በቀጥታ ወደ ዋናው ጉዳይ ግባ

በቀጥታ ወደ ርዕስ ማውጫው ሂድ

እውነተኛ ደስታ የሚያስገኘው ምን ዓይነት ፍቅር ነው?

እውነተኛ ደስታ የሚያስገኘው ምን ዓይነት ፍቅር ነው?

“አምላኩ ይሖዋ የሆነለት ሕዝብ ደስተኛ ነው!”—መዝ. 144:15

መዝሙሮች፦ 111, 109

1. የምንኖረው በዓይነቱ ልዩ በሆነ ዘመን ውስጥ ነው እንድንል የሚያደርገን ምንድን ነው?

የምንኖረው በሰው ዘር ታሪክ በዓይነቱ ልዩ በሆነ ዘመን ውስጥ ነው። በመጽሐፍ ቅዱስ ውስጥ አስቀድሞ እንደተነገረው ይሖዋ “ከሁሉም ብሔራት፣ ነገዶች፣ ሕዝቦችና ቋንቋዎች የተውጣጡ . . . እጅግ ብዙ ሕዝብ” እየሰበሰበ ነው። ደስተኛ የሆኑት እነዚህ ሰዎች “ቀንና ሌሊት [ለአምላክ] ቅዱስ አገልግሎት እያቀረቡለት” ሲሆን በአሁኑ ጊዜ ከስምንት ሚሊዮን በላይ ሰዎችን ያቀፈ “ኃያል ብሔር” ሆነዋል። (ራእይ 7:9, 15፤ ኢሳ. 60:22) በእርግጥም አምላክንና ባልንጀሮቻቸውን የሚወዱ ብዛት ያላቸው ሰዎች የኖሩበት እንዲህ ያለ ዘመን ታይቶ አያውቅም።

2. ከአምላክ የራቁ ሰዎች የሚያሳዩት ፍቅር ምን ዓይነት ነው? (በመግቢያው ላይ ያለውን ፎቶግራፍ ተመልከት።)

2 በሌላ በኩል ግን ከላይ ከተጠቀሰው በጣም የተለየ ዓይነት ፍቅር የሚያሳዩ ሰዎችም በዚህ ዘመን እንደሚኖሩ ቅዱሳን መጻሕፍት አስቀድመው ተናግረዋል፤ ከአምላክ የራቁት እነዚህ ሰዎች የሚያሳዩት ፍቅር ራስ ወዳድነት የሚንጸባረቅበት ነው። ሐዋርያው ጳውሎስ “በመጨረሻዎቹ ቀናት . . . ሰዎች ራሳቸውን የሚወዱ፣ ገንዘብ የሚወዱ፣ . . . ከአምላክ ይልቅ ሥጋዊ ደስታን የሚወዱ ይሆናሉ” በማለት ጽፏል። (2 ጢሞ. 3:1-4) እነዚህ ሰዎች የሚያሳዩት ራስ ወዳድነት የሚንጸባረቅበት ፍቅር ለአምላክ ካለን ፍቅር ጋር ይቃረናል። ራስ ወዳድነት የሚንጸባረቅባቸው ግቦችን የሚያሳድዱ ሰዎች የሚፈልጉትን ደስታ አያገኙም። እንዲያውም እንዲህ ያለው ፍቅር፣ ዓለማችን ራስ ወዳድ በሆኑ ግለሰቦች የተሞላና “ለመቋቋም የሚያስቸግር” እንዲሆን አድርጓል።

3. በዚህ ርዕስ ውስጥ ምን እንመረምራለን? ይህን ማድረጋችንስ ምን ጥቅም አለው?

