በቀጥታ ወደ ዋናው ጉዳይ ግባ

በቀጥታ ወደ ርዕስ ማውጫው ሂድ

ወጣቶች—“የራሳችሁን መዳን ከፍጻሜ ለማድረስ ተግታችሁ ሥሩ”

ወጣቶች—“የራሳችሁን መዳን ከፍጻሜ ለማድረስ ተግታችሁ ሥሩ”

“ሁልጊዜ ታዛዥ እንደሆናችሁ ሁሉ በፍርሃትና በመንቀጥቀጥ የራሳችሁን መዳን ከፍጻሜ ለማድረስ ተግታችሁ ሥሩ።”—ፊልጵ. 2:12

መዝሙሮች፦ 133, 135

1. ጥምቀት አስፈላጊ እርምጃ ነው የምንለው ለምንድን ነው? (በመግቢያው ላይ ያለውን ፎቶግራፍ ተመልከት።)

በየዓመቱ በሺዎች የሚቆጠሩ የመጽሐፍ ቅዱስ ጥናቶች ይጠመቃሉ። ከእነዚህ መካከል ብዙዎቹ፣ ልጆች አሊያም በአሥራዎቹ ዕድሜ የሚገኙ ወጣቶች ናቸው። እነዚህ ወጣቶች በእውነት ቤት ያደጉ ሊሆኑ ይችላሉ። አንተስ እንዲህ ዓይነት ውሳኔ ካደረጉ ወጣቶች መካከል ነህ? ከሆነ እንዲህ ያለ እርምጃ መውሰድህ የሚደነቅ ነው። ጥምቀት ከሁሉም ክርስቲያኖች የሚጠበቅ ብቃት ከመሆኑም በላይ መዳን ለማግኘት አስፈላጊ የሆነ እርምጃ ነው።—ማቴ. 28:19, 20፤ 1 ጴጥ. 3:21

2. አንድ ወጣት ራሱን ከመወሰን ወደኋላ ማለት የማይገባው ለምንድን ነው?

2 ጥምቀት የተለያዩ በረከቶችን ለማግኘት በር የሚከፍት ቢሆንም የሚያስከትለው ኃላፊነትም አለ። ይህ ሲባል ምን ማለት ነው? በተጠመቃችሁበት ቀን ከቀረቡላችሁ ጥያቄዎች መካከል “በኢየሱስ ክርስቶስ መሥዋዕት በማመን ከኃጢአታችሁ ንስሐ ገብታችሁ የይሖዋን ፈቃድ ለማድረግ ራሳችሁን ወስናችኋል?” የሚለው ይገኝበታል፤ እናንተም ‘አዎ’ የሚል መልስ ሰጥታችኋል። ጥምቀት፣ ራሳችሁን ለይሖዋ መወሰናችሁን ለማሳየት የወሰዳችሁት እርምጃ ነው። ስትጠመቁ፣ ይሖዋን ለመውደድና የእሱን ፈቃድ ከምንም ነገር በላይ ለማስቀደም ቃል ገብታችኋል። በዚህ መንገድ የገባችሁትን ቃል በቁም ነገር ልታዩት ይገባል። እንዲህ ዓይነት ቃል መግባት የሚያስቆጭ ነው? በፍጹም አይደለም። ሕይወታችሁን ለይሖዋ መስጠታችሁ መቼም ቢሆን የተሳሳተ እርምጃ ሊሆን አይችልም። እንዲህ ያለ ውሳኔ ባታደርጉ ኖሮ ሌላው አማራጭ ምን ሊሆን እንደሚችል እስቲ አስቡት። አንድ ሰው ከይሖዋ ርቆ የሚኖር ከሆነ የሰይጣን ዓለም ክፍል መሆኑ አይቀርም። ሰይጣን ደግሞ የእናንተ መዳን ጨርሶ ግድ አይሰጠውም። እንዲያውም ከእሱ ጎን ሆናችሁ የይሖዋን ሉዓላዊነት ብትቃወሙና የዘላለም ሕይወት ብታጡ ደስታውን አይችለውም።

3. ራሳችሁን ለይሖዋ መወሰናችሁ ምን በረከቶች ያስገኝላችኋል?

