“የምድር ሁሉ ዳኛ” ምንጊዜም ትክክል የሆነውን ነገር ያደርጋል
“እሱ ዓለት፣ የሚያደርገውም ነገር ሁሉ ፍጹም ነው፤ መንገዶቹ ሁሉ ፍትሕ ናቸውና።”—ዘዳ. 32:4
1. አብርሃም ይሖዋ ፍትሐዊ እርምጃ እንደሚወስድ ያለውን እምነት የገለጸው እንዴት ነው? (በመግቢያው ላይ ያለውን ሥዕል ተመልከት።)
“የምድር ሁሉ ዳኛ ትክክል የሆነውን ነገር አያደርግም?” (ዘፍ. 18:25) አብርሃም ይህን ጥያቄ ሲያነሳ፣ ይሖዋ ከሰዶምና ከገሞራ ጋር በተያያዘ ፍጹም ፍትሐዊ የሆነ ፍርድ እንደሚያስተላልፍ ያለውን እምነት መግለጹ ነበር። ይሖዋ “ጻድቁን ከኃጢአተኛው ጋር አንድ ላይ [በመግደል]” ፍትሕ እንደማያዛባ አብርሃም እርግጠኛ ነበር። አብርሃም እንዲህ ያለው ድርጊት “ፈጽሞ የማይታሰብ ነገር” እንደሆነ ገልጿል። አብርሃም ይህን ካለ ከ400 ዓመታት ገደማ በኋላ ይሖዋ ስለ ራሱ ሲናገር እንዲህ ብሏል፦ “እሱ ዓለት፣ የሚያደርገውም ነገር ሁሉ ፍጹም ነው፤ መንገዶቹ ሁሉ ፍትሕ ናቸውና። እሱ ፈጽሞ ፍትሕን የማያጓድል ታማኝ አምላክ ነው፤ ጻድቅና ትክክለኛ ነው።”—ዘዳ. 31:19፤ 32:4
2. ይሖዋ ፈጽሞ ፍትሕን ሊያዛባ አይችልም የምንለው ለምንድን ነው?
2 አብርሃም፣ ይሖዋ ምንጊዜም በጽድቅ እንደሚፈርድ እርግጠኛ የሆነው ለምንድን ነው? ፍትሕንና ጽድቅን በማንጸባረቅ ረገድ ከሁሉ የላቀው ምሳሌ ይሖዋ ስለሆነ ነው። “ፍትሕ” እና “ጽድቅ” ተብለው የሚተረጎሙት የዕብራይስጥ ቃላት በዕብራይስጥ ቅዱሳን መጻሕፍት ውስጥ ብዙ ጊዜ አብረው ይጠቀሳሉ። በመሠረቱ፣ ፍትሐዊ በሆነው ነገርና ትክክል ወይም ጽድቅ በሆነው ነገር መካከል ልዩነት የለም። ደግሞም የይሖዋ መሥፈርቶች ምንጊዜም መዝ. 33:5
ትክክለኛ ወይም ጽድቅ የሚንጸባረቅባቸው በመሆናቸው አንድን ጉዳይ አስመልክቶ የሚያስተላልፈው ፍርድ ሁልጊዜ ፍትሐዊ ነው። በተጨማሪም ቃሉ መጽሐፍ ቅዱስ እንደሚናገረው ይሖዋ “ጽድቅንና ፍትሕን ይወዳል።”—3. በዛሬው ጊዜ በዓለም ላይ የሚፈጸመውን የፍትሕ መጓደል የሚያሳይ ምሳሌ ጥቀስ።
3 ይህ ዓለም በፍትሕ መጓደል የተሞላ በመሆኑ ቅን ልብ ያላቸው ሰዎች፣ ይሖዋ ምንጊዜም ፍትሐዊ መሆኑን ማወቃቸው ያጽናናቸዋል። አንዳንድ ጊዜ ሰዎች ከባድ ግፍ ይፈጸምባቸዋል። ለምሳሌ ያለጥፋታቸው ተፈርዶባቸው ወህኒ የወረዱ ሰዎች አሉ። አንዳንዶች ባልፈጸሙት ወንጀል ለብዙ አሥርተ ዓመታት የታሰሩ ሲሆን ነፃ መውጣት የቻሉት ጥፋተኛ አለመሆናቸውን የሚያሳይ የዲ ኤን ኤ ማስረጃ በመገኘቱ ነው። ሰዎች እንዲህ ባለ ፍትሐዊ ያልሆነ ፍርድ ምክንያት ለእስራት መዳረጋቸው የሚያበሳጭና የሚያስቆጣ እንደሆነ የታወቀ ነው፤ ክርስቲያኖች ግን ከዚህ ይበልጥ ስሜትን የሚጎዳ የፍትሕ መጓደል ሊያጋጥማቸው ይችላል።
በጉባኤ ውስጥ
4. አንድ ክርስቲያን እምነቱን የሚፈትን ምን ሁኔታ ሊያጋጥመው ይችላል?
