በቀጥታ ወደ ዋናው ጉዳይ ግባ

በቀጥታ ወደ ርዕስ ማውጫው ሂድ

የጥናት ርዕስ 42

መዝሙር 103 እረኞች—ስጦታ የሆኑ ወንዶች

‘ስጦታ ለሆኑት ሰዎች’ አድናቆት አሳዩ

‘ስጦታ ለሆኑት ሰዎች’ አድናቆት አሳዩ

“ወደ ላይ በወጣ ጊዜ [ሰዎችን] ስጦታ አድርጎ ሰጠ።”ኤፌ. 4:8

ዓላማ

የጉባኤ አገልጋዮች፣ ሽማግሌዎችና የወረዳ የበላይ ተመልካቾች የሚረዱን እንዴት ነው? እነዚህ ታማኝ ወንዶች ለሚያከናውኑት ሥራ ያለንን አድናቆት ማሳየት የምንችለውስ እንዴት ነው?

1. ከኢየሱስ ካገኘናቸው ስጦታዎች መካከል አንዳንዶቹ የትኞቹ ናቸው?

 የኢየሱስን ያህል ልግስና ያሳየ ማንም ሰው የለም። ምድር ላይ በነበረበት ወቅት ተአምር የመፈጸም ችሎታውን ተጠቅሞ ሌሎችን በተደጋጋሚ ረድቷል። (ሉቃስ 9:12-17) ሕይወቱን ለእኛ ሲል አሳልፎ በመስጠት ከሁሉ የላቀውን ስጦታ ሰጥቶናል። (ዮሐ. 15:13) ኢየሱስ ከሞት ከተነሳ በኋላም ልግስና ማሳየቱን ቀጥሏል። ቃል በገባው መሠረት፣ የሚያስተምረንንና የሚያጽናናንን መንፈስ ቅዱስን እንዲሰጠን ይሖዋን ጠይቆታል። (ዮሐ. 14:16, 17 ግርጌ፤ 16:13) በተጨማሪም ኢየሱስ በመላው ዓለም ሰዎችን ደቀ መዛሙርት እንድናደርግ በጉባኤ ስብሰባዎቻችን አማካኝነት እኛን ማስታጠቁን ቀጥሏል።—ማቴ. 28:18-20

2. በኤፌሶን 4:7, 8 ላይ ከተጠቀሱት ‘ስጦታ የሆኑ ሰዎች’ መካከል እነማን ይገኙበታል?

2 ኢየሱስ ሌላም ስጦታ ሰጥቶናል። ሐዋርያው ጳውሎስ፣ ኢየሱስ ወደ ሰማይ ከወጣ በኋላ ‘ሰዎችን ስጦታ አድርጎ እንደሰጠ’ ገልጿል። (ኤፌሶን 4:7, 8ን አንብብ።) ጳውሎስ፣ ኢየሱስ ይህን ስጦታ የሰጠን ጉባኤውን በተለያዩ መንገዶች ለመደገፍ እንደሆነ ተናግሯል። (ኤፌ. 1:22, 23፤ 4:11-13) በዛሬው ጊዜ ‘ስጦታ ከሆኑት ሰዎች’ መካከል የጉባኤ አገልጋዮች፣ የጉባኤ ሽማግሌዎችና የወረዳ የበላይ ተመልካቾች ይገኙበታል። a እርግጥ ነው፣ እነዚህ ሰዎች ፍጹማን ስላልሆኑ ስህተት መሥራታቸው አይቀርም። (ያዕ. 3:2) ሆኖም ጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስ እኛን ለመርዳት በእነዚህ ውድ ወንድሞች ይጠቀማል።

