የሌሎችን ስሜት የምትረዳ ሁን
እንዲህ አለማድረግ ምን ችግር አለው?
ሌሎች ከእኛ ጋር ባላቸው ልዩነት ላይ ከልክ በላይ የምናተኩር ከሆነ ይህን ልዩነት እንደ ድክመት ወይም እንደ ጉድለት ልንመለከተው እንችላለን። ይህም ከእኛ የተለዩ ሰዎችን ከእኛ እንደሚያንሱ አድርገን እንድንመለከት ያደርገናል። ስለ ሌሎች እንዲህ ያለ አሉታዊ አመለካከት ከያዝን ስሜታቸውን መረዳት ይከብደናል። የሌሎችን ስሜት መረዳት አለመቻል ደግሞ ከባድ ችግር ይኸውም ጭፍን ጥላቻ እንዳለብን የሚጠቁም ምልክት ሊሆን ይችላል።
የመጽሐፍ ቅዱስ መመሪያ
“ደስ ከሚላቸው ጋር ደስ ይበላችሁ፤ ከሚያለቅሱ ጋር አልቅሱ።”—ሮም 12:15
ከዚህ ጥቅስ ምን ትምህርት እናገኛለን? ይህ ጥቅስ የያዘው ሐሳብ በሦስት ቃላት ሊጠቃለል ይችላል፦ የሌሎችን ስሜት ተረዱ። የሌሎችን ስሜት መረዳት ማለት ራሳችንን በእነሱ ቦታ አስቀምጠን እኛ ብንሆን ምን ሊሰማን እንደሚችል ማሰብ ማለት ነው።
የሌሎችን ስሜት መረዳት ጠቃሚ የሆነው ለምንድን ነው?
የአንድን ሰው ስሜት ለመረዳት ጥረት ስናደርግ ግለሰቡ ከእኛ ጋር ምን ያህል እንደሚመሳሰል ይገባናል። የሚሰማን ስሜትም ሆነ ለአንድ ነገር የምንሰጠው ምላሽ በአብዛኛው ተመሳሳይ እንደሆነ እንገነዘባለን። የሌሎችን ስሜት መረዳታችን ሁላችንም በመካከላችን ምንም ያህል ልዩነት ቢኖር አንድ ቤተሰብ እንደሆንን እንድናስተውል ይረዳናል። ሌሎችን ከእኛ ጋር በሚያመሳስላቸው ነገር ላይ ይበልጥ ባተኮርን መጠን ለእነሱ አሉታዊ አመለካከት የመያዝ አጋጣሚያችን እየቀነሰ ይሄዳል።
የሌሎችን ስሜት መረዳታችን ለእነሱ አክብሮት እንዲኖረንም ይረዳናል። በሴኔጋል የምትኖር አን ማሪ የተባለች ሴት በማኅበረሰቡ ዘንድ ዝቅ ተደርገው የሚታዩ ሰዎችን ትንቅ ነበር። የሌሎችን ስሜት መረዳቷ የጠቀማት እንዴት እንደሆነ ስትናገር እንዲህ ብላለች፦ “እነዚህ ሰዎች የሚደርስባቸውን መከራ ስመለከት ‘እኔ በእነሱ ቦታ ብሆን ኖሮ ምን ይሰማኝ ነበር?’ ብዬ ራሴን ጠየቅኩ። ይህም ከእነሱ የተሻልኩ እንድሆን የሚያደርገኝ ምንም ነገር እንደሌለ እንድገነዘብ ረዳኝ። ምክንያቱም በማኅበረሰቡ ዘንድ የነበረኝ ከፍ ያለ ቦታ በምርጫም ሆነ በጥረት ያገኘሁት አይደለም።” በእርግጥም ሌሎች ሰዎች የሚያጋጥማቸውን ተፈታታኝ ሁኔታ ለመረዳት ጥረት ማድረጋችን እነሱን ከመንቀፍ ይልቅ ስሜታቸውን እንድንረዳ ያስችለናል።
ምን ማድረግ ትችላለህ?
ለሌሎች አሉታዊ አመለካከት ካለህ ከእነሱ ጋር የሚያለያዩህን ነገሮች ወደጎን ትተህ ከእነሱ ጋር የሚያመሳስሉህን ነገሮች ለማግኘት ጥረት አድርግ። ለምሳሌ በሚከተሉት ሁኔታዎች ሥር ምን እንደሚሰማቸው ለማሰብ ሞክር፦
የሌሎችን ስሜት ለመረዳት ጥረት ማድረጋችን ሁሉም ሰው አንድ ቤተሰብ እንደሆነ እንድንገነዘብ ይረዳናል
ከቤተሰባቸው ጋር አብረው ሲመገቡ
በሥራ ሲደክሙ ውለው ቤታቸው ሲገቡ
ከወዳጆቻቸው ጋር ሲጨዋወቱ
የሚወዱትን ሙዚቃ ሲያዳምጡ
ቀጥሎ ደግሞ የሚከተሉት ሁኔታዎች ሲያጋጥሟቸው አንተ በእነሱ ቦታ ብትሆን ኖሮ ምን እንደሚሰማህ ለማሰብ ሞክር፦
‘አንድ ሰው ምንም እንደማልረባ እንዲሰማኝ የሚያደርግ ነገር ቢፈጽምብኝ ምን ምላሽ እሰጣለሁ?’
‘ስለ እኔ ምንም የማያውቁ ሰዎች በተሳሳተ መንገድ ቢፈርጁኝ ምን ይሰማኛል?’
‘እኔ ራሴ በአሉታዊ ቡድን የምመለከተው ቡድን አባል ብሆን ኖሮ ሌሎች ለእኔ ምን አመለካከት እንዲኖራቸው እፈልጋለሁ?’