ወጣቶች “ከግድያ ባሕል” እንዲያመልጡ መርዳት
ወጣቶች “ከግድያ ባሕል” እንዲያመልጡ መርዳት
ዛሬ በወጣቶች ዘንድ ስለሞት ትልቅ ጉጉት የተፈጠረበት ምክንያት ምንድን ነው? የኢሊኖይዝ ግዛት ተወካይ የሆኑት ሄንሪ ሐይድ “በእነዚህ ወጣቶች ውስጥ መንፈሳዊ ክፍተት ያለ ሲሆን ይህም ክፍተት በግድያና በዓመፅ የተሞላ ነው” ብለዋል።
አንድ የታይም መጽሔት አንባቢ “በዛሬዎቹ ወጣቶቻችን የግድያ ንዑስ ባሕል እንዲሰርጽ ምክንያት የሆኑት ሰነፍ ወላጆች፣ የጭካኔ ድርጊቶች የሚታዩባቸው መዝናኛዎችና የሥነ ምግባርና የመንፈሳዊ መሠረት መናወጥ ናቸው” ሲሉ ጽፈዋል።
ከዋነኞቹ የወጣቶች ችግሮች መካከል ሌላው ብቸኝነት ነው። አንዳንዶቹ የሚኖሩት ሁለቱም ወላጆች ሥራ በሚውሉባቸውና አብዛኛውን ጊዜ ከቤታቸው ውጭ በሚሆኑባቸው ቤቶች ነው። ሌሎቹ ደግሞ አንድ ወላጅ ብቻ ያላቸው ናቸው። አንድ ምንጭ እንዳመለከተው በዩናይትድ ስቴትስ የሚኖሩ ጎረምሶች በየቀኑ 3.5 ሰዓት ያህል በብቸኝነት የሚያሳልፉ ሲሆኑ በየሳምንቱ ከወላጆቻቸው ጋር የሚያሳልፉት ጊዜ በ60ዎቹ ከነበሩት ወጣቶች በ11 ሰዓት ያንሳል። እንዲያውም አንዳንድ ወጣቶች ወላጆቻቸውን ፈጽሞ አያገኟቸውም ወይም ወላጆቻቸው ምንም ዓይነት ስሜታዊ ድጋፍ አይሰጧቸውም።
ወላጆች ምን ሊያደርጉ ይችላሉ?
የወጣቶች ዋነኛ ችግር የሆነውን “መንፈሳዊ ክፍተት” ስንመለከት ወላጆች የሚጫወቱት ሚና ምን
ያህል አስፈላጊ ነው? አዋቂ የሆኑ ወላጆች ልጆቻቸው በአንድ በኩል ጤናማ የሆነ መዝናኛ፣ በሌላ በኩል ደግሞ የማይቋረጥ የቅርብ ክትትል እንደሚያስፈልጋቸው ያውቃሉ። ወላጆች በፍቅራዊ አሳቢነት ተነሳስተው ልጆቻቸው ስለሚመርጡት ሙዚቃ፣ የቴሌቪዥን ፕሮግራም፣ ቪዲዮ፣ ልብ ወለድ ጽሑፍ፣ የቪዲዮ ጨዋታና ፊልሞች ሊያነጋግሯቸው ይችላሉ። ብዙ ወጣቶች አውጥተው ባይናገሩም የወላጆቻቸውን ፍቅርና አመራር ለማግኘት ይናፍቃሉ። የሚኖሩበት ዓለም ምንም ነገር በእርግጠኝነት የማይታወቅበት ስለሆነ ለጥያቄዎቻቸው ቀጥተኛ መልስ ለማግኘት ይፈልጋሉ። ትላልቅ ሰዎች የዛሬዎቹ ልጆች የሚኖሩበት ዓለም እነርሱ ይኖሩበት ከነበረው ዓለም እጅግ በጣም የተወሳሰበ መሆኑን መረዳት አለባቸው።