4 ክርስቲያኖች ከጉባኤ ውጭ ያሉ ሰዎች ፍትሐዊ ያልሆነ ድርጊት ሊፈጽሙባቸው እንደሚችሉ ይጠብቃሉ። ይሁንና በጉባኤ ውስጥ፣ ፍትሐዊ እንዳልሆነ የሚሰማን ነገር ብንመለከት ወይም በእኛ ላይ ቢፈጸም እምነታችን ሊፈተን ይችላል። አንተስ ጉባኤው ወይም አንድ የእምነት ባልንጀራህ በደል እንደፈጸመብህ ቢሰማህ ምን ታደርጋለህ? ይህ ሁኔታ እንዲያሰናክልህ ትፈቅዳለህ?
5. አንድ ክርስቲያን ፍትሐዊ ያልሆነ ነገር በጉባኤው ውስጥ ቢመለከት ወይም ቢያጋጥመው ሊገረም የማይገባው ለምንድን ነው?
5 ሁላችንም ፍጽምና የሚጎድለን ከመሆኑም ሌላ የኃጢአት ዝንባሌ አለን፤ በመሆኑም በክርስቲያን ጉባኤ ውስጥም እንኳ ሌሎች ሊበድሉን እንደሚችሉ ወይም እኛ ራሳችን ሌሎችን ልንበድል እንደምንችል የታወቀ ነው። (1 ዮሐ. 1:8) እንዲህ ያለው ነገር እምብዛም የሚያጋጥም ባይሆንም ታማኝ ክርስቲያኖች የፍትሕ መጓደል ቢያጋጥማቸው ነገሩ እንግዳ ሊሆንባቸው ወይም ሊሰናከሉ አይገባም። ይሖዋ የእምነት አጋሮቻችን ቢበድሉን እንኳ ንጹሕ አቋማችንን ጠብቀን ለመመላለስ የሚረዳ ጠቃሚ ምክር በቃሉ ውስጥ እንዲካተት አድርጎልናል።—መዝ. 55:12-14
6, 7. አንድ ወንድም በጉባኤ ውስጥ ምን ዓይነት የፍትሕ መጓደል አጋጥሞታል? ጉዳዩን በተገቢው መንገድ እንዲይዝ የረዱት ባሕርያት የትኞቹ ናቸው?
