“ከይሖዋ ጎን የሚቆም ማን ነው?”
“አምላክህን ይሖዋን ፍራ፤ አገልግለው፤ ከእሱም ጋር ተጣበቅ።”—ዘዳ. 10:20
1, 2. (ሀ) ከይሖዋ ጎን መቆም የጥበብ አካሄድ የሆነው ለምንድን ነው? (ለ) በዚህ ርዕስ ውስጥ ምን እንመለከታለን?
ከይሖዋ ጋር መጣበቅ ተገቢ ነው። እንደ አምላካችን ያለ ኃያል፣ ጥበበኛና አፍቃሪ አካል የለም! ከመካከላችን ከእሱ ጎን መቆም የማይፈልግ ማን አለ? (መዝ. 96:4-6) ያም ሆኖ ከአምላክ አገልጋዮች መካከል አንዳንዶቹ ከይሖዋ ጎን መቆም የሚጠይቅ ሁኔታ ባጋጠማቸው ጊዜ እንዲህ ሳያደርጉ ቀርተዋል።
2 በዚህ ርዕስ ውስጥ፣ ከይሖዋ ጎን እንደቆሙ እየተናገሩ በሌላ በኩል ግን እሱን የሚያሳዝን አካሄድ ይከተሉ የነበሩ ሰዎችን ምሳሌ እንመለከታለን። እነዚህ ዘገባዎች ለይሖዋ ሙሉ በሙሉ ታማኝ ሆነን እንድንቀጥል የሚረዱ ጠቃሚ ትምህርቶችን ይዘዋል።
ይሖዋ ልብን ይመረምራል
3. ይሖዋ ቃየንን ያስጠነቀቀው ለምን ነበር? ምን በማለትስ አስጠነቀቀው?
3 የቃየንን ሁኔታ እንደ ምሳሌ እንውሰድ። ቃየን የሚያመልከው የሐሰት አማልክትን ሳይሆን ይሖዋን ነበር። ሆኖም አምልኮው በአምላክ ዘንድ ተቀባይነት አላገኘም። ምክንያቱም በልቡ ውስጥ የክፋት ሐሳብ እያቆጠቆጠ ነበር። (1 ዮሐ. 3:12) ይሖዋ ቃየንን ሊረዳው ስላሰበ እንዲህ የሚል ማስጠንቀቂያ ሰጠው፦ “መልካም ወደ ማድረግ ብታዘነብል ኖሮ ሞገስ አታገኝም ነበር? መልካም ወደ ማድረግ ካላዘነበልክ ግን ኃጢአት በደጅህ እያደባ ነው፤ ሊቆጣጠርህም ይፈልጋል፤ ታዲያ አንተ ትቆጣጠረው ይሆን?” (ዘፍ. 4:6, 7) በሌላ አነጋገር ይሖዋ “ንስሐ ከገባህና ከጎኔ ጸንተህ ከቆምክ እኔም ከጎንህ እሆናለሁ” እያለው ነበር።
4. ቃየን ከይሖዋ ጎን እንደሚቆም ማሳየት የሚችልበት አጋጣሚ ቢሰጠውም ምን አደረገ?
4 ቃየን አስተሳሰቡን እስካስተካከለ ድረስ ይሖዋ መልሶ ሞገሱን ሊያሳየው ፈቃደኛ ነበር። ቃየን ግን ምክሩን አልሰማም። በውስጡ የነበረው የተሳሳተ አስተሳሰብና የራስ ወዳድነት ምኞት የተሳሳተ ድርጊት ወደመፈጸም መርቶታል። (ያዕ. 1:14, 15) ቃየን ልጅ ሳለ፣ ይሖዋን የሚቃወም ድርጊት እፈጽማለሁ ብሎ ጨርሶ አስቦ ላያውቅ ይችላል። ከጊዜ በኋላ ግን በአምላክ ላይ በማመፅና የገዛ ወንድሙን በመግደል እጅግ አሳዛኝ ድርጊት ፈጸመ!
5. የይሖዋን ሞገስ ሊያሳጣን የሚችለው እንዴት ያለው አስተሳሰብ ነው?