3 ከሰይጣን ጎን ከመቆም ይልቅ ራሳችሁን ለይሖዋ መወሰናችሁ እና መጠመቃችሁ የሚያስገኛቸውን በረከቶች እስቲ አስቡ። ሕይወታችሁን ለይሖዋ መስጠታችሁ “ይሖዋ ከጎኔ ነው፤ አልፈራም። ሰው ምን ሊያደርገኝ ይችላል?” ብላችሁ በልበ ሙሉነት ለመናገር ያስችላችኋል። (መዝ. 118:6) ከአምላክ ጎን ከመቆምና የእሱን ሞገስ ከማግኘት ጋር የሚወዳደር ታላቅ መብት በሕይወታችሁ ውስጥ ልታገኙ አትችሉም።

በግለሰብ ደረጃ የምትሸከመው ኃላፊነት

4, 5. (ሀ) ራስን መወሰን አንድ ሰው በግለሰብ ደረጃ የሚሸከመው ኃላፊነት ነው የምንለው ለምንድን ነው? (ለ) በየትኛውም የዕድሜ ክልል ላይ የሚገኙ ክርስቲያኖች ምን ተፈታታኝ ሁኔታዎች ያጋጥሟቸዋል?

4 አንድ የተጠመቀ ክርስቲያን ከይሖዋ ጋር የሚኖረው ዝምድና፣ ከቤተሰቡ በውርስ የሚያገኘው ነገር አይደለም። የተጠመቅህ ወጣት ከሆንክ ለመዳን የሚያስፈልገውን እርምጃ መውሰድ የአንተ ኃላፊነት ነው፤ የምትኖረው ከወላጆችህ ጋር መሆኑ ይህን እውነታ አይቀይረውም። ይህን ማስታወስ አስፈላጊ የሆነው ለምንድን ነው? ምክንያቱም ምን ዓይነት ተፈታታኝ ሁኔታዎች እንደሚያጋጥሙህ አስቀድመህ ማወቅ የምትችለው ሁልጊዜ አይደለም። ለምሳሌ፣ የተጠመቅከው በልጅነትህ ከሆነ የጉርምስና ዕድሜ ላይ ስትደርስ አዳዲስ ስሜቶች ሊፈጠሩብህ እንዲሁም የተለያዩ ተጽዕኖዎች ሊያጋጥሙህ ይችላሉ። አንዲት የ18 ዓመት ወጣት ይህ ሊሆን የሚችልበትን መንገድ ስትገልጽ እንዲህ ብላለች፦ “አንድ ልጅ [ልደቱ ስላልተከበረለት] ብቻ፣ የይሖዋ ምሥክር በመሆኑ የቀረበት ነገር እንዳለ አይሰማው ይሆናል። የፆታ ስሜት የሚያይልበት ዕድሜ ላይ ሲደርስ ግን የይሖዋን ሕጎች መታዘዝ ምንጊዜም የተሻለ አካሄድ ስለመሆኑ ከልቡ ማመን ያስፈልገዋል።”

5 እርግጥ ነው፣ ያልጠበቋቸው ተፈታታኝ ሁኔታዎች የሚያጋጥሟቸው ወጣቶች ብቻ አይደሉም። ትልቅ ከሆኑ በኋላ የተጠመቁ ክርስቲያኖችም እንኳ በርካታ ያልተጠበቁ የእምነት ፈተናዎች ያጋጥሟቸዋል። ከትዳር፣ ከጤንነት አሊያም ከሥራ ጋር በተያያዘ የሚያጋጥሙ ፈታኝ ሁኔታዎችን እንደ ምሳሌ መጥቀስ ይቻላል። በእርግጥም በየትኛውም የዕድሜ ክልል ላይ የሚገኝ ክርስቲያን ለይሖዋ ያለውን ታማኝነት የሚፈትኑ ሁኔታዎች ያጋጥሙታል።—ያዕ. 1:12-14