3 ጳውሎስ በብዙዎች ዘንድ የተስፋፋው ራስ ወዳድነት የሚንጸባረቅበት ፍቅር፣ በክርስቲያኖችም ላይ መጥፎ ተጽዕኖ ሊያሳድር እንደሚችል ተገንዝቦ ነበር። በመሆኑም እንዲህ ያለውን ተገቢ ያልሆነ ፍቅር ከሚያሳዩ ሰዎች ‘እንዲርቁ’ አሳስቧል። (2 ጢሞ. 3:5) ይሁን እንጂ እንደነዚህ ካሉ ሰዎች ጋር ምንም ዓይነት ግንኙነት እንዳይኖረን ማድረግ አንችልም። ታዲያ በዓለም ላይ ተስፋፍቶ ያለው አመለካከት እንዳይጋባብን በመጠንቀቅ የፍቅር አምላክ የሆነውን ይሖዋን ማስደሰት የምንችለው እንዴት ነው? አምላክ እንድናዳብር በሚፈልገው ዓይነት ፍቅርና በ2 ጢሞቴዎስ 3:2-4 ላይ በተገለጸው ዓይነት ፍቅር መካከል ያለውን ልዩነት እስቲ እንመልከት። እንዲህ ማድረጋችን ትክክለኛውን ዓይነት ፍቅር እያሳየን መሆኑን ራሳችንን ለመመርመር እንዲሁም እውነተኛ ደስታና እርካታ የሚያስገኘውን ፍቅር እንዴት ማሳየት እንደምንችል ለማወቅ ይረዳናል።

አምላክን መውደድ ወይስ ራስን መውደድ?

4. ሚዛናዊ በሆነ መንገድ ራስን መውደድ ስህተት እንዳልሆነ እንዴት እናውቃለን?

4 ሐዋርያው ጳውሎስ “ሰዎች ራሳቸውን የሚወዱ” እንደሚሆኑ ተናግሯል። ታዲያ ራስን መውደድ ስህተት ነው ማለት ነው? አይደለም፤ እንዲያውም ሚዛናዊ በሆነ መንገድ ራስን መውደድ፣ ተገቢ ከመሆኑም በላይ አስፈላጊ ነው። ይሖዋ የፈጠረን እንዲህ ዓይነት ፍቅር እንዲኖረን አድርጎ ነው። ኢየሱስም “ባልንጀራህን እንደ ራስህ ውደድ” ብሏል። (ማር. 12:31) ራሳችንን የማንወድ ከሆነ ባልንጀራችንን መውደድ አንችልም። በተጨማሪም መጽሐፍ ቅዱስ እንዲህ ይላል፦ “ባሎች ሚስቶቻቸውን እንደ ገዛ አካላቸው አድርገው ሊወዷቸው ይገባል። ሚስቱን የሚወድ ሰው ራሱን ይወዳል፤ የገዛ አካሉን የሚጠላ ማንም ሰው የለምና፤ ከዚህ ይልቅ ይመግበዋል እንዲሁም ይሳሳለታል።” (ኤፌ. 5:28, 29) ከዚህ ለማየት እንደሚቻለው በተገቢው መጠን ራሳችንን ልንወድ ይገባል።

5. ራሳቸውን ከመጠን በላይ ስለሚወዱ ሰዎች ምን ማለት ይቻላል?

5 በ2 ጢሞቴዎስ 3:2 ላይ የተጠቀሰው ዓይነት ፍቅር ተገቢ ከሆነው ፍቅር የተለየ ነው። ጳውሎስ የተናገረው ራሳቸውን ከመጠን በላይ ስለሚወዱ ሰዎች ነው። እንዲህ ያሉት ራስ ወዳድ ሰዎች ከሚገባው በላይ ስለ ራሳቸው ያስባሉ። (ሮም 12:3ን አንብብ።) በሕይወታቸው ውስጥ ትልቁን ቦታ የሚሰጡት ለራሳቸው ስለሆነ ለሌሎች ያን ያህል ግድ የላቸውም። የሆነ ስህተት ሲፈጠር ጥፋታቸውን ከማመን ይልቅ በሌሎች ላይ ማሳበብ ይቀናቸዋል። ስለ ራሳቸው ብቻ የሚያስቡ እንደነዚህ ያሉ ሰዎች እውነተኛ ደስታ የላቸውም።

6. አምላክን የሚወዱ ሰዎች ምን ያገኛሉ?