5 እንደ ቃየን ሁሉ በዛሬው ጊዜ ያለ አንድ ክርስቲያንም ይሖዋን እንደሚያመልክ እየተናገረ የተሳሳተ አካሄድ ሊከተል ይችላል። (ይሁዳ 11) ለምሳሌ የብልግና ምኞቶችን ሊያውጠነጥን፣ የስግብግብነት ሐሳብ በውስጡ እንዲያቆጠቁጥ ሊፈቅድ አሊያም ለእምነት ባልንጀራው ጥላቻ ሊያዳብር ይችላል። (1 ዮሐ. 2:15-17፤ 3:15) እንዲህ ያለው አስተሳሰብ የኃጢአት ድርጊት ወደመፈጸም ሊመራ ይችላል። አንድ ክርስቲያን እንዲህ ያለ ሐሳብ በውስጡ እያውጠነጠነም በአገልግሎት ንቁ ተሳትፎ ያደርግ እንዲሁም በጉባኤ ስብሰባዎች ላይ አዘውትሮ ይገኝ ይሆናል። ሌሎች ሰዎች አስተሳሰባችንንና ምግባራችንን መመልከት ባይችሉም ይሖዋ ግን ሁሉንም ነገር ማየት ስለሚችል በሙሉ ልብ ከእሱ ጎን መቆም አለመቆማችንን ማወቅ ይችላል።—ኤርምያስ 17:9, 10ን አንብብ።
6. ይሖዋ ከእሱ ጎን ለመቆም ቁርጥ ውሳኔ ካደረግን የኃጢአት ዝንባሌያችንን ‘እንድንቆጣጠር’ የሚረዳን እንዴት ነው?
6 ያም ቢሆን ይሖዋ በእኛ ላይ ቶሎ ተስፋ አይቆርጥም። ከአምላክ የሚያርቀንን አካሄድ መከተል ስንጀምር ይሖዋ “ወደ እኔ ተመለሱ፤ እኔም ወደ እናንተ እመለሳለሁ” በማለት አጥብቆ ያሳስበናል። (ሚል. 3:7) ይሖዋ በተለይም ከድክመቶቻችን ጋር በምንታገልበት ወቅት ክፋትን አጥብቀን እንድንቃወም ይፈልጋል። (ኢሳ. 55:7) እንዲህ የምናደርግ ከሆነ እሱም የኃጢአት ዝንባሌያችንን ‘እንድንቆጣጠር’ የሚያስችለንን መንፈሳዊ፣ ስሜታዊና አካላዊ ጥንካሬ በመስጠት ከጎናችን እንደሆነ ያሳያል።—ዘፍ. 4:7
“አትታለሉ”
7. ሰለሞን በይሖዋ ፊት የነበረውን ጥሩ አቋም ያጣው እንዴት ነው?
7 ከንጉሥ ሰለሞን ምሳሌ ብዙ ትምህርት እናገኛለን። ሰለሞን ወጣት ሳለ የይሖዋን መመሪያ ለማግኘት ጥረት ያደርግ ነበር። አምላክ ከፍተኛ ጥበብ የሰጠው ከመሆኑም ሌላ በኢየሩሳሌም ያለውን ዕፁብ ድንቅ ቤተ መቅደስ የመገንባት ኃላፊነት ሰጥቶታል። ከጊዜ በኋላ ግን ሰለሞን ከይሖዋ ጋር የነበረውን ወዳጅነት አጥቷል። (1 ነገ. 3:12፤ 11:1, 2) የአምላክ ሕግ አንድ ዕብራዊ ንጉሥ “ልቡ ከትክክለኛው መንገድ ዞር እንዳይል ለራሱ ሚስቶች አያብዛ” የሚል ቀጥተኛ መመሪያ ይሰጥ ነበር። (ዘዳ. 17:17) ሰለሞን ግን ይህን መመሪያ በመጣስ 700 ሴቶችን አገባ፤ በተጨማሪም 300 ቁባቶችን ለራሱ ወሰደ። (1 ነገ. 11:3) ከሚስቶቹ መካከል አብዛኞቹ እስራኤላውያን ያልሆኑና የሐሰት አማልክትን የሚያመልኩ ነበሩ። በመሆኑም ሰለሞን እስራኤላውያን የባዕድ አገር ሴቶችን እንዳያገቡ የሚከለክለውን የአምላክ ሕግም ጥሷል።—ዘዳ. 7:3, 4
8. ሰለሞን የፈጸመው ይሖዋን የሚያሳዝን ድርጊት ምን ያህል ከባድ ነበር?