6. (ሀ) ለይሖዋ የገባኸውን ቃል መጠበቅህ በሁኔታዎች ላይ የተመካ አይደለም የምንለው ለምንድን ነው? (ለ) ከፊልጵስዩስ 4:11-13 ምን እንማራለን?

6 ምንም ዓይነት ፈተና ቢያጋጥምህ ታማኝ ለመሆን እንድትችል የሚረዳህ ነገር አለ፤ ይህም ለይሖዋ ቃል ስትገባ በየትኛውም ዓይነት ሁኔታ ውስጥ እሱን ለማገልገል እንደተሳልክ ምንጊዜም ማስታወስህ ነው። እንዲህ ሲባል ጓደኞችህ ወይም ወላጆችህ ይሖዋን ማገልገላቸውን ቢያቆሙ እንኳ አንተ እሱን ማገልገልህን እንደምትቀጥል ለአጽናፈ ዓለሙ ሉዓላዊ ገዢ ነግረኸዋል ማለት ነው። (መዝ. 27:10) ምንም ዓይነት ሁኔታ ቢያጋጥምህ ይሖዋ ከውሳኔህ ጋር በሚስማማ መንገድ ለመኖር የሚያስችልህን ብርታት እንድታገኝ ይረዳሃል።—ፊልጵስዩስ 4:11-13ን አንብብ።

7. “በፍርሃትና በመንቀጥቀጥ” የራስን መዳን ከፍጻሜ ለማድረስ ተግቶ መሥራት ሲባል ምን ማለት ነው?

7 ይሖዋ፣ ወዳጁ እንድትሆን ይፈልጋል። ሆኖም ከእሱ ጋር የመሠረትከውን ወዳጅነት ጠብቆ ማቆየትና የራስህን መዳን ከፍጻሜ ማድረስ ጥረት ይጠይቃል። እንዲያውም ፊልጵስዩስ 2:12 “በፍርሃትና በመንቀጥቀጥ የራሳችሁን መዳን ከፍጻሜ ለማድረስ ተግታችሁ ሥሩ” ይላል። ይህ ጥቅስ፣ ምንም ዓይነት ፈተና ቢያጋጥምህ ከይሖዋ ጋር የመሠረትከውን ወዳጅነት ጠብቀህ የማቆየትንና ለእሱ ታማኝ የመሆንን ጉዳይ ልታስብበት እንደሚገባ ይጠቁማል። በዚህ ረገድ ከልክ በላይ በራስህ መተማመን አይኖርብህም። ለረጅም ዓመታት አምላክን ያገለገሉ አንዳንድ ክርስቲያኖችም እንኳ ከእውነት ቤት ወጥተዋል። ታዲያ የራስህን መዳን ከፍጻሜ ለማድረስ ተግተህ መሥራት እንድትችል የትኞቹ ነገሮች ይረዱሃል?

መጽሐፍ ቅዱስን ማጥናት ወሳኝ ነው

8. መጽሐፍ ቅዱስን በግል ማጥናት ሲባል ምን ነገሮችን ይጨምራል? ይህስ አስፈላጊ የሆነው ለምንድን ነው?