6 ጳውሎስ በመጨረሻዎቹ ቀናት በስፋት እንደሚታዩ ከጠቀሳቸው መጥፎ ባሕርያት መካከል መጀመሪያ ላይ ያስቀመጠው ራስን መውደድን ነው፤ አንዳንድ የመጽሐፍ ቅዱስ ምሁራን እንደሚናገሩት ጳውሎስ እንዲህ ያደረገው አንድ ሰው፣ ሌሎቹን መጥፎ ባሕርያት እንዲያንጸባርቅ የሚያነሳሳው ራስ ወዳድነት ስለሆነ ነው። ከዚህ በተቃራኒ አምላክን የሚወዱ ሰዎች መልካም ባሕርያትን ያንጸባርቃሉ። መጽሐፍ ቅዱስ፣ አምላክ እንድናዳብር የሚፈልገውን ዓይነት ፍቅር ከደስታ፣ ከሰላም፣ ከትዕግሥት፣ ከደግነት፣ ከጥሩነት፣ ከእምነት፣ ከገርነትና ራስን ከመግዛት ጋር አያይዞ ጠቅሶታል። (ገላ. 5:22, 23) መዝሙራዊው “አምላኩ ይሖዋ የሆነለት ሕዝብ ደስተኛ ነው!” በማለት ጽፏል። (መዝ. 144:15) ይሖዋ ደስተኛ አምላክ ነው፤ ሕዝቡም ቢሆን ደስተኛ ነው። ከዚህም ሌላ ራሳቸውን ከሚወዱና ከሌሎች ስለሚያገኙት ነገር ብቻ ከሚያስቡ ሰዎች በተለየ የይሖዋ አገልጋዮች ለሌሎች በመስጠት ደስታ ያገኛሉ።—ሥራ 20:35

ለራሳችን ሚዛናዊ አመለካከት ለማዳበር ምን ይረዳናል? (አንቀጽ 7⁠ን ተመልከት)

7. አምላክን ከራሳችን አስበልጠን እንደምንወደው ለማወቅ የትኞቹ ጥያቄዎች ይረዱናል?

7 አምላክን ከራሳችን አስበልጠን እንደምንወደው ማወቅ የምንችለው እንዴት ነው? በፊልጵስዩስ 2:3, 4 ላይ የሚገኘውን የሚከተለውን ምክር ልብ እንበል፦ “ሌሎች ከእናንተ እንደሚበልጡ በትሕትና አስቡ እንጂ በጠበኝነት መንፈስ ወይም በትምክህተኝነት ምንም ነገር አታድርጉ፤ ስለ ራሳችሁ ፍላጎት ብቻ ከማሰብ ይልቅ እያንዳንዳችሁ ለሌሎች ሰዎች ፍላጎትም ትኩረት ስጡ።” ራሳችንን እንዲህ እያልን መጠየቅ እንችላለን፦ ‘ይህን ምክር በሕይወቴ ውስጥ ተግባራዊ አደርጋለሁ? የአምላክን ፈቃድ ለመፈጸም ከልቤ እጥራለሁ? በጉባኤ ውስጥም ሆነ በአገልግሎት ላይ ሌሎችን ለመርዳት የሚያስችሉ አጋጣሚዎችን እፈልጋለሁ?’ እርግጥ ነው፣ ጊዜያችንንና ጉልበታችንን ሌሎችን ለመርዳት ማዋል ሁልጊዜ ቀላል ይሆናል ማለት አይደለም። የራሳችንን ጥቅም መሠዋት ብሎም ከፍተኛ ጥረት ማድረግ ሊኖርብን ይችላል። ይሁንና የአጽናፈ ዓለሙን ሉዓላዊ ገዢ ሞገስ እንዳገኘን ከማወቅ በላይ ምን ሊያስደስተን ይችላል?

