የሕይወት ታሪክ
ይሖዋ የሚጠይቀንን ማድረግ በረከት ያስገኛል
“ለምን እኛ አንሄድም?” እኔና ባለቤቴ እንዲሁም ወንድሜና ባለቤቱ ለአንድ ተልእኮ ሰው እንደሚያስፈልግ በተነገረን ወቅት ምላሽ የሰጠነው በዚህ መንገድ ነበር። ይህን ተልእኮ ለመቀበል ፈቃደኛ የሆንነው ለምን ነበር? ይሖዋስ የባረከን እንዴት ነው? እስቲ በመጀመሪያ ስለ ራሴ ጥቂት ልንገራችሁ።
በኢንግላድ፣ ዮክሸር በምትገኝ ሄምስዎርዝ የምትባል ከተማ ውስጥ በ1923 ተወለድኩ። ቦብ የሚባል አንድ ታላቅ ወንድም አለኝ። ዘጠኝ ዓመት ገደማ ሲሆነኝ ሃይማኖታዊ ግብዝነትን ይጠላ የነበረው አባታችን የሐሰት ሃይማኖትን የሚያጋልጡ መጻሕፍት አገኘ። አባቴ ባነበበው ነገር በጣም ተገረመ። ከጥቂት ዓመታት በኋላ ቦብ አትኪንሰን የተባለ ወንድም ቤታችን መጥቶ በሸክላ ከተቀዱ የወንድም ራዘርፎርድ ንግግሮች መካከል አንዱን አስደመጠን። ንግግሩን ስንሰማ፣ ይህን ንግግር ያዘጋጁት እነዚያን መጻሕፍት ያዘጋጁት ሰዎች እንደሆኑ ተረዳን! ወላጆቼ ወንድም አትኪንሰን ሁልጊዜ ከእኛ ጋር ራት እንዲበላና ያሉንን በርካታ የመጽሐፍ ቅዱስ ጥያቄዎች እንዲመልስልን ሐሳብ አቀረቡ። ጥቂት ኪሎ ሜትር ርቆ በሚገኝ የአንድ ወንድም ቤት ውስጥ በሚደረግ ስብሰባ ላይ እንድንገኝ የተጋበዝን ሲሆን እኛም ወዲያውኑ በስብሰባዎች ላይ መገኘት ጀመርን። ከዚያም በሄምስዎርዝ አንድ አነስተኛ ጉባኤ ተቋቋመ። ብዙም ሳይቆይ የዞን አገልጋዮችን (በአሁኑ ጊዜ የወረዳ የበላይ ተመልካቾች ይባላሉ) በእንግድነት መቀበልና በአቅራቢያችን ያሉ አቅኚዎችን ቤታችን መጋበዝ ጀመርን። በእርግጥም ከእነሱ ጋር መቀራረቤ በጎ ተጽዕኖ አሳድሮብኛል።
ቤተሰባችን አንድ የንግድ ሥራ ጀምሮ ነበር፤ ሆኖም አባቴ ወንድሜን “አቅኚ መሆን የምትፈልግ ከሆነ ይህን ሥራ እንተወዋለን” አለው። ቦብም በአባቴ ሐሳብ የተስማማ ሲሆን በ21 ዓመቱ በአቅኚነት ለማገልገል ወደ ሌላ አካባቢ ሄደ። ከሁለት ዓመት በኋላ ማለትም በ16 ዓመቴ እኔም አቅኚ ሆኜ ተሾምኩ። ከቅዳሜና ከእሁድ ውጭ ያሉትን ቀናት አብዛኛውን ጊዜ የማገለግለው ብቻዬን ነበር፤ በአገልግሎት ላይ የምሥክርነት መስጫ ካርድና በሸክላ የተቀዳ ንግግር እጠቀም ነበር። ይሖዋም ፈጣን እድገት የምታደርግ የመጽሐፍ ቅዱስ ጥናት በመስጠት ባረከኝ። ከጥናቴ ቤተሰቦች መካከል ብዙዎቹ ከጊዜ በኋላ እውነትን ተቀበሉ። በቀጣዩ ዓመት ሜሪ ሄንሸል ከምትባል እህት ጋር ልዩ አቅኚ ሆኜ እንዳገለግል ተሾምኩ። እኔና ሜሪ የምሥራቹ ሰባኪዎች በሌሉበት የቼሸር ግዛት ውስጥ እንድናገለግል ተመደብን።
