የጥናት ርዕስ 13
መዝሙር 127 ምን ዓይነት ሰው መሆን አለብኝ?
ይሖዋ እንደሚደሰትባችሁ በማወቅ ተጽናኑ
“በአንተ ደስ ይለኛል።”—ሉቃስ 3:22
ዓላማ
ይሖዋ በግለሰብ ደረጃ እንደሚደሰትብን ለራሳችን ማረጋገጥ የምንችልበት መንገድ።
1. አንዳንድ ታማኝ የይሖዋ አገልጋዮች ከየትኛው ስሜት ጋር ይታገላሉ?
መጽሐፍ ቅዱስ “ይሖዋ በሕዝቡ ደስ ይሰኛል” ይላል። (መዝ. 149:4) በእርግጥም ይሖዋ በቡድን ደረጃ በሕዝቡ እንደሚደሰት ማወቅ በጣም የሚያጽናና ነው! ይሁንና አንዳንዶች ተስፋ ሲቆርጡ ‘ይሖዋ በግለሰብ ደረጃ በእኔ ይደሰት ይሆን?’ የሚል ጥርጣሬ ይፈጠርባቸዋል። በጥንት ዘመን የኖሩ የይሖዋ ታማኝ አገልጋዮች ከእንዲህ ዓይነት ስሜት ጋር የታገሉበት ወቅት ነበር።—1 ሳሙ. 1:6-10፤ ኢዮብ 29:2, 4፤ መዝ. 51:11
2. ይሖዋ የሚደሰተው በእነማን ነው?
2 መጽሐፍ ቅዱስ በግልጽ እንደሚያሳየው ፍጹማን ያልሆኑ ሰዎች የይሖዋን ሞገስ ማግኘት ይችላሉ። ታዲያ በእሱ ዘንድ ተቀባይነት ማግኘት የምንችለው እንዴት ነው? በኢየሱስ ክርስቶስ ማመን እንዲሁም መጠመቅ ይኖርብናል። (ዮሐ. 3:16) ይህን ስናደርግ ከኃጢአታችን ንስሐ እንደገባንና የአምላክን ፈቃድ ለማድረግ ለእሱ ቃል እንደገባን በሕዝብ ፊት እናሳያለን። (ሥራ 2:38፤ 3:19) ይሖዋ የእሱ ወዳጆች ለመሆን ስንል እነዚህን እርምጃዎች መውሰዳችን ያስደስተዋል። ራሳችንን ስንወስን ከገባነው ቃል ጋር ተስማምተን ለመኖር የምንችለውን ሁሉ እስካደረግን ድረስ ይሖዋ ይደሰትብናል፤ እንደ ቅርብ ወዳጆቹ አድርጎም ይመለከተናል።—መዝ. 25:14
3. በዚህ ርዕስ ላይ ምን እንመለከታለን?
3 ይሁንና አንዳንዶች አምላክ እንደማይደሰትባቸው አልፎ አልፎ የሚሰማቸው ለምንድን ነው? ይሖዋ እንደሚደሰትብን የሚያሳየን እንዴት ነው? እንዲሁም ይሖዋ በግለሰብ ደረጃ እንደሚደሰትብን ይበልጥ እርግጠኞች እንድንሆን የሚያደርጉ ምን ተጨማሪ ምክንያቶች አሉ?
አንዳንዶች ይሖዋ እንደማይደሰትባቸው የሚሰማቸው ለምንድን ነው?
4-5. የዋጋ ቢስነት ስሜት ቢሰማንም ስለ ምን ነገር እርግጠኞች መሆን እንችላለን?