8. አንዳንዶች ለአምላክ ያላቸው ፍቅር ምን እንዲያደርጉ አነሳስቷቸዋል?

8 አንዳንዶች ይሖዋን ይበልጥ ለማገልገል ሲሉ፣ ዳጎስ ያለ ገቢ ሊያስገኝ የሚችል ሥራቸውን ትተዋል፤ ይህን እንዲያደርጉ ያነሳሳቸው ለአምላክ ያላቸው ፍቅር ነው። በዩናይትድ ስቴትስ የምትኖረውን ኤሪካን እንደ ምሳሌ እንውሰድ። ኤሪካ ሐኪም ብትሆንም በዚህ ሙያ ትልቅ ደረጃ ላይ ለመድረስ ከመጣር ይልቅ የዘወትር አቅኚ ሆነች፤ በተጨማሪም ከባለቤቷ ጋር ሆነው ወደተለያዩ አገሮች እየሄዱ አገልግለዋል። እንዲህ ብላለች፦ “የውጭ አገር ቋንቋ በሚነገርበት አካባቢ ስናገለግል ያገኘናቸው በርካታ ተሞክሮዎች እንዲሁም ያፈራናቸው ወዳጆች ሕይወታችን በጣም አስደሳች እንዲሆን አድርገዋል። አሁንም ቢሆን ሐኪም ሆኜ መሥራቴን አልተውኩም፤ ሆኖም ጊዜዬንና ጉልበቴን በዋነኝነት የማውለው ሰዎችን በመንፈሳዊ ለመርዳትና በጉባኤ ውስጥ አንዳንድ ነገሮችን ለማከናወን መሆኑ ልባዊ ደስታና ጥልቅ እርካታ አስገኝቶልኛል።”

በሰማይ ያለ ሀብት ወይስ በምድር ያለ ሀብት?

9. ገንዘብን መውደድ ደስታ የማያስገኘው ለምንድን ነው?

9 ጳውሎስ፣ በመጨረሻው ዘመን የሚኖሩ ሰዎች “ገንዘብ የሚወዱ” እንደሚሆኑ ጽፏል። በአየርላንድ የሚኖር አንድ አቅኚ ከተወሰኑ ዓመታት በፊት ከአንድ ሰው ጋር ስለ አምላክ ተወያይቶ ነበር። ሰውየው ከኪስ ቦርሳው ውስጥ ገንዘብ አውጥቶ ለወንድም እያሳየ “የእኔ አምላክ ይሄ ነው!” በማለት በኩራት ተናገረ። ብዙዎች እንደዚህ ሰው አመለካከታቸውን በግልጽ ባይናገሩም ዓለማችን ገንዘብንና ገንዘብ የሚገዛቸውን ነገሮች በሚወዱ ሰዎች የተሞላ እንደሆነ ጥያቄ የለውም። በሌላ በኩል ግን መጽሐፍ ቅዱስ “ብርን የሚወድ ብርን አይጠግብም፤ ሀብትንም የሚወድ በሚያገኘው ገቢ አይረካም” የሚል ማሳሰቢያ ይሰጣል። (መክ. 5:10) ገንዘብን የሚወዱ ሰዎች ምንጊዜም ተጨማሪ ለማግኘት ይጥራሉ እንጂ በቃኝ አይሉም፤ ይህ ደግሞ “ብዙ ሥቃይ” ያስከትልባቸዋል።—1 ጢሞ. 6:9, 10

10. መጽሐፍ ቅዱስ ሀብትንና ድህነትን በተመለከተ ምን ይላል?

