ችግሩ
ስጋት እንዲያድርብን የሚያደርጉ ነገሮች
“ይህ ትውልድ በቴክኖሎጂና በሳይንስ ከዚህ በፊት ታይቶ የማይታወቅ እድገት አስመዝግቧል፤ ከዚህም ሌላ ከፍተኛ መጠን ያለው ሀብት አካብቷል። . . . ይሁንና ከፖለቲካው እና ከኢኮኖሚው ሥርዓት እንዲሁም ከምድር ሥነ ምህዳር ጋር በተያያዘ ዓለምን ወደ ውድቀት አፋፍ እየመራ ያለውም ይኸው ትውልድ ሳይሆን አይቀርም።”—ዘ ግሎባል ሪስክስ ሪፖርት 2018፣ ዎርልድ ኢኮኖሚክ ፎረም
የችግሩን አሳሳቢነት የተረዱ በርካታ ሰዎች፣ ስለ ሰውም ሆነ ስለ ምድር የወደፊት ዕጣ የሚጨነቁት ለምንድን ነው? በዛሬው ጊዜ እያጋጠሙን ካሉት ተፈታታኝ ነገሮች መካከል እስቲ አንዳንዶቹን ብቻ እንመልከት።
-
በኢንተርኔት የሚፈጸም ወንጀል፦ ዚ አውስትራሊያን የተሰኘው ጋዜጣ የሚከተለውን ዘገባ አውጥቷል፦ “ኢንተርኔት የሚያስከትለው አደጋ ከጊዜ ወደ ጊዜ እየጨመረ ነው። ኢንተርኔት ሕፃናትን የሚያስነውሩ፣ ሌሎችን የሚያስፈራሩ፣ አወዛጋቢ ጉዳዮችን የሚያወጡ እና የኮምፒውተር መረጃዎችን የሚሰርቁ ሰዎች መሸሸጊያ ሆኗል።” ጋዜጣው አክሎም እንዲህ ሲል ገልጿል፦ “በኢንተርኔት አማካኝነት የሚፈጸም የማንነት ስርቆት በዓለም ላይ በጣም እየተስፋፉ ካሉ ወንጀሎች አንዱ ነው። . . . ኢንተርኔት የሰው ልጅ ምን ያህል ክፉና ጨካኝ ሊሆን እንደሚችል የሚታይበት አጋጣሚ ከፍቷል።”
-
ከፍተኛ የኑሮ ልዩነት፦ ኦክስፋም የተባለው ድርጅት በቅርቡ ባወጣው ዓለም አቀፍ ሪፖርት መሠረት፣ በጣም ሀብታም የሆኑት ስምንት ሰዎች ያላቸው ሀብት በጣም ድሃ የሆነው ግማሹ የዓለም ኅብረተሰብ በድምሩ ካለው ሀብት ጋር እኩል ነው። ኦክስፋም በዘገባው ላይ “የተንኮታኮተው ኢኮኖሚያችን ጥቂት ሀብታሞች ይበልጥ እንዲበለጽጉ፣ ከፍተኛ ቁጥር ያለው የዓለም ኅብረተሰብ ግን በድህነት እንዲማቅቅ እያደረገ ነው፤ ከድሃው ኅብረተሰብ መካከል አብዛኞቹ ደግሞ ሴቶች ናቸው” ብሏል። አንዳንዶች የኑሮ ልዩነቱ ከጊዜ ወደ ጊዜ እየሰፋ መሄዱ የሕዝብ ዓመፅ እንዲቀሰቀስ ሊያደርግ ይችላል ብለው ይሰጋሉ።
-
በተለያዩ ቦታዎች የሚነሱ ግጭቶችና ስደት፦ የተባበሩት መንግሥታት የስደተኞች ተቋም በ2018 ያወጣው አንድ ዘገባ እንደሚያመለክተው “በአሁኑ ጊዜ ከመኖሪያቸው የሚፈናቀሉ ሰዎች ቁጥር እስከ ዛሬ ከተመዘገቡት ሁሉ እጅግ ከፍተኛው ነው።” ከ68 ሚሊዮን የሚበልጡ ሰዎች የትውልድ ቀዬአቸውን ጥለው ለመሄድ የተገደዱ ሲሆን አብዛኞቹ የተሰደዱት በተለያዩ ቦታዎች በሚነሱ ግጭቶች እንዲሁም በሃይማኖት፣ በፖለቲካ አሊያም በዘር ልዩነት ሳቢያ በሚፈጸም በደል የተነሳ ነው። ዘገባው አክሎም “በየሁለት ሴኮንዱ ማለት ይቻላል፣ 1 ሰው ሳይወድ በግዱ ከመኖሪያ ቦታው ይፈናቀላል” ሲል ገልጿል።
-
በተፈጥሮ ላይ የሚደርስ ጉዳት፦ ዘ ግሎባል ሪስክስ ሪፖርት እንደገለጸው “በርካታ የዕፀዋት እና የእንስሳት ዝርያዎች በከፍተኛ ፍጥነት ከምድር ገጽ እየጠፉ ነው፤ . . . አየሩና ባሕሩ መበከሉ በሰው ጤንነት ላይ አስጊ ሁኔታ እየፈጠረ ነው።” በተጨማሪም በአንዳንድ አገሮች የትናንሽ ነፍሳት ቁጥር በፍጥነት እያሽቆለቆለ ይገኛል። ተክሎች እንዲራቡ የሚያደርጉት ትናንሽ ነፍሳት ስለሆኑ ቁጥራቸው መመናመኑ “ከፍተኛ ሥነ ምህዳራዊ ቀውስ” ሊያስከትል እንደሚችል የሳይንስ ሊቃውንት እያስጠነቀቁ ነው።
ታዲያ ዓለማችን ከስጋት ነፃ መሆን እንድትችል አስፈላጊ የሆኑ የለውጥ እርምጃዎችን መውሰድ እንችል ይሆን? አንዳንዶች፣ ሰዎችን ማስተማር ለውጥ እንደሚያመጣ ይናገራሉ። ይሁንና እንዲህ ዓይነት ለውጥ የሚያመጣው ምን ዓይነት ትምህርት ነው? ቀጣዮቹ ርዕሶች ለእነዚህ ጥያቄዎች መልስ ይሰጣሉ።