ይህን ያውቁ ኖሯል?
እስራኤላውያን በግብፅ ባሪያ እንደነበሩ የሚያሳይ ማስረጃ ከመጽሐፍ ቅዱስ ውጭ ይገኛል?
ምድያማውያን ዮሴፍን ወደ ግብፅ ከወሰዱት በኋላ ያዕቆብና ቤተሰቡ ከከነዓን ተነስተው በግብፅ መኖር እንደጀመሩ መጽሐፍ ቅዱስ ይናገራል። ያዕቆብና ቤተሰቡ ግብፅ ውስጥ በናይል ሰርጥ (ዴልታ) በሚገኘው ጎሸን የተባለ አካባቢ ሰፈሩ። (ዘፍ. 47:1, 6) እስራኤላውያን “[ቁጥራቸው] በከፍተኛ ፍጥነት እየጨመረና ኃያል እየሆኑ ሄዱ።” በዚህም የተነሳ ግብፃውያን እስራኤላውያንን ስለፈሯቸው በባርነት ይገዟቸው ጀመር።—ዘፀ. 1:7-14
በዘመናችን ያሉ አንዳንድ ምሁራን ይህ የመጽሐፍ ቅዱስ ዘገባ አፈ ታሪክ እንደሆነ በመግለጽ ተችተውታል። ይሁንና ሴማውያን * በጥንቷ ግብፅ ውስጥ ባሪያዎች ሆነው እንደኖሩ የሚያሳይ ማስረጃ አለ።
ለምሳሌ ያህል፣ የአርኪኦሎጂ ባለሙያዎች በሰሜናዊ ግብፅ አንዳንድ ጥንታዊ መኖሪያዎችን በቁፋሮ አግኝተዋል። ዶክተር ጆን ቢምሰን እንደገለጹት በዚያ አካባቢ 20 ወይም ከዚያ የሚበልጡ የሴማውያን መኖሪያ ሰፈሮች እንደነበሩ የሚያሳይ ማስረጃ አለ። በተጨማሪም ስለ ጥንቷ ግብፅ የሚያጠኑት ጄምስ ሆፍማየር የተባሉት ምሁር “ከ1800 እስከ 1540 ዓ.ዓ. ገደማ ባለው ጊዜ ውስጥ፣ [የያዕቆብ ቤተሰቦች መኖሪያ በሆነው] በምዕራብ እስያ ይኖሩ የነበሩ ሴማዊ ቋንቋ ተናጋሪ የሆኑ ሕዝቦች ወደ ግብፅ ሄደው ለመኖር ይጓጉ ነበር” ብለዋል። አክለውም “በተለምዶ ‘የእስራኤላውያን አባቶች ዘመን’ ተብሎ የሚጠራው ወቅትም ይኸው ነበር፤ እንዲሁም ይህ ታሪክ በዘፍጥረት ዘገባ ውስጥ ከተገለጸው ጊዜና ሁኔታ ጋር ይስማማል” በማለት ተናግረዋል።
ከደቡባዊ ግብፅ የተገኘ ተጨማሪ ማስረጃም አለ። በደቡባዊ ግብፅ ውስጥ በሚገኝ አንድ ቤት ውስጥ ይሠሩ የነበሩ ባሪያዎችን ስም የያዘ ከ2000 ዓ.ዓ. ገደማ እስከ 1600 ዓ.ዓ. ገደማ ባለው ጊዜ ውስጥ እንደተዘጋጀ የሚገመት አንድ ፓፒረስ ተገኝቷል። ከእነዚህ ስሞች መካከል ከ40 በላይ የሚሆኑት ሴማዊ ናቸው። እነዚህ ባሪያዎች ምግብ አብሳይ፣ ሸማኔ እና የጉልበት ሠራተኛ ሆነው ይሠሩ ነበር። ጄምስ ሆፍማየር እንዲህ ብለዋል፦ “በቲቤይድ [ደቡባዊ ግብፅ] በሚገኘው በዚህ አንድ ቤት ውስጥ ከ40 የሚበልጡ ሴማውያን ይሠሩ ከነበረ፣ በመላዋ ግብፅ በተለይም በናይል ሰርጥ ውስጥ የነበሩት ሴማውያን ቁጥር ከፍተኛ መሆን አለበት።”
የአርኪኦሎጂ ባለሙያ የሆኑት ዴቪድ ሮል እንደጻፉት ከባሪያዎቹ ስሞች መካከል አንዳንዶቹ “በመጽሐፍ ቅዱስ ውስጥ ከሚገኙት ስሞች ጋር በጣም ይመሳሰላሉ።” ለምሳሌ ይሳኮር፣ አሴርና ሺፍራ ከሚሉት ስሞች ጋር የሚመሳሰሉ ስሞች ተገኝተዋል። (ዘፀ. 1:3, 4, 15) ዴቪድ ሮል “ይህ እስራኤላውያን በግብፅ ባሪያዎች እንደነበሩ የሚያሳይ ትክክለኛ ማስረጃ ነው” በማለት ደምድመዋል።
ዶክተር ቢምሰን “እስራኤላውያን በግብፅ ግዞተኞች እንደነበሩና በኋላም ነፃ እንደወጡ የሚገልጸው የመጽሐፍ ቅዱስ ዘገባ ጠንካራ ታሪካዊ መሠረት አለው” ብለዋል።
^ አን.4 ሴማውያን የሚባሉት ከኖኅ ሦስት ልጆች አንዱ የሆነው የሴም ዘሮች ናቸው። ከሴም ዘሮች መካከል ኤላማውያን፣ አሦራውያን፣ የጥንቶቹ ከለዳውያን፣ ዕብራውያን፣ ሶርያውያንና የተለያዩ የአረብ ጎሳዎች ሳይገኙበት አይቀሩም።