10 ሁላችንም ገንዘብ እንደሚያስፈልገን የታወቀ ነው። ገንዘብ በተወሰነ መጠንም ቢሆን ጥበቃ ያስገኛል። (መክ. 7:12) ይሁን እንጂ ለመሠረታዊ ፍላጎቶቹ ብቻ የሚበቃ ገንዘብ ያለው ሰው እውነተኛ ደስታ ማግኘት ይችላል? አዎ ይችላል! (መክብብ 5:12ን አንብብ።) የያቄ ልጅ አጉር “ድሃም ሆነ ባለጸጋ አታድርገኝ። ብቻ የሚያስፈልገኝን ቀለብ አታሳጣኝ” ሲል ጽፏል። አጉር በድህነት መቆራመድ ያልፈለገበትን ምክንያት መረዳት አይከብደንም። ቀጥሎ እንደተናገረው ድህነት ወደ ስርቆት ሊመራው ይችላል፤ ይህ ደግሞ የአምላክን ስም ያሰድባል። አጉር “ባለጸጋ አታድርገኝ” በማለት የጸለየውስ ለምንድን ነው? እንዲህ ብሏል፦ “አለዚያ እጠግብና እክድሃለሁ፤ ከዚያም ‘ይሖዋ ማን ነው?’ እላለሁ።” (ምሳሌ 30:8, 9) አንተም ከአምላክ ይልቅ በሀብታቸው የሚታመኑ ሰዎችን ታውቅ ይሆናል።

11. ኢየሱስ ገንዘብን በተመለከተ ምን ምክር ሰጥቷል?

11 ገንዘብን የሚወዱ ሰዎች አምላክን ማስደሰት አይችሉም። ኢየሱስ እንዲህ ብሏል፦ “ለሁለት ጌቶች ባሪያ ሆኖ መገዛት የሚችል ማንም የለም፤ አንዱን ጠልቶ ሌላውን ይወዳል ወይም አንዱን ደግፎ ሌላውን ይንቃል። ለአምላክም ለሀብትም በአንድነት መገዛት አትችሉም።” ኢየሱስ ይህን ምክር ከመስጠቱ በፊት እንደሚከተለው በማለት ተናግሮ ነበር፦ “ብል ሊበላው፣ ዝገት ሊያበላሸውና ሌባ ገብቶ ሊሰርቀው በሚችልበት በምድር ላይ ለራሳችሁ ሀብት አታከማቹ። ከዚህ ይልቅ ብል ሊበላው፣ ዝገት ሊያበላሸውና ሌባ ገብቶ ሊሰርቀው በማይችልበት በሰማይ ለራሳችሁ ሀብት አከማቹ።”—ማቴ. 6:19, 20, 24

12. አኗኗርን ቀላል ማድረግ አምላክን ይበልጥ ለማገልገል የሚያስችለው እንዴት ነው? ምሳሌ ስጥ።

12 ብዙዎች አኗኗራቸውን ቀላል ማድረጋቸው ይበልጥ ደስተኞች ለመሆን ያስቻላቸው ከመሆኑም በላይ ይሖዋን ለማገልገል ተጨማሪ ጊዜ አስገኝቶላቸዋል። በዩናይትድ ስቴትስ የሚኖረው ጃክ ከባለቤቱ ጋር በአቅኚነት ለማገልገል ስለፈለገ የነበራቸውን ትልቅ ቤትና ድርጅታቸውን ሸጠ። ጃክ እንዲህ ብሏል፦ “ከከተማ ወጣ ብሎ የሚገኘውን የሚያምር ቤታችንንና ንብረታችንን ለመሸጥ መወሰን ቀላል አልነበረም። ይሁን እንጂ ለዓመታት፣ በሥራ ቦታ በሚያጋጥሙኝ ችግሮች የተነሳ ወደ ቤት የምመለሰው እየተበሳጨሁ ነበር። የዘወትር አቅኚ የሆነችው ባለቤቴ ግን ምንጊዜም ደስተኛ ናት። ‘የእኔ አለቃ ከማንም የተሻለ ነው!’ ትለኝ ነበር። አሁን እኔም አቅኚ ስለሆንኩ ሁለታችንም የምንሠራው ለአንድ አካል ይኸውም ለይሖዋ ነው።”

