ከዓለም አካባቢ
ከዓለም አካባቢ
የቁማር ሱስ በአውስትራሊያ
“ቁማር፣ በአውስትራሊያ ቢያንስ 330, 000 የሚሆኑ ሱሰኞችን በቀጥታ የሚያጠቃ ሥር የሰደደ የጤና ችግር እየሆነ መጥቷል” በማለት ዚ አውስትራሊያን የተባለው ጋዜጣ ዘግቧል። እንደ ጋዜጣው ዘገባ ከሆነ በዓለም ዙሪያ ከሚገኙት ኤሌክትሮኒክስ የቁማር መጫዎቻ ማሺኖች መካከል ከአምስቱ አንዱ የሚገኘው 82 በመቶ የሚሆኑት አዋቂዎች ቁማርተኛ በሆኑባት በአውስትራሊያ ነው። በአውስትራሊያ የሚገኘውን የቁማር ኢንዱስትሪ የሚያጠና አንድ ኮሚሽን 2.3 በመቶ የሚሆኑት አዋቂ አውስትራሊያውያን ሥር የሰደደ የቁማር ችግር እንዳለባቸው ደርሶበታል። ከእነዚህ መካከል 37 በመቶ የሚሆኑት ራሳቸውን ለመግደል ያስባሉ፣ ከ11 በመቶ የሚበልጡት ራስን የመግደል ሙከራ ያደርጋሉ እንዲሁም 90 ከመቶ የሚሆኑት ቁማር ከመጫወታቸው ጋር በተያያዘ ከፍተኛ የመንፈስ ጭንቀት ይሰቃያሉ። ኮሚሽኑ የቁማር ማጫዎቻዎችን በተመለከተ ማስተካከያዎች እንዲደረጉ ጥሪ ያቀረበ ሲሆን በቁማር ቤቶች ላይም የማስጠንቀቂያ ምልክቶች እንዲለጠፉ ሐሳብ አቅርቧል።
መርዝ ለቁንጅና
በአሁኑ ጊዜ የፊት መጨማደድን ለማስወገድ ቦቹሊነም የተባለውን አደገኛ መርዝ የሚያመነጩ ባክቴሪያዎችን በመውጋት የሚደረግ የመዋቢያ ሕክምና ሥራ ላይ መዋሉን ዘ ቶሮንቶ ስታር ዘግቧል። መርዙ የተመረጡ የፊት ላይ ጡንቻዎችን ሽባ ስለሚያደርግ ጡንቻዎቹ በጥቂት ቀናት ውስጥ የመኮማተር ኃይላቸውን ያጡና የተጨማደደው ይዘረጋል። ሕክምናው ለአራት ወራት ያህል የሚቆይ ሲሆን የበሽተኛው ፊት ይበልጥ የተዝናናና የወጣትነት መልክ ያለው ይሆናል። ይሁን እንጂ ይህ ዓይነቱ ሕክምና የሚያስከትለው ጉዳት አለው። ሪፖርቱ እንዳስጠነቀቀው “የዚህ ሕክምና ተጠቃሚዎች የቆዳቸውን መጨማደድ በሚያስወግዱበት ጊዜ በመደነቅ ቅንድባቸውን ወደ ላይ መግፋትም ሆነ በዓይናቸው አካባቢ ፈገግ የማለት መልክ የማሳየት ችሎታቸውን ያጣሉ።” ዘገባው “የወጣትነት ውበት ለማግኘት ሲባል የተወሰኑ የፊት ክፍሎችን ሽባ ለማድረግ” ዝግጁ የመሆን ጉዳይ ሲል ገልጿል።
ለልጆች ሥራ መስጠት
“በዛሬው ጊዜ ያሉት ሥራ የሚበዛባቸው ወላጆች ልጆቻቸው በቤት ውስጥ ሥራዎች እንዲረዷቸው የማድረግ ልማድ አላቸው” ይላል ዘ ቶሮንቶ ስታር። ምንም እንኳ ሥራ “ለልጆች ተቀዳሚው ምርጫ ሊሆን ባይችልም” ይላሉ ፖዘቲቭ ዲሲፕሊን የተባለው መጽሐፍ ደራሲ የሆኑት ጄን ኔልሰን፣ እንዲህ ያሉት ሥራዎች “በራስ የመተማመንና በራስ የመመካት መንፈስ ይገነባሉ።” ቻይልድ በተባለው መጽሔት ላይ የወጣ አንድ ጥናት እንዳመለከተው ከሆነ ለሁለትና