4 አንዳንዶቻችን ከልጅነታችን ጀምሮ የዋጋ ቢስነት ስሜት ያታግለናል። (መዝ. 88:15) አድሪያን የተባለ ወንድም እንዲህ ብሏል፦ “ከልጅነቴ ጀምሮ ዋጋ ቢስ እንደሆንኩ ይሰማኝ ነበር። ትዝ ይለኛል ልጅ ሳለሁ፣ ቤተሰቤ ገነት እንዲገባ እጸልይ ነበር፤ እኔ ግን እዚያ ለመግባት ብቁ እንዳልሆንኩ እርግጠኛ ነበርኩ።” ቶኒ የተባለው ክርስቲያን ያደገው በእውነት ቤት ውስጥ አይደለም። ስለ አስተዳደጉ ሲናገር እንዲህ ብሏል፦ “ወላጆቼ እንደሚወዱኝም ሆነ እንደሚኮሩብኝ ፈጽሞ ነግረውኝ አያውቁም። ሁሌም የሚቀረኝ ነገር እንዳለ እንዲሰማኝ አድርገው ነው ያሳደጉኝ።”
5 እኛም አልፎ አልፎ ከዋጋ ቢስነት ስሜት ጋር የምንታገል ከሆነ አንድ እውነታ እናስታውስ፤ ይሖዋን እያገለገልን ያለነው እሱ ራሱ ስለሳበን ነው። (ዮሐ. 6:44) እኛ እንኳ እንዳለን የማናውቀውን መልካም ነገር በውስጣችን አይቷል፤ ልባችንንም ያውቃል። (1 ሳሙ. 16:7፤ 2 ዜና 6:30) ስለዚህ በፊቱ ውድ እንደሆንን ሲነግረን ልናምነው ይገባል።—1 ዮሐ. 3:19, 20
6. ሐዋርያው ጳውሎስ ቀደም ሲል ስለፈጸማቸው ኃጢአቶች ምን ተሰምቶታል?
6 አንዳንዶቻችን እውነትን ከመስማታችን በፊት ባደረግናቸው ነገሮች የተነሳ አሁንም የበደለኝነት ስሜት ይደቁሰን ይሆናል። (1 ጴጥ. 4:3) ታማኝ ክርስቲያኖችም እንኳ ከኃጢአት ዝንባሌዎች ጋር መታገል ያስፈልጋቸዋል። አንተስ ልብህ እየኮነነህ ይሆን? ከሆነ አይዞህ፤ ታማኝ የይሖዋ አገልጋዮችም እንኳ ከእንዲህ ዓይነት ስሜት ጋር ታግለዋል። ለምሳሌ ያህል፣ ሐዋርያው ጳውሎስ ስላሉበት ድክመቶች ሲያስብ ስሜቱ ተደቁሶ ነበር። (ሮም 7:24) እርግጥ ነው፣ ጳውሎስ ከኃጢአቱ ንስሐ ገብቶ ተጠምቋል። ያም ቢሆን ስለ ራሱ ሲናገር “ከሐዋርያት ሁሉ የማንስ” እንዲሁም “ከኃጢአተኞች . . . ዋነኛ ነኝ” ብሏል።—1 ቆሮ. 15:9፤ 1 ጢሞ. 1:15
7. ከዚህ ቀደም የፈጸምናቸውን ኃጢአቶች በተመለከተ ልናስታውሰው የሚገባው ነገር ምንድን ነው?
7 ሰማያዊው አባታችን ንስሐ ከገባን ይቅር እንደሚለን ቃል ገብቶልናል። (መዝ. 86:5) ስለዚህ ከልባችን ንስሐ ከገባን ይሖዋ ቃል በገባው መሠረት ይቅር እንዳለን እርግጠኞች መሆን እንችላለን።—ቆላ. 2:13
8-9. የምናደርገው ነገር ይሖዋን ለማስደሰት በቂ ሊሆን እንደማይችል ሲሰማን ምን ይረዳናል?
