የጥናት ርዕስ 4
መዝሙር 18 ለቤዛው አመስጋኝ መሆን
ቤዛው ምን ያስተምረናል?
“የአምላክ ፍቅር . . . በዚህ መንገድ ተገልጧል።”—1 ዮሐ. 4:9
ዓላማ
ቤዛው ይሖዋ አምላክና ኢየሱስ ክርስቶስ ስላሏቸው ግሩም ባሕርያት ምን ያስተምረናል?
1. በየዓመቱ በሚከበረው የክርስቶስ ሞት መታሰቢያ በዓል ላይ መገኘታችን የሚጠቅመን እንዴት ነው?
ቤዛው በዋጋ የማይተመን ስጦታ ነው ቢባል እንደምትስማማ ምንም ጥርጥር የለውም! (2 ቆሮ. 9:15) ከይሖዋ ጋር የጠበቀ ወዳጅነት መመሥረት የቻልነው ኢየሱስ ሰብዓዊ ሕይወቱን መሥዋዕት አድርጎ ስለከፈለ ነው። የዘላለም ሕይወት ተስፋም አስገኝቶልናል። ይሖዋ በፍቅር ተነሳስቶ የቤዛውን ዝግጅት ስላደረገልን አመስጋኝ መሆናችን ምንኛ የተገባ ነው! (ሮም 5:8) ኢየሱስ አመስጋኝ ሆነን እንድንቀጥልና ቤዛውን አቅልለን እንዳንመለከት ሲል የሞቱን መታሰቢያ በዓል በየዓመቱ እንድናከብር አዞናል።—ሉቃስ 22:19, 20
2. በዚህ ርዕስ ውስጥ ምን እንመለከታለን?
2 በዚህ ዓመት የመታሰቢያው በዓል የሚከበረው ቅዳሜ፣ ሚያዝያ 12, 2025 ነው። ሁላችንም ለመገኘት እንደምንፈልግ ጥርጥር የለውም። በመታሰቢያው በዓል ሰሞን ይሖዋና ልጁ ስላደረጉልን ነገር ጊዜ ወስደን ማሰላሰላችን a በእጅጉ ይጠቅመናል። በዚህ ርዕስ ውስጥ፣ ቤዛው ስለ ይሖዋና ስለ ልጁ ምን እንደሚያስተምረን እንመለከታለን። በቀጣዩ ርዕስ ላይ ደግሞ ከቤዛው ምን ጥቅም ማግኘት እንደምንችል እንዲሁም አመስጋኝነታችንን ማሳየት የምንችለው እንዴት እንደሆነ እንመረምራለን።
ቤዛው ስለ ይሖዋ ምን ያስተምረናል?
3. የአንድ ሰው መሞት በሚሊዮኖች የሚቆጠሩ ሰዎችን ነፃ ሊያወጣ የሚችለው እንዴት ነው? (ሥዕሉንም ተመልከት።)
3 ቤዛው ስለ ይሖዋ ፍትሕ ያስተምረናል። (ዘዳ. 32:4) እንዴት? አዳም ታዛዥ ባለመሆኑ ከእሱ ኃጢአትንና ሞትን ወርሰናል። (ሮም 5:12) ይሖዋ እኛን ከኃጢአትና ከሞት ነፃ ለማውጣት ሲል ልጁ ቤዛ እንዲሆንልን አደረገ። ይሁንና የአንድ ፍጹም ሰው ሕይወት መሥዋዕት መሆኑ በሚሊዮኖች የሚቆጠሩ ሰዎችን ነፃ ሊያወጣ የሚችለው እንዴት ነው? ሐዋርያው ጳውሎስ እንዲህ በማለት መልሱን ሰጥቶናል፦ “በአንዱ ሰው [በአዳም] አለመታዘዝ ብዙዎች ኃጢአተኞች እንደሆኑ ሁሉ በአንዱ ሰው [በኢየሱስ] መታዘዝም ብዙዎች ጻድቃን ይሆናሉ።” (ሮም 5:19፤ 1 ጢሞ. 2:6) በሌላ አባባል፣ ለኃጢአትና ለሞት ባርነት የዳረገን የአንድ ፍጹም ሰው አለመታዘዝ እንደሆነ ሁሉ ነፃ የምንወጣውም በአንድ ፍጹም ሰው መታዘዝ ምክንያት ነው።
4. ይሖዋ ቀና ልብ ያላቸው የአዳም ዘሮች ለዘላለም እንዲኖሩ እንዲሁ ያልፈቀደው ለምንድን ነው?