3. ሁላችንም ‘ስጦታ የሆኑት ሰዎች’ የሚያከናውኑትን ሥራ መደገፍ የምንችለው እንዴት እንደሆነ በምሳሌ አስረዳ።

3 ኢየሱስ ለእነዚህ ‘ስጦታ የሆኑ ሰዎች’ ጉባኤውን የመገንባት ኃላፊነት ሰጥቷቸዋል። (ኤፌ. 4:12) ሆኖም ሌሎቻችንም ይህን ወሳኝ ኃላፊነት እንዲወጡ ልንረዳቸው እንችላለን። ለምሳሌ ያህል፣ አንድ የስብሰባ አዳራሽ በሚገነባበት ወቅት አንዳንዶቻችን በግንባታ ሥራው በቀጥታ እንካፈላለን። ሌሎች ደግሞ ምግብ በማዘጋጀት፣ ዕቃ በማጓጓዝ ወይም በሌሎች መንገዶች ሥራውን ይደግፋሉ። በተመሳሳይም ሁላችንም የጉባኤ አገልጋዮች፣ የጉባኤ ሽማግሌዎችና የወረዳ የበላይ ተመልካቾች የሚያከናውኑትን ሥራ በንግግራችንም ሆነ በድርጊታችን መደገፍ እንችላለን። እነዚህ ወንድሞች በትጋት ከሚያከናውኑት ሥራ መጠቀም የምንችለው እንዴት እንደሆነ እንዲሁም “ስጦታ” ለሆኑት ለእነዚህ ወንድሞች ያለንን አድናቆት ለእነሱም ሆነ ስጦታውን ለሰጠን ለኢየሱስ ማሳየት የምንችለው እንዴት እንደሆነ እንመልከት።

“ጠቃሚ አገልግሎት የሚያከናውኑ” የጉባኤ አገልጋዮች

4. በመጀመሪያው መቶ ዘመን የጉባኤ አገልጋዮች የትኞቹን ‘ጠቃሚ አገልግሎቶች’ ያከናውኑ ነበር?

4 በመጀመሪያው መቶ ዘመን አንዳንድ ወንድሞች የጉባኤ አገልጋዮች ሆነው ተሹመው ነበር። (1 ጢሞ. 3:8) ጳውሎስ አንዳንዶች ‘ጠቃሚ አገልግሎት እንደሚያከናውኑ’ ሲጽፍ ስለ እነሱ መጥቀሱ ሳይሆን አይቀርም። (1 ቆሮ. 12:28) ሽማግሌዎች በማስተማሩና በእረኝነቱ ሥራ ላይ ትኩረት ማድረግ እንዲችሉ የጉባኤ አገልጋዮች ሌሎች አስፈላጊ ጉዳዮችን ያከናውኑ እንደነበር ከሁኔታዎች መረዳት ይቻላል። ለምሳሌ የጉባኤ አገልጋዮች የቅዱሳን መጻሕፍትን ግልባጭ በማዘጋጀት ወይም ለዚህ ሥራ የሚያስፈልጉትን ቁሳቁሶች በመግዛት እገዛ አበርክተው ሊሆን ይችላል።

5. በዛሬው ጊዜ ያሉ የጉባኤ አገልጋዮች የትኞቹን ጠቃሚ አገልግሎቶች ያከናውናሉ?

5 በጉባኤያችሁ ያሉ የጉባኤ አገልጋዮች የሚያከናውኗቸውን አንዳንድ ጠቃሚ አገልግሎቶች እንመልከት። (1 ጴጥ. 4:10) የጉባኤውን ሒሳብ እንዲከታተሉ፣ ክልል እንዲያደራጁ፣ ጽሑፎችን እንዲያዝዙና ለአስፋፊዎች እንዲሰጡ፣ የኦዲዮና የቪዲዮ መሣሪያዎች ላይ እንዲሠሩ፣ አስተናጋጅ እንዲሆኑ ወይም በስብሰባ አዳራሹ ጥገና ሥራ እንዲካፈሉ ይመደቡ ይሆናል። ጉባኤው በተገቢው መንገድ ሥራውን እንዲያከናውን እነዚህ አገልግሎቶች የግድ አስፈላጊ ናቸው። (1 ቆሮ. 14:40) በተጨማሪም አንዳንድ አገልጋዮች በክርስቲያናዊ ሕይወትና አገልግሎት ስብሰባ ላይ ክፍል ያቀርባሉ፤ እንዲሁም የሕዝብ ንግግር ይሰጣሉ። ከዚህም ሌላ፣ አንድ የጉባኤ አገልጋይ የቡድን የበላይ ተመልካቹ ረዳት ሆኖ ሊመደብ ይችላል። አንዳንድ ጊዜ ደግሞ ብቃት ያላቸው የጉባኤ አገልጋዮች ከጉባኤ ሽማግሌዎች ጋር አብረው እረኝነት ያደርጋሉ።

