መጽሐፍ ቅዱስ ምን ይላል?
አካላዊ ውበት
ለአካላዊ ውበት ሚዛናዊ አመለካከት ማዳበራችን ደስተኛ እንድንሆን የሚያደርገን ሲሆን እንዲህ ዓይነት አመለካከት አለማዳበር ደግሞ ደስታችንን እንድናጣ ሊያደርገን ይችላል።
ውበትን የምናደንቀው ለምንድን ነው?
የሰው አእምሮ ውበትን የሚረዳበት መንገድ እንቆቅልሽ ነው። መጽሐፍ ቅዱስ ስለዚህ ጉዳይ ባያብራራም ውበትን የምናደንቀው አምላክ የራሱን ባሕርያት እንድናንጸባርቅ አድርጎ ስለፈጠረን እንደሆነ ይገልጻል። (ዘፍጥረት 1:27፤ መክብብ 3:11) በተጨማሪም አምላክ እጅግ ውስብስብ የሆነውን የሰው አካል የፈጠረ ሲሆን አካላችን አስደናቂ የሆነ ቅርጽ እንዲኖረውና አስገራሚ ተግባራትን እንዲያከናውን አድርጓል። ይህን በሚመለከት በጥንት ዘመን የኖረ አንድ መዝሙራዊ እንደሚከተለው በማለት ጽፏል፦ “በሚያስደምም ሁኔታ ግሩምና ድንቅ ሆኜ [ተፈጥሬአለሁ]።”—መዝሙር 139:14
ይሁንና በዛሬው ጊዜ ሰዎች ለአካላዊ ውበት ያላቸው አመለካከት በአብዛኛው ሚዛኑን የሳተ ነው፤ ለዚህም የፋሽን ኢንዱስትሪውና የመገናኛ ብዙኃን አስተዋጽኦ ያደርጋሉ። በምዕራባውያን ዘንድ የተካሄዱ በርካታ ጥናቶች እንደሚያሳዩት “አንድ ሰው ለራሱ በሚኖረው አመለካከት ላይ ትልቅ ተጽዕኖ የሚያሳድረው መልክና ቁመናው” መሆኑን ቦዲ ኢሜጅ የተሰኘው መጽሐፍ ተናግሯል። ይሁን እንጂ እንደዚህ ያለው ጠባብ አመለካከት፣ ግለሰቡ ከአካላዊ መልክና ቁመና ለሚልቀው ነገር ይኸውም ለውስጣዊ ማንነቱ ወይም ለልቡ ትኩረት እንዳይሰጥ ሊያደርገው ይችላል።—1 ሳሙኤል 16:7
ለውጫዊ ውበት ከሚሰጠው ሚዛናዊ ያልሆነ ግምት ባልተናነሰ፣ በተለይ ከሴቶች ጋር በተያያዘ የፆታ ስሜትን ለሚያነሳሱ የሰውነት ክፍሎች የተጋነነ ትኩረት እየተሰጠ መጥቷል። በ2007 የወጣ የአሜሪካ የሥነ ልቦና ማኅበር ሪፖርት እንደገለጸው፣ “ጥናት ከተካሄደባቸው የመገናኛ ብዙኃን ዘርፎች መካከል በሁሉም ላይ ማለት ይቻላል፣ ሴቶችን የፆታ ስሜት በሚቀሰቅስ መልኩ ማቅረብ የተለመደ” ሆኗል። መጽሐፍ ቅዱስ እንዲህ ያለው ዝንባሌ ተጽዕኖ እንዳያሳድርብን መጠንቀቅ እንዳለብን አጥብቆ ያሳስበናል፤ እንዲህ ማድረጉም ተገቢ ነው!—ቆላስይስ 3:5, 6
“ውበታችሁ በውጫዊ ነገሮች በማጌጥ . . . አይሁን፤ ከዚህ ይልቅ ውበታችሁ የማይጠፋውን ጌጥ ይኸውም በአምላክ ፊት ከፍተኛ ግምት የሚሰጠውን የሰከነና ገር መንፈስ የተላበሰ የተሰወረ የልብ ሰው ይሁን።”—1 ጴጥሮስ 3:3, 4
ሚዛናዊ አመለካከት መያዝ የጥበብ አካሄድ የሆነው ለምንድን ነው?