6 ወንድም ዊሊ ዲየል ያጋጠመውን ሁኔታ እንደ ምሳሌ እንመልከት። ወንድም ዲየል በበርን፣ ስዊዘርላንድ በሚገኘው ቤቴል ውስጥ ከ1931 ጀምሮ በታማኝነት አገልግሏል። በተጨማሪም በ1946 በኒው ዮርክ፣ ዩናይትድ ስቴትስ በተካሄደው ስምንተኛው የጊልያድ ትምህርት ቤት ሠልጥኗል። ከትምህርት ቤቱ ከተመረቀ ከተወሰነ ጊዜ በኋላ ስዊዘርላንድ ውስጥ በወረዳ ሥራ እንዲያገለግል ተመደበ። ወንድም ዲየል የሕይወት ታሪኩን ሲናገር እንዲህ ብሏል፦ ‘በ1949 ግንቦት ወር፣ በበርን ለሚገኘው ዋና መሥሪያ ቤት ለማግባት ማቀዴን ገለጽኩ።’ በበርን የሚገኘው ቢሮ ምን ምላሽ ሰጠው? ወንድም ዲየል “ከዘወትር አቅኚነት በስተቀር ሌላው መብት ሁሉ ተወሰደብኝ” ብሏል። አክሎም “ንግግር እንድሰጥ አልተፈቀደልኝም . . . ብዙዎች ከዚያ ወዲያ ልክ እንደተወገድን በመቁጠር ሰላም አይሉንም ነበር” በማለት ተናግሯል።
7 ታዲያ ወንድም ዲየል ምን አደረገ? እንዲህ ብሏል፦ “መጋባት ቅዱስ ጽሑፋዊ ያልሆነ ነገር አለመሆኑን እናውቅ ስለነበር ጸሎትን መሸሺያችን በማድረግ በይሖዋ ተማመንን።” ወንድም ዲየል እንዲህ ያለ የፍትሕ መጓደል የደረሰበት አንዳንዶች ስለ ጋብቻ የተሳሳተ አመለካከት ስለነበራቸው ነው፤ ውሎ አድሮ ግን እንዲህ ያለው አመለካከት በመስተካከሉ ወንድም ዲየል የአገልግሎት መብቶቹ ተመለሱለት። በእርግጥም ለይሖዋ ታማኝ መሆኑ ወሮታ አስገኝቶለታል። * እኛም ራሳችንን እንደሚከተለው ብለን መጠየቃችን ጠቃሚ ነው፦ ‘እኔስ እንዲህ ያለ የፍትሕ መጓደል ቢያጋጥመኝ ይሖዋ ነገሮችን እስኪያስተካክል በትዕግሥት እጠብቃለሁ? ወይስ ሁኔታውን ለማስተካከል የራሴን እርምጃ እወስዳለሁ?’—ምሳሌ 11:2፤ ሚክያስ 7:7ን አንብብ።
8. በአንተ ወይም በሌላ የጉባኤው አባል ላይ ፍትሕ የጎደለው ድርጊት እንደተፈጸመ ቢሰማህ ተሳስተህ ሊሆን እንደሚችል ማሰቡ ጠቃሚ የሆነው ለምንድን ነው?
8 በሌላ በኩል ደግሞ በአንተ ወይም በሌላ የጉባኤው አባል ላይ ፍትሕ የጎደለው ድርጊት እንደተፈጸመ ቢሰማህ ምናልባት ተሳስተህ ሊሆን እንደሚችል ማስታወስህ ጠቃሚ ነው። እንዲህ የሚሰማን ፍጽምና የጎደለን በመሆናችን ነገሮችን በተሳሳተ መንገድ ስለተረዳን አሊያም ስለ ጉዳዩ የተሟላ መረጃ ስለሌለን ሊሆን ይችላል። ስለ ጉዳዩ ያለን እውቀት ትክክልም ይሁን ስህተት፣ ወደ ይሖዋ መጸለያችንና በእሱ መታመናችን እንዲሁም ታማኝነታችንን መጠበቃችን ‘በይሖዋ ላይ ከመቆጣት’ እንድንቆጠብ ይረዳናል።—ምሳሌ 19:3ን አንብብ።
9. በዚህና በሚቀጥለው ርዕስ ላይ የትኞቹን ታሪኮች እንመረምራለን?