6. ታታሪ የሆኑትን የጉባኤ አገልጋዮቻችንን የምናደንቃቸው ለምንድን ነው?

6 የጉባኤ አገልጋዮች የሚያከናውኑት ሥራ ጉባኤውን የሚጠቅመው እንዴት ነው? በቦሊቪያ የምትኖር ቤበርሊ b የተባለች እህት እንዲህ ብላለች፦ “ከስብሰባዎቻችን የተሟላ ጥቅም ማግኘት የቻልኩት የጉባኤ አገልጋዮቻችን ስላሉ ነው። እነሱ በሚያከናውኑት ሥራ የተነሳ መዘመር፣ ሐሳብ መስጠት፣ ንግግሮችን ማዳመጥ እንዲሁም ከቪዲዮዎቹና ከሥዕሎቹ ትምህርት ማግኘት እችላለሁ። የደህንነት ስጋት የሚፈጥር ነገር እንዳይኖር በንቃት ይከታተላሉ፤ በተጨማሪም ስብሰባው በቪዲዮ ኮንፈረንስ አማካኝነት እንዲተላለፍ ያደርጋሉ። ከስብሰባው በኋላ ግንባር ቀደም ሆነው በጽዳት ሥራ ይካፈላሉ፤ የሒሳብ ሥራ ይሠራሉ፤ እንዲሁም የሚያስፈልገንን ጽሑፍ እንድናገኝ ያደርጋሉ። እነሱ በመኖራቸው በጣም አመስጋኝ ነኝ።” በኮሎምቢያ የምትኖረው ሌስሊ ባለቤቷ የጉባኤ ሽማግሌ ነው። እንዲህ ብላለች፦ “ባለቤቴ የተለያዩ ሥራዎችን ለማከናወን የጉባኤ አገልጋዮች እርዳታ ያስፈልገዋል። እነሱ ባይኖሩ ኖሮ ሥራ ይበልጥ ይበዛበት ነበር። ስለዚህ ለሚያሳዩት ቅንዓትና በፈቃደኝነት መንፈስ ለሚያበረክቱት እርዳታ በጣም አመስጋኝ ነኝ።” አንተም ስለ ጉባኤ አገልጋዮች እንደዚህ እንደሚሰማህ ምንም ጥያቄ የለውም።—1 ጢሞ. 3:13

7. ለጉባኤ አገልጋዮች ያለንን አድናቆት ማሳየት የምንችለው እንዴት ነው? (ሥዕሉንም ተመልከት።)