8 ሁላችንም በይሖዋ አገልግሎት አቅማችን የፈቀደውን ሁሉ ማድረግ እንፈልጋለን። ይሁንና አንዳንዶች ይሖዋን ለማስደሰት ምንም ያህል ቢጥሩ የሚያደርጉት ነገር በቂ እንዳልሆነ ይሰማቸው ይሆናል። አማንዳ የተባለች እህት እንዲህ ብላለች፦ “ለይሖዋ ምርጤን ለመስጠት ሁሌም ተጨማሪ ነገር ማድረግ እንዳለብኝ የሚሰማኝ ጊዜ አለ። ብዙውን ጊዜ፣ ማድረግ ከምችለው በላይ ከራሴ እጠብቃለሁ። ያሰብኩትን ማድረግ ሲያቅተኝ በራሴ በጣም አዝናለሁ፤ እኔ እንዲህ ከተሰማኝ ይሖዋም እንደዚያ እንደሚሰማው አስባለሁ።”
9 የምናደርገው ነገር መቼም ቢሆን ይሖዋን ለማስደሰት በቂ እንዳልሆነ የሚፈጠርብንን ስሜት ማሸነፍ የምንችለው እንዴት ነው? ይሖዋ ከእኛ በሚጠብቀው ነገር ድርቅ ያለ እንዳልሆነ አስታውስ። ማድረግ ከምንችለው በላይ አይጠብቅብንም። ምርጣችንን እስከሰጠነው ድረስ በምናደርገው ነገር ይደሰታል። ይሖዋን በሙሉ ነፍሳቸው ባገለገሉ የመጽሐፍ ቅዱስ ምሳሌዎች ላይ ማሰላሰላችንም ጠቃሚ ነው። ጳውሎስን እንደ ምሳሌ እንውሰድ። በሺዎች የሚቆጠሩ ኪሎ ሜትሮችን በመጓዝ ለዓመታት በትጋት ሠርቷል፤ በርካታ ጉባኤዎችንም አቋቁሟል። በኋላ ላይ ግን በስብከቱ ሥራ የሚያደርገውን ተሳትፎ የሚገድብ ነገር አጋጠመው። ታዲያ በዚህ ጊዜ የአምላክን ሞገስ አጣ? በፍጹም። አቅሙ የፈቀደውን ሁሉ ማድረጉን ቀጥሏል፤ ይሖዋም ባርኮታል። (ሥራ 28:30, 31) እኛም ለይሖዋ መስጠት የምንችለው ነገር እንደ ሁኔታው ሊለያይ ይችላል። እሱ ትልቅ ቦታ የሚሰጠው ግን ለመስጠት የተነሳሳንበትን ምክንያት ነው። እስቲ አሁን ደግሞ ይሖዋ እንደሚደሰትብን የሚያሳይባቸውን አንዳንድ መንገዶች እንመልከት።
ይሖዋ እንደሚደሰትብን የሚገልጽባቸው መንገዶች
10. ይሖዋ እንደሚወደን ሲናገር መስማት የምንችለው እንዴት ነው? (ዮሐንስ 16:27)
10 መጽሐፍ ቅዱስ። ይሖዋ አገልጋዮቹን እንደሚወዳቸውና እንደሚደሰትባቸው መግለጽ ያስደስተዋል። ለምሳሌ ይሖዋ፣ ኢየሱስን የሚወደውና የሚደሰትበት ልጁ እንደሆነ የገለጸባቸው ሁለት አጋጣሚዎች በቅዱሳን መጻሕፍት ላይ ተዘግበዋል። (ማቴ. 3:17፤ 17:5) አንተስ ይሖዋ እንደሚደሰትብህ ሲነግርህ መስማት ትፈልጋለህ? ይሖዋ ከሰማይ ሆኖ አያናግረንም። በቃሉ አማካኝነት ግን ያናግረናል። ኢየሱስ በወንጌል ዘገባዎች ላይ የተናገረውን ስናነብ ይሖዋ እንደሚደሰትብን ሲናገር የምንሰማ ያህል ነው። (ዮሐንስ 16:27ን አንብብ።) ኢየሱስ የአባቱን ባሕርያት ፍጹም በሆነ መንገድ አንጸባርቋል። በመሆኑም ኢየሱስ ፍጹማን ባይሆኑም ታማኝ የሆኑ ተከታዮቹን እንደሚወዳቸው የተናገረባቸውን ዘገባዎች ስናነብ ይሖዋ ለእኛ እነዚህን ቃላት እንደተናገረ አድርገን ማሰብ እንችላለን።—ዮሐ. 15:9, 15
11. መከራ ደረሰብን ማለት የአምላክን ሞገስ አጥተናል ማለት ያልሆነው ለምንድን ነው? (ያዕቆብ 1:12)
11 የሚያደርግልን ነገር። ይሖዋ እኛን መርዳት ያስደስተዋል፤ ለምሳሌ በቁሳዊ የሚያስፈልገንን ነገር ይሰጠናል። አንዳንድ ጊዜ እንደ ጻድቁ ኢዮብ ሁሉ መከራ እንዲደርስብን ሊፈቅድ ይችላል። (ኢዮብ 1:8-11) መከራ ደረሰብን ማለት የአምላክን ሞገስ አጥተናል ማለት አይደለም። እንዲያውም መከራዎች ይሖዋን ምን ያህል እንደምንወደውና እንደምንተማመንበት ለማሳየት አጋጣሚ ይሰጡናል። (ያዕቆብ 1:12ን አንብብ።) መከራ ሲደርስብን የይሖዋን ፍቅራዊ እንክብካቤና ድጋፍ ለመቅመስም አጋጣሚ እናገኛለን።
12. ዲሚትሪ ካጋጠመው ነገር ምን እንማራለን?