ለገንዘብና ሚዛናዊ አመለካከት ለማዳበር ምን ይረዳናል? (አንቀጽ 13⁠ን ተመልከት)

13. ለገንዘብ ያለን አመለካከት ሚዛናዊ መሆኑን መመርመር የምንችለው እንዴት ነው?

13 ለገንዘብ ያለን አመለካከት ሚዛናዊ መሆኑን ለማወቅ የሚከተሉትን ጥያቄዎች በመጠቀም ራሳችንን በሐቀኝነት መመርመራችን ጠቃሚ ነው፦ ‘መጽሐፍ ቅዱስ ገንዘብን በተመለከተ የሚሰጠውን ምክር ከልቤ አምንበታለሁ? አኗኗሬስ ይህን ያሳያል? በሕይወቴ ውስጥ ከምንም በላይ የሚያሳስበኝ ገንዘብ የማግኘት ጉዳይ ነው? ከይሖዋና ከሰዎች ጋር ካለኝ ወዳጅነት ይበልጥ ትልቅ ቦታ የምሰጠው ለቁሳዊ ነገሮች ነው? ይሖዋ የሚያስፈልጉኝን ነገሮች እንደሚያሟላልኝ ሙሉ በሙሉ እተማመናለሁ?’ ይሖዋ እሱን ተስፋ የሚያደርጉትን መቼም ቢሆን እንደማያሳፍራቸው እርግጠኞች መሆን እንችላለን።—ማቴ. 6:33

ይሖዋን መውደድ ወይስ ሥጋዊ ደስታን ማሳደድ?

14. ደስታ በሚያስገኙ እንቅስቃሴዎች ከመካፈል ጋር በተያያዘ ምን አመለካከት ሊኖረን ይገባል?

14 በመጨረሻዎቹ ቀናት የሚኖሩ ብዙ ሰዎች “ሥጋዊ ደስታን የሚወዱ” እንደሚሆኑም አስቀድሞ ተነግሯል። በተገቢው መጠን ራሳችንን መውደድም ሆነ ስለ ገንዘብ ማሰብ ስህተት እንዳልሆነ ሁሉ፣ በሚያስደስቱን እንቅስቃሴዎች ሚዛናዊ በሆነ መንገድ መካፈልም ምንም ስህተት የለውም። ይሖዋ የሚፈልገው የመናኞች ዓይነት ሕይወት እንድንመራ ወይም ደስታ በሚያስገኙ ጤናማ እንቅስቃሴዎች ከመካፈል እንድንርቅ አይደለም። መጽሐፍ ቅዱስ “ሂድ፣ ምግብህን በደስታ ብላ፤ ልብህም ደስ ብሎት ወይንህን ጠጣ” በማለት የአምላክን አገልጋዮች ይመክራል።—መክ. 9:7

15. “ሥጋዊ ደስታን የሚወዱ” የሚለው አገላለጽ ምን ያመለክታል?