7 ለጉባኤ አገልጋዮቻችን የአመስጋኝነት ስሜት ቢሰማንም መጽሐፍ ቅዱስ “አመስጋኝ መሆናችሁን አሳዩ” የሚል ምክር እንደሚሰጥ ማስታወስ ይኖርብናል። (ቆላ. 3:15) ክሪስቶፍ የተባለ በፊንላንድ የሚኖር የጉባኤ ሽማግሌ አመስጋኝነቱን የሚያሳየው እንዴት እንደሆነ ሲገልጽ እንዲህ ብሏል፦ “ፖስት ካርድ ወይም የጽሑፍ መልእክት እልክላቸዋለሁ። በመልእክቱ ውስጥ አንድ ጥቅስ አካትታለሁ፤ በተጨማሪም ያበረታቱኝ እንዴት እንደሆነ ለይቼ በመጥቀስ ወይም አገልግሎታቸውን የማደንቀው ለምን እንደሆነ በመግለጽ አመሰግናቸዋለሁ።” በኒው ካሊዶኒያ የሚኖሩት ፓስካል እና ጃኤል ስለ ጉባኤ አገልጋዮች ይጸልያሉ። ፓስካል እንዲህ ብሏል፦ “ሰሞኑን በጉባኤያችን ውስጥ የሚያገለግሉትን የጉባኤ አገልጋዮች አስመልክቶ ልመና፣ ምልጃና ምስጋና እናቀርባለን።” ይሖዋ እንዲህ ያሉትን ጸሎቶች ይሰማል፤ በዚህም መላው ጉባኤ ይጠቀማል።—2 ቆሮ. 1:11

“በመካከላችሁ በትጋት እየሠሩ” ያሉ የጉባኤ ሽማግሌዎች

8. ጳውሎስ በመጀመሪያው መቶ ዘመን የነበሩት ሽማግሌዎች ‘በትጋት እንደሚሠሩ’ የተናገረው ለምንድን ነው? (1 ተሰሎንቄ 5:12, 13)

8 በመጀመሪያው መቶ ዘመን የነበሩት ሽማግሌዎች ጉባኤውን ለመንከባከብ በትጋት ይሠሩ ነበር። (1 ተሰሎንቄ 5:12, 13ን አንብብ፤ 1 ጢሞ. 5:17) ስብሰባዎችን በመምራት እንዲሁም በሽማግሌዎች አካል ደረጃ ውሳኔ በማድረግ ለጉባኤው ‘አመራር ይሰጣሉ።’ ለወንድሞቻቸውና ለእህቶቻቸው ቀጥተኛ ሆኖም ፍቅር የሚንጸባረቅበት ‘ምክር በመለገስ’ ጉባኤውን ከጉዳት ይጠብቃሉ። (1 ተሰ. 2:11, 12፤ 2 ጢሞ. 4:2) እነዚህ ወንድሞች ቤተሰባቸውን ለማስተዳደርና የራሳቸውን መንፈሳዊነት ለማጠናከርም በትጋት ይሠሩ እንደነበር ምንም ጥያቄ የለውም።—1 ጢሞ. 3:2, 4፤ ቲቶ 1:6-9

9. በዛሬው ጊዜ ያሉ የጉባኤ ሽማግሌዎች የትኞቹን ኃላፊነቶች ይወጣሉ?

9 በዛሬው ጊዜ ያሉ ሽማግሌዎች ብዙ ሥራ አለባቸው። ወንጌላውያን ናቸው። (2 ጢሞ. 4:5) ግንባር ቀደም ሆነው በስብከቱ ሥራ በቅንዓት ይካፈላሉ፤ በክልላቸው ውስጥ የስብከቱን ሥራ ያደራጃሉ፤ እንዲሁም ውጤታማ በሆነ መንገድ መስበክና ማስተማር እንድንችል ያሠለጥኑናል። በተጨማሪም ምሕረት በሚንጸባረቅበትና ከአድልዎ ነፃ በሆነ መንገድ የፍርድ ሥራ ያከናውናሉ። አንድ ክርስቲያን ከባድ ኃጢአት በሚፈጽምበት ጊዜ ሽማግሌዎች ከይሖዋ ጋር ያለውን ወዳጅነት እንዲያድስ ለመርዳት ጥረት ያደርጋሉ። በሌላ በኩል ደግሞ የጉባኤውን ንጽሕና ለማስጠበቅ ጥረት ያደርጋሉ። (1 ቆሮ. 5:12, 13፤ ገላ. 6:1) በዋነኝነት ደግሞ ሽማግሌዎች እረኞች ናቸው። (1 ጴጥ. 5:1-3) ጥሩ ዝግጅት አድርገው ቅዱስ ጽሑፋዊ ንግግሮችን ያቀርባሉ፤ በጉባኤው ውስጥ ያለውን እያንዳንዱን ሰው ለማወቅ ይጥራሉ፤ እንዲሁም የእረኝነት ጉብኝት ያደርጋሉ። አንዳንድ ሽማግሌዎች ደግሞ ከእነዚህ ኃላፊነቶች በተጨማሪ በስብሰባ አዳራሽ ግንባታና ጥገና ሥራ ይካፈላሉ፤ የክልል ስብሰባዎችን ያደራጃሉ፤ እንዲሁም በሆስፒታል አገናኝ ኮሚቴዎችና በሕሙማን ጠያቂ ቡድኖች ውስጥ ያገለግላሉ። በእርግጥም ሽማግሌዎች እኛን ለመርዳት በትጋት ይሠራሉ!