12 በእስያ የሚኖር ዲሚትሪ የተባለ ወንድም ያጋጠመውን እንመልከት። ሥራውን አጣ፤ ከዚያ በኋላ ባሉት በርካታ ወራትም ሌላ ሥራ ማግኘት አልቻለም። በመሆኑም በይሖዋ በመታመን በአገልግሎት የሚያደርገውን ተሳትፎ ለመጨመር ወሰነ። በዚህ ሁኔታ ወራት አለፉ፤ ሥራ ማግኘት ግን አልቻለም። ከዚያም የጤና እክል አጋጠመውና የአልጋ ቁራኛ ሆነ። እንደ ባልና እንደ አባት የሚጠበቅበትን ነገር ማድረግ እንደተሳነው ተሰማው፤ ‘የይሖዋን ሞገስ አጥቼ ይሆን?’ ብሎ ማሰብም ጀመረ። አንድ ምሽት ላይ ልጁ “ሳትረበሹ፣ ተማምናችሁ በመኖር ብርቱ መሆናችሁን ታሳያላችሁ” የሚለውን የኢሳይያስ 30:15 ጥቅስ በወረቀት ላይ አትማ አመጣችለት። ከዚያም “አባዬ፣ ስታዝን ይህን ጥቅስ አስታውስ” በማለት አልጋው አጠገብ አስቀመጠችለት። ዲሚትሪ ሁኔታውን ሲያስብ በይሖዋ እርዳታ ቤተሰቡ አሁንም ምግብ፣ ልብስና መጠለያ እንዳላጣ አስተዋለ። “ከእኔ የሚጠበቀው ሳልረበሽ በአምላኬ ተማምኜ መኖር ነው” ብሏል። አንተም እንዲህ ያለ ሁኔታ አጋጥሞህ ከሆነ ይሖዋ እንደሚያስብልህ እርግጠኛ ሁን፤ መጽናት እንድትችልም ይረዳሃል።
13. ይሖዋ እንደሚደሰትብን ለመግለጽ በእነማን ሊጠቀም ይችላል? እንዴትስ?
13 የእምነት ባልንጀሮቻችን። ይሖዋ እንደሚደሰትብን ለመግለጽ ወንድሞቻችንን እና እህቶቻችንን ይጠቀማል። ለምሳሌ፣ ልክ በሚያስፈልገን ጊዜ የሚያጽናናን ነገር እንዲናገሩን ሊያነሳሳቸው ይችላል። በእስያ የምትኖር አንዲት እህት በጣም በተጨነቀችበት ወቅት ይህን ተመልክታለች። ሥራዋን ማጣቷ ሳያንስ በጠና ታመመች። ከዚያ ደግሞ ባለቤቷ ከባድ ኃጢአት ስለሠራ ከሽምግልና ወረደ። እንዲህ ብላለች፦ “‘ይህ ሁሉ ነገር እኔ ላይ የደረሰው ለምንድን ነው?’ ብዬ ማሰብ ጀመርኩ። ‘የይሖዋን ሞገስ የሚያሳጣ መጥፎ ነገር ሠርቼ ይሆን?’ ብዬም አሰብኩ።” እህታችን እንደሚወዳት እንዲያረጋግጥላት ይሖዋን ለመነችው። ታዲያ ይህን ያደረገው እንዴት ነው? እንዲህ ብላለች፦ “የጉባኤዬ ሽማግሌዎች አነጋገሩኝ፤ ይሖዋ እንደሚወደኝም አረጋገጡልኝ።” ከተወሰነ ጊዜ በኋላም እህታችን ይሖዋ እንዲረዳት እንደገና ጠየቀችው። ይሖዋ እንዴት መልስ እንደሰጣት ስትገልጽ እንዲህ ብላለች፦ “በዚያኑ ዕለት፣ በጉባኤዬ ያሉ ወንድሞችና እህቶች የጻፉት ደብዳቤ ደረሰኝ። የጻፉልኝን የሚያጽናና ሐሳብ ሳነብ፣ ይሖዋ ጸሎቴን እንደሰማኝ ገባኝ።” በእርግጥም ይሖዋ በሌሎች ማበረታቻ አማካኝነት እንደሚደሰትብን ይገልጽልናል።—መዝ. 10:17
14. ይሖዋ ሞገሱን ለእኛ የሚያሳይበት ሌላው መንገድ ምንድን ነው?