8 ከይሖዋ ጋር የመሠረትከውን ወዳጅነት ይዘህ ለመቀጠል፣ እሱ ሲያናግርህ ማዳመጥ እንዲሁም ሐሳብህን ለእሱ መግለጽ ያስፈልግሃል። ይሖዋ ሲናገር ማዳመጥ የምንችልበት ዋነኛው መንገድ መጽሐፍ ቅዱስን በግላችን ማጥናት ነው። ይህም የአምላክን ቃል እና በመጽሐፍ ቅዱስ ላይ የተመሠረቱ ጽሑፎቻችንን በማንበብ እንዲሁም ባነበብነው ላይ በማሰላሰል እውቀት መቅሰምን ይጨምራል። ይሁን እንጂ መጽሐፍ ቅዱስን ማጥናት እንዲሁ የአእምሮ እውቀት ለማካበት ተብሎ የሚደረግ ነገር እንዳልሆነ አስታውስ። ወይም ደግሞ የትምህርት ቤት ፈተና ለማለፍ እንደምታደርገው መረጃዎችን ሸምድዶ የመያዝ ጉዳይ አይደለም። ውጤታማ የሆነ ጥናት፣ አዳዲስ ነገሮችን ለማወቅ ከሚያስችል አስደሳች ጉዞ ጋር ሊመሳሰል ይችላል፤ እንዲህ ያለው ጥናት ስለ ይሖዋ ማንነት ከዚህ በፊት የማታውቃቸውን ነገሮች ለመገንዘብ ያስችልሃል። ይህ ደግሞ ወደ አምላክ ለመቅረብ ይረዳሃል፤ እሱም በምላሹ ወደ አንተ ይቀርባል።—ያዕ. 4:8

ይሖዋ ሲያናግርህ ታዳምጣለህ? አንተስ ሐሳብህን ትገልጽለታለህ? (ከአንቀጽ 8-11⁠ን ተመልከት)

9. ለግል ጥናትህ ጠቃሚ ሆነው ያገኘሃቸው መሣሪያዎች የትኞቹ ናቸው?

9 የይሖዋ ድርጅት፣ የጥናት ፕሮግራምህ ውጤታማ እንዲሆን የሚረዱህ የተለያዩ መሣሪያዎችን አዘጋጅቷል። ለምሳሌ፣ jw.org/am ላይ “ወጣቶች” በሚለው ሥር የሚገኙት “የመጽሐፍ ቅዱስ ጥናት መልመጃዎች” ከመጽሐፍ ቅዱስ ታሪኮች ጠቃሚ ትምህርት እንድታገኝ ይረዱሃል። በተጨማሪም jw.org/am ላይ የሚወጡት “ትክክለኛው የመጽሐፍ ቅዱስ ትምህርት ምንድን ነው?” ለተባለው መጽሐፍ የተዘጋጁት የማጥኛ ጽሑፎች፣ የምታምንባቸው ነገሮች በአሳማኝ ማስረጃ ላይ የተመሠረቱ መሆናቸውን ለማረጋገጥ ያስችሉሃል። እነዚህ የማጥኛ ጽሑፎች የምታምንባቸውን ነገሮች ለሌሎች እንዴት ማስረዳት እንደምትችል ለመለማመድም ይረዱሃል። ለጥናት የሚያግዙ ተጨማሪ ሐሳቦችን በሚያዝያ 2009 ንቁ! ላይ በወጣው “የወጣቶች ጥያቄ . . . የመጽሐፍ ቅዱስ ንባቤን አስደሳች ማድረግ የምችለው እንዴት ነው?” በሚለው ርዕስ ሥር ማግኘት ትችላለህ። የራስህን መዳን ከፍጻሜ ለማድረስ ተግተህ በመሥራት ረገድ ጥናትና ማሰላሰል ወሳኝ ሚና አላቸው።መዝሙር 119:105ን አንብብ።

ጸሎት በጣም አስፈላጊ ነው

10. ጸሎት ለአንድ የተጠመቀ ክርስቲያን በጣም አስፈላጊ የሆነው ለምንድን ነው?