10. ታታሪ የሆኑትን ሽማግሌዎቻችንን የምናደንቃቸው ለምንድን ነው?

10 ይሖዋ በሚገባ የሚንከባከቡን እረኞች ስለሚሰጠን ‘እንደማንፈራና እንደማንሸበር’ ትንቢት ተናግሯል። (ኤር. 23:4) በፊንላንድ የምትኖር ዮሐና የተባለች እህት፣ እናቷ በጠና በታመመችበት ወቅት የእነዚህን ቃላት እውነተኝነት ተመልክታለች። እንዲህ ብላለች፦ “ስሜቴን ለሌሎች መናገር ይከብደኛል። ሆኖም በደንብ የማላውቀው አንድ የጉባኤ ሽማግሌ ትዕግሥት አሳየኝ፤ አብሮኝ ጸለየ፤ እንዲሁም ይሖዋ እንደሚወደኝ እንድተማመን ረዳኝ። የተናገራቸው ቃላት ትዝ አይሉኝም፤ ሆኖም የተሰማኝን የመረጋጋት ስሜት አልረሳውም። ይሖዋ ልክ በሚያስፈልገኝ ጊዜ እኔን ለመርዳት ያንን ወንድም እንደላከልኝ እርግጠኛ ነኝ።” አንተስ በጉባኤህ ውስጥ ያሉት ሽማግሌዎች የረዱህ እንዴት ነው?

11. ለሽማግሌዎች ያለንን አድናቆት ማሳየት የምንችለው እንዴት ነው? (ሥዕሉንም ተመልከት።)

11 ይሖዋ ሽማግሌዎች “በሚያከናውኑት ሥራ የተነሳ” ልባዊ አድናቆት እንድናሳያቸው ይፈልጋል። (1 ተሰ. 5:12, 13) በፊንላንድ የምትኖረው ሄንሪዬታ እንዲህ ብላለች፦ “ሽማግሌዎች ሌሎችን በፈቃደኝነት ይረዳሉ፤ ሆኖም ይህ ሲባል ትርፍ ጊዜና ጉልበት አላቸው ወይም በሕይወታቸው ውስጥ ምንም ተፈታታኝ ሁኔታ አያጋጥማቸውም ማለት አይደለም። አንዳንድ ጊዜ እንዲሁ ሄጄ ‘በጣም ጥሩ ሽማግሌ እንደሆንክ ታውቃለህ? የመጣሁት ይህን ልነግርህ ብዬ ነው’ እላቸዋለሁ።” በቱርክዬ c የምትኖር ሴራ የተባለች እህት እንዲህ ብላለች፦ “ሽማግሌዎች ማገልገላቸውን እንዲቀጥሉ ‘ነዳጅ’ ያስፈልጋቸዋል። ስለዚህ ፖስት ካርድ ልንሰጣቸው፣ ቤታችን ልንጋብዛቸው ወይም አብረናቸው ልናገለግል እንችላለን።” በጣም የምታደንቀው የጉባኤ ሽማግሌ አለ? ከሆነ፣ አድናቆትህን መግለጽ የምትችልባቸውን መንገዶች ፈልግ።—1 ቆሮ. 16:18