8 ሰለሞን ቀስ በቀስ ከይሖዋ መሥፈርቶች እየራቀ መሄዱ የከፋ ኃጢአት ወደመፈጸም መርቶታል። አስታሮት ለተባለችው እንስት አምላክና ከሞሽ ለተባለው ጣዖት መሠዊያዎችን የሠራ ሲሆን በዚያም ከሚስቶቹ ጋር በጣዖት አምልኮ ተካፍሏል። ደግሞም ካልጠፋ ቦታ እነዚህን መሠዊያዎች የሠራው የይሖዋን ቤተ መቅደስ ከገነባበት ከኢየሩሳሌም ፊት ለፊት ባለ ተራራ ላይ ነው! (1 ነገ. 11:5-8፤ 2 ነገ. 23:13) ምናልባትም ሰለሞን በቤተ መቅደሱም መሥዋዕት ማቅረቡን እስከቀጠለ ድረስ ይሖዋ መጥፎ ድርጊቱን ችላ ብሎ እንደሚያልፍለት በማሰብ ራሱን አታልሎ ሊሆን ይችላል።
9. ሰለሞን የአምላክን ማስጠንቀቂያዎች ችላ ማለቱ ምን መዘዝ አስከትሏል?
9 ይሁንና ይሖዋ መጥፎ ድርጊትን ፈጽሞ በቸልታ አያልፍም። የመጽሐፍ ቅዱስ ዘገባ እንዲህ ይላል፦ “ሰለሞን ሁለት ጊዜ ከተገለጠለት . . . ከይሖዋ ልቡ ስለሸፈተ ይሖዋ በሰለሞን ላይ ተቆጣ፤ ደግሞም ሌሎች አማልክትን እንዳይከተል በማዘዝ ይህንኑ ጉዳይ አስመልክቶ አስጠንቅቆት ነበር። እሱ ግን ይሖዋ ያዘዘውን ነገር አልጠበቀም።” በዚህም የተነሳ ሰለሞን የአምላክን ሞገስና ድጋፍ አጥቷል። የሰለሞን ዘሮች አንድ በሆነው የእስራኤል መንግሥት ላይ መግዛት ያልቻሉ ከመሆኑም ሌላ ለበርካታ ትውልዶች የሚዘልቅ መከራ ደርሶባቸዋል።—1 ነገ. 11:9-13
10. በይሖዋ ፊት ያለንን ጥሩ አቋም አደጋ ላይ የሚጥለው ምን ሊሆን ይችላል?
10 ከሰለሞን ሕይወት ማየት እንደሚቻለው መንፈሳዊነታችንን ከባድ አደጋ ላይ ሊጥሉ ከሚችሉ ነገሮች መካከል አንዱ የይሖዋን መሥፈርቶች ከማያውቁ ወይም ከማያከብሩ ሰዎች ጋር መወዳጀት ነው። አንዳንዶቹ የክርስቲያን ጉባኤ አባላት ቢሆኑም በመንፈሳዊ ደካሞች ሊሆኑ ይችላሉ። ሌሎቹ ደግሞ ይሖዋን የማያመልኩ ዘመዶቻችን፣ ጎረቤቶቻችን፣ የሥራ ባልደረቦቻችን ወይም አብረውን የሚማሩ ልጆች ሊሆኑ ይችላሉ። ያም ሆነ ይህ የምንቀርባቸው ሰዎች ለይሖዋ መሥፈርቶች አክብሮት ከሌላቸው በጊዜ ሂደት በአምላክ ፊት ያለንን ጥሩ አቋም ሊያበላሹብን ይችላሉ።
11. አንድ ሰው ጥሩ ወዳጅ ሊሆነን እንደማይችል ለመወሰን ምን ሊረዳን ይችላል?
