በቀጥታ ወደ ዋናው ጉዳይ ግባ

በቀጥታ ወደ ርዕስ ማውጫው ሂድ

መጽሐፍ ቅዱስ ምን ይላል?

አመስጋኝነት

አመስጋኝነት

አመስጋኝነት በርካታ አካላዊ፣ አእምሯዊና ስሜታዊ ጥቅሞች እንዳሉት ተረጋግጧል፤ በመሆኑም ሁሉም ሰው በዕለት ተዕለት ሕይወቱ አመስጋኝ መሆኑ በጣም አስፈላጊ ነው።

አመስጋኝነት ለጤንነታችን ጠቃሚ የሆነው እንዴት ነው?

የሕክምናው ሳይንስ ምን ይላል?

ሃርቫርድ ሜንታል ኸልዝ ሌተር በተባለው ጽሑፍ ላይ የወጣ አንድ ርዕስ “አመስጋኝነት ይበልጥ ደስተኛ ለመሆን ከፍተኛ አስተዋጽኦ ያደርጋል” ብሏል። አመስጋኝነት ሰዎች ጥሩ ስሜት እንዲሰማቸው፣ መልካም ነገር ሲያጋጥማቸው እንዲደሰቱ፣ ጤናቸው እንዲሻሻል፣ ችግሮችን እንዲቋቋሙ እንዲሁም ከሌሎች ጋር ጠንካራ ዝምድና መመሥረት እንዲችሉ ይረዳቸዋል።

መጽሐፍ ቅዱስ ምን ይላል?

መጽሐፍ ቅዱስ የአመስጋኝነት መንፈስ እንድናዳብር ያበረታታናል። ሐዋርያው ጳውሎስ “አመስጋኝ መሆናችሁን አሳዩ” በማለት የጻፈ ሲሆን እሱ ራሱም በዚህ ረገድ ጥሩ ምሳሌ ትቷል። ለምሳሌ ያህል፣ ሰዎች ለነገራቸው መልእክት ጥሩ ምላሽ በመስጠታቸው ‘አምላክን ያለማቋረጥ አመስግኗል።’ (ቆላስይስ 3:15፤ 1 ተሰሎንቄ 2:13) ዘላቂ ደስታ ማግኘት የሚቻለው እንዲሁ አልፎ አልፎ ‘አመሰግናለሁ’ በማለት ሳይሆን የአመስጋኝነት መንፈስ በማዳበር ነው። ይህን ማድረጋችን አንድ ነገር ‘ይገባኛል’ የሚል ስሜት ከማዳበር እንዲሁም ከቅናትና ከምሬት ይጠብቀናል፤ እነዚህ ስሜቶች ሰዎች እንዲርቁን አልፎ ተርፎም በሕይወታችን ደስታ እንድናጣ ያደርጋሉ።

ፈጣሪያችን፣ እዚህ ግቡ የማንባለውን የሰው ልጆች እንኳ በማድነቅ ጥሩ ምሳሌ ትቶልናል። ዕብራውያን 6:10 “አምላክ . . . የምታከናውኑትን ሥራ እንዲሁም ለስሙ ያሳያችሁትን ፍቅር በመርሳት ፍትሕ አያዛባም” ይላል። በእርግጥም ፈጣሪያችን፣ አመስጋኝ አለመሆንን ፍትሕ እንደማዛባት ወይም እንደ ዓመፅ ይቆጥረዋል።

“ሁልጊዜ ደስ ይበላችሁ። ለሁሉም ነገር አመስግኑ።”1 ተሰሎንቄ 5:16, 18

አመስጋኝነት ከሌሎች ጋር ያለንን ግንኙነት የሚያሻሽለው እንዴት ነው?

ከተሞክሮ ምን ማየት ይቻላል?

ለተሰጠን ስጦታ፣ ማበረታቻ ወይም እርዳታ ከልባችን ስናመሰግን ሰጪው ከፍ አድርገን እንደምንመለከተውና እንደምናደንቀው እንዲሰማው እናደርጋለን። የማናውቃቸው ሰዎችም እንኳ ደግነት ሲያሳዩን፣ ለምሳሌ በር ከፍተው ቀድመን እንድናልፍ ሲያደርጉ ከልባችን ካመሰገንናቸው ጥሩ ምላሽ መስጠታቸው አይቀርም።

መጽሐፍ ቅዱስ ምን ይላል?