የተሾሙ ወንድሞች ማገልገላቸውን እንዲቀጥሉ የሚያስችል “ነዳጅ” ልትሰጧቸው ትችላላችሁ (አንቀጽ 7, 11, 15ን ተመልከት)


ጉባኤዎችን የሚያንጹ የወረዳ የበላይ ተመልካቾች

12. በመጀመሪያው መቶ ዘመን ጉባኤዎችን ለማነጽ ምን ዝግጅት ተደርጎ ነበር? (1 ተሰሎንቄ 2:7, 8)

12 ክርስቶስ ኢየሱስ በሌላ መንገድ የሚያገለግሉ ‘ስጦታ የሆኑ ሰዎችንም’ ሰጥቷል። በኢየሩሳሌም የነበሩት ሽማግሌዎች በእሱ አመራር ሥር ሆነው ጳውሎስን፣ በርናባስንና ሌሎችን ተጓዥ የበላይ ተመልካቾች አድርገው ልከዋቸው ነበር። (ሥራ 11:22) ለምን? ዓላማው የጉባኤ አገልጋዮችና ሽማግሌዎች ከሚሾሙበት ምክንያት ጋር ተመሳሳይ ነው፦ ጉባኤዎችን ማነጽ። (ሥራ 15:40, 41) እነዚህ ወንድሞች ሌሎችን ለማስተማርና ለማበረታታት ሲሉ ምቾታቸውን መሥዋዕት አድርገዋል፤ ሌላው ቀርቶ ሕይወታቸውንም ለአደጋ አጋልጠዋል።—1 ተሰሎንቄ 2:7, 8ን አንብብ።

13. የወረዳ የበላይ ተመልካቾች የትኞቹን ኃላፊነቶች ይወጣሉ?

13 የወረዳ የበላይ ተመልካቾች ሁልጊዜ ጉዞ ላይ ናቸው። አንዳንዶቹ ከአንዱ ጉባኤ ወደ ሌላው ጉባኤ ለመሄድ በመቶዎች የሚቆጠሩ ኪሎ ሜትሮችን መጓዝ ያስፈልጋቸዋል። አንድ የወረዳ የበላይ ተመልካች በየሳምንቱ የተለያዩ ንግግሮችን ያቀርባል፤ እረኝነት ያደርጋል፤ እንዲሁም የአቅኚዎች ስብሰባ፣ የሽማግሌዎች ስብሰባና የስምሪት ስብሰባዎችን ይመራል። ንግግሮችን ይዘጋጃል፤ እንዲሁም የወረዳ ስብሰባዎችንና የክልል ስብሰባዎችን ያደራጃል። በአቅኚዎች ትምህርት ቤት ላይ ያስተምራል፤ በወረዳው ውስጥ ካሉ አቅኚዎች ጋር የሚደረገውን ልዩ ስብሰባ ያደራጃል፤ እንዲሁም ቅርንጫፍ ቢሮው የሚሰጠውን ሌሎች ኃላፊነቶች ይወጣል፤ እነዚህ ኃላፊነቶች አንዳንድ ጊዜ አስቸኳይ ሊሆኑ ይችላሉ።

14. ታታሪ የሆኑትን የወረዳ የበላይ ተመልካቾቻችንን የምናደንቃቸው ለምንድን ነው?