ለሦስት ዓመት ሕፃናት የሚሰጡት አንዳንድ ቀላል የቤት ውስጥ ሥራዎች የአሻንጉሊት መጫወቻዎችን ማነሳሳትንና የቆሸሹ ልብሶችን ቅርጫት ውስጥ መጨመርን የሚያካትቱ ሊሆኑ ይችላሉ። ከሦስት እስከ አምስት ዓመት ባለው የዕድሜ ክልል ውስጥ የሚገኙ ሕፃናት ማዕድ የሚቀርብበትን ጠረጴዛ ሊያሰናዱ፣ ምግብ የተበላባቸውን ዕቃዎች ወደሚታጠቡበት ቦታ ሊወስዱና የሚጫወቱበትን አካባቢ ሊያጸዱ ይችላሉ። ከ5 እስከ 9 ዓመት ዕድሜ ያላቸው ሕፃናት የራሳቸውን አልጋ ሊያነጥፉ፣ የወዳደቁ ቅጠላ ቅጠሎችን ሊሰበስቡና አረሞችን ሊያርሙ የሚችሉ ሲሆን ከ9 እስከ 12 ዓመት ዕድሜ ያላቸው ደግሞ ዕቃ ማጠብና ማድረቅ፣ ቆሻሻ መድፋት፣ የግቢን ሣር ማጨድና ቤት ማጽዳትን የመሳሰሉ ሥራዎች ሊሠሩ ይችላሉ። “ሥራውን ሠርተው የሚያጠናቅቁበትን ጊዜ መመደቡ የተሻለ ውጤት ይኖረዋል” ሲሉ ኔልሰን አክለው ተናግረዋል።
ውጥረትን መዋጋት
ውጥረት ይሰማሃል? ኤል ዩኒቨርሳል የተባለው ጋዜጣ እንደዘገበው የሜክሲኮ ማኅበራዊ ዋስትና ተቋም የሚከተሉትን ውጥረት ለመዋጋት የሚረዱ መመሪያዎች ሰጥቷል:- ሰውነትህ የሚፈልገውን ማለትም በቀን ከስድስት እስከ አሥር ሰዓት እንቅልፍ አትንፈገው። የተሟላና የተመጣጠነ ቁርስ፣ መጠነኛ ምሳና ቀላል እራት ብላ። በተጨማሪም የመስኩ ጠበብት ቅባት መቀነስንና ጨውና በተለይ ከ40 ዓመት በኋላ የስኳርና የወተት ፍጆታህን በጣም መቀነስ እንደሚያስፈልግ ይመክራሉ። የምታሰላስልበት ፀጥ ያለ ጊዜ ለማግኘት ሞክር። በተጨማሪም ተፈጥሮን በመመልከት ውጥረትህን መቀነስ ትችላለህ።
“አምላክ የየትኛው ቡድን ደጋፊ ሊሆን ነው?”
የስፖርት አምድ አዘጋጅ የሆኑት ሳም ስሚዝ “የማንንም እምነት ለማንቋሸሽ ፈልጌ አይደለም። ይሁን እንጂ ይህ በስፖርት ሜዳዎች የሚታየው የሃይማኖተኝነት መልክ እንዲያው ቅጥ አላጣምን? ኳስ ተጫዋቾች ግብ ካገቡ በኋላ የሚጸልዩት ለምንድን ነው?” አንድ ላይ እጅብ ብለው የጸለዩት እነዚያው ተጫዋቾች ናቸው በመልበሻ ክፍል ውስጥ “ሪፖርተሮቻችንን ሲሳደቡ” ወይም በስፖርት ውድድሩ ውስጥ ጨዋታው በሚፋፋምበት ጊዜ “በሌሎች ተጫዋቾች ላይ ጉዳት ለማድረስ ሲሞክሩ” የሚታዩት። አምላክ ከአንደኛው ቡድን ሌላውን ያስበልጣል ብሎ ማሰብ “በአምላክ ላይ ማመንን የሚያቃልል ይመስላል” ብለዋል። ስለሆነም በዚህ ጽሑፍ አስተያየታቸውን ሲደመድሙ “ስፖርቶች ከስፖርትነት አልፈው ሃይማኖታዊ ትርጉም እንዲኖራቸው አናድርግ” ብለዋል።
አደገኛ የሥራ ዓይነቶች