10 የግል ጥናት ይሖዋ ሲያናግረን የምናዳምጥበት መንገድ ሲሆን ጸሎት ደግሞ ሐሳባችንን ለእሱ ለመግለጽ ያስችለናል። አንድ ክርስቲያን ጸሎት፣ አንድን ጉዳይ ለማሳካት የሚረዳ ምትሃታዊ ኃይል እንዳለው ሊያስብ አይገባም፤ አሊያም ጸሎትን በዘልማድ እንደሚከናወን የአምልኮ ሥርዓት አድርጎ ማየት የለበትም። ጸሎት ለፈጣሪያችን የልባችንን አውጥተን የምንገልጽበት መንገድ ነው። ይሖዋ ሐሳብህን ስትገልጽ መስማት ይፈልጋል። (ፊልጵስዩስ 4:6ን አንብብ።) የሚያስጨንቅ ሁኔታ በሚያጋጥምህ ጊዜስ ምን ማድረግ ትችላለህ? መጽሐፍ ቅዱስ “ሸክምህን በይሖዋ ላይ ጣል” የሚል ጥበብ ያዘለ ምክር ይሰጥሃል። (መዝ. 55:22) ይህን ምክር መከተል በእርግጥ ጠቃሚ እንደሆነ ይሰማሃል? በሚሊዮን የሚቆጠሩ ወንድሞችና እህቶች በመጸለያቸው እንደተጠቀሙ ሊያረጋግጡልህ ይችላሉ። ጸሎት አንተንም ሊረዳህ ይችላል!

11. ምንጊዜም ይሖዋን ማመስገንህ አስፈላጊ የሆነው ለምንድን ነው?

11 ጸሎት፣ የይሖዋን እርዳታ ለመለመን እንደሚያስችል ዝግጅት ብቻ ተደርጎ መታየት የለበትም። መጽሐፍ ቅዱስ “አመስጋኝ መሆናችሁን አሳዩ” ይላል። (ቆላ. 3:15) አንዳንድ ጊዜ፣ አእምሯችን ባጋጠሙን ችግሮች ከመወጠሩ የተነሳ ያሉንን ብዙ በረከቶች ማስተዋል ሊሳነን ይችላል። በእያንዳንዱ ቀን አመስጋኝ ለመሆን የሚያነሳሱህን ቢያንስ ሦስት ነገሮች ቆም ብለህ ለማሰብ ለምን ግብ አታወጣም? ከዚያም ለእነዚህ በረከቶች ይሖዋን አመስግነው። በ12 ዓመቷ የተጠመቀችውና አሁን 18 ዓመት የሆናት አቢጋኤል እንዲህ ብላለች፦ “በአጽናፈ ዓለም ውስጥ ከማንም በላይ ሊመሰገን የሚገባው ይሖዋ እንደሆነ ይሰማኛል። ከእሱ ላገኘናቸው ስጦታዎች አመስጋኝ ለመሆን የሚያስችለን ማንኛውም አጋጣሚ ሊያመልጠን አይገባም። በአንድ ወቅት እንዲህ የሚል ግሩም ሐሳብ ሰምቻለሁ፦ ‘ዛሬ ይሖዋን ሳናመሰግን የቀረንባቸውን ነገሮች በሙሉ፣ ነገ ጠዋት ከእንቅልፋችን ስንነቃ የምናጣቸው ቢሆን አለን የምንለው ምን ነገር ይኖረን ነበር?’” *

የይሖዋን እጅ ማየት ያለው ጥቅም

12, 13. የይሖዋን ጥሩነት በግለሰብ ደረጃ የቀመስከው እንዴት እንደሆነ ማስተዋልህ አስፈላጊ የሆነው ለምንድን ነው?