14 ጉባኤዎች፣ ስጦታ የሆኑት የወረዳ የበላይ ተመልካቾች ከሚያከናውኑት ሥራ የሚጠቀሙት እንዴት ነው? በቱርክዬ የሚኖር አንድ ወንድም ስለ ወረዳ የበላይ ተመልካቾች ጉብኝት ሲናገር እንዲህ ብሏል፦ “እያንዳንዱ ጉብኝት ወንድሞቼንና እህቶቼን በመርዳት ተጨማሪ ጊዜ እንዳሳልፍ ያነሳሳኛል። ብዙ የወረዳ የበላይ ተመልካቾችን አግኝቼ አውቃለሁ፤ ሆኖም አንዳቸውም ተቀራቢ እንዳልሆኑ ወይም ለእኔ ጊዜ እንደሌላቸው ተሰምቶኝ አያውቅም።” ቀደም ሲል የተጠቀሰችው ዮሐና ከአንድ የወረዳ የበላይ ተመልካች ጋር አገልግላ ነበር፤ ሆኖም አንድም ሰው ቤት አላገኙም። ያም ቢሆን እንዲህ ብላለች፦ “ያንን ቀን ፈጽሞ አልረሳውም። ሁለቱም እህቶቼ አካባቢ በመቀየራቸው በጣም ናፍቀውኝ ነበር። የወረዳ የበላይ ተመልካቹ በጣም አበረታታኝ። እንዲሁም ይሖዋን እስካገለገልን ድረስ የምንራራቀው ለአጭር ጊዜ ብቻ እንደሆነ አስታወሰኝ፤ በአዲሱ ዓለም አብረን ጊዜ ማሳለፍ የምንችልባቸው ስፍር ቁጥር የሌላቸው አጋጣሚዎች እናገኛለን።” ሌሎች በርካታ የወረዳ የበላይ ተመልካቾችም በወንድሞች ዘንድ ተወዳጅነት አትርፈዋል።—ሥራ 20:37–21:1

15. (ሀ) በ3 ዮሐንስ 5-8 መሠረት ለወረዳ የበላይ ተመልካቾች ያለንን አድናቆት ማሳየት የምንችለው እንዴት ነው? (ሥዕሉንም ተመልከት።) (ለ) ለተሾሙ ወንድሞች ሚስቶች አሳቢነት ማሳየት ያለብን ለምንድን ነው? (“ ሚስቶቻቸውን አስቧቸው” የሚለውን ሣጥን ተመልከት።)

15 ሐዋርያው ዮሐንስ፣ ጋይዮስ ሊጎበኟቸው ለሚመጡት ወንድሞች የእንግዳ ተቀባይነት መንፈስ እንዲያሳይ እንዲሁም ‘አምላክ ደስ በሚሰኝበት ሁኔታ እንዲሸኛቸው’ አበረታቶታል። (3 ዮሐንስ 5-8ን አንብብ።) ይህን ማድረግ የምንችልበት አንዱ መንገድ የወረዳ የበላይ ተመልካቹን ምግብ መጋበዝ ነው። ሌላው መንገድ ደግሞ በጉብኝቱ ወቅት የሚደረጉትን የአገልግሎት ዝግጅቶች መደገፍ ነው። ቀደም ሲል የተጠቀሰችው ሌስሊ በሌሎች መንገዶችም አመስጋኝነቷን ታሳያለች። እንዲህ ብላለች፦ “ይሖዋ የሚያስፈልጋቸውን ነገር እንዲያሟላላቸው እጸልያለሁ። በተጨማሪም እኔና ባለቤቴ ለእነሱ ደብዳቤ በመጻፍ ጉብኝታቸው ምን ያህል እንደጠቀመን እንገልጽላቸዋለን።” የወረዳ የበላይ ተመልካቾች ከሌላው ሰው የተለየ አቅም እንደሌላቸው አስታውስ። አንዳንድ ጊዜ ሊታመሙ፣ በጭንቀት ሊዋጡ አልፎ ተርፎም ተስፋ ሊቆርጡ ይችላሉ። የምንናገራቸው ደግነት የሚንጸባረቅባቸው ቃላት ወይም የምንሰጣቸው አነስተኛ ስጦታ የጸሎታቸው መልስ ሊሆን ይችላል።—ምሳሌ 12:25

‘ስጦታ የሚሆኑ ሰዎች’ ያስፈልጉናል

16. በምሳሌ 3:27 መሠረት ወንድሞች ራሳቸውን ምን ብለው ሊጠይቁ ይችላሉ?