ኢየሱስ ክርስቶስ እንዲህ ብሏል፦ “ለሰዎች ስጡ፤ እነሱም ይሰጧችኋል። ተትረፍርፎ እስኪፈስ ድረስ በተጠቀጠቀና በተነቀነቀ ጥሩ መስፈሪያ ሰፍረው በእቅፋችሁ ይሰጧችኋል።” (ሉቃስ 6:38) በደቡብ ፓስፊክ በሚገኘው በቫኑአቱ ደሴት የምትኖር ሮዝ የተባለች መስማት የተሳናት ልጅ ያጋጠማትን እስቲ እንመልከት።

ሮዝ የይሖዋ ምሥክሮች በሚያደርጓቸው ክርስቲያናዊ ስብሰባዎች ላይ ትገኝ የነበረ ቢሆንም እሷም ሆነች በጉባኤው ውስጥ ያሉ ሰዎች የምልክት ቋንቋ ስለማይችሉ ከስብሰባዎቹ እምብዛም ጥቅም ማግኘት አልቻለችም ነበር። የምልክት ቋንቋ በደንብ የሚችሉ አንድ ባልና ሚስት ወደ ጉባኤው በመጡ ጊዜ ይህን ችግር ስላስተዋሉ የምልክት ቋንቋ ትምህርት መስጠት ጀመሩ። ሮዝ ለተደረገላት ነገር በጣም አመስጋኝ ናት። “የሚወዱኝ ብዙ ጓደኞች ስላሉኝ ደስተኛ ነኝ” በማለት ተናግራለች። እርዳታ ያበረከቱላት ባልና ሚስትም፣ የሮዝን አመስጋኝነት እንዲሁም አሁን በስብሰባዎች ላይ የምታደርገውን ተሳትፎ ሲያዩ በእጅጉ እንደተካሱ ተሰምቷቸዋል። ሮዝ፣ ሌሎች ከእሷ ጋር ለመነጋገር ሲሉ የምልክት ቋንቋ ለመማር የሚያደርጉትን ጥረትም በጣም ታደንቃለች።—የሐዋርያት ሥራ 20:35

‘ምስጋናን መሥዋዕት አድርጎ የሚያቀርብ አምላክን ያከብራል።’መዝሙር 50:23

የአመስጋኝነት መንፈስ ማዳበር የምትችለው እንዴት ነው?

መጽሐፍ ቅዱስ ምን ይላል?

ስሜታችን ከአስተሳሰባችን ጋር በጥብቅ የተቆራኘ ነው። መጽሐፍ ቅዱስን ከጻፉት ሰዎች አንዱ የሆነው ዳዊት ለአምላክ ባቀረበው ጸሎት ላይ እንዲህ ብሏል፦ “ባከናወንካቸው ነገሮች ሁሉ ላይ አሰላስላለሁ፤ የእጆችህን ሥራ በታላቅ ጉጉት አውጠነጥናለሁ።” (መዝሙር 143:5) በእርግጥም ዳዊት አምላክ ባደረገለት ነገር ላይ ያሰላስል ነበር። የአመስጋኝነት መንፈስ ሊኖረው የቻለው ስለ አምላክ መንገዶች አዘውትሮ በማውጠንጠኑ ነው፤ በሕይወቱ ሙሉ ይህን የማድረግ ልማድ ነበረው።—መዝሙር 71:5, 17

መጽሐፍ ቅዱስ የሚከተለውን ግሩም ምክር ይሰጠናል፦ “እውነት የሆነውን ነገር ሁሉ፣ . . . ተወዳጅ የሆነውን ነገር ሁሉ፣ በመልካም የሚነሳውን ነገር ሁሉ፣ በጎ የሆነውን ሁሉና ምስጋና የሚገባውን ነገር ሁሉ ማውጠንጠናችሁን አታቋርጡ።” (ፊልጵስዩስ 4:8 የግርጌ ማስታወሻ) “ማውጠንጠናችሁን አታቋርጡ” የሚለው አገላለጽም ቢሆን ስለተደረጉልን ነገሮች አዘውትረን ማሰላሰል እንዳለብን ይጠቁመናል፤ ይህን ማድረጋችን የአመስጋኝነት መንፈስ ለማዳበር አስፈላጊ ነው።

“በልቤም የማሰላስለው ነገር ማስተዋልን ይገልጣል።”መዝሙር 49:3