ጊዜው ሁለተኛው የዓለም ጦርነት እየተካሄደ የነበረበት ወቅት ሲሆን ሴቶችም ከጦርነቱ ጋር በተያያዙ ጉዳዮች እገዛ እንዲያደርጉ ይጠበቅባቸው ነበር። እኛ ልዩ አቅኚዎች፣ የሙሉ ጊዜ አገልጋዮች እንደመሆናችን መጠን ልክ እንደ ሌሎቹ ሃይማኖታዊ አገልጋዮች ከወታደራዊ አገልግሎት ነፃ እንደረጋለን ብለን ጠብቀን ነበር። ይሁን እንጂ ፍርድ ቤቶቹ በዚህ አልተስማሙም፤ በመሆኑም የ31 ቀን እስራት ተፈርዶብኝ እስር ቤት ገባሁ። በቀጣዩ ዓመት ዕድሜዬ 19 ዓመት ሲሞላ፣ በሕሊናዬ የተነሳ ወታደራዊ አገልግሎት መስጠት እንደማልችል የሚገልጽ ማመልከቻ አስገባሁ። ከዚያም በሁለት የተለያዩ ችሎቶች ፊት እንድቀርብ ኢሳ. 41:10, 13
ከተደረግኩ በኋላ ክሱ ተነሳልኝ። በዚህ ሁሉ ወቅት መንፈስ ቅዱስ እየረዳኝ እንደሆነ እንዲሁም ይሖዋ እጄን ይዞ እያበረታኝና እያጠነከረኝ እንዳለ እርግጠኛ ነበርኩ።—አዲስ ጓደኛ
በ1946 አርተር ማቲውስ ከሚባል ሰው ጋር ተዋወቅኩ። አርተር በሕሊናው ምክንያት ወታደራዊ አገልግሎት ለመስጠት ፈቃደኛ ባለመሆኑ ሦስት ወር ተፈርዶበት እስር ቤት ገብቶ ነበር፤ ከእስር ቤት እንደወጣ ወደ ሄምስዎርዝ መጥቶ በዚያ ልዩ አቅኚ ሆኖ ከሚያገለግለው ከወንድሙ ከዴኒስ ጋር አብሮ ማገልገል ጀመረ። አርተርንና ዴኒስን አባታቸው ስለ ይሖዋ ያስተማራቸው ገና ከሕፃንነታቸው አንስቶ ነበር፤ እነሱም በአሥራዎቹ ዕድሜ ላይ ሳሉ ተጠመቁ። ብዙም ሳይቆይ ዴኒስ አየርላንድ ውስጥ እንዲያገለግል ስለተመደበ አርተር ብቻውን ያለ አገልግሎት ጓደኛ ቀረ። ወላጆቼ በአቅኚነት በሚያገለግለው በዚህ ትጉ ወጣት አኗኗር ስለተገረሙ ከእነሱ ጋር እንዲኖር ጋበዙት። ቤተሰቦቼን ልጠይቅ ስሄድ እኔና አርተር ምግብ ከተበላ በኋላ ዕቃዎቹን አብረን እናጥብ ነበር። ውሎ አድሮም ደብዳቤ መጻጻፍ ጀመርን። በ1948 አርተር በድጋሚ የሦስት ወር እስራት ተፈረደበት። ከዚያም ጥር 1949 ከአርተር ጋር ትዳር መሠረትን። ግባችን እስከቻልነው ድረስ በሙሉ ጊዜ አገልግሎት መቀጠል ነበር። ያለንን ነገር አብቃቅተን እንጠቀም የነበረ ከመሆኑም ሌላ በእረፍት ጊዜያችን ፍራፍሬ በመልቀም የተወሰነ ገንዘብ እናገኝ ነበር፤ ይሖዋም ጥረታችንን ስለባረከልን በአቅኚነት አገልግሎት መቀጠል ቻልን።
