ከዓለም አካባቢ
ከዓለም አካባቢ
እሳት በማስነሳት የተወነጀሉ ቁራዎች
ካማኢሺ ጃፓን ውስጥ ቁራዎች ሁለት የእሳት አደጋዎች ሳያስነሱ እንዳልቀሩ ተገምቷል። አንደኛው የእሳት አደጋ በአንድ የመቃብር ሥፍራ አቅራቢያ የተነሳ ሲሆን በእሳት የተያያዘውን ሣር ለማጥፋት የሄዱ የእሳት አደጋ ሠራተኞች ድርጊቱን ቁራዎች እንደፈጸሙት የሚያመለክት ማስረጃ አግኝተዋል። ኒኬ ሺምቡን እንዲህ ሲል ገልጿል:- “ቁራዎቹ በአንድ መቃብር ላይ የተቀመጡ ጣፋጭ ምግቦችን አንስተው ሲበርሩ ወዲያውኑ እነሱ በሄዱበት አቅጣጫ እሳት ተነሳ። እየነደዱ እንዳሉ ከተተዉት የዕጣን ማጨሻ ጭራሮዎች መካከል አንዳንዶቹ ካለመገኘታቸውም በላይ እሳት በተነሳበት ቦታ ላይ ቁራዎቹ የጣሏቸው ናቸው ተብለው የተገመቱ ከረሜላዎች ተገኝተዋል።” ከአንድ ዓመት ገደማ በኋላ በዚያው አካባቢ በአንድ ተራራ አጠገብ እሳት እንደተነሳ ዴይሊ ዮሚዩሪ የተባለው ጋዜጣ ዘግቧል። በዚያ ቦታ አንድ የእሳት አደጋ መከላከያ ሠራተኛ አንድ ቁራ እየነደደ ያለ ካርቶን በአፉ ይዞ ሲበርና በአቅራቢያው በሚገኝ ወንዝ ውስጥ ሲጥለው ተመልክቷል። የእሳት አደጋ መከላከያ ሠራተኞች እሳቱ መጀመሪያ በተነሳበት ቦታ አቅራቢያ ሌላ የተቃጠለ ካርቶን አግኝተዋል። በዚህኛው ወቅት ቁራዎቹ በእሳት የተያያዘውን ካርቶን ያገኙት ከየት ሊሆን ይችላል? በአቅራቢያው የሚኖር አንድ ሰው ባዶ የድንች ጥብስ ካርቶኖችን በከሰል ማንደጃ ላይ ሲያቃጥል እንደነበረ ታውቋል።
በውትድርና ዓለም የተሰማሩ ተጨማሪ ልጆች
“ልጆችን ወደ ጦርነት የማሰማራቱ ተግባር እንደቀጠለ ሲሆን ከሁለትና ሦስት ዓመት በፊት በጦርነቶች ውስጥ የሚካፈሉት ልጆች ቁጥር 250, 000 የነበረ ሲሆን በአሁኑ ጊዜ ግን ወደ 300, 000 እንደደረሰ ይገመታል” ሲል መንግሥታዊ ባልሆነው የተባበሩት መንግሥታት አገናኝ አካል የሚታተመው ጎ ቢትዊን የተባለው ጽሑፍ ገልጿል። ዕድሜያቸው እስከ ስምንት ዓመት የሚደርስ በውትድርና ዓለም የተሰማሩ ልጆች በአሁኑ ጊዜ በዓለም ዙሪያ በሚካሄዱ ከ30 በሚበልጡ ጦርነቶች ውስጥ በመሳተፍ ላይ ናቸው። በልጆችና በትጥቅ ትግል ጉዳይ የተመድ ዋና ጸሐፊ ልዩ መልእክተኛ የሆኑት ኦላራ ኦቱኑ እንዳሉት ከሆነ “ልጆች የጦርነት መሣሪያዎች ሆነው እንዲያገለግሉ ይገደዳሉ። ወታደሮች እንዲሆኑ ይመለመላሉ ወይም ታፍሰው ይወሰዳሉ። በመሆኑም የዐዋቂዎችን የጥላቻ ስሜት በኃይል እርምጃ ለመተግበር ይገደዳሉ።” እያሻቀበ ያለውን በውትድርና ዓለም የሚሰማሩ ልጆች ቁጥር ለመግታት የተባበሩት መንግሥታት የሕፃናት መርጃ ድርጅት “ለጦር ኃይሎች የሚመለመሉ ወጣቶች ዕድሜ ከ18 ዓመት በላይ እንዲሆንና ዕድሜያቸው ከዚያ በታች የሆኑ ልጆችን መመልመል የጦር ወንጀል ተደርጎ እንዲታይ” የሚያደርገውን ሐሳብ የደገፈው መሆኑን ፋክትስ ኤንድ ፊገርስ 1998 የተባለው ጽሑፍ ገልጿል።
ጉንፋንን መከላከል ትችላለህን?