12 ይሖዋ ከበርካታ መከራዎች የታደገው ንጉሥ ዳዊት “ይሖዋ ጥሩ መሆኑን ቅመሱ፤ እዩም፤ እሱን መጠጊያ የሚያደርግ ሰው ደስተኛ ነው” በማለት ዘምሯል። (መዝ. 34:8) ይህ ጥቅስ የይሖዋን እጅ በራሳችን ሕይወት ማየት ምን ያህል ዋጋ እንዳለው ያጎላል። አምላክ ታማኝ አገልጋዮቹን እንዴት እንደረዳቸው የሚገልጹ የሚያበረታቱ ተሞክሮዎችን በመጽሐፍ ቅዱስና በጽሑፎቻችን ላይ አንብበህ እንዲሁም በክርስቲያናዊ ስብሰባዎች ላይ አዳምጠህ ሊሆን ይችላል። ይሁንና በመንፈሳዊ እድገት እያደረግህ ስትሄድ የይሖዋን እጅ በራስህ ሕይወት የተመለከትከው እንዴት እንደሆነ ማስተዋል ያስፈልግሃል። አንተ በግልህ የይሖዋን ጥሩነት ቀምሰህ ያየህባቸው አጋጣሚዎች አሉ?

13 ይሖዋ፣ ሁሉንም ክርስቲያኖች ወደ ራሱና ወደ ልጁ እንዲቀርቡ በመሳብ የእሱን ጥሩነት ልዩ በሆነ መንገድ ቀምሰው እንዲያዩ አድርጓል። ኢየሱስ “የላከኝ አብ ካልሳበው በቀር ወደ እኔ ሊመጣ የሚችል ሰው የለም” ብሏል። (ዮሐ. 6:44) ይህ ጥቅስ ከአንተ ጋር በተያያዘም እንደሚሠራ ይሰማሃል? ምናልባት አንድ ወጣት ‘ይሖዋ የሳበው ወላጆቼን ነው፤ እኔ እነሱን ተከትዬ ነው የመጣሁት’ ብሎ ያስብ ይሆናል። ይሁን እንጂ ራስህን ለይሖዋ ስትወስንና ስትጠመቅ፣ አንተ ራስህ በግለሰብ ደረጃ ከእሱ ጋር ልዩ ዝምድና እንደመሠረትክ የሚያሳይ እርምጃ ወስደሃል። አሁን በእሱ ዘንድ በሚገባ ታውቀሃል። መጽሐፍ ቅዱስ “አንድ ሰው አምላክን የሚወድ ከሆነ በእሱ ዘንድ የታወቀ ነው” የሚል ማረጋገጫ ይሰጠናል። (1 ቆሮ. 8:3) እንግዲያው ይሖዋ በድርጅቱ ውስጥ የሰጠህን ቦታ ምንጊዜም ከፍ አድርገህ ተመልከተው።

14, 15. አገልግሎት እምነትህ እንዲጠናከር የሚረዳህ እንዴት ነው?

14 የይሖዋን ጥሩነት መቅመስ የምትችልበት ሌላው መንገድ ደግሞ የምታምንባቸውን ነገሮች ለሌሎች ስትናገር ይሖዋ እንዴት እንደሚደግፍህ መመልከትህ ነው። በአገልግሎት ስትካፈል አሊያም በትምህርት ቤትህ ስትመሠክር የይሖዋን እጅ ማየት ትችላለህ። አንዳንዶች በትምህርት ቤት ለእኩዮቻቸው መስበክ ተፈታታኝ ይሆንባቸዋል። ለምን እንዲህ እንደሚሰማቸው አንተም መረዳት አይከብድህ ይሆናል። አብረውህ የሚማሩት ልጆች ምሥራቹን ስትነግራቸው ምን ዓይነት ምላሽ እንደሚሰጡህ አስቀድመህ ማወቅ አትችልም። ብዙ ተማሪዎች ሰብሰብ ባሉበት መናገር ደግሞ ለአንድ የክፍል ጓደኛህ ከመስበክ ይበልጥ ከባድ ሊሆንብህ ይችላል። ታዲያ ድፍረት ለማግኘት ምን ይረዳሃል?