15 ሁለተኛ ጢሞቴዎስ 3:4 ሥጋዊ ደስታን በማሳደድ ተጠምደው በሕይወታቸው ውስጥ ለአምላክ ቦታ ስለማይሰጡ ሰዎች ይገልጻል። ጥቅሱ የሚናገረው ሰዎች ‘ከአምላክ ይበልጥ ሥጋዊ ደስታን እንደሚወዱ’ አለመሆኑን ልብ እንበል፤ እንደዚያ ቢሆን ኖሮ እነዚህ ሰዎች በተወሰነ መጠንም ቢሆን ለአምላክ ፍቅር እንዳላቸው የሚጠቁም ይሆን ነበር። ጳውሎስ የተናገረው ‘ከአምላክ ይልቅ ሥጋዊ ደስታን እንደሚወዱ’ ነው። አንድ ምሁር እንዲህ ብለዋል፦ “ይህ [ጥቅስ] ሰዎቹ በተወሰነ ደረጃ አምላክን እንደሚወዱ የሚገልጽ አይደለም። ከዚህ ይልቅ አምላክን ፈጽሞ እንደማይወዱት የሚያመለክት ነው።” ሥጋዊ ደስታን ከመጠን በላይ የሚወዱ ሰዎች ይህን ነጥብ በቁም ነገር ሊያስቡበት ይገባል! “ሥጋዊ ደስታን የሚወዱ” የተባሉት ‘በዚህ ዓለም ሥጋዊ ደስታ ትኩረታቸው የተከፋፈለ’ ሰዎች እንደሆኑ መጽሐፍ ቅዱስ ይጠቁማል።—ሉቃስ 8:14

16, 17. ደስታ በሚያስገኙ እንቅስቃሴዎች በመካፈል ረገድ ኢየሱስ ምን አመለካከት ነበረው?

16 ኢየሱስ፣ ደስታ በሚያስገኙ እንቅስቃሴዎች በመካፈል ረገድ ሚዛናዊ አመለካከት ነበረው። በአንድ ወቅት ‘በሠርግ ድግስ’ ላይ በሌላ ጊዜ ደግሞ ሌዊ ባዘጋጀው “ትልቅ ግብዣ” ላይ ተገኝቷል። (ዮሐ. 2:1-10፤ ሉቃስ 5:29) በሠርጉ ድግስ ላይ የወይን ጠጅ ባለቀበት ወቅት ውኃውን ወደ ወይን ጠጅ በመቀየር ተአምር ፈጽሟል። በሌላ አጋጣሚ ደግሞ፣ ተመጻዳቂ የሆኑ ሰዎች ኢየሱስን በመብላቱና በመጠጣቱ በነቀፉት ጊዜ፣ አመለካከታቸውን ማስተካከል እንዳለባቸው በግልጽ ነግሯቸዋል።—ሉቃስ 7:33-36

17 ይህ ሲባል ግን የኢየሱስ ሕይወት ሥጋዊ ደስታን በማሳደድ ላይ ያተኮረ ነበር ማለት አይደለም። በሕይወቱ ውስጥ ይሖዋን ያስቀደመ ከመሆኑም ሌላ ሰዎችን ለመርዳት አቅሙ የፈቀደውን ሁሉ አድርጓል። በተጨማሪም ብዙዎች ሕይወት እንዲያገኙ ሲል በመከራ እንጨት ላይ ተሠቃይቶ ለመሞት ፈቃደኛ ሆኗል። ኢየሱስ ተከታዮቹን እንዲህ ብሏቸዋል፦ “በእኔ ምክንያት ሰዎች ሲነቅፏችሁ፣ ስደት ሲያደርሱባችሁና ክፉውን ሁሉ በውሸት ሲያስወሩባችሁ ደስተኞች ናችሁ። በሰማያት የሚጠብቃችሁ ሽልማት ታላቅ ስለሆነ ሐሴት አድርጉ፤ በደስታም ፈንጥዙ፤ ከእናንተ በፊት የነበሩትን ነቢያት እንደዚሁ ስደት አድርሰውባቸው ነበርና።”—ማቴ. 5:11, 12

ለሥጋዊ ደስታ ሚዛናዊ አመለካከት ለማዳበር ምን ይረዳናል? (አንቀጽ 18⁠ን ተመልከት)

18. ሥጋዊ ደስታ ለሚያስገኙ ነገሮች ያለንን አመለካከት ለማወቅ የሚረዱን የትኞቹ ጥያቄዎች ናቸው?

