ለባለትዳሮች
1፦ ቃል ኪዳንን ማክበር
ምን ማለት ነው?
ቃል ኪዳናቸውን የሚያከብሩ ባልና ሚስቶች ትዳራቸውን የሚመለከቱት ዘላቂ ጥምረት እንደሆነ አድርገው ሲሆን ይህም በመካከላቸው የመተማመን ስሜት ይፈጥራል። አስቸጋሪ ሁኔታዎች ቢፈጠሩ እንኳ የትዳር ጓደኛቸው እንደማይከዳቸው እርግጠኛ ናቸው።
አንዳንድ ባለትዳሮች አብረው ለመኖር የሚገደዱት ማኅበረሰቡ ወይም ዘመዶቻቸው ፍቺውን ስለሚቃወሙ ነው። ሆኖም አብረው ለመኖር የሚያነሳሳቸው በፍቅርና በአክብሮት ላይ የተመሠረተውን ቃል ኪዳናቸውን ለመጠበቅ ያላቸው ፍላጎት መሆን አለበት።
የመጽሐፍ ቅዱስ መመሪያ፦ “ባልም ሚስቱን መተው የለበትም።”—1 ቆሮንቶስ 7:11
“የጋብቻ ቃል ኪዳንህን የምታከብር ከሆነ ሊያናድድ የሚችል ነገር ቢያጋጥምህም በቀላሉ አትናደድም። ይቅር ለማለትም ሆነ ይቅርታ ለመጠየቅ አትዘገይም። ችግሮችን እንደ ጊዜያዊ መሰናክል እንጂ ለፍቺ እንደሚያበቃ ምክንያት አድርገህ አትመለከታቸውም።”—ማይካ
አስፈላጊ የሆነው ለምንድን ነው?
ቃል ኪዳናቸውን የማያከብሩ ባለትዳሮች ችግሮች ሲያጋጥሟቸው ‘በቃ ልንጣጣም አልቻልንም’ ብለው ያስባሉ፤ ከዚያም ከትዳሩ መገላገል የሚችሉባቸውን መንገዶች ይፈልጋሉ።
“ብዙ ሰዎች ትዳር ውስጥ የሚገቡት ‘ካልሆነ እንፋታለን’ ብለው ነው። ሰዎች ትዳር የሚመሠርቱት ስለመፋታት እያሰቡ ከሆነ መጀመሪያውኑ እውነተኛ ቃል ኪዳን ገብተዋል ብሎ ማሰብ ያስቸግራል።”—ጂን
ምን ማድረግ ትችላለህ?
ራስህን ፈትሽ
በመካከላችሁ አለመግባባት በሚፈጠርበት ጊዜ . . .
-
የትዳር ጓደኛህን በማግባትህ ትቆጫለህ?
-
ሌላ ሴት ብታገባ ኖሮ ሕይወትህ ምን ሊመስል እንደሚችል ታስባለህ?
-
“የአንቺስ ነገር በቃኝ” ወይም “ለእኔ የምትሆነኝን አላጣም” እንደሚሉት ያሉ ሐሳቦችን ትሰነዝራለህ?
ከእነዚህ ጥያቄዎች መካከል ለአንዱ እንኳ አዎ የሚል መልስ ከሰጠህ ይህ የገባኸውን ቃል ኪዳን በቁም ነገር መመልከት እንዳለብህ የሚጠቁም ነው።
የሚከተሉትን ጥያቄዎች ከትዳር ጓደኛችሁ ጋር ተወያዩባቸው
-
የጋብቻ ቃል ኪዳናችንን ችላ ማለት ጀምረን ይሆን? ከሆነ ለምን?
-
ቃል ኪዳናችንን አክብረን ለመኖር የትኞቹን እርምጃዎች መውሰድ እንችላለን?
ጠቃሚ ምክሮች
-
አልፎ አልፎ፣ ለትዳር ጓደኛህ ያለህን ፍቅር የሚገልጽ አጭር ነገር ጽፈህ ላክላት
-
በሥራ ቦታህ የትዳር ጓደኛህን ፎቶግራፍ ጠረጴዛ ላይ በማስቀመጥ ቃል ኪዳንህን ከፍ አድርገህ እንደምትመለከት አሳይ
-
በየቀኑ፣ አብራችሁ በማትሆኑበት አጋጣሚ ሁሉ ለትዳር ጓደኛህ ስልክ ደውልላት
የመጽሐፍ ቅዱስ መመሪያ፦ “አምላክ ያጣመረውን ማንም ሰው አይለያየው።”—ማቴዎስ 19:6