15 በቅድሚያ፣ የምታምንባቸው ነገሮች ትክክል ስለመሆናቸው እርግጠኛ የሆንከው ለምን እንደሆነ ለማሰብ ሞክር። በjw.org/am ላይ የሚገኙትን የማጥኛ ጽሑፎች በሚገባ ተጠቀምባቸው። እነዚህ የማጥኛ ጽሑፎች ስለምታምንባቸው ነገሮች፣ ለምን እንዳመንክባቸው እንዲሁም እነዚህን ነገሮች ለሌሎች ማስረዳት የምትችልበትን መንገድ ቆም ብለህ እንድታስብ ለመርዳት ተብለው የተዘጋጁ ናቸው። የምታምንባቸው ነገሮች ትክክል መሆናቸውን ማረጋገጥህና ጥሩ ዝግጅት ማድረግህ ስለ ይሖዋ ስም ለመመሥከር ይገፋፋሃል።—ኤር. 20:8, 9

16. ስለምታምንባቸው ነገሮች ለመናገር ስታስብ የሚሰማህን ፍርሃት ማሸነፍ የምትችለው እንዴት ነው?

16 አስቀድመህ ጥሩ ዝግጅት ብታደርግም እንኳ ስለምታምንባቸው ነገሮች ለመናገር ፈራ ተባ ትል ይሆናል። የ13 ዓመት ልጅ እያለች የተጠመቀች አንዲት የ18 ዓመት ወጣት “በማምንበት ነገር ላይ ጥርጣሬ የለኝም፤ ያም ቢሆን ሐሳቤን አውጥቼ ለመናገር የምቸገርባቸው ጊዜያት አሉ” ብላለች። ታዲያ ይህን ሁኔታ መወጣት የቻለችው እንዴት ነው? በቀጥታ ለመስበክ ከመሞከር ይልቅ በጨዋታ መሃል ስለ መጽሐፍ ቅዱስ ታነሳለች። ይህቺ ወጣት እንዲህ ብላለች፦ “የክፍሌ ልጆች፣ ስለሚያደርጓቸው ነገሮች በነፃነት ያወራሉ። ታዲያ እኔስ ስላከናወንኳቸው ነገሮች ለማውራት ምን ያስፈራኛል? በመሆኑም በወሬ መሃል፣ አንድ ነገር ጣል ለማድረግ እሞክራለሁ፤ ለምሳሌ ‘ባለፈው መጽሐፍ ቅዱስን ሳስተምር . . .’ ብዬ እጀምርና ማስተላለፍ የፈለግኩትን መልእክት እነግራቸዋለሁ። በዚያ ወቅት እየተወራ ያለው ስለ መጽሐፍ ቅዱስ ባይሆንም እንኳ አብዛኞቹ ልጆች መጽሐፍ ቅዱስን ሳስተምር ምን እንደማደርግ ለማወቅ ይጓጓሉ። አንዳንድ ጊዜም ጥያቄ ይጠይቁኛል። ይህን ዘዴ ደጋግሜ በመጠቀሜ መስበክ ቀላል እየሆነልኝ ሄዷል። እንዲህ ያለ ድፍረት ባሳየሁ ቁጥር ሁልጊዜ ታላቅ ደስታ ይሰማኛል!”

17. ስለምታምንባቸው ነገሮች ያለህ አመለካከት ለሌሎች ለመስበክ የሚረዳህ እንዴት ነው?