11 አንደኛ ቆሮንቶስ 15:33ን አንብብ። አብዛኞቹ ሰዎች አንዳንድ ጥሩ ባሕርያት ይኖሯቸው ይሆናል፤ ደግሞም ዓይን ያወጣ መጥፎ ድርጊት የማይፈጽሙ የይሖዋ ምሥክር ያልሆኑ በርካታ ሰዎች ሊኖሩ ይችላሉ። እንዲህ ሲባል ታዲያ እነዚህ ሰዎች ጥሩ ወዳጆች ሊሆኑህ ይችላሉ ማለት ነው? ከእነሱ ጋር ጊዜ ማሳለፍህ ከይሖዋ ጋር ባለህ ዝምድና ላይ ምን ተጽዕኖ እንደሚያሳድር ለማሰብ ሞክር። ከይሖዋ ጋር ያለህ ዝምድና እንዲጠናከር ይረዱሃል? በልባቸው ውስጥ ያለው ነገር ምንድን ነው? ለምሳሌ ያህል፣ ወሬያቸው ሁሉ ስለ ፋሽን፣ ስለ ገንዘብ፣ ስለ ኤሌክትሮኒክ መሣሪያዎች፣ ስለ መዝናኛ ወይም ሌሎች ቁሳዊ ነገሮችን ስለማሳደድ ነው? ሌሎችን የሚያንቋሽሽ ነገር መናገር ወይም የብልግና ቀልዶችን መቀለድ ይቀናቸዋል? በእርግጥም ኢየሱስ “አንደበት የሚናገረው በልብ ውስጥ የሞላውን ነው” በማለት የተናገረው ያለምክንያት አይደለም። (ማቴ. 12:34) ጓደኞችህ በይሖዋ ፊት ያለህን ጥሩ አቋም አደጋ ላይ እየጣሉት እንዳሉ ከተገነዘብክ ከእነሱ ጋር ባለህ ግንኙነት ላይ ገደብ በማበጀት፣ አስፈላጊ ከሆነም ከነጭራሹ ግንኙነትህን በማቆም ቆራጥ እርምጃ ውሰድ።—ምሳሌ 13:20
ይሖዋ እሱ ብቻ እንዲመለክ ይፈልጋል
12. (ሀ) እስራኤላውያን ከግብፅ ከወጡ ብዙም ሳይቆይ ይሖዋ ምን ነገር ግልጽ አደረገላቸው? (ለ) እስራኤላውያን ይሖዋ እሱ ብቻ እንዲመለክ የሚፈልግ አምላክ መሆኑን ሲገልጽላቸው ምን ምላሽ ሰጡ?
12 እስራኤላውያን ከግብፅ ከወጡ ብዙም ሳይቆይ ከተከናወነው ነገር ተጨማሪ ትምህርት ዘፀ. 19:16-19) ከዚያም ‘እሱ ብቻ እንዲመለክ የሚፈልግ አምላክ’ መሆኑን ለእስራኤላውያን ገለጠ። በተጨማሪም ለሚወዱትና ትእዛዛቱን ለሚጠብቁ ታማኝ እንደሚሆን ማረጋገጫ ሰጠ። (ዘፀአት 20:1-6ን አንብብ።) በሌላ አነጋገር ይሖዋ ሕዝቡን “ከጎኔ ከሆናችሁ እኔም ከጎናችሁ እሆናለሁ” እያላቸው ነበር። አንተስ ይሖዋ ታማኝነቱን እንደሚያሳይህ በዚህ መንገድ ቃል ቢገባልህ ምን ምላሽ ትሰጥ ነበር? እስራኤላውያን የሰጡት ዓይነት ምላሽ እንደምትሰጥ ጥርጥር የለውም። እስራኤላውያን በአንድ ድምፅ “ይሖዋ የተናገረውን ቃል በሙሉ ለመፈጸም ፈቃደኞች ነን” በማለት መልስ ሰጡ። (ዘፀ. 24:3) ብዙም ሳይቆይ ግን የእስራኤላውያንን ታማኝነት የሚፈትን አንድ ያልተጠበቀ ነገር ተከሰተ።
ማግኘት እንችላለን። ሕዝቡ ከሲና ተራራ ፊት ለፊት ተሰበሰበ። በዚያም ይሖዋ፣ በመካከላቸው መገኘቱን አስገራሚ በሆነ መንገድ አሳወቀ። ተአምራዊ በሆነ መንገድ ጥቁር ደመና ተፈጠረ። ይሖዋ ነጎድጓድ እንዲሰማ፣ መብረቅ እንዲታይ፣ ጭስ እንዲወጣና ከፍተኛ የቀንደ መለከት ድምፅ ያለማቋረጥ እንዲሰማ አደረገ። (13. የእስራኤላውያንን ታማኝነት የሚፈትን ምን ሁኔታ ተከሰተ?