16 በዓለም ዙሪያ “ስጦታ” የሚሆኑ ተጨማሪ ወንድሞች ያስፈልጉናል። የተጠመቅክ ወንድም ከሆንክ በዚህ ረገድ “ለመርዳት የሚያስችል አቅም” አለህ? (ምሳሌ 3:27ን አንብብ።) የጉባኤ አገልጋይ ለመሆን የሚያስፈልገውን ብቃት ለማሟላት ፈቃደኛ ነህ? ወንድሞችህን ይበልጥ መርዳት እንድትችል የጉባኤ ሽማግሌ ለመሆን መጣጣር ትችል ይሆን? d ሁኔታህን አመቻችተህ በመንግሥቱ ወንጌላውያን ትምህርት ቤት ለመካፈል ማመልከት ትችላለህ? ይህ ትምህርት ቤት ኢየሱስ ይበልጥ በተሟላ ሁኔታ እንዲጠቀምብህ ያሠለጥንሃል። እነዚህን ነገሮች ለማድረግ ብቁ እንዳልሆንክ የሚሰማህ ከሆነ ወደ ይሖዋ ጸልይ። የተሰጠህን ማንኛውንም ኃላፊነት በተሳካ ሁኔታ መወጣት እንድትችል በቅዱስ መንፈሱ አማካኝነት እንዲረዳህ ጠይቀው።—ሉቃስ 11:13፤ ሥራ 20:28

17. ‘ስጦታ የሆኑት ሰዎች’ ንጉሣችንን ኢየሱስ ክርስቶስን በተመለከተ ምን ያረጋግጣሉ?

17 ኢየሱስ “ስጦታ” አድርጎ የሾማቸው ወንድሞች በእነዚህ የመጨረሻ ቀናት እሱ እየመራን እንዳለ የሚያሳዩ ማስረጃዎች ናቸው። (ማቴ. 28:20) እሱ ምን እንደሚያስፈልገን ስለሚያውቅ ብቃት ያላቸውን ወንድሞች ሾሞልናል። እንዲህ ያለ ለጋስና አፍቃሪ ንጉሥ ያለን በመሆኑ አመስጋኝ አይደለህም? እንግዲያው ለእነዚህ ታታሪ ወንድሞች ያለህን አድናቆት ማሳየት የምትችልባቸውን አጋጣሚዎች ፈልግ። በተጨማሪም ‘የመልካም ስጦታ ሁሉና የፍጹም ገጸ በረከት ሁሉ’ ምንጭ የሆነውን ይሖዋን ማመስገንህን አትርሳ።—ያዕ. 1:17

መዝሙር 99 እልፍ አእላፋት ወንድሞች

a የበላይ አካል አባላት፣ የበላይ አካሉ ረዳቶች እንዲሁም የቅርንጫፍ ኮሚቴ አባላት ሆነው የሚያገለግሉት ሽማግሌዎችም ሆኑ በሌሎች ኃላፊነቶች የሚያገለግሉት ሽማግሌዎችም ‘ስጦታ ከሆኑት ሰዎች’ መካከል ይካተታሉ።

b አንዳንዶቹ ስሞች ተቀይረዋል።

c ቀደም ሲል ቱርክ ትባል ነበር።

d የጉባኤ አገልጋይ ወይም ሽማግሌ ሆኖ ለማገልገል መጣጣር የሚቻለው እንዴት እንደሆነ ተጨማሪ መረጃ ለማግኘት በኅዳር 2024 መጠበቂያ ግንብ ላይ የወጡትን “ወንድሞች—የጉባኤ አገልጋይ ለመሆን እየተጣጣራችሁ ነው?” እና “ወንድሞች—የጉባኤ ሽማግሌ ለመሆን እየተጣጣራችሁ ነው?” የሚሉትን ርዕሶች ተመልከት።