ጉንፋንን ሙሉ በሙሉ መከላከል አትችል ይሆናል፤ ሆኖም ልትወስዳቸው የምትችላቸው ቅድመ ጥንቃቄዎች አሉ ይላል ዘ ኒው ዮርክ ታይምስ። የሚከተሉት እርምጃዎች በጣም ወሳኝ ናቸው:- በተቻለ መጠን ሰዎች በብዛት ከሚገኙበት ቦታ ለመራቅ ሞክር፣ በተጨማሪም ጉንፋን የያዛቸውን ሰዎች ላለመጨበጥ ጥንቃቄ አድርግ። ከዚህም ሌላ ዓይህንና አፍንጫህን አትሽ። እጆችህንም ቶሎ ቶሎ ታጠብ። እጆች ብዙውን ጊዜ የጉንፋን ቫይረሶችን በቀላሉ ሊጎዱ ወደሚችሉ የዓይንና የአፍንጫ ገለፈቶች ስለሚያሸጋግሩ እንዲህ ዓይነቶቹን ቅድመ ጥንቃቄዎች መውሰዱ ጠቃሚ ነው። በሆነ ገጽ ላይ ወይም በእጅ ላይ ያሉ የጉንፋን ቫይረሶች ረዘም ላለ ሰዓት ሕያው ሆነው መቆየት የሚችሉ ከመሆኑም በላይ አንድ ጉንፋን የያዘው ሰው የበሽታው ምልክቶች ከመታየታቸው በፊትና በኋላ ባሉት የተወሰኑ ጊዜያት በሽታውን ሊያስተላልፍ ይችላል። ሌሎቹ ቅድመ ጥንቃቄዎች ደግሞ የተመጣጠነ ምግብ መብላትና ከልጆች ጋር በምትሆንበት ጊዜ ይበልጥ ጥንቃቄ ማድረግን የሚጨምሩ ናቸው። ለምን? ምክንያቱም ልጆች በዓመት ውስጥ ከአምስት እስከ ስምንት ጊዜ ያህል በጉንፋን ይያዛሉ!
ኤድስ—“ግንባር ቀደሙ ተዛማች ቀሳፊ በሽታ”
“በአሁኑ ጊዜ ተዛማች ከሆኑ በሽታዎች መካከል ብዙ ሰዎችን ለሕልፈተ ሕይወት በመዳረግ ረገድ ኤድስ ተወዳዳሪ አልተገኘለትም” ሲሉ የተባበሩት መንግሥታት የኤድስ ፕሮግራም ዋና ዲሬክተር የሆኑት ፒተር ፕዮ ተናግረዋል። ሳይንስ መጽሔት ሪፖርት እንዳደረገው በ1997 ኤድስ በዓለም አቀፍ ደረጃ የብዙ ሰዎችን ሕይወት በመቅጠፍ ረገድ የሰባተኛነትን ደረጃ ይዞ ነበር። በ1998 ግን ደመከል (ischemia) ተብሎ ከሚጠራው የልብ በሽታ፣ ከሴሪብሮቫስኩላር በሽታና አጣዳፊ ከሆነው የታችኛዎቹ መተንፈሻ አካላት በሽታ በስተቀር ከሌሎቹ ሁሉ በልጦ ተገኝቷል። እነዚህኛዎቹ በሽታዎች ደግሞ ተዛማች አይደሉም። በተጨማሪም ኤድስ በአፍሪካ ውስጥ ተዛማጅ ካልሆኑትም በሽታዎች ሁሉ በልጦ ቁጥር አንድ ቀሳፊ በሽታ ሆኗል። ባለፈው ዓመት በአፍሪካ ውስጥ ብቻ ኤድስ 1, 830, 000 ገደማ የሚሆኑ ሰዎችን ሕይወት የቀጠፈ ሲሆን ይህም በዚህ አህጉር ውስጥ ብዙ ሰዎችን ለሕልፈተ ሕይወት በመዳረግ ሁለተኛውን ደረጃ የያዘው የወባ በሽታ ከገደላቸው ሰዎች ቁጥር ጋር ሲነጻጸር በሁለት እጥፍ ይበልጣል።
ከመጠን በላይ መወፈር የሚያስከትላቸው ጉዳቶች
