በቀጥታ ወደ ዋናው ጉዳይ ግባ

በቀጥታ ወደ ርዕስ ማውጫው ሂድ

ሲሚንቶ ጡቦችን አጣብቆ እንደሚይዝ ሁሉ አክብሮት የተሞላበት ንግግርም የትዳርን ጥምረት ያጠናክራል

ለባለትዳሮች

3፦ መከባበር

3፦ መከባበር

ምን ማለት ነው?

እርስ በርስ የሚከባበሩ ባለትዳሮች በአንድ ጉዳይ ላይ በማይስማሙበት ጊዜም አንዳቸው ለሌላው ያስባሉ። ቴን ሌሰንስ ቱ ትራንስፎርም ዩር ሜሬጅ የተባለው መጽሐፍ እንዲህ ይላል፦ “እንዲህ ያሉ ባለትዳሮች ከአቋማቸው ፍንክች የማይሉ ግትር ሰዎች አይደሉም። ከዚህ ይልቅ በመካከላቸው ስለተፈጠረው ልዩነት ይነጋገራሉ። የትዳር ጓደኛቸውን አመለካከት በአክብሮት ያዳምጣሉ፤ ከዚያም ለሁለቱም የሚስማማ አስታራቂ ሐሳብ ይፈልጋሉ።”

የመጽሐፍ ቅዱስ መመሪያ፦ “ፍቅር . . . የራሱን ፍላጎት አያስቀድምም።”—1 ቆሮንቶስ 13:4, 5

“ሚስቴን ስለማከብራት እሷ ከፍ አድርጋ የምትመለከተውን ነገር አደንቃለሁ እንዲሁም እሷንም ሆነ ትዳራችንን የሚጎዳ ምንም ነገር ማድረግ አልፈልግም።”—ማይካ

አስፈላጊ የሆነው ለምንድን ነው?

በትዳር ውስጥ መከባበር ከሌለ ባልና ሚስት ሲነጋገሩ ሽሙጥና ትችት ይሰነዝራሉ፤ እንዲሁም አንዳቸው ለሌላው ንቀት እንዳላቸው ያሳያሉ። እንዲህ ያሉ ባሕርያት ደግሞ ተመራማሪዎች እንደሚሉት ትዳሩ እንደሚፈርስ የሚጠቁሙ የመጀመሪያ ምልክቶች ናቸው።

“ስለ ሚስትህ መጥፎ አስተያየት መስጠት፣ አሉባልታ ማውራት፣ ወይም በእሷ ላይ መቀለድ በራስ የመተማመን ስሜቷ እንዲጠፋ፣ በአንተ ላይ ያላት አመኔታ እንዲቀንስና ትዳራችሁ አደጋ እንዲያንዣብብበት ከማድረግ ውጪ የሚፈይደው ነገር የለም።”—ብሪያን

ምን ማድረግ ትችላለህ?

ራስህን ፈትሽ

ለአንድ ሳምንት ያህል፣ ከትዳር ጓደኛህ ጋር ስትሆን የምታደርገው ነገርና ጭውውታችሁ ምን እንደሚመስል ለማስተዋል ሞክር። ከዚያም ራስህን እንዲህ ብለህ ጠይቅ፦

  • ‘የትዳር ጓደኛዬን የነቀፍኳት ምን ያህል ጊዜ ነው? ያመሰገንኳትስ ምን ያህል ጊዜ ነው?’

  • ‘ለትዳር ጓደኛዬ አክብሮት ያሳየሁት በየትኞቹ መንገዶች ነው?’

የሚከተሉትን ጥያቄዎች ከትዳር ጓደኛችሁ ጋር ተወያዩባቸው

  • የትዳር ጓደኛህ እንዳከበረችህ የሚሰማህ ምን ስታደርግልህ ወይም ስትልህ ነው?

  • የትዳር ጓደኛህ እንዳላከበረችህ የሚሰማህ ምን ስታደርግ ወይም ስትል ነው?

ጠቃሚ ምክሮች

  • የትዳር ጓደኛህ አክብሮት እንድታሳይህ የምትፈልገው በየትኞቹ ሦስት መንገዶች እንደሆነ ጻፍ። የትዳር ጓደኛህም እንደዚሁ ታድርግ። ከዚያም የጻፋችሁትን ወረቀት ተለዋወጡና በእነዚህ መንገዶች አክብሮት ለማሳየት ጠንክራችሁ ሥሩ።

  • የትዳር ጓደኛችሁ ካሉት ባሕርያት ውስጥ የምታደንቋቸውን ጻፉ። ከዚያም እነዚያን ባሕርያት ምን ያህል እንደምታደንቋቸው ለትዳር ጓደኛችሁ ንገሩት።

“ባሌን የማከብረው ከሆነ ከፍ አድርጌ እንደምመለከተውና ደስተኛ እንዲሆን እንደምፈልግ የሚያሳዩ ነገሮችን አደርጋለሁ። ይህን ለማሳየት የግድ ትልቅ ነገር ማድረግ አይጠበቅብኝም፤ ሁልጊዜ የማደርጋቸው ትናንሽ ነገሮች ባሌን ከልቤ እንደማከብር ሊያሳዩ ይችላሉ።”—ሜጋን

ዋናው ነገር እናንተ የትዳር ጓደኛችሁን እንደምታከብሩ የሚሰማችሁ መሆኑ ሳይሆን እነሱ እንደምታከብሯቸው የሚሰማቸው መሆኑ ነው።

የመጽሐፍ ቅዱስ መመሪያ፦ “ከአንጀት የመነጨ ርኅራኄን፣ ደግነትን፣ ትሕትናን፣ ገርነትንና ትዕግሥትን ልበሱ።”—ቆላስይስ 3:12