ለወላጆች
5፦ የሐሳብ ልውውጥ ማድረግ
ምን ማለት ነው?
በእናንተና በልጆቻችሁ መካከል ጥሩ የሐሳብ ልውውጥ አለ የሚባለው እናንተም ሆናችሁ ልጆቻችሁ ሐሳባችሁንና ስሜታችሁን በግልጽ የምትነጋገሩ ከሆነ ነው።
አስፈላጊ የሆነው ለምንድን ነው?
በአሥራዎቹ ዕድሜ ላይ ከሚገኙ ልጆች ጋር የሐሳብ ልውውጥ ማድረግ አስቸጋሪ ሊሆን ይችላል። ብሬኪንግ ዘ ኮድ የተባለው መጽሐፍ እንደገለጸው “ከመድረክ በስተጀርባ ያለውን የልጆቻችሁን ሕይወት ለማየት የይለፍ ፈቃድ ያላችሁ ያህል” ሆኖ ይሰማችሁ የነበረበት ጊዜ ብዙ ሩቅ አይደለም። “አሁን ግን ያላችሁ አማራጭ ከሌሎች ተመልካቾች ጋር ቁጭ ብላችሁ [የልጆቻችሁን ሕይወት] ማየት ብቻ ነው፤ ያውም የምታገኙት ቦታ ጥሩ ላይሆን ይችላል።” በዚህ ወቅት ልጆች የሐሳብ ልውውጥ ማድረግ የማይፈልጉ ሊመስል ይችላል፤ ሆኖም ከመቼውም ጊዜ ይበልጥ የሐሳብ ልውውጥ ማድረግ የሚያስፈልጋቸው በዚህ ወቅት ነው!
ምን ማድረግ ትችላላችሁ?
ልጆቻችሁ ሊያነጋግሯችሁ በሚፈልጉበት ጊዜ ሁሉ ለማዳመጥ ዝግጁ ሁኑ። ልጆቻችሁ ሊያነጋግሯችሁ የፈለጉት በጣም ከመሸ በኋላ ቢሆንም እንኳ ለማዳመጥ ፈቃደኛ ሁኑ።
“‘አሁን ነው ማውራት የምትፈልገው? ቀኑን ሙሉ አብሬህ አልነበርኩ?’ ለማለት ትፈተኑ ይሆናል። ይሁን እንጂ ልጆቻችን ሊያነጋግሩን በመፈለጋቸው ልንማረር አይገባም። ማንኛውም ወላጅ የሚፈልገው ይህን አይደለም?”—ሊሳ
“የምወደው በጊዜ መተኛት ቢሆንም በአብዛኛው በአሥራዎቹ ዕድሜ ውስጥ ከሚገኙ ልጆቼ ጋር በጣም ጥሩ ጭውውት የማደርገው ከእኩለ ሌሊት በኋላ ነበር።”—ኸርበርት
የመጽሐፍ ቅዱስ መመሪያ፦ “እያንዳንዱ ሰው ምንጊዜም የራሱን ጥቅም ሳይሆን የሌላውን ሰው ጥቅም ይፈልግ።”—1 ቆሮንቶስ 10:24
በትኩረት አዳምጧቸው። አንድ አባት እንዲህ ብሏል፦ “አንዳንድ ጊዜ ልጆቼ እያናገሩኝ ሐሳቤ ይከፋፈልብኛል። ልጆቼ ደግሞ ሌላ ነገር እያሰብኩ እንደሆነ ያውቁብኛል!”
አንተም ትኩረትህ የሚከፋፈል ከሆነ ቴሌቪዥኑን ማጥፋት ወይም ሌሎች ኤሌክትሮኒክ መሣሪያዎችህን ማስቀመጥ ሊያስፈልግህ ይችላል። ልጆቻችሁ በሚናገሩት ነገር ላይ ትኩረት አድርጉ፤ እነሱን ያሳሰባቸው ጉዳይ ለእናንተ ተራ ነገር ቢመስልም እንኳ ሙሉ ትኩረት ሰጥታችሁ አዳምጧቸው።
“ልጆቻችን ለሚያሳስቧቸው ነገሮች ትልቅ ቦታ እንደምንሰጥ እንዲገነዘቡ ማድረግ ይኖርብናል። ልጆቻችን ስለሚያሳስቧቸው ነገሮች ግድ እንደሌለን ከተሰማቸው ድብቅ ይሆናሉ፤ ወይም እርዳታ ለማግኘት ወደ ሌላ ሰው ዘወር ይላሉ።”—ማራንዳ
“የልጃችሁ ሐሳብ ትክክል እንዳልሆነ ቢሰማችሁ እንኳ አትቆጡ።”—አንቶኒ
የመጽሐፍ ቅዱስ መመሪያ፦ “እንዴት እንደምታዳምጡ በጥሞና አስቡ።”—ሉቃስ 8:18
ለመነጋገር የሚያስችሉ አጋጣሚዎችን ተጠቀሙባቸው። ልጆች ከወላጆቻቸው ጋር ቁጭ ብለው ከሚያወሩበት ጊዜ ይልቅ የልባቸውን አውጥተው የሚናገሩት በሌሎች ጊዜያት ነው።
“በመኪና አብረን ስንሄድ ከልጄ ጋር እናወራለን። ፊት ለፊት ተቀምጦ ከማውራት ይልቅ መኪና ውስጥ ጎን ለጎን ሆኖ መጓዝ ጥሩ ጭውውት ለማድረግ አጋጣሚ ይከፍትልናል።”—ኒኮል
የምግብ ሰዓትም ጥሩ ጭውውት ለማድረግ የሚያስችል አጋጣሚ ይከፍታል።
“ራት ስንበላ ሁላችንም በቀኑ ውስጥ ያጋጠመንን ጥሩም ሆነ መጥፎ ነገር እናወራለን። ይህም አንድነት እንዲኖረንና የሚያጋጥሙንን ችግሮች ለመወጣት የሚረዱን ሰዎች እንዳሉ እንድንገነዘብ አድርጎናል።”—ሮቢን
የመጽሐፍ ቅዱስ መመሪያ፦ “ሰው ሁሉ ለመስማት የፈጠነ፣ ለመናገር የዘገየ . . . መሆን አለበት።”—ያዕቆብ 1:19