4 እኛ እንድንድን ኢየሱስ የግድ መሞት ነበረበት? ይሖዋ ቀና ልብ ያላቸው የአዳም ዘሮች ለዘላለም እንዲኖሩ እንዲሁ ሊፈቅድላቸው አይችልም ነበር? ፍጹማን ካልሆኑ ሰዎች አመለካከት አንጻር ይህ የተሻለ መፍትሔ መስሎ ሊታይ ይችላል። ሆኖም ይህ አመለካከት የይሖዋን ፍጹም ፍትሕ ከግንዛቤ ያስገባ አይደለም። ይሖዋ ፍትሐዊ አምላክ ስለሆነ የአዳምን ዓይን ያወጣ ዓመፅ በቸልታ ሊያልፈው አይችልም።
5. ይሖዋ ሁልጊዜም ትክክል የሆነውን ነገር እንደሚያደርግ እርግጠኞች መሆን የምንችለው ለምንድን ነው?
5 ይሖዋ የፍትሕ መሥፈርቱን በመጣስ፣ ቤዛው ሳይከፈል ፍጹማን ያልሆኑት የአዳም ዘሮች ለዘላለም እንዲኖሩ ቢፈቅድላቸው ኖሮ ምን ይፈጠር ነበር? ሰዎች፣ ይሖዋ በሌሎች ጉዳዮችም የፍትሕ መሥፈርቶቹን ይጥስ ይሆናል የሚል ስጋት ሊያድርባቸው ይችል ነበር። ለምሳሌ ከሰጣቸው ተስፋዎች መካከል አንዳንዶቹን ሳይፈጽም ይቀር ይሆን? እንደዚህ ዓይነት ነገር ይፈጠራል ብለን አንሰጋም። ይሖዋ ልጁን መሥዋዕት እስከማድረግ ድረስ ከፍተኛ ዋጋ ቢያስከፍለውም እንኳ የፍትሕ መሥፈርቱን ማክበሩ ሁልጊዜም ትክክል የሆነውን ነገር እንደሚያደርግ ያረጋግጥልናል።
6. ቤዛው የይሖዋን ፍቅር የሚያሳየው እንዴት ነው? (1 ዮሐንስ 4:9, 10)
6 ቤዛው የይሖዋን ፍትሕ እንድንረዳ ከማድረግ በተጨማሪ እሱ ለእኛ ያለው ፍቅር ምን ያህል ጥልቅ እንደሆነም ያስገነዝበናል። (ዮሐ. 3:16፤ 1 ዮሐንስ 4:9, 10ን አንብብ።) ይሖዋ ቤዛውን የከፈለው ለዘላለም እንድንኖር ብቻ ሳይሆን የእሱ ቤተሰብ አባላት እንድንሆንም ጭምር ነው። እስቲ አስበው፦ አዳም ኃጢአት በሠራ ጊዜ ይሖዋ ታማኝ አገልጋዮቹን ካቀፈው ቤተሰቡ አባረረው። በመሆኑም ሁላችንም ስንወለድ ጀምሮ የአምላክ ቤተሰብ አባላት አይደለንም። ሆኖም ይሖዋ ቤዛውን መሠረት በማድረግ ኃጢአታችንን ይቅር ይለናል፤ እንዲሁም እምነት ያላቸውና ታዛዥ የሆኑ የሰው ዘሮች ቤተሰቡን እንዲቀላቀሉ ይፈቅድላቸዋል። አሁንም እንኳ ከይሖዋና አብረውን እሱን ከሚያገለግሉ ሰዎች ጋር የቅርብ ወዳጅነት መመሥረት እንችላለን። በእርግጥም አምላክ ታላቅ ፍቅር አሳይቶናል!—ሮም 5:10, 11
7. ኢየሱስ የደረሰበት ሥቃይ ይሖዋ ምን ያህል እንደሚወደን የሚያሳየው እንዴት ነው?