ከአንድ ዓመት ብዙም ከማይበልጥ ጊዜ በኋላ ወደ ሰሜናዊ አየርላንድ እንድንሄድ ተጠየቅን። በመጀመሪያ ወደ አርማ፣ ከዚያም ወደ ኒውሪ ሄድን፤ ሁለቱም ከተሞች ካቶሊኮች የሚበዙባቸው ነበሩ። በአካባቢው ውጥረት ነግሦ ስለነበር ከሰዎች ጋር ስንነጋገር በጣም ጠንቃቆችና አስተዋዮች መሆን ያስፈልገን ነበር። ስብሰባ የምናደርገው እኛ ከምንኖርበት አካባቢ 16 ኪሎ ሜትር ርቆ በሚገኝ የአንድ ወንድምና እህት ቤት ውስጥ ነበር። የተሰብሳቢዎቹ ብዛት በአጠቃላይ ስምንት ገደማ ይሆናል። ስብሰባ የምናደርግበት ቤት ባለቤቶች አንዳንድ ጊዜ እዚያው እንድናድር ይጋብዙናል፤ እዚያ ስናድር የምንተኛው ወለል ላይ ሲሆን በማግስቱም ልዩ ቁርስ ይቀርብልናል። በአሁኑ ጊዜ በዚያ አካባቢ ብዙ የይሖዋ ምሥክሮች እንዳሉ ማወቅ በጣም ያስደስታል።
“ለምን እኛ አንሄድም?”
ወንድሜና ባለቤቱ ሎቲ በሰሜናዊ አየርላንድ በልዩ አቅኚነት እያገለገሉ ነበር፤ በ1952 አራታችንም በቤልፋስት በተደረገ ትልቅ ስብሰባ ላይ ተገኘን። በወቅቱ አንድ ወንድም አራታችንንና በብሪታንያ የቅርንጫፍ ቢሮ አገልጋይ የነበረውን ፕራይስ ሂዩዝን ቤቱ በእንግድነት አሳርፎን ነበር። አንድ ቀን ማታ፣ የአምላክ መንገድ ፍቅር ነው (እንግሊዝኛ) የሚል ርዕስ ስላለው በዋነኝነት ለአየርላንድ የተዘጋጀ ቡክሌት መውጣት እየተወያየን ነበር። ወንድም ሂዩዝ በአይሪሽ ሪፑብሊክ ውስጥ ያሉ ካቶሊኮች ምሥራቹ እንዲደርሳቸው ማድረግ በጣም አስቸጋሪ እንደሆነ ተናገረ። ወንድሞች ከመኖሪያ ቤታቸው ይፈናቀሉ የነበረ ከመሆኑም ሌላ በቀሳውስቱ ቆስቋሽነት ሕዝባዊ ዓመፅ ያጋጥማቸው ነበር። ወንድም ፕራይስ “ይህን ቡክሌት በመላው አገሪቱ ለማሰራጨት በሚደረገው ልዩ ዘመቻ የሚካፈሉ መኪና ያላቸው ባልና ሚስቶች ያስፈልጉናል” አለ። * እኛም ወዲያውኑ “ለምን እኛ አንሄድም?” አልን። በመግቢያው ላይ የጠቀስኩትን ሐሳብ የተናገርነው በዚህ ወቅት ነበር።
ደብሊን ውስጥ የምትኖር ለረጅም ጊዜ ይሖዋን በታማኝነት ያገለገለች ማ ረትላንድ የተባለች እህት ነበረች፤ ይህች እህት ምንጊዜም አቅኚዎችን ቤቷ ለመቀበል ፈቃደኛ የነበረች ሲሆን አራታችንም ለጥቂት ጊዜ እሷ ጋ አረፍን። ከዚያም አንዳንድ ንብረቶቻችንን
ከሸጥን በኋላ ከጎኑ ተጎታች ጋሪ በተገጠመለት የቦብ ሞተር ብስክሌት ላይ ተሳፍረን ለጉዟችን የሚሆን መኪና ለመግዛት ሄድን። የምንፈልገውን ዓይነት ያገለገለ መኪና አግኝተን የገዛን ቢሆንም ከመካከላችን መንዳት የሚችል ሰው አልነበረም፤ ስለዚህ የሸጠልንን ሰው መኪናውን ያለንበት ቦታ እንዲያደርስልን ጠየቅነው። ያን ዕለት ምሽት አርተር አልጋ ላይ ቁጭ ብሎ መኪና እየነዳ እንዳለ አድርጎ በማሰብ ማርሽ ሲቀያይር አደረ። በማግስቱ ጠዋት መኪናውን ከቆመበት ነድቶ ለማውጣት እየሞከረ ሳለ በሚስዮናዊነት የምታገለግለው እህት ሚልድሬድ ዊሌት (ከጊዜ በኋላ ጆን ባርን ያገባችው) ወዳረፍንበት ቤት መጣች። እሷ ደግሞ መኪና መንዳት ትችላለች! በመሆኑም ከእሷ ጋር ተጨማሪ ልምምድ ካደረግን በኋላ ለጉዞ ዝግጁ ሆንን!