እናቴ እንዲህ ታማሚ የሆነችው ለምንድን ነው?
ወጣቶች የሚጠይቋቸው ጥያቄዎች . . .
እናቴ እንዲህ ታማሚ የሆነችው ለምንድን ነው?
የአል አባት በካንሠር በሽታ ሕይወቱ አልፏል። * አል በመጽሐፍ ቅዱስ ውስጥ የተገለጸውን የትንሣኤ ተስፋ የተማረ በመሆኑ በተወሰነ ደረጃ መጽናናት ችሎ ነበር። ሆኖም እናቱ ካንሰር እንደያዛት በታወቀ ጊዜ እንደገና በጭንቀትና በፍርሃት ተዋጠ። እናቱን ደግሞ ሊያጣ መሆኑን ሲያስበው በጣም ተሸበረ። ‘ለምን የእኔ እናት ትታመማለች?’ በማለት በምሬት ራሱን ይጠይቃል።
ዶክተር ሌናርድ ፌልዴር እንዳሉት ከሆነ “የሚወዱት ሰው የታመመባቸው ወይም የአካል ጉዳተኛ የሆነባቸው . . . ከስድስት ሚልዮን የሚልቁ አሜሪካውያን አሉ።” ፌልዴር “በየትኛውም ቀን ከአራት አሜሪካውያን ሠራተኞች አንዱ የታመመ ወላጁን” ወይም የሚወደውን ሌላ ሰው “የማስታመም ተጨማሪ ኃላፊነት ይገጥመዋል” ሲሉ አክለው ተናግረዋል። አንተም እንዲህ ዓይነት ሁኔታ ገጥሞህ ከሆነ በአንተ ላይ ብቻ የደረሰ እንደሆነ አድርገህ አታስብ። ያም ሆኖ ግን አንድ የምትወደው ሰው ታምሞ ማየቱ ስጋት የሚፈጥርና በጣም የሚረብሽ ነገር ነው። ይህን ሁኔታ መቋቋም የምትችለው እንዴት ነው?
እናቴ የታመመችው ለምንድን ነው?
ምሳሌ 15:13 “በልብ ኀዘን . . . ነፍስ ትሰበራለች” ይላል። ወላጅህ ስትታመም በርካታ ስሜቶች ወደ አእምሮህ እንደሚመጡ የታወቀ ነው። ለምሳሌ ያህል ለወላጅህ መታመም ተጠያቂው አንተ እንደሆንክ አድርገህ ታስብ ይሆናል። ምናልባት ከወላጅህ ጋር በሆነ ጉዳይ ላይ አልተግባባችሁ ይሆናል። አንድ ሁለቴ ተጨቃጭቃችሁ ይሆናል። አሁን ወላጅህ ስትታመም ጥፋተኛው አንተ እንደሆንክ ሆኖ ይሰማህ ይሆናል። ይሁን እንጂ በቤተሰብ አባላት መካከል የሚፈጠር ግጭት ለውጥረት መንስኤ ሊሆን ቢችልም እንኳ ለከባድ ሕመም የመዳረጉ አጋጣሚ ግን በጣም የጠበበ ነው። ውጥረትና ቀላል የሆኑ ግጭቶች ፍቅር በሰፈነባቸው ክርስቲያን ቤተሰቦችም ውስጥ ሊከሰቱ ይችላሉ። ስለዚህ ለወላጅህ የጤና ችግር ተጠያቂው አንተ እንደሆንክ አድርገህ በማሰብ የጥፋተኝነት ስሜት ሊያድርብህ አይገባም።
በመሠረቱ እናትህ ወይም አባትህ የታመሙት የመጀመሪያዎቹ ወላጆቻችን አዳምና ሔዋን በሠሩት ኃጢአት ሳቢያ ነው። (ሮሜ 5:12) በዚያ የመጀመሪያ ኃጢአት የተነሳ “ፍጥረት ሁሉ እስከ አሁን ድረስ አብሮ በመቃተትና በምጥ” በመኖር ላይ ነው።—ሮሜ 8:22
የሚረብሹ ስሜቶች
ያም ሆኖ ግን ልትጨነቅና ልትረበሽ ትችላለህ። የቴሪ እናት ከባድ ጉዳት በሚያስከትለው ሉፐስ በተባለው በሽታ ተይዛለች። “ቤት በማልኖርበት ጊዜ ሁሉ እማዬ ደህና ትሆን ይሆን እያልኩ እጨነቃለሁ። ሐሳቤን ማሰባሰብ ይቸግረኛል። ሆኖም ላስጨንቃት ስለማልፈልግ ስሜቴን ዋጥ አድርጌ እይዘዋለሁ።”