7 ቤዛው ይሖዋን ምን ያህል ዋጋ እንዳስከፈለው ስናስብ የፍቅሩን ጥልቀት እንገነዘባለን። ሰይጣን ማንኛውም የይሖዋ አገልጋይ ከባድ ሁኔታ ሲያጋጥመው ለእሱ ታማኝ ሆኖ አይቀጥልም የሚል ክስ ሰንዝሯል። ይሖዋ ለዚህ ክስ ምላሽ ለመስጠት ሲል ኢየሱስ ከመሞቱ በፊት እንዲሠቃይ ፈቅዷል። (ኢዮብ 2:1-5፤ 1 ጴጥ. 2:21) ኢየሱስ ተቃዋሚዎቹ ሲያሾፉበት፣ ወታደሮች ሲገርፉትና በእንጨት ላይ ሲቸነከር ይሖዋ እየተመለከተ ነበር። ከዚያም ይሖዋ የሚወደው ልጁ ተሠቃይቶ ሲሞት አይቷል። (ማቴ. 27:28-31, 39) ይሖዋ በልጁ ላይ የሚደርሰውን መከራ በየትኛውም ሰዓት ላይ ጣልቃ ገብቶ ማስቆም ይችል ነበር። ለምሳሌ ተቃዋሚዎች “አምላክ ከወደደው እስቲ አሁን ያድነው” ባሉ ጊዜ ይሖዋ ልክ ያሉትን ማድረግ ይችል ነበር። (ማቴ. 27:42, 43) ሆኖም አምላክ ጣልቃ ቢገባ ኖሮ ቤዛው አይከፈልም ነበር፤ እኛም ያለተስፋ እንቀር ነበር። ስለሆነም ይሖዋ፣ ልጁ የመጨረሻ ትንፋሹን እስኪተነፍስ ድረስ እንዲሠቃይ ፈቅዷል።
8. ይሖዋ ልጁ ሥቃይ ሲደርስበት ሲመለከት አዝኖ እንደነበር እንዴት እናውቃለን? (ሥዕሉንም ተመልከት።)
8 አምላክ ሁሉን ቻይ ስለሆነ ስሜት የለውም ብለን ልናስብ አይገባም። በእሱ አምሳል የተፈጠሩት ሰዎች ስሜት ካላቸው እሱም ስሜት አለው ብሎ ማሰብ ምክንያታዊ ነው። መጽሐፍ ቅዱስ፣ ይሖዋ ‘ስሜቱ እንደተጎዳ’ እና ‘እጅግ እንዳዘነ’ ይናገራል። (መዝ. 78:40, 41) የአብርሃምንና የይስሐቅን ታሪክም አስታውስ። አብርሃም አንድያ ልጁን መሥዋዕት እንዲያደርግ ታዞ ነበር። (ዘፍ. 22:9-12፤ ዕብ. 11:17-19) አብርሃም ልጁን ይስሐቅን በቢላ ለማረድ እየተዘጋጀ በነበረበት ወቅት ምን ዓይነት ስሜቶች እየተፈራረቁበት እንደነበር ለመገመት እንኳ ያዳግታል። ታዲያ ይሖዋ ልጁ ዓመፀኛ በሆኑ ሰዎች እጅ ተሠቃይቶ ሲገደል ሲመለከት ምንኛ አዝኖ ይሆን!—በእምነታቸው ምሰሏቸው—አብርሃም፣ ክፍል 2 የተባለውን ቪዲዮ jw.org ላይ ተመልከት።
9. ሮም 8:32, 38, 39 ይሖዋ ለእኛም ሆነ ለእምነት አጋሮቻችን ስላለው ፍቅር ምን ያስተምረናል?