13 እስራኤላውያን ጥቁር ደመናውንና መብረቁን ጨምሮ አምላክ የፈጸማቸውን ሌሎች አስገራሚ ምልክቶች ሲያዩ በጣም ፈሩ። በመሆኑም ሙሴ እስራኤላውያን ባቀረቡለት ጥያቄ መሠረት እነሱን ወክሎ ከይሖዋ ጋር ለመነጋገር ወደ ሲና ተራራ ወጣ። (ዘፀ. 20:18-21) ሆኖም ሙሴ ከተራራው ሳይወርድ እዚያ ብዙ ቆየ። እስራኤላውያን እምነት የሚጥሉበት መሪያቸው ሄዶ በመቅረቱ በምድረ በዳ ያለረዳት የተተዉ ይመስል ነበር። ከሁኔታዎች መረዳት እንደሚቻለው እስራኤላውያን ሙሉ እምነታቸውን የጣሉት በዓይን በሚያዩት በሙሴ ላይ ነበር። በተፈጠረው ነገር ስለተጨነቁ አሮንን እንዲህ አሉት፦ “እንግዲህ ከግብፅ ምድር መርቶ ያወጣን ያ ሙሴ ምን እንደደረሰበት ስለማናውቅ . . . ከፊት ከፊታችን የሚሄድ አምላክ ሥራልን።”—ዘፀ. 32:1, 2
14. እስራኤላውያን ምን ብለው በማሰብ ራሳቸውን አታለው ነበር? ይሖዋስ ምን ተሰማው?
14 እስራኤላውያን ጣዖት አምልኮ ይሖዋን የሚያሳዝን ከባድ ኃጢአት እንደሆነ ያውቁ ነበር። (ዘፀ. 20:3-5) ሆኖም ብዙም ሳይቆይ የወርቅ ጥጃ ማምለክ ጀመሩ! እስራኤላውያን እንዲህ ባለ ግልጽ የሆነ መንገድ የይሖዋን ትእዛዝ ቢጥሱም አሁንም ከይሖዋ ጎን እንደሆኑ አድርገው በማሰብ ራሳቸውን አታለው ነበር። እንዲያውም አሮን የጥጃ አምልኳቸውን “ለይሖዋ የሚከበር በዓል” በማለት ጠርቶታል! ይሖዋ ምን ተሰማው? ሕዝቡ የፈጸመውን ድርጊት እንደ ክህደት ቆጥሮታል። እስራኤላውያን “ምግባረ ብልሹ [እንደሆኑ]” እንዲሁም ‘እንዲሄዱበት ካዘዛቸው መንገድ ዞር እንዳሉ’ ለሙሴ ነግሮታል። ይሖዋ ‘ቁጣው ከመንደዱ’ የተነሳ አዲስ የተቋቋመውን የእስራኤልን ብሔር ሙሉ በሙሉ ለማጥፋት አስቦ ነበር።—ዘፀ. 32:5-10
15, 16. ሙሴና አሮን ከይሖዋ ጎን ለመቆም ቁርጥ ውሳኔ እንዳደረጉ ያሳዩት እንዴት ነው? (በመግቢያው ላይ ያለውን ሥዕል ተመልከት።)
15 ይሖዋ እስራኤላውያንን ላለማጥፋት ወሰነ። የይሖዋ ምሕረት፣ ታማኝ አምላኪዎቹ ከእሱ ጎን ለመቆም ቁርጥ ውሳኔ ማድረጋቸውን የሚያሳዩበት አጋጣሚ ከፍቶላቸዋል። (ዘፀ. 32:14) ሙሴ ሕዝቡ በጣዖቱ ፊት በመጮኽ፣ በመዝፈንና በመጨፈር ተገቢ ያልሆነ ምግባር ሲያሳይ ሲመለከት የወርቅ ጥጃውን ሰባብሮ ዱቄት አደረገው። ከዚያም “ከይሖዋ ጎን የሚቆም ማን ነው? ወደ እኔ ይምጣ!” አለ። በዚህ ጊዜ “ሌዋውያን በሙሉ በዙሪያው ተሰበሰቡ።”—ዘፀ. 32:17-20, 26
