በቀጥታ ወደ ዋናው ጉዳይ ግባ

በቀጥታ ወደ ርዕስ ማውጫው ሂድ

አስደናቂው ክላውን ፊሽ

ብርቱካናማ ክላውን ፊሽ

አስደናቂው ክላውን ፊሽ

የክላውን ፊሽን ያህል ትኩረታችንን የሚስቡ ብዙ የዓሣ ዝርያዎች የሉም። ምናልባትም ቀልባችንን የሚስበው፣ ቀለሙ የሰርከስ ተዋንያን የሚለብሱትን በቀለማት ያሸበረቀ ልብስ ስለሚመስል ሊሆን ይችላል። አሊያም ደግሞ ለመኖሪያ የሚመርጠው ቦታ ያስገርመን ይሆናል፤ ክላውን ፊሽ የሚኖረው አኔመኒ በሚባሉት ተናዳፊ የባሕር ፍጥረታት ቴንታክሎች (ይህ ፍጥረት እንደ እጅ የሚገለገልበት መርዛማ የአካል ክፍል) መካከል ነው። በመሆኑም ክላውን ፊሽ፣ አኔመኒፊሽ ተብሎ የሚጠራ መሆኑ አያስገርምም።

እንደ ብዙዎቹ ታዋቂ ተዋንያን ሁሉ ክላውን ፊሽም ፎቶግራፍ ለመነሳት ፈቃደኛ ነው። ክላውን ፊሽ ከመኖሪያ አካባቢው ርቆ ስለማይሄድ እንዲሁም ሰው ሲጠጋው ስለማይሸሽ ውኃ ውስጥ ጠልቀው የሚዋኙ ዋናተኞች በቀላሉ ፎቶ ሊያነሱት ይችላሉ።

ክላውን ፊሽን በጣም አስደናቂ የሚያደርገው ግን መኖሪያ አካባቢው አደገኛ መሆኑ ነው። መርዛማ በሆኑት የአኔመኒ ቴንታክሎች መካከል መኖር በእባቦች መካከል ከመኖር ተለይቶ አይታይም። ያም ቢሆን ክላውን ፊሹና አኔመኒው ተስማምተው ይኖራሉ። እንዲህ ያለውን እንግዳ የሆነ ዝምድና ሊመሠርቱና ተስማምተው ሊኖሩ የቻሉት እንዴት ነው?

‘ያለ አንተ መኖር አልችልም’

ባለ ሁለት መስመር ክላውን ፊሽ

በክላውን ፊሽና በአኔመኒ መካከል ያለው ይህ ስኬታማ ዝምድና በመደጋገፍና በመረዳዳት ላይ የተመሠረተ ነው። የእነዚህ ፍጥረታት ዝምድና ለክላውን ፊሽ ተስማሚ ብቻ ሳይሆን የግድ አስፈላጊ ነው። የባሕር ውስጥ የሥነ ሕይወት ተመራማሪዎች፣ ክላውን ፊሽ ያለ አኔመኒ ድጋፍ መኖር እንደማይችል ደርሰውበታል። ይህ ዓሣ፣ በፍጥነት መዋኘት ስለማይችል የአኔመኒውን ጥበቃ ካላገኘ የተራቡ አዳኞች ራት መሆኑ አይቀርም። እንዲያውም ክላውን ፊሽ፣ ከአኔመኒው ጋር መኖሩና አደጋ ሲያጋጥመው ወደ እሱ መሸሹ እስከ አሥር ዓመት ድረስ እንዲኖር ያስችለዋል።

አኔመኒው ለክላውን ፊሹ የሚራባበትና የሚኖርበት ቦታ ይሰጠዋል። ክላውን ፊሾች እንቁላሎቻቸውን በሚኖሩበት አኔመኒ መካከል ከጣሉ በኋላ ሁለቱም ጥንዶች በጥንቃቄ እንቁላሎቹን ይጠብቃሉ። እንቁላሎቹ ከተፈለፈሉ በኋላ ደግሞ የክላውን ፊሹ ቤተሰብ አኔመኒው አካባቢ ሲዋኝ ሊታይ ይችላል።