14 ይሖዋ በእምነት አጋሮቻችን ተጠቅሞ እንደሚደሰትብን የሚገልጽበት ሌላው መንገድ የሚያስፈልገንን ምክር መስጠት ነው። ለምሳሌ በመጀመሪያው መቶ ዘመን ይሖዋ በሐዋርያው ጳውሎስ ተጠቅሟል፤ በመንፈስ መሪነት ለእምነት ባልንጀሮቹ 14 ደብዳቤዎችን እንዲጽፍ አነሳስቶታል። በእነዚህ ደብዳቤዎች ላይ ጳውሎስ ጠንከር ያለ ሆኖም ፍቅር የሚንጸባረቅበት ምክር ሰጥቷል። ጳውሎስ እንዲህ ያለውን ምክር በደብዳቤው ላይ እንዲያካትት ይሖዋ በመንፈሱ የመራው ለምንድን ነው? ጥሩ አባት ስለሆነ ነው፤ “የሚወዳቸውን” ልጆቹን ይገሥጻቸዋል። (ምሳሌ 3:11, 12) እንግዲያው በመጽሐፍ ቅዱስ ላይ የተመሠረተ ምክር ከተሰጠን ይህ ይሖዋ እንዳዘነብን ሳይሆን እንደሚደሰትብን የሚያሳይ ማስረጃ እንደሆነ አድርገን እንመልከተው። (ዕብ. 12:6) የይሖዋን ሞገስ እንዳገኘን የሚያሳዩ ሌሎች ማስረጃዎችስ የትኞቹ ናቸው?
ይሖዋ እንደሚደሰትብን የሚያሳዩ ሌሎች ማስረጃዎች
15. ይሖዋ ቅዱስ መንፈሱን የሚሰጠው ለእነማን ነው? ይህስ የእርግጠኝነት ስሜታችንን የሚጨምረው ለምንድን ነው?
15 ይሖዋ ለሚደሰትባቸው ሰዎች ቅዱስ መንፈሱን ይሰጣል። (ማቴ. 12:18) እስቲ የሚከተለውን ጥያቄ አስብበት፦ ‘የአምላክ መንፈስ ፍሬ ገጽታ የሆኑ ባሕርያትን በሕይወቴ ውስጥ በተወሰነ መጠንም ቢሆን ማፍራት ችያለሁ?’ ለምሳሌ እውነትን ከማወቅህ በፊት ከነበርከው ይበልጥ ታጋሽ እንደሆንክ ታስተውል ይሆናል። አዎ፣ የአምላክ መንፈስ ፍሬ ገጽታ የሆኑ ባሕርያትን ይበልጥ ባዳበርክ መጠን ይሖዋ እንደሚደሰትብህ ያለህ እርግጠኝነትም እየጨመረ ይሄዳል።—“ የመንፈስ ፍሬ . . .” የሚለውን ሣጥን ተመልከት።
16. ይሖዋ ምሥራቹን በአደራ የሰጠው ለእነማን ነው? ይህን ማወቅህ ምን ስሜት ይፈጥርብሃል? (1 ተሰሎንቄ 2:4)
16 ይሖዋ ለሚደሰትባቸው ሰዎች ምሥራቹን በአደራ ሰጥቷቸዋል። (1 ተሰሎንቄ 2:4ን አንብብ።) ጆስሊን የተባለች እህት ምሥራቹን ለሌሎች መናገሯ እንዴት እንደጠቀማት እስቲ እንመልከት። አንድ ቀን ከእንቅልፏ ስትነሳ መጥፎ ስሜት ተጫጭኗት ነበር። ጆስሊን እንዲህ ብላለች፦ “ምንም እንደማልጠቅም ተሰምቶኝ ነበር። ሆኖም አቅኚ ነበርኩ፤ ያ ቀን ደግሞ የአገልግሎት ቀኔ ነው። ስለዚህ ወደ ይሖዋ ጸለይኩና አገልግሎት ወጣሁ።” የዚያን ዕለት ጆስሊን፣ ሜሪ የተባለች ሴት አነጋገረች፤ እሷም መጽሐፍ ቅዱስን ለማጥናት ተስማማች። ከተወሰኑ ወራት በኋላ ሜሪ፣ ጆስሊን ወደ ቤቷ በመጣችበት ቀን አምላክ እንዲረዳት እየጸለየች እንደነበር ነገረቻት። ጆስሊን በወቅቱ የተሰማትን ስትገልጽ “ይሖዋ ‘በአንቺ ተደስቻለሁ’ እንዳለኝ ተሰማኝ” ብላለች። እርግጥ ነው፣ ምሥራቹን የሚቀበለን ሁሉም ሰው አይደለም። ሆኖም ምሥራቹን ለመስበክ አቅማችን የፈቀደውን ሁሉ ስናደርግ ይሖዋ እንደሚደሰትብን እርግጠኞች መሆን እንችላለን።