“በአውሮፓ ውስጥ እንደ ወረርሽኝ እየተስፋፋ ባለው ከመጠን በላይ የመወፈር ችግር” የተነሳ የስኳር በሽታ፣ የልብ በሽታና ሌሎችም በሽታዎች በከፍተኛ ሁኔታ እንደሚጨምሩ ይጠበቃል ሲል የለንደኑ ዘ ኢንዲፔንደንት ዘግቧል። ከመጠን በላይ የመወፈርን ችግር ለማስወገድ የተቋቋመው ዓለም አቀፍ ግብረ ኃይል ሊቀመንበር ሚላን፣ ኢጣሊያ ውስጥ ከ26 አገሮች ለተውጣጡ የሕክምና ጠበብት ባደረጉት ንግግር “ይህ ዓለም አቀፍ ቀውስ ነው። ከባድ ሕመምና ከጊዜ ወደ ጊዜ እየጨመሩ የሚሄዱ የጤና እክሎች የሚያስከትለውን ይህን ስውር ወረርሽኝ ለመከላከል አፋጣኝ እርምጃ መውሰድ ያሻል። እርምጃ ካልወሰድን ከባድ የጤና ችግር ይጠብቀናል” ብለዋል። ይህ ችግር በሁሉም የአውሮፓ አገሮች የተከሰተ ሲሆን በአንዳንድ አገሮች ከ40 እስከ 50 በመቶ የሚሆነው ሕዝብ የዚህ ችግር ተጠቂ ሆኗል። እንግሊዝ ውስጥ ከ1980 ጀምሮ ከመጠን በላይ የሚወፍሩት ሴቶች ቁጥር ከ8 በመቶ ወደ
20 በመቶ ያደገ ሲሆን የወንዶቹ ቁጥር ደግሞ ከ6 ወደ 17 በመቶ አድጓል። ለዚህ በምክንያትነት ከተጠቀሱት ነገሮች መካከል አብዛኛውን ጊዜ በመቀመጥ ማሳለፍና ቅባት የበዛባቸው ምግቦች መብላት ይገኙባቸዋል። ሁለቱም እያደገ ከመጣው ብልጽግና ጋር ዝምድና ያላቸው ነገሮች ናቸው። ከሁሉ ይበልጥ አሳሳቢ የሆነው ደግሞ ከመጠን በላይ ወፍራም የሆኑ ልጆች እየተበራከቱ መምጣታቸው ነው። በውፍረት ላይ ምርምር የሚያካሂደው የአውሮፓ ማኅበር ፕሬዚዳንት የሆኑት ፕሮፌሰር ያፕ ዛይዴል እንዳሉት ከሆነ “ከቀጣዩ ትውልድ መካከል አብዛኛው ገና በለጋ ዕድሜው ከልክ በላይ እንደሚወፍርና ክብደት እንደሚጨምር የሚጠቁሙ ምልክቶች አሉ።”መሣሪያ መታጠቅ ያለው አደጋ
“የዘራፊዎች ጥቃት ሰለባ የሆኑ መሣሪያ የታጠቁ ባለ መኪናዎች መሣሪያ ከማይታጠቁት ጋር ሲነፃፀሩ በጥይት ሊመቱ የሚችሉበት አጋጣሚ አራት እጥፍ ገደማ ይበልጣል” ሲል ዘ ናታል ዊትነስ የተባለው የደቡብ አፍሪካ ጋዜጣ ገልጿል። “መሣሪያ የታጠቁ የዚህ ጥቃት ሰለባዎች መሣሪያውን ሊነጠቁ የሚችሉበት አጋጣሚ መሣሪያውን ሊጠቀሙበት ከሚችሉበት አጋጣሚ ጋር ሲነፃፀር አራት እጥፍ ይበልጣል” ሲል ዘገባው አክሎ ተናግሯል። በፖሊስ ጣቢያ በሚገኙ ሰነዶች ላይ በተካሄደው ምርመራ እንደተረጋገጠው ጥቃቱን የሚሰነዝሩት ሰዎች የጥቃታቸው ሰለባ በሆኑት ሰዎች ላይ መሣሪያ የተኮሱት 12 በመቶ የሚሆኑትን የወንጀል ድርጊቶች ሲፈጽሙ ብቻ ነው። ይሁን እንጂ የጥቃቱ ሰለባዎች ራሳቸውን ለመከላከል መሣሪያ በሚመዙበት ጊዜ ወንጀለኞቹ መሣሪያቸውን የሚተኩሱበት አጋጣሚ ወደ 73 በመቶ ከፍ ይላል። ተመራማሪው አንቶኒ አልትቤከር “መሣሪያ መያዝ ደህነት እንዲሰማችሁ ሊያደርግ ቢችልም ችግር ሲፈጠር ግን ለደህንነት ዋስትና አይሆንም” ሲሉ ደምድመዋል።
