ትክክለኛ መረጃ ለማግኘት ሞክር
እንዲህ አለማድረግ ምን ችግር አለው?
ጭፍን ጥላቻ በአብዛኛው የሚመነጨው ከተሳሳተ መረጃ ነው። እስቲ የሚከተሉትን ምሳሌዎች ተመልከት፦
-
አንዳንድ አሠሪዎች ሴቶች ከሳይንስ ወይም ከቴክኒክ ጋር ለተያያዙ ሥራዎች ብቁ አይደሉም የሚል የተሳሳተ አመለካከት አላቸው።
-
አውሮፓ ውስጥ በመካከለኛው መቶ ዘመን፣ አይሁዶች በሽታ ያዛምታሉ እንዲሁም የውኃ ጉድጓዶችን ይመርዛሉ በሚል በሐሰት ተወንጅለው ነበር፤ በናዚ አገዛዝ ወቅትም ጀርመን ውስጥ የኢኮኖሚ ቀውስ እንዲከሰት አድርገዋል የሚል ክስ ተሰንዝሮባቸዋል። በሁለቱም አጋጣሚዎች አይሁዶች እንዲህ ያለ ክስ የተሰነዘረባቸው በጭፍን ጥላቻ ምክንያት ነው። ይህ ጭፍን ጥላቻ በዛሬው ጊዜም ሙሉ በሙሉ አልተወገደም።
-
ብዙ ሰዎች፣ የአካል ጉዳተኞች ደስታ የራቃቸውና በምሬት የተሞሉ ናቸው የሚል የተሳሳተ ግንዛቤ አላቸው።
እንዲህ ያሉ የተሳሳቱ አመለካከቶች ያሏቸው ሰዎች ይህን አመለካከታቸውን ይደግፋሉ ብለው የሚያስቧቸውን ምሳሌዎች ወይም ማስረጃዎች ሊጠቅሱ ይችላሉ። ይባስ ብሎ ደግሞ በእነሱ ሐሳብ የማይስማሙ ሁሉ የግንዛቤ ጉድለት እንዳለባቸው ይሰማቸዋል።
የመጽሐፍ ቅዱስ መመሪያ
“እውቀት የሌለው ሰው ጥሩ አይደለም።”—ምሳሌ 19:2
ከዚህ ጥቅስ ምን ትምህርት እናገኛለን? ትክክለኛ መረጃ ከሌለን የተሳሳተ መደምደሚያ ላይ ልንደርስ እንችላለን። እውነታውን ሳናጣራ የምንሰማውን ነገር ብቻ የምናምን ከሆነ ሰዎችን በተሳሳተ መንገድ መፈረጃችን አይቀርም።
ትክክለኛ መረጃ ማግኘት ጠቃሚ የሆነው ለምንድን ነው?
ትክክለኛ መረጃ ካለን ስለ አንዳንዶች በስፋት የሚነገሩ ሆኖም የተሳሳቱ አመለካከቶችን የምንቀበልበት አጋጣሚ
ጠባብ ይሆናል። ደግሞም ስለ አንድ ቡድን የተነገረን መረጃ ውሸት መሆኑን ከተገነዘብን ስለ ሌሎች ቡድኖች የተነገሩን ነገሮችም ትክክል ስለመሆናቸው ጥያቄ ማንሳታችን አይቀርም።ምን ማድረግ ትችላለህ?
-
ሰዎች ስለ አንድ ቡድን ያላቸው አሉታዊ አመለካከት በዚያ ቡድን ውስጥ ያለውን እያንዳንዱን ሰው ይወክላል ማለት እንዳልሆነ አስታውስ።
-
ስለ ሌሎች ያለህ መረጃ ውስን ሊሆን እንደሚችል አምነህ ተቀበል።
-
ተአማኒነት ካለው ምንጭ መረጃ ለማግኘት ጥረት አድርግ።