17 ለሰዎች አክብሮትና አሳቢነት የምታሳይ ከሆነ እነሱም እንደዚያው ማድረጋቸው አይቀርም። በልጅነቷ የተጠመቀችውና አሁን 17 ዓመት የሆናት ኦሊቪያ “ስለ ሌላ ነገር እየተወራ እያለ እኔ ስለ መጽሐፍ ቅዱስ የምናገር ከሆነ ሰዎች አክራሪ እንደሆንኩ አድርገው ይመለከቱኛል ብዬ ሁልጊዜ እፈራ ነበር” ብላለች። ውሎ አድሮ ግን ነገሩን በሌላ አቅጣጫ ለማየት ሞከረች። ኦሊቪያ እንድትፈራ ባደረጓት ነገሮች ላይ ከማተኮር ይልቅ እንደሚከተለው ብላ ማሰብ ጀመረች፦ “ብዙ ወጣቶች ስለ ይሖዋ ምሥክሮች ምንም የሚያውቁት ነገር የለም። የሚያውቋቸው የይሖዋ ምሥክሮች እኛ ብቻ ነን። በመሆኑም የእኛ ሁኔታ በአመለካከታቸው ላይ ለውጥ ያመጣል። ስለ እምነታችን መናገር የሚያስፈራን አሊያም የሚያሸማቅቀን ቢሆን ምን ይሰማቸዋል? የይሖዋ ምሥክር በመሆናችን እንደምናፍር ሊያስቡ ይችላሉ። እንዲያውም በራስ የመተማመን መንፈስ እንደሌለን ሲመለከቱ ደግነት በጎደለው መንገድ ይይዙን ይሆናል። ይሁንና ስለምናምንባቸው ነገሮች በእርግጠኝነትና በተረጋጋ ሁኔታ የምንነግራቸው ከሆነ አክብሮት ማሳየታቸው አይቀርም።”

የራስህን መዳን ከፍጻሜ ለማድረስ ተግተህ ሥራ

18. የራስን መዳን ከፍጻሜ ለማድረስ ተግቶ መሥራት ምን ነገሮችን ይጨምራል?

18 ቀደም ሲል እንደተመለከትነው የራስን መዳን ከፍጻሜ ለማድረስ ተግቶ መሥራት በቁም ነገር ሊታይ የሚገባው ኃላፊነት ነው። እዚህ ግብ ላይ ለመድረስ ከሚረዱህ ነገሮች መካከል የአምላክን ቃል ማንበብና ባነበብከው ላይ ማሰላሰል፣ ወደ ይሖዋ መጸለይ እንዲሁም በግለሰብ ደረጃ የይሖዋን እጅ ያየህባቸውን መንገዶች ቆም ብለህ ማሰብ ይገኙበታል። እነዚህን ነገሮች ማድረግህ ይሖዋ ወዳጅህ መሆኑን እንድትተማመን ይረዳሃል። ይህ ደግሞ ስለምታምንባቸው ነገሮች በድፍረት ለመናገር ያነሳሳሃል።—መዝሙር 73:28ን አንብብ።

19. መዳን ለማግኘት የምታደርገው ጥረት የማያስቆጭ የሆነው ለምንድን ነው?

19 ኢየሱስ እንዲህ ብሏል፦ “ሊከተለኝ የሚፈልግ ማንም ቢኖር ራሱን ይካድ፤ የራሱን የመከራ እንጨት ይሸከም፤ ያለማቋረጥም ይከተለኝ።” (ማቴ. 16:24) በእርግጥም የክርስቶስ ተከታይ መሆን የሚፈልግ ሁሉ ራሱን ለይሖዋ መወሰን እና መጠመቅ ይጠበቅበታል። ይህን ማድረጉ በአሁኑ ጊዜ የተትረፈረፈ በረከት፣ በአምላክ አዲስ ዓለም ውስጥ ደግሞ የዘላለም ሕይወት ያስገኝለታል። በእርግጥም የራስህን መዳን ከፍጻሜ ለማድረስ ተግተህ እንድትሠራ የሚያነሳሳ በቂ ምክንያት አለህ!

^ አን.11 ተጨማሪ ሐሳቦች ለማግኘት jw.org/am ላይ የወጣውን “የወጣቶች ጥያቄ—መጸለይ ጥቅም አለው?” የሚለውን ርዕስ እና በዚህ ርዕስ ሥር የሚገኘውን የመልመጃ ሣጥን ተመልከት።