9 ቤዛው የቅርብ ዘመዶቻችንንና ጓደኞቻችንን ጨምሮ የይሖዋን ያህል የሚወደን ማንም ሰው እንደሌለ ያስገነዝበናል። (ሮም 8:32, 38, 39ን አንብብ።) ይሖዋ እኛ ራሳችንን ከምንወደውም ይበልጥ ይወደናል። ለዘላለም መኖር ትፈልጋለህ? ከአንተ ይበልጥ ይሖዋ ይህን ይመኝልሃል። ኃጢአትህ ይቅር እንዲባልልህ ትፈልጋለህ? አንተ ኃጢአትህ ይቅር እንዲባል ከምትፈልገው ይበልጥ ይሖዋ ይቅር ሊልህ ይፈልጋል። ይሖዋ ከእኛ የሚፈልገው እምነት በማሳየትና ታዛዥ በመሆን እሱ የሰጠንን የጸጋ ስጦታ እንድንቀበል ብቻ ነው። በእርግጥም ቤዛው የአምላክን ጥልቅ ፍቅር የሚያሳይ ውድ ስጦታ ነው። በአዲሱ ዓለም ውስጥ ደግሞ ስለ ይሖዋ ፍቅር ከአሁኑም ይበልጥ እንማራለን።—መክ. 3:11
ቤዛው ስለ ኢየሱስ ምን ያስተምረናል?
10. (ሀ) ኢየሱስ ከሞቱ ጋር በተያያዘ በተለይ ያሳሰበው ምን ነበር? (ለ) ኢየሱስ የይሖዋን ስም ከነቀፋ ነፃ ያደረገው በየትኞቹ መንገዶች ነው? (“ ኢየሱስ ንጹሕ አቋሙን በመጠበቅ የይሖዋን ስም ከነቀፋ ነፃ አድርጓል” የሚለውን ሣጥንም ተመልከት።)
10 ኢየሱስ ለአባቱ ስም ይቆረቆራል። (ዮሐ. 14:31) ኢየሱስ፣ አምላክን ተሳድቧል በሚል ወንጀል መከሰሱ በአባቱ ስም ላይ ሊያመጣ የሚችለው ነቀፋ በጣም አሳስቦት ነበር። “አባቴ ሆይ፣ የሚቻል ከሆነ ይህ ጽዋ ከእኔ ይለፍ” በማለት የጸለየው ለዚህ ነው። (ማቴ. 26:39) ኢየሱስ እስከ ሞት ድረስ ንጹሕ አቋሙን በመጠበቅ የአባቱን ስም ከነቀፋ ነፃ አድርጓል።
11. ኢየሱስ ለሰዎች ጥልቅ ፍቅር ያሳየው እንዴት ነው? (ዮሐንስ 13:1)
11 በተጨማሪም ቤዛው፣ ኢየሱስ ለሰዎች በጥልቅ እንደሚያስብ ያስገነዝበናል፤ በተለይ ለደቀ መዛሙርቱ በጣም ያስብላቸዋል። (ምሳሌ 8:31፤ ዮሐንስ 13:1ን አንብብ።) ለምሳሌ ኢየሱስ ወደ ምድር ሲመጣ አስቸጋሪ ሁኔታዎች እንደሚያጋጥሙት አልፎ ተርፎም በአሰቃቂ ሁኔታ እንደሚሞት ያውቅ ነበር። ሆኖም ኢየሱስ ሥራውን ያከናወነው ግዴታ ስለሆነበት ብቻ አይደለም። ከዚህ ይልቅ የሰበከው፣ ያስተማረውና ሌሎችን ያገለገለው በፍቅር ተነሳስቶ ነው። በሞተበት ዕለት እንኳ የሐዋርያቱን እግር ያጠበ ከመሆኑም ሌላ ማጽናኛና ትምህርት ሰጥቷቸዋል። (ዮሐ. 13:12-15) በእንጨት ላይ ተሰቅሎ እያለም ጭምር ሊሞት ለተቃረበው ወንጀለኛ ተስፋ ሰጥቶታል፤ እንዲሁም እናቱ እንክብካቤ የምታገኝበትን ዝግጅት አድርጓል። (ሉቃስ 23:42, 43፤ ዮሐ. 19:26, 27) በመሆኑም የኢየሱስ ጥልቅ ፍቅር የታየው በሞቱ ብቻ ሳይሆን በምድር ላይ ባሳለፈው በመላ ሕይወቱ ጭምር ነው።
12. ኢየሱስ በአሁኑ ጊዜ የትኞቹን ነገሮች እያደረገልን ነው?
