት አስፈላጊ ነው።
ለልጆችና ለቤተሰቦች ሙያዊ ምክር የሚሰጡት ላሊኔክ “ልጆች የፈጸሙት ድርጊት የሚያስከትልባቸውን መዘዝ እንዲገነዘቡ የማናደርግ ከሆነ ብዙ መማር የሚችሉበትን አጋጣሚ እየዘጋንባቸው ነው” በማለት ተጨማሪ ሐሳብ ሰጥተዋል። ልል መሆን በልጁ እድገት ላይ አሉታዊ ተጽእኖ ሊያሳድር ይችላል።
ልጆች ማሳደግን በተመለከተ መጽሐፍ ቅዱስ የሚሰጠው ጊዜ የማይሽረውና ጥበብ ያለበት ምክር በጣም ተስማሚ ነው። መጽሐፍ ቅዱስ “ነገር ግን ቃላችሁ አዎን አዎን ወይም አይደለም አይደለም ይሁን” በማለት ይናገራል። (ማቴዎስ 5:37፣ በሰያፍ የጻፍነው እኛ ነን።) አንድ ጊዜ ምክንያታዊ የሆኑ መመሪያዎች ካወጣችሁና ልጆቻችሁም እነዚህን መመሪያዎች ከተረዷቸው ወዲያውኑ በተግባር ላይ እንዲያውሏቸው አድርጉ። በተጨማሪም እነዚህ መመሪያዎች የሚለዋወጡ መሆን የለባቸውም። ቃላችሁ ውጤታማ በሆነ ተግባር የተደገፈ ይሁን። ይህም ወላጆች የሚያወጧቸውን መመሪያዎችና ከልጆቻቸው የሚጠብቋቸውን ነገሮች በተመለከተ የማያሻማ መልእክት ያስተላልፋል። በሌላ አባባል ሰው ‘የዘራውን እንደሚያጭድ’ እንዲገነዘቡ ያደርጋቸዋል። (ገላትያ 6:7፤ ሮሜ 2:6) በፍቅር ላይ የተመሠረተ ውጤታማ ተግሳጽ ዋና ዓላማ ልጆች መመሪያዎችን በተግባር ላይ ማዋልን እንዲሁም ተስፋ የሚያስቆርጥ ነገር ቢገጥማቸውና የጓጉለትን ነገር ቶሎ ሳያገኙ ቢቀሩ መታገስን እንዲማሩ ማድረግ ነው። እንዲህ ከሆነ ልጆች ሥርዓት ያላቸውና ኃላፊነት የሚሰማቸው ዐዋቂዎች ለመሆን የሚያስፈልጓቸውን ባሕርያት ሊኮተኩቱ ይችላሉ።
ለልጆች ፍቅራዊ ተግሳጽ መስጠትን በተመለከተ አምላክ ለወላጆች የሰጠው ተጨማሪ ምክር ለቤተሰብ ደስታ ቁልፉ ምንድን ነው? በተባለው መጽሐፍ ውስጥ ይገኛል። ይህንን ባለ 192 ገጽ መጽሐፍ ማግኘት የሚፈልጉ ከሆነ ከታች ያለውን ቅጽ ሞልተው በቅጹ ላይ ወዳለው አድራሻ ወይም በዚህ መጽሔት ገጽ 5 ላይ ከሚገኙት አድራሻዎች አመቺ ወደሆነው መላክ ይችላሉ።
□ ለቤተሰብ ደስታ ቁልፉ ምንድን ነው? የተሰኘውን መጽሐፍ ማግኘት እፈልጋለሁ። በየትኛው ቋንቋ እንደሚፈልጉ ይጥቀሱ
□ መጽሐፍ ቅዱስን መማር ስለምፈልግ እባካችሁ አነጋግሩኝ።