ምሳሌ 12:25 “ሰውን የልቡ ኀዘን ያዋርደዋል” ይላል። በዚህ ሁኔታ ሥር ያሉ ወጣቶች ብዙውን ጊዜ የመንፈስ ጭንቀት ያድርባቸዋል። ቴሪ እናቷ ቀላል ሥራዎችን እንኳ ማከናወን ተስኗት ስትመለከታት በጣም እንዳዘነች ተናግራለች። ውጥረቱን ይበልጥ የሚያባብሰው ደግሞ ወጣቶች በተለይ ደግሞ ልጃገረዶች ብዙውን ጊዜ ተጨማሪ ኃላፊነቶች ለመሸከም የሚገደዱ መሆናቸው ነው። ፕሮፌሰር ብሩስ ኮምፓስ እንዳሉት ከሆነ “ልጃገረዶች የቤት ውስጥ ሥራዎችን እንደ መሥራትና ታናናሾቻቸውን እንደመንከባከብ ያሉ የቤተሰብ ኃላፊነቶችን ይሸከማሉ። እነዚህ ኃላፊነቶች ከአቅማቸው በላይ ከመሆናቸውም ሌላ በማኅበራዊ ዕድገታቸው ላይ እንቅፋት ይፈጥራሉ።” በአሥራዎቹ ዕድሜ ላይ የሚገኙ አንዳንድ ወጣቶች ተስፋ የሚያስቆርጥና የሚያስጨንቅ ሙዚቃ በመስማት ራሳቸውን ያገልላሉ።—ምሳሌ 18:1
ብዙውን ጊዜ ወላጄ ልትሞት ትችላለች የሚለውም ሐሳብ ወደ አእምሮ ይመጣል። ቴሪ ወንድምና እህት የሌላት ከመሆኑም በላይ እናቷ ነጠላ ወላጅ ነች። ቴሪ እናቷ ወደ ሆስፒታል በሄደች ቁጥር በዚያው ትቀር ይሆናል በሚል ስጋት ታለቅስ ነበር። “ከሁለታችን ሌላ ማንም የለም። ከማንም በላይ የምትቀርበኝን ጓደኛዬን ማጣት አልፈለግኩም” ብላለች። ልክ እንደዚሁም ማርታ የተባለች አንዲት በአሥራዎቹ ዕድሜ ላይ የምትገኝ ልጃገረድ “አስራ ስምንት ዓመት ሆኖኛል። ሆኖም አሁንም ድረስ ወላጆቼን ማጣት ያስፈራኛል። ልቋቋመው የማልችለው የብቸኝነት ስሜት ይፈጥርብኛል” ብላለች። ብዙውን ጊዜ ወላጅ ሲታመም የሚከሰቱት ሌሎች ችግሮች የእንቅልፍ ችግር፣ ቅዠትና የአመጋገብ ሥርዓት መዛባት ናቸው።
ምን ልታደርግ ትችላለህ?
በእንዲህ ዓይነቱ ወቅት ሁኔታው በጣም አስቸጋሪ መስሎ ቢታይህም እንኳ ልትቋቋመው ትችላለህ! በመጀመሪያ ያደረብህን ስጋትና ጭንቀት ለወላጆችህ ልታካፍል ትችላለህ። እናትህ ወይም አባትህ ያሉበት ሁኔታ ምን ያህል አስጊ ነው? ማገገም የመቻላቸው አጋጣሚ ምን ያህል ነው? ከበሽታቸው ማገገም ሳይችሉ ቢቀሩ ለአንተ ደህንነት የሚበጅ ምን ዝግጅት ተደርጓል? አንተም በኋለኛው የሕይወት ዘመንህ ተመሳሳይ ችግር ሊገጥምህ የሚችልበት አጋጣሚ ምን ያህል ነው? እንዲህ ዓይነቶቹን ነገሮች ከወላጆች ጋር መነጋገሩ ከባድ ቢሆንም እንኳ በረጋ መንፈስና አክብሮት በተሞላበት መንገድ እርዳታቸውን ለማግኘት ከጣርክ አንተን ለመርዳትና ለመደገፍ የተቻላቸውን ሁሉ ያደርጋሉ።