ቀጥሎ የሚያስፈልገን ማረፊያ ቤት ነበር። ተቃዋሚዎች እሳት ሊለኩሱበት ስለሚችሉ ተጎታች ቤት ውስጥ እንዳንኖር ማስጠንቀቂያ ተሰጥቶን ነበር። በመሆኑም ቤት ለማግኘት ጥረት አደረግን፤ ሆኖም ጥረታችን አልተሳካም። ያን ዕለት ሌሊት አራታችንም መኪናው ውስጥ አደርን። በቀጣዩም ቀን ቢሆን ያገኘነው ሁለት ተደራራቢ አልጋዎች ያሉት አንድ አነስተኛ ተጎታች ቤት ብቻ ነበር። በመሆኑም በዚህ ተጎታች ቤት ውስጥ መኖር ጀመርን። የሚገርመው ነገር ተጎታች ቤታችንን ግቢያቸው ውስጥ እንድናቆም የሚፈቅዱልን ደግ ገበሬዎች ለማግኘት ተቸግረን አናውቅም። ተጎታች ቤታችንን አቁመን በመሄድ ከ16 እስከ 24 ኪሎ ሜትር ርቀው የሚገኙ ክልሎችን እንሸፍን ነበር። ከዚያም ተጎታች ቤታችንን ወደ ሌላ ቦታ ወስደን ካቆምን በኋላ ቀደም ሲል አቁመን ወደነበርንበት አካባቢ ተመልሰን በዚያ ላሉት ሰዎች እንሰብካለን።
ያን ያህል የጎላ ችግር ሳያጋጥመን በሪፑብሊኩ ደቡባዊ ምሥራቅ የሚገኙ ቤቶችን በሙሉ ማዳረስ ቻልን፤ ከ20,000 በላይ የሚሆኑ ቡክሌቶችን ያሰራጨን ሲሆን ፍላጎት ያሳዩ ሰዎችን ስም ለብሪታንያ ቅርንጫፍ ቢሮ አስተላልፈናል። በአሁኑ ጊዜ በዚያ አካባቢ በመቶዎች የሚቆጠሩ የይሖዋ ምሥክሮች እንዳሉ ስናይ ይሖዋ ጥረታችንን በእጅጉ እንደባረከው ይሰማናል!
ወደ ኢንግላድ ተመለስን፤ ከዚያም ወደ ስኮትላንድ ሄድን
ከጊዜ በኋላ ወደ ደቡባዊ ለንደን ተመልሰን በዚያ እንድናገለግል ተመደብን። ከጥቂት ሳምንታት በኋላ አርተር ከብሪታንያ ቅርንጫፍ ቢሮ ስልክ ተደወለለትና በቀጣዩ ቀን የወረዳ የበላይ ተመልካችነት ሥራ እንዲጀምር ተነገረው! ከአንድ ሳምንት ሥልጠና በኋላ በስኮትላንድ ወደሚገኘው ወረዳችን ተጓዝን። አርተር ንግግሮቹን የሚዘጋጅበት ምንም ጊዜ አልነበረውም፤ ሆኖም በይሖዋ አገልግሎት ውስጥ የሚያጋጥመውን ማንኛውንም ተፈታታኝ ሁኔታ ለመጋፈጥ የነበረው ዝግጁነት ለእኔም የብርታት ምንጭ ሆኖኛል። በወረዳ ሥራ ማገልገል በጣም አስደሳች ነበር። ላለፉት ዓመታት የምሥራቹ ሰባኪዎች ባልተመደቡባቸው ክልሎች ውስጥ ስናገለግል ስለቆየን ከበርካታ ወንድሞችና እህቶች ጋር አብረን የማገልገል አጋጣሚ ማግኘታችን በጣም አስደስቶን ነበር!