ለመሆኑ አኔመኒው ከዚህ ዝምድና የሚያገኘው ጥቅም ምንድን ነው? ክላውን ፊሹ፣ ለአኔመኒው እንደ ዘብ ጠባቂ በመሆን ቴንታክሎቹን ለመብላት የሚመጡትን በተርፍላይ ፊሽ የተባሉ ዓሦች ያባርርለታል። እንዲያውም ከክላውን ፊሽ ውጭ ጨርሶ በሕይወት መኖር የማይችል አንድ የአኔመኒ ዝርያ አለ። ይህ አኔመኒ፣ ተመራማሪዎች በውስጡ የሚኖረውን ክላውን ፊሽ ሲወስዱበት በበተርፍላይ ፊሽ በመበላቱ ምክንያት በ24 ሰዓት ውስጥ ሙሉ በሙሉ ጠፋ!

ክላውን ፊሽ፣ ለሚኖርበት አኔመኒ የኃይል ምንጭም እንደሆነ ይገመታል። ክላውን ፊሽ የሚያስወጣው አሞኒየም የአኔመኒውን እድገት ያፋጥነዋል። በተጨማሪም ክላውን ፊሽ በአኔመኒው ቴንታክሎች መካከል በሚዋኝበት ጊዜ በኦክሲጅን የበለጸገ ውኃ ለአኔመኒው ያቀርብለታል።

ሌሎች ዓሦች ወደማይደፍሩት አካባቢ መሄድ

ሮዝ ሸለምጥማጥ ክላውን ፊሽ

የክላውን ፊሹ ደህንነት የተመካው በቆዳው ላይ ነው። በቆዳው ላይ እንዳይነደፍ የሚከላከልለት ዝልግልግ ፈሳሽ አለው። ክላውን ፊሹ በዚህ ኬሚካል በመሸፈኑ ምክንያት አኔመኒው የራሱ ዝርያ እንደሆነ አድርጎ ይቆጥረዋል። አንድ የባሕር ውስጥ የሥነ ሕይወት ተመራማሪ እንደገለጹት ክላውን ፊሹ “የአኔመኒ ለምድ የለበሰ ዓሣ” ይሆናል።

አንዳንድ ጥናቶች እንደሚያሳዩት ክላውን ፊሽ ለመኖሪያ የሚሆነውን አኔመኒ ሲመርጥ በመጀመሪያ ከአኔመኒው ጋር መላመድ ይጠበቅበታል። ዓሣው ለመጀመሪያ ጊዜ ወደ አንድ አኔመኒ ሲመጣ ለተወሰኑ ሰዓታት አለፍ አለፍ እያለ አኔመኒውን እንደሚነካው ተስተውሏል። ክላውን ፊሹ በዚህ መልኩ አኔመኒውን መንካቱ፣ መከላከያ ሽፋኑን አዲሱ አኔመኒ ካለው መርዝ ጋር ለማስማማት ያስችለዋል። እርግጥ ነው፣ በዚህ ሂደት ውስጥ ክላውን ፊሹ ሊነደፍ ይችላል። ይህን ሂደት ካለፈ በኋላ ግን ክላውን ፊሹና አኔመኒው ተስማምተው መኖር ይችላሉ።

እነዚህ ፍጹም የተለያዩ ፍጥረታት የሚያደርጉት ትብብር፣ በኅብረት በመሥራት ረገድ ግሩም ትምህርት ይሰጠናል። የተለያየ ባሕልና አስተዳደግ ያላቸው ሰዎች ተባብረው መሥራታቸው በተለያዩ መስኮች አስደናቂ ውጤት አስገኝቷል። ልክ እንደ ክላውን ፊሽ፣ ከሌሎች ጋር አብሮ መሥራትን ለመልመድ የተወሰነ ጊዜ ሊወስድብን ቢችልም ውጤቱ ግን ፈጽሞ አያስቆጭም።