የተበከለ ዝናብ
በአውሮፓ ውስጥ ከፍተኛ መጠን ያላቸው የሟሙ የተባይ ማጥፊያ መድኃኒቶች አንዳንዱ የዝናብ ውኃ ለመጠጥ ውኃነት እንዳያገለግል እንቅፋት ሆነዋል ሲል ኒው ሳይንቲስት የተባለው መጽሔት ዘግቧል። በስዊዘርላንድ የሚገኙ ኬሚስቶች ኃይለኛ ዝናብ በሚዘንብበት ጊዜ በመጀመሪያዎቹ ደቂቃዎች ላይ ከሚወርደው ዝናብ ላይ የወሰዷቸው ናሙናዎች ብዙውን ጊዜ በአውሮፓ ኅብረትም ሆነ በስዊዘርላንድ ተቀባይነት ካለው ደረጃ በበለጠ ከፍተኛ መጠን ያላቸው የተባይ ማጥፊያ መድኃኒቶች ያሏቸው ሆነው ተገኝተዋል። ለዚህ መንስኤ ተደርገው የተጠቀሱት በሰብሎች ላይ የሚረጩት የተባይ ማጥፊያ መድኃኒቶች ሲሆኑ የእነዚህ መርዘኛ ኬሚካሎች ከፍተኛ ክምችት የሚታየው ረዘም ካለ ደረቅ ወቅት በኋላ ለመጀመሪያ ጊዜ ሲዘንብ ነው። ይህ በእንዲህ እንዳለ የስዊድን ተመራማሪዎች የካንሰር ዓይነት የሆነው ሊምፎሳይቲክ ሊምፎማ በከፍተኛ ፍጥነት እየጨመረ መምጣቱ በስፋት ጥቅም ላይ ከዋሉት በሰብል ላይ የሚረጩ በርካታ የተባይ ማጥፊያ መድኃኒቶች ጋር ዝምድና እንዳለው ይናገራሉ። በጣሪያዎች ላይ ቅጠላ ቅጠሎች እንዳያድጉ የሚከላከሉ ኬሚካሎችም ከሕንፃዎች ላይ የሚወርደውን የዝናብ ውኃ ይበክሉታል።
ለየት ያሉ የኃይል ምንጮች
▪ በኒው ካሊዶኒያ የምትገኘው የዩቬያ ደሴት ነዳጅ ዘይት ባይኖራትም እንኳ የኤሌክትሪክ ኃይል ለማመንጨት የኮከናት ዘይት ትጠቀማለች ሲል ሳይንስ ኤ አቭኒር የተባለው የፈረንሳይ መጽሔት ዘግቧል። ፈረንሳዊው መሃንዲስ አላን ልዬናር በኮከናት ዘይት የሚንቀሳቀስ ሞተር ለመሥራት 18 ዓመት ወስዶባቸዋል። ሞተሩ ጀነሬተር የሚያንቀሳቅስ ሲሆን ጀነሬተሩ ደግሞ በደሴቷ ውስጥ ለሚኖሩት 235 ቤተሰቦች የመጠጥ ውኃ የሚያቀርበውን የውኃ ማጣሪያ ፋብሪካ ያንቀሳቅሳል። ልዬናር ባለ 165-ኪሎዋት መሣሪያቸው በኃይል ውጣት (output) እና በነዳጅ ፍጆታ ከዲዝል ሞተሮች እንደማይተናነስ ይናገራሉ።