12 ኢየሱስ የሞተው “ለአንዴና ለመጨረሻ ጊዜ” ቢሆንም አሁንም ብዙ ነገሮችን እያደረገልን ነው። (ሮም 6:10) እንዴት? ከቤዛው ጥቅም እንድናገኝ አሁንም እየሠራ ነው። እስቲ ምን እያደረገ እንደሆነ ለማሰብ ሞክር። ንጉሣችን፣ ሊቀ ካህናታችንና የጉባኤው ራስ ሆኖ እያገለገለ ነው። (1 ቆሮ. 15:25፤ ኤፌ. 5:23፤ ዕብ. 2:17) ታላቁ መከራ ከማብቃቱ በፊት የሚጠናቀቀውን ቅቡዓኑንና እጅግ ብዙ ሕዝብን የመሰብሰቡን ሥራ በበላይነት እየመራ ነው። b (ማቴ. 25:32፤ ማር. 13:27) በእነዚህ የመጨረሻ ቀናት ታማኝ አገልጋዮቹ የሚያስፈልጋቸውን መንፈሳዊ ምግብ እንዲያገኙ እያደረገ ነው። (ማቴ. 24:45) በሺህ ዓመት ግዛቱም እኛን የሚጠቅሙ ነገሮችን ማከናወኑን ይቀጥላል። በእርግጥም ይሖዋ ልጁን የሰጠን እንዲሞትልን ብቻ ሳይሆን የሚጠቅሙንን ብዙ ነገሮች እንዲያደርግልንም ጭምር ነው።
መማርህን ፈጽሞ አታቋርጥ
13. ማሰላሰልህ አምላክና ክርስቶስ ለእኛ ስላላቸው ፍቅር መማርህን እንድትቀጥል የሚረዳህ እንዴት ነው?
13 ይሖዋ አምላክና ኢየሱስ ክርስቶስ ባደረጉልን ነገር ላይ ማሰላሰልህን ከቀጠልክ ለእኛ ስላላቸው ፍቅር ይበልጥ መማር ትችላለህ። ምናልባትም የመታሰቢያው በዓል በሚከበርበት ሰሞን አንዳንዶቹን የወንጌል መጻሕፍት በጥሞና ለማንበብ ጥረት ልታደርግ ትችላለህ። በአንድ ጊዜ ብዙ ምዕራፎችን ለማንበብ አትሞክር። ከዚህ ይልቅ፣ ረጋ ብለህ ይሖዋንና ኢየሱስን ለመውደድ የሚያነሳሱንን ተጨማሪ ምክንያቶች ለማግኘት ሞክር። እንዲሁም ያገኘኸውን ትምህርት በቻልከው መጠን ለሌሎች አካፍል።
14. በመዝሙር 119:97 እና በግርጌ ማስታወሻው መሠረት፣ ምርምር ማድረጋችን ስለ ቤዛውና ስለ ሌሎች ርዕሰ ጉዳዮች መማራችንን እንድንቀጥል የሚረዳን እንዴት ነው? (ሥዕሉንም ተመልከት።)
14 በእውነት ውስጥ ለብዙ ዓመታት ቆይተህ ከሆነ ስለ ይሖዋ ፍትሕ፣ ስለ ፍቅሩ፣ ስለ ቤዛው ወይም እንደዚህ ስለመሳሰሉ የተለመዱ ርዕሰ ጉዳዮች አዲስ እውቀት ማግኘት የምትችል አይመስልህ ይሆናል። እንደ እውነቱ ከሆነ ግን ስለ እነዚህም ሆነ ስለ ሌሎች ርዕሰ ጉዳዮች ገና የማናውቀው ብዙ ነገር አለ። ታዲያ ምን ማድረግ ትችላለህ? በጽሑፎቻችን ውስጥ ብዙ መረጃ ይገኛል፤ ስለዚህ ጽሑፎቻችንን ጥሩ አድርገህ ተጠቀምባቸው። አንድን ጥቅስ መረዳት ከከበደህ ምርምር አድርግ። ከዚያም የዕለት ተዕለት እንቅስቃሴህን በምታከናውንበት ጊዜ ስታጠና ስላገኘኸው ሐሳብ እንዲሁም ስለ ይሖዋ፣ ስለ ልጁና እነሱ ለእኛ ስላላቸው ፍቅር ስላገኘኸው ትምህርት አሰላስል።—መዝሙር 119:97ን እና የግርጌ ማስታወሻውን አንብብ።
15. መንፈሳዊ ዕንቁዎችን መፈለጋችንን መቀጠል ያለብን ለምንድን ነው?