17. ቪኪ ስለ ቤዛው ከተናገረችው ነገር ምን ትምህርት አግኝተሃል? (መዝሙር 5:12)
17 ይሖዋ፣ የሚደሰትባቸው ሰዎች ከቤዛው ጥቅም እንዲያገኙ ያደርጋል። (1 ጢሞ. 2:5, 6) አንዳንድ ጊዜ ግን በቤዛው አምነን ተጠምቀንም እንኳ ልባችን፣ ይሖዋ እንደሚደሰትብን መቀበል ሊከብደው ይችላል። አንተም እንዲህ የሚሰማህ ከሆነ ይህን አስታውስ፦ የእኛ ስሜት አይታመንም፤ ይሖዋን ግን ሁሌም ልንተማመንበት እንችላለን። በቤዛው ላይ እምነት ያላቸው ሰዎች በእሱ ዓይን ጻድቅ ተደርገው ይቆጠራሉ፤ እንደሚባርካቸውም ቃል ገብቷል። (መዝሙር 5:12ን አንብብ፤ ሮም 3:26) ቪኪ በቤዛው ላይ ማሰላሰሏ ረድቷታል። አንድ ቀን በቤዛው ላይ በጥልቀት ካሰላሰለች በኋላ አንድ መደምደሚያ ላይ ደረሰች። እንዲህ ብላለች፦ “ይሖዋ ለረጅም ጊዜ እንደታገሠኝ . . . ተገነዘብኩ። ለካስ እኔ ይሖዋን ‘ፍቅርህ ምንም ያህል ታላቅ ቢሆን እኔን ልትወደኝ አትችልም። የልጅህ መሥዋዕትም ቢሆን የእኔን ኃጢአት ለመሸፈን በቂ አይደለም’ እያልኩት ያለሁ ያህል ነበር።” ቪኪ በቤዛው ስጦታ ላይ ማሰላሰሏ ይሖዋ እንደሚወዳት እንዲሰማት አድርጓታል። እኛም በቤዛው ላይ ስናሰላስል የይሖዋን ሞገስ እንዳገኘንና እንደሚወደን ይሰማናል።
18. ይሖዋን እስከወደድነው ድረስ ስለ ምን ነገር እርግጠኞች መሆን እንችላለን?
18 እርግጥ ነው፣ ከላይ ያሉትን ሐሳቦች በተግባር ለማዋል የምንችለውን ሁሉ አድርገንም እንኳ ተስፋ የምንቆርጥበትና የይሖዋ ሞገስ እንዳለን የምንጠራጠርበት ጊዜ ይኖራል። እንዲህ ዓይነት ሁኔታ ካጋጠመህ ይሖዋ ‘እሱን በሚወዱት’ እንደሚደሰት አስታውስ። (ያዕ. 1:12) ስለዚህ ከይሖዋ ጋር ያለህን ወዳጅነት ማጠናከርህን ቀጥል። የእሱን ሞገስ እንዳገኘህ የሚያሳዩ ማስረጃዎችን ለማስተዋል ጥረት አድርግ። ይሖዋ “ከእያንዳንዳችን የራቀ [እንዳልሆነ]” ፈጽሞ አትርሳ።—ሥራ 17:27
ምን ብለህ ትመልሳለህ?
-
አንዳንዶች ይሖዋ እንደማይደሰትባቸው የሚሰማቸው ለምን ሊሆን ይችላል?
-
ይሖዋ እንደሚደሰትብን የሚገልጽባቸው አንዳንድ መንገዶች የትኞቹ ናቸው?
-
ይሖዋ እንደሚደሰትብን እርግጠኞች መሆን የምንችለው ለምንድን ነው?
መዝሙር 88 መንገድህን አሳውቀኝ