ለእነርሱ ያለህን ገንቢ ስሜትም አካፍላቸው። አል እናቱ በካንሰር በሽታ ሳቢያ ወደ ሞት አፋፍ እያመራች መሆኑን ባወቀበት ወቅት ይህን ሳያደርግ እንደቀረ ያስታውሳል። እንዲህ ሲል ተናግሯል:- “ምን ያህል እንደምወዳት አልገለጽኩላትም። ይህ የፍቅር መግለጫ ከአፌ ሲወጣ መስማት ትፈልግ እንደነበረ አውቃለሁ፤ ሆኖም በአሥራዎቹ ዕድሜ ላይ የምገኝ ወጣት እንደመሆኔ መጠን እንዲህ ዓይነቱን ስሜት ለእሷ መግለጹ ያሳፍረኝ ነበር። ብዙም ሳይቆይ ሕይወቷ አለፈ። አጋጣሚውን ሳልጠቀምበት በመቅረቴ አሁን የጥፋተኝነት ስሜት ይሰማኛል። በሕይወቴ ውስጥ ትልቁን ቦታ የያዘች ሰው ነበረች።” ወላጆችህን ምን ያህል እንደምትወዳቸው ከመግለጽ ወደ ኋላ አትበል።
የሚቻል ከሆነ ስለ ወላጅህ ሕመም በደንብ ለማወቅ ጥረት አድርግ። (ምሳሌ 18:15) ምናልባት ወላጅህን የሚከታተለው ሐኪም በዚህ ረገድ ሊረዳህ ይችል ይሆናል። ስለ ሕመሙ በቂ ግንዛቤ ማግኘትህ ይበልጥ አሳቢ፣ ታጋሽና የወላጅህን ችግር የምትረዳ እንድትሆን ያደርግሃል። በተጨማሪም እንደ ጠባሳ፣ የፀጉር መርገፍ ወይም ድካም የመሰሉት በወላጅህ ላይ ሊከሰቱ የሚችሉ አካላዊ ለውጦች እንግዳ አይሆኑብህም።
ወላጅህ ሆስፒታል ገብታለች? እንግዲያው ጥየቃህ አስደሳችና ገንቢ እንዲሆን ጥረት አድርግ። ከወላጅህ ጋር የምታደርገው ጭውውት በተቻለ መጠን አዎንታዊ መንፈስ የሰፈነበት ይሁን። ስለ ትምህርትህና ስለ ክርስቲያናዊ እንቅስቃሴዎችህ ንገራት። (ከምሳሌ 25:25 ጋር አወዳድር።) በአገራችሁ ባለው ባሕል መሠረት ዘመዶች ለታካሚው ምግብ ማዘጋጀትና ሌሎች ግልጋሎቶች መስጠት የሚጠበቅባቸው ከሆነ ምንም ቅር ሳትሰኝ በሥራው ላይ ተሳትፎ አድርግ። ንጹሕና ሥርዓታማ የሆነ አለባበስ ወላጅህን የሚያስደስት ከመሆኑም በላይ በሆስፒታሉ ሠራተኞችና ዶክተሮች ላይ ጥሩ ተጽዕኖ ያሳድራል። ይህ ወላጅህ ይበልጥ ጥራት ያለው ሕክምና እንድታገኝ አስተዋጽኦ ሊያደርግ ይችላል። *
ወላጅህ ቤት እያገገመች ከሆነስ? እንደዚያ ከሆነ ወላጅህን ለመርዳት የምትችለውን ሁሉ አድርግ። አቅምህ የሚፈቅድልህን ያህል የቤት ውስጥ ሥራዎችን ለመሥራት ራስህን አዘጋጅ። ራስህን ‘ሳትነቅፍ በልግስና’ በማቅረብ ያዕቆብ 1:5) ላለማጉረምረም እንዲሁም አዎንታዊና ገንቢ መንፈስ ለማንጸባረቅ የምትችለውን ሁሉ ጥረት አድርግ።
ይሖዋን ለመምሰል ጥረት አድርግ። (እርግጥ በዚህም ጊዜ ቢሆን የትምህርት ቤት ሥራ እንደሚኖርብህ የታወቀ ነው። ትምህርትም አስፈላጊ በመሆኑ ለትምህርት የሚሆን ጊዜ ለመመደብ ሞክር። ከቻልክ ደግሞ ለዕረፍትና ለመዝናኛ የሚሆን ጥቂት ጊዜ ለማግኘት ጥረት አድርግ። (መክብብ 4:6) ይህ ኃይልህን ሊያድስልህና ወላጅህን በተሻለ ሁኔታ እንድትረዳ ሊያግዝህ ይችላል። በመጨረሻም፣ ራስህን አታግልል። መሰል ክርስቲያኖች የሚሰጡትን እርዳታ ተጠቀምበት። (ገላትያ 6:2) ቴሪ “ጉባኤው ቤተሰቤ ሆኖልኛል። ሽማግሌዎቹ ምንጊዜም እኔን ለማነጋገርና ለማበረታታት ዝግጁዎች ናቸው። ይህን መቼም አልረሳውም” ብላለች።
