ከፈንጂዎች የጸዳች ምድር
ከፈንጂዎች የጸዳች ምድር
ፈንጂዎች የሚያስከትሉትን ችግር ለዘለቄታው ሊያስወግድልን የሚችለው ማን ነው? እንደተመለከትነው የሰው ልጆች ጥረት ጥላቻን፣ ስግብግብነትን፣ ስስትን ከሥሩ ነቅሎ ሊያስወግድ አይችልም። ይሁን እንጂ መጽሐፍ ቅዱስን የሚማሩ ሰዎች ፈጣሪ ዘላቂ መፍትሔ እንደሚያመጣ ይገነዘባሉ። ግን ይህን ሊያደርግ የሚችለው እንዴት ነው?
ሰላማዊ የሆነ ኅብረተሰብ ማቋቋም
ጦርነቶች የሚካሄዱት በሰዎች እንጂ በጦር መሣሪያዎች አይደለም። ስለዚህ ሰላም ሰፍኖ ለማየት ከፈለግን የሰው ልጆችን በጎሣ፣ በዘር፣ በብሔር የሚከፋፍለው ጥላቻ ሙሉ በሙሉ መወገድ አለበት። አምላክ በመላው ምድር የሚኖሩ በሚልዮን የሚቆጠሩ ሰዎች በሚጸልዩለት መንግሥቱ አማካኝነት ይህንን እንደሚያከናውን ቃል ገብቷል።—ማቴዎስ 6:9, 10
መጽሐፍ ቅዱስ ይሖዋ ‘የሰላም አምላክ’ እንደሆነ ይናገራል። (ሮሜ 15:33) አምላክ የሚሰጠን ሰላም በእገዳዎችና በስምምነቶች ላይ ወይም በሚገባ የታጠቀ የጠላት ብሔር የሚያደርሰውን በቀል በመፍራት ላይ የተመሠረተ ሰላም አይደለም። ከዚህ ይልቅ አምላክ የሚሰጠው ሰላም ሰዎች ለሌሎች የሰው ልጆች በሚኖራቸው አስተሳሰብና ዝንባሌ ላይ በሚመጣ ለውጥ የሚገኝ ነው።
ይሖዋ አምላክ ቅን ሰዎችን በእሱ የሰላም መንገድ ያስተምራቸዋል። (መዝሙር 25:9) ቃሉ መጽሐፍ ቅዱስ በምድር ላይ የሚኖሩ ሁሉ ‘ከይሖዋ የተማሩ የሚሆኑበትና የልጆቹ ሰላም ብዙ የሚሆንበት’ ጊዜ እንደሚመጣ ተስፋ ይሰጣል። (ኢሳይያስ 54:13) ይህ በአሁኑ ጊዜ እንኳ መጠነኛ ፍጻሜ በማግኘት ላይ ነው። የይሖዋ ምሥክሮች በመላው ዓለም በጣም የተለያየ መሠረት ያላቸው ሰዎች እንኳን በሰላምና በአንድነት እንዲኖር በማስቻላቸው የታወቁ ሆነዋል። በጣም ከፍተኛ የሆኑትን የመጽሐፍ ቅዱስ መሠረታዊ ሥርዓቶች የተማሩ ሰዎች በመካከላቸው ምንም ዓይነት የሚከፋፍሉ ሁኔታዎች ቢኖሩም በአንድነትና በሕብረት ለመኖር ጥረት ያደርጋሉ። የሚያገኙት የመጽሐፍ ቅዱስ ትምህርት የነበራቸውን የጥላቻ አመለካከት ለውጦ ፍቅር እንዲኖራቸው ያደርጋል።—ዮሐንስ 13:34, 35፤ 1 ቆሮንቶስ 13:4-8
የጦር መሣሪያዎችን ለማስወገድ ከትምህርት በተጨማሪ ዓለም አቀፍ ሕብረትና አንድነት መኖሩ በጣም አስፈላጊ እንደሆነ ከታወቀ ብዙ ጊዜ ሆኗል። ለምሳሌ ዓለም አቀፉ የቀይ መስቀል ኮሚቴ የተቀበሩ ፈንጂዎች የሚያስከትሉትን አደጋ ለመከላከል ብሎም ለማስወገድ የሚያስችል እርምጃ ለመውሰድ አንድ ሆኖ የሚሠራ ዓለም አቀፍ ማኅበረሰብ ማቋቋም አስፈላጊ እንደሆነ አሳስቧል።