▪ ይህ በእንዲህ እንዳለ በሕንድ ጉጃራት ግዛት ካላሊ መንደር ውስጥ በተካሄደ አንድ ሙከራ የወይፈኖች ጉልበት የኤሌክትሪክ ኃይል ለማመንጨት ጥቅም ላይ ውሏል። የኒው ዴልሂው ዳውን ቱ ኧርዝ የተሰኘው መጽሔት አንድ ሳይንቲስትና የወንድማቸው ልጅ ኃይል ማመንጨት የሚቻልበት አንድ ሐሳብ እንደመጣላቸው ዘግቧል። አራት ወይፈኖች ኃይል ከሚተላለፍባቸው ጥርሶች ጋር የተያያዘ ዘንግ ያሽከረክራሉ። ዘንጉ አንድን ትንሽ ጀነሬተር ያንቀሳቅሳል። ጀነሬተሩ ለውኃ ፓምፕና ለወፍጮ ኃይል ከሚሰጡ ባትሪዎች ጋር የተገናኘ ነው። በዚህ መንገድ ለሚገኘው አንድ አሃድ (unit) ኃይል የሚከፈለው አሥር ሳንቲም ገደማ ሲሆን በሽክርክረ ነፋስ ለሚገኘው አንድ አሃድ ኃይል 1 ዶላር፣ በፀሐይ ጨረር ለሚመነጨው አንድ አሃድ ኃይል ደግሞ 24 ዶላር ይከፈላል ይላል ዳውን ቱ ኧርዝ። ሆኖም መንደርተኞቹ በዓመት ውስጥ ለሦስት ወራት ያህል ወይፈኖቹን በማሳዎቻቸው ላይ ስለሚያሠሯቸው ይህን የኃይል ማመንጫ ዘዴ የፈበረኩት ሰዎች ወይፈኖቹ በማይኖሩበት ጊዜ ጥቅም ላይ ሊውል የሚችል ኃይል ማከማቸት የሚቻልበትን ውጤታማ ዘዴ በመፈለግ ላይ ናቸው።
ጤናማ የአመጋገብ ልማድ
በአማካይ ሲታይ ልጃገረዶች ከ10 እስከ 14 ዓመት ባለው የዕድሜ ክልል ውስጥ 25 ሴንቲ ሜትር ቁመትና ከ18 እስከ 22 ኪሎ ግራም ክብደት የሚጨምሩ ሲሆን ወንዶች ልጆች ደግሞ ከ12 እስከ 16 ዓመት ባለው የዕድሜ ክልል ውስጥ 30 ሴንቲ ሜትር ገደማ ቁመትና ከ22 እስከ 27 ኪሎ ግራም ክብደት ይጨምራሉ። በዚህ ፈጣን ዕድገት በሚታይበት ወቅት በአሥራዎቹ የዕድሜ ክልል የሚገኙ ወጣቶች በሰውነታቸው ክብደት መረበሻቸው የተለመደ ነገር ነው። ብዙዎቹ የሰውነታቸውን ክብደት የመቆጣጠሩ ጉዳይ በጣም ያሳስባቸዋል። “ይሁን እንጂ የሰውነት ክብደትን ለመቀነስ ሲባል የምግብን መጠን መቀነስ የሚደገፍ ካለመሆኑም በላይ ጥሩ መፍትሔ አይደለም” ሲሉ የአመጋገብ ሥርዓት አማካሪ የሆኑት ሊን ሮብሊን ዘ ቶሮንቶ ስታር ላይ ጽፈዋል። እንዲህ ዓይነቱ እርምጃ ሰውነት ገንቢ ንጥረ ነገሮችን እንዳያገኝ እንቅፋት ይፈጥራል ሲሉ ሮብሊን ገልጸዋል። በተጨማሪም የምግብ መጠንን በመቀነስ የሰውነትን ክብደት ለመቆጣጠር መሞከር “ጤናማ ያልሆነ የአመጋገብ ልማድ ሊያስከትልና ከአመጋገብ ሥርዓት መዛባት ጋር ግንኙነት ያላቸው ይበልጥ ከባድ የሆኑ ችግሮች ሊፈጥር ይችላል።” በአሥራዎቹ ዕድሜ ላይ የሚገኙ ወጣቶች አሉ ሮብሊን፣ ስለ ቁመናቸው ይበልጥ በእውነታ ላይ የተመረኮዘ አመለካከት ሊኖራቸው የሚገባ ከመሆኑም በላይ “ጤናማ የአመጋገብ ልማድ በማዳበር፣ እንቅስቃሴ በማድረግና ባላቸው አቋም በመርካት” ጤናማ የሆነ የሰውነት ክብደት እንዲኖራቸው ማድረግ ይችላሉ።