የሽፋኑ ርዕሰ ጉዳይ | መጽሐፍ ቅዱስ በእርግጥ የአምላክ ቃል ነው?
መጽሐፍ ቅዱስ በእርግጥ “በአምላክ መንፈስ መሪነት” የተጻፈ ነው?
መጽሐፍ ቅዱስ የአምላክ ቃል ነው ብለህ ታምናለህ? ወይስ የሰዎችን ሐሳብ የያዘ መጽሐፍ እንደሆነ ይሰማሃል?
ይህ ጉዳይ ክርስቲያን ነን የሚሉ ሰዎችንም ጭምር ሲያከራክር ቆይቷል። ለምሳሌ በ2014 በዩናይትድ ስቴትስ ውስጥ የተደረገ ጥናት እንደሚያሳየው ክርስቲያን ነን ከሚሉ ሰዎች መካከል አብዛኞቹ “መጽሐፍ ቅዱስ በሆነ መንገድ ከአምላክ ጋር ግንኙነት ያለው መጽሐፍ” እንደሆነ ያምናሉ። ይሁንና በጥናቱ ከተካተቱት ሰዎች መካከል ከአምስቱ አንዱ የሚያስበው መጽሐፍ ቅዱስ “ጥንታዊ ተረቶችን፣ አፈ ታሪኮችንና አንዳንድ ሰዎች የሰጧቸውን ምክሮች” የያዘ መጽሐፍ እንደሆነ አድርጎ ነው። ከዚህ መረዳት እንደምንችለው መጽሐፍ ቅዱስ “ቅዱሳን መጻሕፍት ሁሉ በአምላክ መንፈስ መሪነት የተጻፉ ናቸው” ቢልም በርካታ ሰዎች በውስጡ የሚገኘው ሐሳብ ምንጭ ማን ነው በሚለው ጉዳይ ላይ የተለያየ አመለካከት አላቸው። በመሆኑም በመጀመሪያ “በአምላክ መንፈስ መሪነት” የተጻፈ የሚለው አገላለጽ ምን ትርጉም እንዳለው እንመልከት።—2 ጢሞቴዎስ 3:16
“በአምላክ መንፈስ መሪነት” የተጻፈ ሲባል ምን ማለት ነው?
መጽሐፍ ቅዱስ፣ 40 የተለያዩ ጸሐፊዎች የጻፏቸውን 66 ትናንሽ መጻሕፍት የያዘ ሲሆን ተጽፎ ያለቀው 1,600 ዓመታት ገደማ በሚሆን ጊዜ ውስጥ ነው። ታዲያ መጽሐፍ ቅዱስን የጻፉት ሰዎች ከሆኑ ‘በአምላክ መንፈስ መሪነት ተጻፈ’ ሊባል የሚችለው እንዴት ነው? በአጭሩ “በአምላክ መንፈስ መሪነት” የተጻፈ የሚለው አገላለጽ በመጽሐፍ ቅዱስ ውስጥ የሚገኘው ሐሳብ ምንጭ አምላክ እንደሆነ ያመለክታል። መጽሐፍ ቅዱስ ስለዚህ ጉዳይ ሲገልጽ “ሰዎች ከአምላክ የተቀበሉትን ትንቢት በመንፈስ ቅዱስ ተገፋፍተው ተናገሩ” ይላል። (2 ጴጥሮስ 1:21) በሌላ አባባል አምላክ የማይታየውን ኃይሉን ማለትም መንፈስ ቅዱስን በመጠቀም የመጽሐፍ ቅዱስን መጻሕፍት ለጻፉት ሰዎች መልእክቱን አስተላልፏል። ለምሳሌ የአንድ ድርጅት አስተዳዳሪ በደብዳቤው ውስጥ እንዲካተት የሚፈልገውን ሐሳብ ለጸሐፊው በመንገር ደብዳቤ እንዲጽፍለት ሊያደርግ ይችላል። በደብዳቤው ላይ የሰፈረው ሐሳብ ምንጭ ግን ጸሐፊው ሳይሆን አስተዳዳሪው እንደሆነ ግልጽ ነው።
አምላክ ለአንዳንዶቹ የመጽሐፍ ቅዱስ ጸሐፊዎች መልእክቱን ያስተላለፈው በመላእክት አማካኝነት ነው። ሌሎቹ ደግሞ ራእይ እንዲያዩ አድርጓል። በሕልም አማካኝነት መልእክቱን ያስተላለፈባቸው ጊዜያትም አሉ። አንዳንድ ጊዜ አምላክ ጸሐፊዎቹ የራሳቸውን አገላለጽ ተጠቅመው መልእክቱን እንዲጽፉ የፈቀደላቸው ሲሆን በሌሎች ጊዜያት ደግሞ የሚጽፉትን ሐሳብ ቃል በቃል ነግሯቸዋል። መልእክቱ የተላለፈበት መንገድ ምንም ይሁን ምን የመጽሐፍ ቅዱስ ጸሐፊዎች ያሰፈሩት የራሳቸውን ሳይሆን የአምላክን ሐሳብ ነው።
ይሁንና የመጽሐፍ ቅዱስ ጸሐፊዎች መጽሐፍ ቅዱስን የጻፉት በአምላክ መንፈስ መሪነት እንደሆነ እርግጠኞች መሆን የምንችለው እንዴት ነው? መጽሐፍ ቅዱስ በእርግጥ የአምላክ ቃል እንደሆነ ያለህን እምነት የሚያጠናክሩ ሦስት ማስረጃዎችን እስቲ ተመልከት።