ይሖዋ ከዚያም የላቀ ነገር ለማድረግ ቃል ገብቷል። ነቢዩ ዳንኤል እንዲህ ሲል ተንብዮአል:- “የሰማይ አምላክ ለዘላለም የማይፈርስ መንግሥት ያስነሳል። . . . እነዚያንም መንግሥታት ሁሉ ትፈጫቸዋለች ታጠፋቸውማለች ለዘላለምም ትቆማለች።”—ዳንኤል 2:44
የአምላክ መንግሥት የሰው ልጅ ማድረግ ያቃተውን ያደርጋል። ለምሳሌ ያህል መዝሙር 46:9 እንዲህ ሲል ይተነብያል:- “[ይሖዋ] እስከ ምድር ዳርቻ ድረስ ጦርነትን ይሽራል። ቀስትን ይሰብራል። ጦርንም ይቆርጣል። በእሳትም ጋሻን ያቃጥላል።” የአምላክ መንግሥት የሰው ልጅ ከፈጣሪውም ሆነ እርስ በርሱ እውነተኛ ሰላም አግኝቶ የሚኖርበት አየር እንዲሰፍን ያደርጋል።—ኢሳይያስ 2:4፤ ሶፎንያስ 3:9፤ ራእይ 21:3, 4፤ 22:2
ባለፈው ርዕስ መግቢያ ላይ የተመለከትነው አውግስቶ በዚህ የመጽሐፍ ቅዱስ መልእክት ተጽናንቷል። የይሖዋ ምሥክሮች የሆኑት ወላጆቹ መጽሐፍ ቅዱስ በሚሰጣቸው አስደናቂ ተስፋዎች እንዲያምን እየረዱት ነው። (ማርቆስ 3:1-5) እርግጥ በአሁኑ ጊዜ አካሉን ያጎደለው ፈንጂ ያደረሰበትን ጉዳት እንደተሸከመ ለመኖር ተገድዷል። ቢሆንም አውግስቶ አምላክ ምድርን ገነት ለማድረግ የሰጠው ተስፋ እውን የሚሆንበትን ጊዜ በናፍቆት በመጠባበቅ ላይ ነው። በዚያ ጊዜ ነቢዩ ኢሳይያስ እንደተነበየው “የእውሮች ዓይን ይገለጣል፣ . . . አንካሳ እንደ ሚዳቋ ይዘልላል።”—ኢሳይያስ 35:5, 6
በዚህች ወደፊት በምትመጣዋ ገነት ፈንጂዎች በሕይወትም ላይ ሆነ በእጅና እግር ላይ ጉዳት ያደርሳሉ የሚል ስጋት አይኖርም። ከዚህ ይልቅ በምድር ማዕዘናት የሚኖሩ ሁሉ ተማምነውና ተረጋግተው በሰላም ይኖራሉ። ነቢዩ ሚክያስ እንዲህ ሲል ገልጾታል:- “ሰው እያንዳንዱ ከወይኑና ከበለሱ በታች ይቀመጣል፤ የሚያስፈራውም የለም።”—ሚክያስ 4:4
የአምላክ ቃል በሆነው በመጽሐፍ ቅዱስ ውስጥ ስለተገለጹት አምላክ ለሰው ልጆች ስለሰጣቸው ተስፋዎች ይበልጥ ለማወቅ ይፈልጋሉን? በአካባቢዎ የሚገኙ የይሖዋ ምሥክሮችን አነጋግሯቸው ወይም በገጽ 5 ላይ ከሚገኙት አድራሻዎች ወደ አንዱ ይጻፉ።
[በገጽ 8, 9 ላይ የሚገኝ ሥዕል]
በአምላክ መንግሥት አገዛዝ ሥር የተቀበሩ ፈንጂዎች ጉዳት ያስከትላሉ የሚል ስጋት አይኖርም