በ1962 አርተር በጊልያድ ትምህርት ቤት የአሥር ወር ሥልጠና እንዲከታተል ሲጋበዝ ከባድ ውሳኔ ተደቀነብን። በጉዳዩ ላይ ከተወያየንበት በኋላ፣ እኔ አብሬው የማልሄድ ቢሆንም አርተር ይህን ግብዣ መቀበሉ የተሻለ እንደሆነ ወሰንን። አርተር ወደ ጊልያድ ሲሄድ የአገልግሎት ጓደኛ ስላልነበረኝ ወደ ሄምስዎርዝ ተመልሼ በመሄድ ልዩ አቅኚ ሆኜ እንዳገለግል ተመደብኩ። አርተር ከአንድ ዓመት በኋላ ሲመለስ በአውራጃ ሥራ እንድናገለግል የተመደብን ሲሆን ስኮትላንድን፣ ሰሜናዊ ኢንግላንድንና ሰሜናዊ አየርላንድን እንጎበኝ ነበር።
በአየርላንድ አዲስ ምድብ ተሰጠን
በ1964 አርተር በአይሪሽ ሪፑብሊክ ውስጥ የቅርንጫፍ ቢሮ አገልጋይ እንዲሆን አዲስ ምድብ ተሰጠው። የተጓዥ የበላይ ተመልካችነቱን ሥራ በጣም ወደነው ስለነበር መጀመሪያ ላይ አዲሱን
ምድብ መቀበል አስፈርቶኝ ነበር። አሁን መለስ ብዬ ሳስበው ግን በቤቴል የማገልገል መብት በማግኘታችን በጣም አመስጋኝ ነኝ። ለመቀበል የሚከብዳችሁን የሥራ ምድብም እንኳ በፈቃደኝነት የምትቀበሉ ከሆነ ይሖዋ ምንጊዜም ይባርካችኋል። በቤቴል ውስጥ የተለያዩ ሥራዎችን ለምሳሌ ጽሑፎችን ማሸግ፣ ምግብ ማብሰል፣ ጽዳትና የቢሮ ሥራዎችን ሠርቻለሁ። በተጨማሪም ለተወሰነ ጊዜ ያህል በአውራጃ ሥራ እንካፈል ስለነበር በመላው አገሪቱ ካሉ ወንድሞች ጋር የመገናኘት አጋጣሚ እናገኝ ነበር። የመጽሐፍ ቅዱስ ጥናቶቻችንም እድገት ሲያደርጉ ማየት ችለናል። እነዚህ ነገሮች፣ በአየርላንድ ካሉ መንፈሳዊ ቤተሰቦቻችን ጋር ጠንካራ ትስስር እንዲኖረን አድርገዋል። በእርግጥም በእጅጉ ተባርከናል!በአየርላንድ ቲኦክራሲያዊ ታሪክ ውስጥ አዲስ ምዕራፍ የከፈተ ክንውን
በ1965 በአየርላንድ ውስጥ በደብሊን ከተማ የመጀመሪያው ብሔራት አቀፍ ስብሰባ ተደረገ። * ከብዙ አቅጣጫዎች ከባድ ተቃውሞ የነበረ ቢሆንም ስብሰባው በተሳካ ሁኔታ ተካሂዷል። በአጠቃላይ 3,948 ተሰብሳቢዎችና 65 ተጠማቂዎች ነበሩ። ከተለያዩ የዓለም ክፍሎች የመጡትን 3,500 ልዑካን ቤታቸው ለተቀበሉ ሁሉ የምስጋና ደብዳቤ ተልኮ ነበር። ልዑካኑን በእንግድነት የተቀበሉትም ቢሆኑ ልዑካኑ ላሳዩት መልካም ምግባር አድናቆታቸውን ገልጸዋል። በእርግጥም ይህ በአየርላንድ ታሪክ ውስጥ አዲስ ምዕራፍ የከፈተ ክንውን ነበር።
በ1966 ሰሜናዊና ደቡባዊ አየርላንድ በደብሊን ቅርንጫፍ ቢሮ ሥር እንዲጠቃለሉ ተደረገ፤ ይህ በደሴቲቱ ላይ ይታይ ከነበረው ፖለቲካዊና ሃይማኖታዊ ክፍፍል ፈጽሞ የተለየ ነበር። በርካታ ካቶሊኮች ወደ እውነት ሲመጡና በአንድ ወቅት ፕሮቴስታንት ከነበሩ ወንድሞች ጋር አብረው ሲያገለግሉ ማየት በጣም አስደሳች ነበር።
በአገልግሎት ምድባችን ላይ ያጋጠመን ትልቅ ለውጥ
በ2011 የብሪታንያና የአየርላንድ ቅርንጫፍ ቢሮዎች ሲዋሃዱና እኛም በለንደን ቤቴል እንድናገለግል ስንመደብ ሕይወታችን ሙሉ በሙሉ ተለወጠ። ይህን ዜና የሰማነው የአርተር የጤና ሁኔታ እያሳሰበኝ በነበረበት ወቅት ነው። አርተር ፓርኪንሰንስ የሚባል የነርቭ በሽታ እንደያዘው በምርመራ ተረጋግጦ ነበር። ግንቦት 20, 2015 የ66 ዓመት የሕይወት አጋሬን በሞት አጣሁ።
ባለፉት ጥቂት ዓመታት ውስጥ የስሜት መደቆስ፣ የመንፈስ ጭንቀትና ከባድ ሐዘን አጋጥሞኛል። ከዚህ በፊት አርተር ምንጊዜም ከጎኔ ነበር። አሁን በጣም ይናፍቀኛል! ይሁን እንጂ እንዲህ ባሉ ሁኔታዎች ውስጥ ማለፋችን ይበልጥ ወደ ይሖዋ እንድንቀርብ ያደርገናል። አርተር በወንድሞች ዘንድ ምን ያህል ተወዳጅ እንደነበር ማወቄም በጣም አጽናንቶኛል። በአየርላንድ፣ በብሪታንያ ሌላው ቀርቶ በዩናይትድ ስቴትስ ጭምር ያሉ ወንድሞች ደብዳቤ ልከውልኛል። እነዚህ ደብዳቤዎች በጣም አበረታተውኛል፤ በተጨማሪም የአርተር ወንድም ዴኒስና ሚስቱ ማቪስ እንዲሁም የወንድሜ ልጆች ሩትና ጁዲ የሚሰጡኝ ማበረታቻ በቃላት ልገልጸው ከምችለው በላይ ረድቶኛል።
በጣም ያጽናናኝ ጥቅስ ኢሳይያስ 30:18 ነው። ጥቅሱ እንዲህ ይላል፦ “ይሖዋ ሞገስ ሊያሳያችሁ በትዕግሥት ይጠባበቃል፤ ምሕረት ሊያሳያችሁም ይነሳል። ይሖዋ የፍትሕ አምላክ ነውና። እሱን በተስፋ የሚጠባበቁ ሁሉ ደስተኞች ናቸው።” ይሖዋ ለችግሮቻችን መፍትሔ ለማምጣትና በመጪው አዲስ ዓለም ውስጥ ለእኛ አስደሳች የሥራ ምድብ ለመስጠት በትዕግሥት እየተጠባበቀ መሆኑን ማወቄ በጣም አጽናንቶኛል።
ያሳለፍነውን ሕይወት መለስ ብዬ ሳስብ ይሖዋ በአየርላንድ ያለውን ሥራ እንደመራውና በእጅጉ እንደባረከው መመልከት እችላለሁ! በአየርላንድ ውስጥ ለታየው መንፈሳዊ እድገት በጥቂቱም ቢሆን አስተዋጽኦ ማበርከት መቻሌ ትልቅ መብት እንደሆነ ይሰማኛል። በእርግጥም ይሖዋ የሚጠይቀንን ማድረግ ምንጊዜም በረከት እንደሚያስገኝ ምንም ጥርጥር የለውም።