16 ምንም እንኳ አሮን መጀመሪያ ላይ ከሕዝቡ ጋር ተባብሮ ጣዖት የሠራ ቢሆንም በኋላ ላይ ንስሐ በመግባት እንደ ሌሎቹ ሌዋውያን ከይሖዋ ጎን ቆሟል። እነዚህ ታማኝ ሌዋውያን ይህን እርምጃ መውሰዳቸው ከይሖዋ ጎን እንደቆሙ ብቻ ሳይሆን ራሳቸውን ከሌሎቹ ዓመፀኞች እንደለዩ የሚያሳይ ነበር። እንዲህ ማድረጋቸው የጥበብ እርምጃ ነበር፤ ምክንያቱም በዚያን ዕለት በሺዎች የሚቆጠሩ ሰዎች በጣዖት አምልኮ በመካፈላቸው ሕይወታቸውን አጥተዋል። ከይሖዋ ጎን የቆሙት ሰዎች ግን ዘፀ. 32:27-29
በረከት እንደሚያገኙ ቃል ተገብቶላቸዋል።—17. ጳውሎስ ስለ ወርቁ ጥጃ ጠቅሶ ከሰጠው ማስጠንቀቂያ ምን ትምህርት እናገኛለን?
17 ሐዋርያው ጳውሎስ ከወርቁ ጥጃ ጋር በተያያዘ የተከሰተውን ሁኔታ በመጥቀስ እንዲህ ሲል አስጠንቅቋል፦ “እነዚህ ነገሮች ለእኛ ምሳሌ ሆነውልናል። . . . ከእነሱ አንዳንዶቹ እንዳደረጉት ጣዖት አምላኪዎች አትሁኑ። እነዚህ ነገሮች [የተጻፉት] የሥርዓቶቹ ፍጻሜ የደረሰብንን እኛን ለማስጠንቀቅ ነው። በመሆኑም የቆመ የሚመስለው እንዳይወድቅ ይጠንቀቅ።” (1 ቆሮ. 10:6, 7, 11, 12) ጳውሎስ እንደጠቆመው እውነተኛ አምላኪዎችም የተሳሳተ ጎዳና መከተል ሊጀምሩ ይችላሉ። በፈተናዎች ተሸንፈው መጥፎ ድርጊት የሚፈጽሙ አንዳንድ ክርስቲያኖች አሁንም በይሖዋ ፊት ጥሩ አቋም እንዳላቸው አድርገው ያስቡ ይሆናል። ሆኖም አንድ ሰው የይሖዋ ወዳጅ መሆን ስለፈለገ ወይም ለእሱ ታማኝ እንደሆነ ስለተናገረ ብቻ ይሖዋ ሞገሱን ያሳየዋል ማለት ላይሆን ይችላል።—1 ቆሮ. 10:1-5
18. ቀስ በቀስ ከይሖዋ እንድንርቅ የሚያደርገን ምን ሊሆን ይችላል? ይህስ ምን ውጤት ያስከትላል?
18 እስራኤላውያን ሙሴ ከሲና ተራራ ሳይወርድ እንደቆየ ባዩ ጊዜ እንደተጨነቁ ሁሉ በዛሬው ጊዜ ያሉ ክርስቲያኖችም የይሖዋ የፍርድ ቀን እንዲሁም አዲሱ ዓለም የሚመጣበት ጊዜ እንደዘገየ አድርገው በማሰብ ሊጨነቁ ይችላሉ። እነዚህ ተስፋዎች የሚፈጸሙበት ጊዜ በጣም ሩቅ እንደሆነ ወይም ተስፋዎቹ የሕልም እንጀራ እንደሆኑ አድርገን ማሰብ እንጀምር ይሆናል። እንዲህ ያለውን አስተሳሰብ ካላስተካከልን ሥጋዊ ምኞቶቻችንን ከይሖዋ ፈቃድ ማስቀደም ልንጀምር እንችላለን። ይህ ደግሞ ቀስ በቀስ ከይሖዋ እንድንርቅና ጥሩ መንፈሳዊ አቋም ላይ በነበርንበት ጊዜ እናደርገዋለን ብለን ፈጽሞ አስበን የማናውቀውን ነገር ወደማድረግ ሊመራን ይችላል።
19. ፈጽሞ ልንዘነጋው የማይገባን ሐቅ የትኛው ነው? ለምንስ?