እጅግ አደገኛ የሆኑት አሥር የሥራ ዓይነቶች የትኞቹ ናቸው? የዩናይትድ ስቴትስ የሥራ ስታትስቲክ ቢሮ ባጠናቀረው መረጃ መሠረት የአንደኛነቱን ቦታ የያዙት ዛፍ ቆራጮች ሲሆኑ ከ100, 000 ሠራተኞች መካከል በ129ኙ ላይ አደጋ ይደርሳል። በሁለተኛነትና በሦስተኛነት በቅርብ ርቀት የሚከተሉት ዓሣ አጥማጆችና የውኃ ላይ መጓጓዣ ሠራተኞች ሲሆኑ ከ100, 000 ሠራተኞች መካከል 123 እና 94 ሰዎች ለሞት አደጋ ይጋለጣሉ። በቀጣይነት የተመዘገቡ ሌሎች አደገኛ የሥራ ዓይነቶች የአውሮፕላን አብራሪዎች፣ የግንባታ ብረታ ብረት ሠራተኞች፣ የማዕድን ሠራተኞች፣ የግንባታ የጉልበት ሠራተኞች፣ የታክሲ አሽከርካሪዎች፣ የከባድ መኪና አሽከርካሪዎችና የእርሻ ሠራተኞች ናቸው። ይሁን እንጂ “በአጠቃላይ በሥራ ላይ የሚደርስ የሞት አደጋ” ባለፉት አምስት ዓመታት 10 በመቶ የቀነሰ ሲሆን ከ100, 000 ሠራተኞች መካከል ለሞት አደጋ የሚጋለጡት 4.7 የሚሆኑት እንደሆኑ” ሳይንቲፊክ አሜሪካን ዘግቧል።
የትልቅ ሶል ፋሽን?
“ፋሽን የሚከተሉ ወጣቶችን ቀልብ በሳቡት” ትልቅ ሶል ያላቸው ጫማዎችና ረጅም ተረከዝ ባላቸው ጫማዎች ሳቢያ በብሪታንያ በዓመት ውስጥ ወደ 10, 000 የሚጠጉ አካላዊ ጉዳቶች ይደርሳሉ ይላል የለንደኑ ዘ ታይምስ። የብሪታንያ ደረጃ መዳቢ ተቋም ቃል አቀባይ የሆኑት ስቲቭ ታይለር “በአብዛኛው የሚደርሰው ጉዳት የቁርጭምጭሚት ወለምታና የእግር መሰበር ቢሆንም እነዚህ ጫማዎች በተለይ ገና በማደግ ላይ ባሉት ወጣት ልጃገረዶች ላይ የወገብ ሕመም ሊያስከትሉ ይችላሉ” ሲሉ ተናግረዋል። ከጥቂት ወራት በፊት በጃፓን ትልቅ ሶል ያላቸው ጫማዎች ባስከተሉት ጦስ ሁለት ሴቶች ሕይወታቸው አልፏል። አንደኛዋ በመዋዕለ ሕፃናት ትሠራ የነበረች የ25 ዓመት ሴት ስትሆን አሥራ ሁለት ሴንቲ ሜትር ከፍታ ያለው ክፍት ጫማ አድርጋ ስትሄድ ተደናቅፋ በመውደቋ የራስ ቅሏ ተሰንጥቆ ልትሞት ችላለች። ሌላዋ ወጣት ደግሞ በመኪና ስትጓዝ መኪናውን አሥራ አምስት ሴንቲ ሜትር ከፍታ ያለው ቦት ጫማ አድርጋ ታሽከረክር የነበረችው ሴት ፍሬን በትክክል መያዝ ባለመቻሏ መኪናው ከሲሚንቶ ምሰሶ ጋር ተጋጭቶ ሕይወቷ ሊያልፍ ችሏል። አንዳንድ አምራቾች ክስ እንዳይመሠረትባቸው ለመከላከል ሲሉ በሚያመርቷቸው ጫማዎች ላይ የማስጠንቀቂያ ምልክቶች መለጠፍ ጀምረዋል።
እንጨት ሰርሳሪ ተርቦች