ልጆቻቸውን ከአደጋ ለማዳን የሚፈልጉ ወላጆች ከልጆቻቸው ጋር አዘውትረው ይነጋገራሉ። በሚገባ ያዳምጧቸዋል። ዘመናዊው ባሕል ስለሚያስከትለው አደጋ ያስጠነቅቋቸዋል። ወላጆች በየጊዜው የማይለዋወጡ ጥብቅ ገደቦችን ሲያወጡ፣ ምክንያታዊና አፍቃሪ ሲሆኑ አብዛኛውን ጊዜ ጥሩ ውጤት ያገኛሉ።—ማቴዎስ 5:37
የይሖዋ ምሥክሮች የሆኑ ወላጆች በመጽሐፍ ቅዱስና መጽሐፍ ቅዱሳዊ በሆኑ ጽሑፎችና ቪዲዮዎች * በመጠቀም ከልጆቻቸው ጋር የዘወትር ውይይት ለማድረግ ይጥራሉ። እንደነዚህ ያሉትን አጋጣሚዎች ልጆቻቸውን ለመውቀስና ለመገሰጽ ሳይሆን በመንፈሳዊ ስለሚያንጹ ርዕሰ ጉዳዮች ለመወያየት ይጠቀማሉ። በእነዚህ የቤተሰብ ስብሰባዎች ወጣቶቹ የተናጠል ትኩረት ለማግኘት እንዲችሉ እያንዳንዱን ልጅ በግል ስለሚነኩ ችግሮችና ተፈታታኝ ሁኔታዎች ይወያያሉ።
ከወላጆቻቸው መንፈሳዊ ድጋፍ የማያገኙ ወጣቶች “አባቴና እናቴ ትተውኛልና፣ እግዚአብሔር ግን ተቀበለኝ” ከሚለው የመዝሙር 27:10 ጥቅስ ማጽናኛ ሊያገኙ ይችላሉ። የርኅራኄና የምህረት አባት የሆነው ይሖዋ ወጣቶችን የሚረዳው እንዴት ነው? የይሖዋ ምሥክሮችን ጉባኤዎች መጠጊያቸው አድርገው የሌሎችን ፍቅር ያገኙና ጥርጣሬያቸውን ያስወገዱ ሰዎች ብዙ ናቸው። እንዲህ ያለው ሁኔታ እውነት ሆኖ ያገኘው ሆሲያስ የተባለ ወጣት እንዲህ ይላል:- “የይሖዋ ድርጅት በጣም አስፈላጊ የሆነ ቦታ አለው። ሕይወት ፈጽሞ ከንቱ እንደሆነ ይሰማኝ ነበር። አለአንዳች ዓላማና ተስፋ እኖር ነበር። ብቻዬን አለመሆኔን ማወቄ ሕይወቴን ሙሉ በሙሉ ለወጠው። በጉባኤ ውስጥ ያሉት ወንድሞች ላጣሁት ቤተሰብ ምትክ ሆኑልኝ። ሽማግሌዎችና በጉባኤ ውስጥ ያሉት ቤተሰቦች የስሜት መዋዠቅ እንዳይደርስብኝ እንደ መልሕቅ ሆኑልኝ።”
ብዙ ወጣቶችና ትላልቅ ሰዎች በይሖዋ ምሥክሮች ስብሰባዎች አዘውትረው በመገኘታቸው የአእምሮና መንፈሳዊ ጤንነታቸው ተሻሽሎላቸዋል። አንትሮፖሎጂስቷ ፓትሪስያ ፎርቱኒ ሎስ ቴስቲጎስ ደ ጀሆቫ ኡና ኦልተርናቲቫ ሬሊጂዮሳ ፓራ ኤንፍሬንታር ኤል ፊን ዴል ሚሌኒዮ (የይሖዋ ምሥክሮች:- የዚህን ሺህ ዓመት ፍጻሜ ለመጋፈጥ የሚያስችል ሃይማኖታዊ አማራጭ) በሚል ርዕስ ባዘጋጁት ጥናታዊ ጽሑፍ “የይሖዋ ምሥክሮች በዕለታዊ ኑሮ ተግባራዊ የሚሆኑ ግልጽና የማያሻሙ ደንቦች፣ አስተሳሰቦችንና ድርጊቶችን የሚመሩ ቀጥተኛ ሕጎች አሏቸው።” . . . እዚህ ላይ የተጠቀሱት “ደንቦች” እና “ሕጎች” በመጽሐፍ ቅዱስ ላይ የተመሠረቱ ናቸው። የይሖዋ ምሥክሮች ጎረቤቶቻቸው የሚደርስባቸው ዓይነት ችግሮች የሚገጥሟቸው ቢሆንም ከዚህ ጥንታዊ መጽሐፍ የሚገኘው በዓይነቱ ልዩ የሆነ ጥበብ ያጠናክራቸዋል። አዎን፣ ምሥክሮቹ በመጽሐፍ ቅዱስ ውስጥ በሚገኙ ግልጽ መሠረተ ትምህርቶችና መሠረታዊ ሥርዓቶች መጠጊያ አግኝተዋል።
‘ሞት በማይኖርበት’ ጊዜ
በይሖዋ ምሥክሮች የመንግሥት አዳራሽ የሚሰጠው ትምህርት አምላክ ቃል የገባውና በቅርቡ የሚመጣው ‘ጽድቅ የሚኖርበትና’ አንድም የሚያስፈራ ነገር የማይኖርበት አዲስ ዓለም በተደጋጋሚ የሚያጎላ ነው። (2 ጴጥሮስ 3:13፤ ሚክያስ 4:4) ከዚህም በላይ ነቢዩ ኢሳይያስ አምላክ “ሞትን ለዘላለም ይውጣል፣ ጌታ እግዚአብሔርም ከፊት ሁሉ እንባን ያብሳል” ሲል ጽፏል። ሞት የሰው ልጆችን መቅሰፍ የጀመረው የመጀመሪያው ሰው አዳም በመተላለፉ ምክንያት ነው። ሆኖም አምላክ በቅርቡ ‘ሞት እንደሚቀር’ ቃል ገብቷል።—ኢሳይያስ 25:8፤ ራእይ 21:3, 4፤ ሮሜ 5:12
እርዳታ ማግኘት የምትፈልግ ወጣት ከሆንክ በመጽሐፍ ቅዱስ አማካኝነት ብሩህ ተስፋ እንዲኖርህና የሕይወት ዓላማ ምን እንደሆነ ታውቅ ዘንድ እንጋብዝሃለን። አምላክ ቃል በገባልን ወደፊት በሚመጣው አዲስ ዓለም ውስጥ የተሻለ ጊዜ እንደሚመጣ ተስፋ ታደርግ ዘንድ የይሖዋ ምሥክሮች ሊረዱህ ይችላሉ።
[የግርጌ ማስታወሻ]
^ አን.8 ኒው ዮርክ የሚገኘው የመጠበቂያ ግንብ መጽሐፍ ቅዱስና ትራክት ማኅበር ወጣቶች የሚጠይቋቸው ጥያቄዎች—እውነተኛ ጓደኛ ላፈራ የምችለው እንዴት ነው? የሚል የቪዲዮ ክር አውጥቷል። በአሁኑ ወቅት በእንግሊዝኛ የሚገኝ ሲሆን ለወጣቶች ተግባራዊ እርዳታ ይሰጣል።
[በገጽ 9 ላይ የሚገኝ ሥዕል]
ወላጆች ጊዜ ወስደው ልጆቻቸውን ማዳመጥና ችግሮቻቸውን መረዳት ይኖርባቸዋል
[በገጽ 10 ላይ የሚገኙ ሥዕሎች]
“የይሖዋ ምሥክሮች በዕለታዊ ኑሮ ተግባራዊ የሚደረጉ ግልጽ የሆኑና የማያሻሙ ደንቦች አሏቸው”