አገልጋይ የሚባለው ማን ነው?
የመጽሐፍ ቅዱስ አመለካከት
አገልጋይ የሚባለው ማን ነው?
በኢየሱስ መሥዋዕታዊ ሞት ዋዜማ በቅርብ ወዳጆቹ መካከል የጦፈ ክርክር ተነሳ። ሉቃስ 22:24 “ማናቸውም ታላቅ ሆኖ እንዲቆጠር በመካከላቸው ክርክር ሆነ” በማለት ይገልጻል። በኢየሱስ ሐዋርያት መካከል እንደዚህ ያለው ክርክር ሲነሳ ይህ ለመጀመሪያ ጊዜ አልነበረም። ኢየሱስ ከዚያ ቀደም ብሎ ቢያንስ ለሁለት ጊዜያት አስተሳሰባቸውን ማረም አስፈልጎት ነበር።
በዚያ ወሳኝ ምሽት ኢየሱስ አንድ ክርስቲያን አገልጋይ እንዴት መመላለስ እንዳለበት ለማሳሰብ መገደዱ የሚያሳዝን ነው። “ከእናንተ ታላቅ የሆነ በመካከላችሁ እንደ ታናሽ፣ የሚገዛም እንደሚያገለግል ይሁን” አላቸው።—ሉቃስ 22:26
ሐዋርያት ሥልጣንና ክብርን በተመለከተ የተሳሳተ አስተሳሰብ የነበራቸው መሆኑ ሊያስገርመን አይገባም። ከኢየሱስ ቀደም ብሎ በሃይማኖታዊ መሪነት ረገድ እንደ ምሳሌ የሚታዩት ጻፎችና ፈሪሳውያን ነበሩ። እነዚህ ሐሰተኛ አገልጋዮች ለሕዝቡ መንፈሳዊ አመራር መስጠት ሲገባቸው ‘መንግሥተ ሰማያትን በሰው ፊት የሚዘጋ’ ድርቅ ያለ ወግና ደንብ አረቀቁ። የሥልጣን ጥመኞች፣ የላቀ ክብር ፈላጊዎችና ራስ ወዳዶች በመሆናቸው ሥራቸውን የሚያደርጉት ‘ለታይታ’ ነበር።—ማቴዎስ 23:4, 5, 13
አዲስ ዓይነት አገልጋይ
ይሁን እንጂ ኢየሱስ ለደቀ መዛሙርቱ አዲስ ዓይነት መንፈሳዊ አገልግሎት አስተዋወቃቸው። እንደዚህ ብሎ አስተማራቸው:- “መምህር ተብላችሁ አትጠሩ፤ መምህራችሁ አንድ ስለ ሆነ እናንተ ሁላችሁ ወንድማማች ናችሁ። አባታችሁ አንድ እርሱም የሰማዩ ነውና በምድር ላይ ማንንም:- አባት ብላችሁ አትጥሩ። . . . ከእናንተ የሚበልጠው አገልጋያችሁ ይሆናል።” (ማቴዎስ 23:8-11) የኢየሱስ ደቀ መዛሙርት በዘመኑ የነበሩትን የሃይማኖት መሪዎች መምሰል አልነበረባቸውም። እውነተኛ አገልጋይ መሆን ከፈለጉ የኢየሱስን ምሳሌ መኮረጅ ነበረባቸው። ኢየሱስ ምን ዓይነት ምሳሌ ትቶላቸው ነበር?
መጽሐፍ ቅዱስ “አገልጋይ” ለማለት በአብዛኛው ዲያኮኖስ የሚለውን ግሪክኛ ቃል ይጠቀማል። ዚ ኢንሳይክሎፔዲያ ኦቭ ሪሊጅን ይህ ቃል የሚያመለክተው “ሥልጣንን ሳይሆን አገልጋዩ ለተገልጋዩ የሚሰጠውን አገልግሎት በተመለከተ በሁለቱ መካከል የሚኖረውን ግንኙነት ነው:- የኢየሱስን ምሳሌ ለመከተል . . . የአገልግሎትን ክርስቲያናዊ ትርጉም መረዳት ወሳኝ ነገር ነው” ሲል አብራርቷል።
ኢየሱስ “አገልጋይ” የሚለው ቃል ካለው ትክክለኛ ትርጉም ጋር በሚስማማ መንገድ ራሱን ማቴዎስ 20:28) ኢየሱስ ሌሎችን በአካላዊም ሆነ በመንፈሳዊ ለመርዳት ጊዜውን፣ ጉልበቱንና ችሎታውን ከራስ ወዳድነት ነፃ በሆነ መንገድ ተጠቅሞበታል። ለምን? ምክንያቱም ወደ እርሱ ይጎርፉ የነበሩት መንፈሳዊ ጉስቁልና የደረሰባቸው ሰዎች ሁኔታ ስላሳዘነው መርዳት ፈልጎ ነበር። አገልግሎቱን እንዲያከናውን ያንቀሳቀሰው ለእነርሱ የነበረው ያልተቆጠበ ፍቅር ሲሆን ደቀ መዛሙርቱም እንዲሁ የመስጠት ዝንባሌ እንዲያሳዩ ይፈልጋል።—ማቴዎስ 9:36