15 ባነበብክ ወይም ምርምር ባደረግክ ቁጥር አዲስ ወይም አስገራሚ ትምህርት አታገኝ ይሆናል፤ ሆኖም ተስፋ ልትቆርጥ አይገባም። ሁኔታው ወርቅ ለማግኘት ከሚደረግ ፍለጋ ጋር ሊመሳሰል ይችላል። ወርቅ የሚፈልጉ ሰዎች አንዲት አነስተኛ የወርቅ ቅንጣት ለማግኘት እንኳ ለሰዓታት ወይም ለቀናት በትዕግሥት ጥረት ማድረግ ሊጠይቅባቸው ይችላል። ሆኖም እያንዳንዱ የወርቅ ቅንጣት ለእነሱ ትልቅ ዋጋ ስላለው ጥረት ማድረጋቸውን ይቀጥላሉ። በመጽሐፍ ቅዱስ ውስጥ የሚገኘው እያንዳንዱ መንፈሳዊ ዕንቁ ደግሞ ከወርቅም የበለጠ ዋጋ አለው! (መዝ. 119:127፤ ምሳሌ 8:10) ስለዚህ ታጋሽ በመሆን መጽሐፍ ቅዱስን በቋሚነት ማንበብህን ቀጥል።—መዝ. 1:2
16. ይሖዋንና ኢየሱስን መምሰል የምንችለው እንዴት ነው?
16 በምታጠናበት ጊዜ ያገኘኸውን ትምህርት በሥራ ላይ ማዋል የምትችልበትን መንገድ አስብ። ለምሳሌ ሌሎችን ከአድልዎ ነፃ በሆነ መንገድ በመያዝ የይሖዋን ፍትሕ ለመኮረጅ ሞክር። ለይሖዋ ስም ስትል መከራ ለመቀበል ፈቃደኛ በመሆንና ራስህን ሳትቆጥብ ወንድሞችህን በማገልገል ኢየሱስ ለአባቱና ለሌሎች ያሳየውን ፍቅር ኮርጅ። በተጨማሪም ለሌሎች በመመሥከር የኢየሱስን ምሳሌ ተከተል፤ እንዲህ ካደረግክ እነሱም የይሖዋን ውድ ስጦታ መቀበል የሚችሉበት አጋጣሚ ይከፈትላቸዋል።
17. በሚቀጥለው ርዕስ ላይ ምን እንመለከታለን?
17 ስለ ቤዛው ይበልጥ በተማርንና አድናቆታችንን ባሳደግን መጠን ለይሖዋና ለልጁ ያለን ፍቅር ይጨምራል። እነሱም በምላሹ እኛን ይበልጥ ይወዱናል። (ዮሐ. 14:21፤ ያዕ. 4:8) እንግዲያው ይሖዋ ያደረገልንን ዝግጅቶች በመጠቀም ስለ ቤዛው መማራችንን እንቀጥል። በሚቀጥለው ርዕስ ላይ፣ ከቤዛው ጥቅም ማግኘትና ይሖዋ ላሳየን ፍቅር አድናቆታችንን መግለጽ የምንችልባቸውን አንዳንድ መንገዶች እንመለከታለን።
መዝሙር 107 መለኮታዊው የፍቅር መንገድ
a ተጨማሪ ማብራሪያ፦ “ማሰላሰል” ማለት ትኩረትን ሰብስቦ በአንድ ጉዳይ ላይ በጥልቀት ማሰብ ማለት ነው።
b ጳውሎስ በኤፌሶን 1:10 ላይ “በሰማያት የሚሆኑ ነገሮችን” ስለመሰብሰብ የተናገረው ሐሳብ ኢየሱስ በማቴዎስ 24:31 እና በማርቆስ 13:27 ላይ “የተመረጡትን” ስለመሰብሰብ ከተናገረው ሐሳብ የተለየ ነው። ጳውሎስ የተናገረው ይሖዋ መንፈሳዊ ልጆቹን በመንፈስ ቅዱስ በመቀባት ስለሚመርጥበት ጊዜ ነው። ኢየሱስ የተናገረው ደግሞ በምድር ላይ የቀሩት ቅቡዓን ክርስቲያኖች በታላቁ መከራ ወቅት ወደ ሰማይ ስለሚሰበሰቡበት ጊዜ ነው።