አንዳንዶች “ቆንጆ ከሆንሽ ውበትሽን አትደብቂው!” ይላሉ። የአሜሪካ የሥነ ልቦና ማኅበር ያወጣው ሪፖርት እንደገለጸው እንዲህ ዓይነቱ አስተሳሰብ በተለመደባቸው ባሕሎች ውስጥ ወጣት ሴቶች ሌላው ቀርቶ ትናንሽ ልጆች እንኳ ራሳቸውን የሚመለከቱት “የሌሎች ምኞት ማርኪያ” እንደሆኑ አድርገው ነው። “ሰዎች ለእነሱ ያላቸው ግምት በመልክና በቁመናቸው ላይ የተመካ እንደሆነ” ይሰማቸዋል። እንዲህ ዓይነት አመለካከት በጣም ጎጂ ነው። እንዲያውም የአሜሪካ የሥነ ልቦና ማኅበር እንደገለጸው ከማኅበራዊ ሕይወትም ሆነ ከጤና አንጻር አሳሳቢ ችግር ሆኗል፤ እንዲህ ያለው አመለካከት “ከስሜት ጋር በተያያዘ በርካታ ችግሮች” ሊያስከትል ይችላል። ከእነዚህ መካከል ጭንቀት እንዲሁም “ራስን መጥላት፣ . . . የተዛባ የአመጋገብ ልማድ፣ ለራስ ጥሩ ግምት ማጣትና የመንፈስ ጭንቀት” ይገኙበታል።
“የሚያስጨንቁ ነገሮችን ከልብህ አስወግድ፤ ጎጂ ነገሮችንም ከሰውነትህ አርቅ፤ ወጣትነትና የለጋነት ዕድሜ ከንቱ ናቸውና።”—መክብብ 11:10
ማስተዋል የሚንጸባረቅበት አመለካከት
መጽሐፍ ቅዱስ ‘ማስተዋልን’ ወይም ጥሩ የማመዛዘን ችሎታን ከልከኝነት ጋር ያያይዘዋል። (1 ጢሞቴዎስ 2:9) ልከኛ የሆኑ ሰዎች ብስለት የጎደላቸው ወይም ኩሩዎች እንዲሁም ስለ መልካቸው ከልክ በላይ የሚጨነቁ አይደሉም፤ ከዚህ ይልቅ ስለ ራሳቸው ጤናማና ሚዛናዊ አመለካከት አላቸው። በተጨማሪም የሌሎችን ስሜት ግምት ውስጥ ያስገባሉ፤ በመሆኑም የሌሎችን አድናቆት፣ አክብሮትና ከሁሉ በላይ ደግሞ የአምላክን ሞገስ ያተርፋሉ። (ሚክያስ 6:8) ከዚህም በላይ እውነተኛ ጓደኞች የማፍራት እንዲሁም ፆታዊ ስሜታቸውን ስለማርካት ብቻ የሚያስቡ ሳይሆን ዘላቂና አስደሳች ጥምረት ለመመሥረት የሚፈልጉ የትዳር አጋሮች የማግኘት አጋጣሚያቸው ሰፊ ነው።
በእርግጥም መጽሐፍ ቅዱስ ‘በተሰወረው የልብ ሰው’ ማለትም በውስጣዊ ማንነታችን ላይ እንድናተኩር ምክር መስጠቱ ተገቢ ነው። (1 ጴጥሮስ 3:3, 4) ደግሞም ውስጣዊ ውበት አያረጅም። እንዲያውም ጊዜ እያለፈ ሲሄድ ይበልጥ እየደመቀ ይሄዳል! ምሳሌ 16:31 “ሽበት በጽድቅ መንገድ ሲገኝ የውበት ዘውድ ነው” ይላል። በመሆኑም የመጽሐፍ ቅዱስን የላቀ ምክር በተግባር የሚያውሉ ወጣቶችም ሆኑ አዋቂዎች፣ ዘላቂ የሆነውን ውበት ብቻ ሳይሆን ክብርና እርካታም ጭምር ያገኛሉ።
“ውበት ሐሰት፣ ቁንጅናም አላፊ ነው፤ ይሖዋን የምትፈራ ሴት ግን ትመሰገናለች።”—ምሳሌ 31:30