ለሌሎች ፍጹም ስጦታ አድርጎ አቅርቧል። ረጋ ብሎ “የሰው ልጅ ሊያገለግል ነፍሱንም ለብዙዎች ቤዛ ሊሰጥ እንጂ እንዲያገለግሉት አልመጣም” ሲል አስረዳቸው። (ኢየሱስ በመላው አኗኗሩ ወደፊት አገልጋይ ለሚሆኑ ሰዎች ምሳሌ ትቶላቸዋል። “መከሩስ ብዙ ነው፣ ሠራተኞች ግን ጥቂቶች ናቸው፤ እንግዲያው የመከሩን ጌታ ወደ መከሩ ሠራተኞችን እንዲልክ ለምኑት አላቸው።” (ማቴዎስ 9:37, 38) አዎን፣ የክርስቶስ አገልጋዮች ዓለም ከዚያ በፊት አይቶት የማያውቀውን ታላቅ ሥራ እንዲያከናውኑ ይኸውም የአምላክን መንግሥት ምሥራች በመስበክና በማስተማር ለመላው የሰው ዘር መንፈሳዊ ማጽናኛን እንዲሰጡ ይጠበቅባቸው ነበር።—ማቴዎስ 28:19, 20
ክርስቶስ ስለ አገልጋይነት ያለውን አመለካከት ልዩ የሚያደርገው ነገር ለሌሎች ጥቅም ሲባል የመስጠቱና የማገልገሉ ጉዳይ ነው። አገልጋዮቹን ያስተማራቸው ትጉህ ሠራተኞች፣ መንፈሳዊ ዓሣ አጥማጆችና እረኞች ሆነው እንዲያገለግሉ እንጂ የተለየ ልብስ የሚለብሱና አሸንክታብ የሚያጠልቁ የባህታዊ ሕይወት የሚመሩ እንዲሁም ልዩ መንፈሳዊ ትምህርት የተቀበሉ ሰዎች እንዲሆኑ አልነበረም።—ማቴዎስ 4:19፤ 23:5፤ ዮሐንስ 21:15-17
የመጽሐፍ ቅዱስ አመለካከት
የሚያሳዝነው ግን ዓመታት እያለፉ ሲሄዱ አገልጋይነት፣ የራስን ጥቅም መሥዋዕት በማድረግ መንፈስ መስበክና ማስተማር ነው የሚለው ትርጉም ሌላ መልክ እየያዘ መጣ። ክርስቲያናዊ አገልግሎት በሚል የተጀመረው ይህ ጉዳይ ቀስ በቀስ ግልጽ ወደ ሆነ የሥልጣን መዋቅር ተሸጋገረ። ደረጃና ማዕረግ ወጣ፤ እንዲሁም ለአንዳንዶች የላቀ ክብርና ሥልጣን ተሰጠ፤ እነርሱም ኪሳቸውን ማደለብን ሥራዬ ብለው ተያያዙት። ይህ ልዩነት ፈጠረ። የተዋቀረው የቀሳውስት ቡድን ትኩረት የሰጠው ሃይማኖታዊ የቁርባን ሥነ ሥርዓቶችን ለመምራትና ስህተት የሚሠሩ ሰዎችን ለመምከር ነበር። የመጀመሪያው መቶ ዘመን ክርስትና በቀጣዮቹ ዓመታት ሁሉም ክርስቲያኖች ንቁ አገልጋይ የሆኑበት ሃይማኖት መሆኑ ቀርቶ የተለየ ሥልጠና ያገኙና የተካኑ የሚባሉ እፍኝ የማይሞሉ ግለሰቦች ሰባኪና አስተማሪ የሆኑበት ሃይማኖት ሆነ።
ይሁን እንጂ መጽሐፍ ቅዱስ እንደሚያሳየው አንድ ክርስቲያን አገልጋይ የሚታወቀው በሚለብሰው የተለየ ልብስ፣ በሚያከናውነው ልዩ ሃይማኖታዊ ሥነ ሥርዓት፣ በሚከፈለው ደመወዝ መጠን ወይም መንግሥት በሚያወጣው ሕግ ሳይሆን ራስ ወዳድነት በሌለው ሥራው ነው። ሐዋርያው ጳውሎስ ክርስቲያን አገልጋዮች ሊያሳዩት ስለሚገባቸው ዝንባሌ ተናግሯል። ‘ከንቱ ውዳሴ በመሻት ምንም ነገር እንዳያደርጉ፤ ከዚህ ይልቅ በትሕትና እንዲመላለሱ’ አበረታቷቸዋል።—ፊልጵስዩስ 2:3
ጳውሎስ ራሱ ያስተማረውን ተግባራዊ እንዳደረገ የታወቀ ነው። ‘ብዙዎች ይድኑ ዘንድ ለጥቅማቸው እንጂ የራሱን ጥቅም ባለመፈለግ’ ክርስቶስ የተወውን ምሳሌ በጥብቅ ተከትሏል። “በወንጌል ካለኝ መብት በሙሉ እንዳልጠቀም” ሲል ከተናገረው መረዳት እንደሚቻለው “ወንጌልን ያለ ዋጋ” የመናገር ኃላፊነት እንዳለበት መገንዘቡን ያሳያል። ‘ከሰዎች ክብርን አልፈለገም።’—1 ቆሮንቶስ 9:16-18፤ 10:33፤ 1 ተሰሎንቄ 2:6
ይህ ለአንድ እውነተኛ ክርስቲያን አገልጋይ ግሩም አብነት ነው! የኢየሱስ ክርስቶስን ግሩም ምሳሌነት የሚኮርጁና ከራስ ወዳድነት ነፃ የሆነ አርዓያነቱን መከተል የሚፈልጉ ሰዎች ለሌሎች መንፈሳዊ እርዳታ ለመስጠትና አጽናኝ የሆነውን ምሥራች ለመስበክ ራሳቸውን ያለ ገደብ የሚያቀርቡ ከሆነ እውነተኛ የአምላክ አገልጋዮች መሆናቸውን እያሳዩ ነው።—1 ጴጥሮስ 2:21