ኢክኒዩመን ተብለው የሚጠሩት ተርቦች “ወደ አዮን በተለወጠ ማንጋኒዝ ወይም ዚንክ የጠነከረ” እንቁላል መጣያ አካል አላቸው ሲል ናሽናል ጂኦግራፊክ ዘግቧል። ተርቦቹ በባዳስጠጌ (host) እጮች አካል ላይ ወይም ሰውነታቸው ውስጥ እንቁላላቸውን ለመጣል ይህን የብረት መሣሪያቸውን በመጠቀም የዛፎችን ግንድ ይሰረስራሉ። “አንዳንዶቹ ተርቦች አንድን ጠንካራ እንጨት እስከ ሰባት ሴንቲ ሜትር ሊሰረስሩ ይችላሉ” ሲሉ የብሪታንያ ኢምፔሪያል ኮሌጅ ባልደረባ የሆኑት ዶናልድ ክዊክ ተናግረዋል። ተርቦቹ ሲፈለፈሉ በግንዱ ውስጥ የሚገኙትን እጮች ይበሉና ከበሏቸው እጮች ባገኟቸው ማዕድናት የጠነከረውን የአፋቸውን ክፍል በመጠቀም ዛፉን እየሰረሰሩ ይወጣሉ።
ወጣቶችና ወንጀል
የስኮትላንድ መንግሥታዊ አካል ያካሄደው አንድ ጥናት እንዳመለከተው በስኮትላንድ ውስጥ ባለፈው ዓመት ከ14 እስከ 15 ዓመት ባለው የዕድሜ ክልል ውስጥ የሚገኙ 85 በመቶ የሚሆኑ ወንዶች ልጆችና 67 በመቶ የሚሆኑ ልጃገረዶች ወንጀል ፈጽመዋል። ዘ ሄራልድ የተባለው የግላስጎው ጋዜጣ ጥናት ከተካሄደባቸው በስድስት ትምህርት ቤቶች ውስጥ ከሚገኙ 1, 000 ተማሪዎች መካከል ምንም ዓይነት ወንጀል ፈጽመው እንደማያውቁ የተናገሩት 12 በመቶዎቹ ብቻ እንደሆኑ ዘግቧል። ወንጀል ከፈጸሙት ተማሪዎች መካከል 69 በመቶ የሚሆኑት ወንዶች ልጆችና 56 በመቶ የሚሆኑት ልጃገረዶች በንብረት ላይ ጉዳት አድርሰዋል። ወደ 66 በመቶ የሚጠጉት ወንዶች ልጆችና 53 በመቶ የሚሆኑት ልጃገረዶች ከሱቅ ዕቃ የሰረቁ ሲሆን ግማሽ ያህል የሚሆኑት ተማሪዎች ደግሞ ከትምህርት ቤት ሰርቀዋል። ሌሎቹ የወንጀል ዓይነቶች ደግሞ በንብረት ላይ እሳት መለኮስንና መሣሪያ ተጠቅሞ ጉዳት ማድረስን የሚጨምሩ ናቸው። በዚህ የዕድሜ ክልል ውስጥ የሚገኙት ወጣቶች ወንጀል እንዲፈጽሙ ዋነኛ ምክንያት የሆናቸው ነገር የእኩዮች ተጽዕኖ እንደሆነ የገለጹ ሲሆን ከ15 ዓመት በላይ የሆኑ ወጣቶች ግን በአብዛኛው ወንጀል የሚፈጽሙት የአደገኛ ዕፅ ሱሳቸውን ለማርካት የሚያስችላቸው ገንዘብ ለማግኘት ሲሉ ነው።
በጥባጭ ተማሪዎች
ቀደም ሲል በጃፓን በአሥራዎቹ የዕድሜ ክልል ውስጥ የሚገኙ ወጣቶች የዓመፅ ድርጊት ሲፈጽሙ እምብዛም አይታይም ነበር። ዛሬ ዛሬ ግን በመላዋ ጃፓን የሚገኙ አስተማሪዎች ቁንጥንጥና በጥባጭ በሆኑ ተማሪዎች ሳቢያ በክፍል ውስጥ ፀጥታን ማስከበር አስቸጋሪ እየሆነ እንደመጣ ሪፖርት አድርገዋል። የቶኪዮ ከተማ አስተዳደር ለሌሎች ሰዎች ያላቸውን ስሜት ለማወቅ የ9፣ የ11 እና የ14 ዓመት ተማሪዎችን አነጋግሮ ነበር። ዘ ዴይሊ ዮሚዩሪ እንዳለው ከሆነ 65 በመቶዎቹ በጓደኞቻቸው፣ 60 በመቶዎቹ በወላጆቻቸውና 50 በመቶዎቹ ደግሞ በአስተማሪዎቻቸው እንደተማረሩና እንደተሰላቹ ተናግረዋል። አርባ በመቶ የሚሆኑት በአብዛኛው ወይም ከናካቴው ቁጣቸውን መቆጣጠር እንደሚሳናቸው ገልጸዋል። ከ5 ተማሪዎቹ አንዱ ወይም አንዷ ቁጣቸውን የሚገልጹት ዕቃ በመስበር ነው።