19 ይሖዋ በሙሉ ልባችን እንድንታዘዘውና እሱን ብቻ እንድናመልከው እንደሚፈልግ ፈጽሞ ልንዘነጋ አይገባም። (ዘፀ. 20:5) በየትኛውም መንገድ ከይሖዋ አምልኮ ፈቀቅ ማለት የሰይጣንን ፈቃድ ከማድረግ ተለይቶ አይታይም፤ ይህ ደግሞ መጨረሻው ጥፋት እንደሆነ ግልጽ ነው። ጳውሎስ “የይሖዋን ጽዋና የአጋንንትን ጽዋ መጠጣት አትችሉም፤ ‘ከይሖዋ ማዕድ’ እና ከአጋንንት ማዕድ መካፈል አትችሉም” በማለት ያሳሰበን ለዚህ ነው።—1 ቆሮ. 10:21
ከይሖዋ ጋር ተጣበቁ!
20. የተሳሳተ ጎዳና መከተል ከጀመርን በኋላም እንኳ ይሖዋ የሚረዳን እንዴት ነው?
20 ስለ ቃየን፣ ስለ ሰለሞንና በሲና ተራራ ስለነበሩት እስራኤላውያን የሚናገሩት የመጽሐፍ ቅዱስ ዘገባዎች ትኩረት የሚስብ የጋራ ነጥብ አላቸው። በሦስቱም ዘገባዎች ላይ የተጠቀሱት ሰዎች ‘ንስሐ የሚገቡበትና የሚመለሱበት’ አጋጣሚ ነበራቸው። (ሥራ 3:19) በግልጽ ማየት እንደሚቻለው ይሖዋ የተሳሳተ ጎዳና በሚከተሉ አገልጋዮቹ ላይ ቶሎ ተስፋ አይቆርጥም። ለምሳሌ አሮንን ይቅር ብሎታል። በዛሬው ጊዜ ይሖዋ በመጽሐፍ ቅዱስ ዘገባዎች፣ በመጽሐፍ ቅዱስ ላይ በተመሠረቱ ጽሑፎች አሊያም የእምነት ባልንጀሮቻችን በሚሰጡን ደግነት የሚንጸባረቅበት ምክር አማካኝነት ያስጠነቅቀናል። እነዚህን ማስጠንቀቂያዎች የምንቀበል ከሆነ ይሖዋ ምሕረቱን እንደሚያሳየን እርግጠኞች መሆን እንችላለን።
21. ለይሖዋ የምናሳየውን ታማኝነት ፈተና ላይ የሚጥሉ ሁኔታዎች ሲያጋጥሙን ቁርጥ ውሳኔያችን ምን ሊሆን ይገባል?
21 ይሖዋ ጸጋውን የሚያሳየው በዓላማ ነው። (2 ቆሮ. 6:1) የአምላክ ጸጋ “ፈሪሃ አምላክ በጎደለው መንገድ መኖርና ዓለማዊ ምኞቶችን መከተል [እንድንተው]” አጋጣሚ ይሰጠናል። (ቲቶ 2:11-14ን አንብብ።) “አሁን ባለው በዚህ ሥርዓት ውስጥ” እስከኖርን ድረስ ለይሖዋ የምናቀርበውን የሙሉ ልብ አምልኮ ፈተና ላይ የሚጥሉ ሁኔታዎች ያጋጥሙናል። እንግዲያው ምንጊዜም ከይሖዋ ጎን ለመቆም ቁርጥ ውሳኔ እናድርግ፤ ምክንያቱም ‘አምላካችንን ይሖዋን ልንፈራው፣ ልናገለግለውና ከእሱ ጋር ልንጣበቅ’ ይገባል!—ዘዳ. 10:20