18 ሥጋዊ ደስታ ለሚያስገኙ ነገሮች ያለን አመለካከት ሚዛናዊ መሆኑን ማወቅ የምንችለው እንዴት ነው? ራሳችንን እንደሚከተለው ብለን መጠየቃችን ጠቃሚ ነው፦ ‘ከስብሰባዎችና ከአገልግሎት ይልቅ ለመዝናኛ ቅድሚያ እሰጣለሁ? አምላክን ለማገልገል ስል የምወዳቸውን ነገሮች መሥዋዕት ለማድረግ ፈቃደኛ ነኝ? መዝናኛ በምመርጥበት ወቅት የይሖዋን አመለካከት ከግምት አስገባለሁ?’ አምላክን ከልባችን የምንወደው ከሆነ እሱን እንደሚያሳዝነው ከምናውቀው ነገር ብቻ ሳይሆን ሊያሳዝነው እንደሚችል ከምናስበው ነገርም ጭምር እንርቃለን።ማቴዎስ 22:37, 38ን አንብብ።

እውነተኛ ደስታ የሚያስገኘው መንገድ

19. የትኛው አካሄድ እውነተኛ ደስታ አያስገኝም?

19 የሰው ልጆች በሰይጣን ዓለም ውስጥ ለ6,000 ዓመታት ያህል ሲሠቃዩ ኖረዋል። ዛሬ የምንኖረው በዚህ ሥርዓት የመጨረሻ ቀናት ውስጥ ሲሆን ምድር ራሳቸውን፣ ገንዘብንና ሥጋዊ ደስታን ከሚገባው በላይ በሚወዱ ሰዎች ተሞልታለች። እነዚህ ሰዎች የሚያስቡት፣ ማግኘት ስለሚችሉት ነገር ብቻ ከመሆኑም ሌላ በሕይወታቸው ውስጥ ትልቁን ቦታ የሚሰጡት ለራሳቸው ፍላጎት ነው። እንዲህ ዓይነቶቹ ሰዎች መቼም ቢሆን እውነተኛ ደስታ ሊኖራቸው አይችልም። ከዚህ በተቃራኒ ግን መዝሙራዊው እንደገለጸው “የያዕቆብ አምላክ ረዳቱ የሆነ፣ በአምላኩ በይሖዋ ተስፋ የሚያደርግ ሰው ደስተኛ ነው።”—መዝ. 146:5

20. አምላክን መውደድህ ደስታ ያስገኘልህ እንዴት ነው?

20 የአምላክ ሕዝቦች ለእሱ ያላቸው ፍቅር ከጊዜ ወደ ጊዜ እየጨመረ ነው፤ ስለ አምላክ የተማሩና ለእሱ ፍቅር ያዳበሩ ሌሎች ብዙዎችም በየዓመቱ ከአምላክ ሕዝቦች ጋር ይተባበራሉ። ይህም የአምላክ መንግሥት እየገዛ እንዳለና በቅርቡ ለምድር ነዋሪዎች አስደናቂ በረከቶችን እንደሚያመጣ የሚያሳይ ማስረጃ ነው። እውነተኛና ዘላቂ የሆነ ደስታ የሚያስገኝልን የአምላክን ፈቃድ ማድረጋችን ብሎም ሉዓላዊውን አምላክ እያስደሰትን እንደሆነ ማወቃችን ነው። ይሖዋን የሚወዱ ሰዎች ለዘላለም ደስተኞች ሆነው ይኖራሉ! በሚቀጥለው ርዕስ ላይ፣ ራስ ወዳድ የሆኑ ሰዎች የሚያንጸባርቋቸውን አንዳንድ መጥፎ ባሕርያት እንመለከታለን፤ በተጨማሪም እነዚህ ባሕርያት የይሖዋ አገልጋዮች ከሚያሳዩአቸው መልካም ባሕርያት እንዴት እንደሚለዩ እንመረምራለን።