መንፈሳዊ ሚዛንህን መጠበቅ
ከሁሉ ይበልጥ አስፈላጊ የሆነው ነገር መንፈሳዊ ሚዛንህን መጠበቅ ነው። መጽሐፍ ቅዱስ በማጥናት፣ በስብሰባዎች ላይ በመገኘት፣ ለሌሎች በመስበክና እነዚህን በመሳሰሉ መንፈሳዊ እንቅስቃሴዎች በመካፈል ራስህን በሥራ አስጠምድ። (1 ቆሮንቶስ 15:58) ቴሪ ትምህርት ቤቶች በሚዘጉባቸው ወራት ረዳት አቅኚ በመሆን በወንጌላዊነት ሥራ የምታደርገውን ተሳትፎ ከፍ ታደርጋለች። እንዲህ ስትል አክላ ተናግራለች:- “እማዬ ዘወትር ለስብሰባዎች እንድዘጋጅና በመንግሥት አዳራሽ እንድገኝ ታበረታታኝ ነበር። ይህ ሁለታችንንም ጠቅሞናል። የምትፈልገውን ያህል በሁሉም ስብሰባዎች ላይ መገኘት ስለማትችል የተሰጡትን ትምህርቶች ለእርሷ ለማካፈል ስል ለስብሰባዎች ከወትሮው ለየት ያለ ትኩረት እሰጥ ነበር። ስብሰባ ላይ መገኘት በማትችልበት ጊዜ መንፈሳዊ ምግብ የምታገኘው ከእኔ ነበር።”
ዘ ኒው ዮርክ ታይምስ “በወላጆቻቸው መታመም ሳቢያ የሚደርስባቸውን የስሜት ቀውስ ተቋቁመው በሚያድጉና አልፎ ተርፎም ስኬታማ ሕይወት በሚመሩ ልጆች ሁልጊዜ የሚደነቁትን” አንዲት የማኅበራዊ አገልግሎት ባለሞያን በማነጋገር ሁኔታውን በጥሩ መንገድ ጠቅለል አድርጎ አስቀምጦታል። እኚህ ባለሞያ እንዲህ ሲሉ ገልጸዋል:- “ልጆቹ ቀደም ሲል የማያውቋቸውን አንዳንድ ችሎታዎች ያዳብራሉ . . . ይህን የስሜት ቀውስ መቋቋም ከቻሉ ሌሎች ብዙ ችግሮችንም ተቋቁመው ማለፍ ይችላሉ።”
አንተም ይህን አስቸጋሪ ወቅት ተቋቁመህ ማለፍ ትችላለህ። ለምሳሌ ያህል የቴሪ እናት በአሁኑ ጊዜ ራሷን መንከባከብ የምትችልበት ጥሩ ሁኔታ ላይ ትገኛለች። ምናልባትም የአንተም ወላጅ ውሎ አድሮ ማገገም ትችል ይሆናል። እስከዚያው ጊዜ ድረስ ግን የሰማያዊ ወዳጅህ የይሖዋ ድጋፍ እንዳለህ አትዘንጋ። “ጸሎት ሰሚ” በመሆኑ ለእርዳታ የምታቀርበውን ጥሪ ይሰማል። (መዝሙር 65:2) አንተም ሆንክ ፈሪሃ አምላክ ያላት ወላጅህ የገጠማችሁን ሁኔታ መቋቋም የምትችሉበትን “ከወትሮው የላቀ ኃይል” ይሰጣችኋል።—2 ቆሮንቶስ 4:7 NW ፤ መዝሙር 41:3
[የግርጌ ማስታወሻዎች]
^ አን.3 አንዳንዶቹ ስሞች ተለውጠዋል።
^ አን.16 “ታካሚን መጠየቅ—እርዳታ ማበርከት የምትችለው እንዴት ነው?” በሚል ርዕስ በመጋቢት 8, 1991 (እንግሊዝኛ) የንቁ! መጽሔት እትም ላይ የወጣው ጽሑፍ በርከት ያሉ ተግባራዊ ሐሳቦች ይዟል።
[በገጽ 23 ላይ የሚገኝ የተቀነጨበ ሐሳብ]
“ቤት በማልኖርበት ጊዜ ሁሉ እማዬ ደህና ትሆን ይሆን እያልኩ እጨነቃለሁ”
[በገጽ 24 ላይ የሚገኙ ሥዕሎች]
ስለ ወላጅህ ሕመም ትክክለኛ ግንዛቤ ማግኘትህ ወላጅህን በተሻለ ሁኔታ ለመርዳት ያስችልሃል