9 በጥንት ዘመን ከነበሩ የአምላክ ሕዝቦች ጋር በተያያዘ ከተፈጸሙ ፍትሕ የጎደላቸው ሦስት ድርጊቶች ምን ትምህርት እንደምናገኝ እስቲ እንመልከት። በዚህ ርዕስ ላይ የአብርሃም ልጅ የሆነው የይስሐቅ የልጅ ልጅ፣ ማለትም ዮሴፍ ከወንድሞቹ ጋር በተያያዘ ያጋጠመውን ሁኔታ እንመለከታለን። በሚቀጥለው ርዕስ ላይ ደግሞ ይሖዋ የእስራኤል ንጉሥ ከነበረው ከአክዓብ ጋር በተያያዘ ያደረገውን ነገር እንዲሁም ሐዋርያው ጴጥሮስ በሶርያዋ አንጾኪያ ያጋጠመውን ሁኔታ እንመረምራለን። እነዚህን ምሳሌዎች በምንመረምርበት ወቅት፣ በተለይ ፍትሕ የጎደለው ድርጊት እንደተፈጸመብህ ሆኖ ሲሰማህ መንፈሳዊነትህንም ሆነ ከይሖዋ ጋር ያለህን ወዳጅነት ጠብቀህ እንድትቀጥል የሚረዱ ነጥቦችን ለማስተዋል ጥረት አድርግ።
ዮሴፍ የደረሰበት የፍትሕ መጓደል
10, 11. (ሀ) ዮሴፍ ምን ዓይነት ግፍ ተፈጽሞበት ነበር? (ለ) ዮሴፍ እስር ቤት ሳለ ምን አጋጣሚ አግኝቶ ነበር?
10 የይሖዋ ታማኝ አገልጋይ የሆነው ዮሴፍ ከባድ የፍትሕ መጓደል ደርሶበት ነበር፤ ሁኔታውን ይበልጥ የከፋ ያደረገው ደግሞ ግፍ የፈጸሙበት ሌሎች ሰዎች ብቻ ሳይሆኑ የገዛ ወንድሞቹም ጭምር መሆናቸው ነው። ዮሴፍ በአሥራዎቹ ዕድሜ መጨረሻ አካባቢ እያለ ወንድሞቹ በባርነት እንዲያገለግል ወደ ባዕድ አገር ሸጡት። በመሆኑም በግዳጅ ወደ ግብፅ ተወሰደ። (ዘፍ. 37:23-28፤ 42:21) በባዕድ አገር የተወሰነ ጊዜ ከቆየ በኋላ ደግሞ አስገድዶ የመድፈር ሙከራ አድርገሃል በሚል በሐሰት ተወነጀለ፤ ከዚያም ለፍርድ እንኳ ሳይቀርብ እስር ቤት ተወረወረ። (ዘፍ. 39:17-20) ዮሴፍ በባርነት እና በእስር 13 ዓመታት ያህል አሳልፏል። እኛስ አንድ የእምነት ባልንጀራችን ፍትሐዊ ያልሆነ ነገር ቢፈጽምብን ዮሴፍ ባጋጠመው ነገር ላይ ማሰላሰላችን የሚጠቅመን እንዴት ነው?
11 ዮሴፍ የደረሰበትን በደል አብሮት ለታሰረ ሰው ለመናገር የሚያስችለው አጋጣሚ አግኝቶ ነበር። ይህ እስረኛ ከዚህ ቀደም የንጉሡ የመጠጥ አሳላፊዎች አለቃ ነበር። ዮሴፍና የመጠጥ አሳላፊው እስር ቤት በነበሩበት ወቅት የመጠጥ አሳላፊው አንድ ሕልም ያየ ሲሆን ዮሴፍ ደግሞ ሕልሙን ተረጎመለት። ዮሴፍ፣ ለመጠጥ አሳላፊው በፈርዖን ቤተ መንግሥት ውስጥ ወደነበረው ወደ ቀድሞ ሹመቱ እንደሚመለስ ገለጸለት። ዮሴፍ በአምላክ መንፈስ መሪነት ሕልሙን በተረጎመበት ወቅት፣ እሱ ራሱ የደረሰበትን በደልም ለመጠጥ አሳላፊው ነገረው። ዮሴፍ የተናገረውን ነገር ብቻ ሳይሆን ሳይናገር የቀረውን ነገርም በመመርመር ጠቃሚ ትምህርት እናገኛለን።—ዘፍ. 40:5-13
12, 13. (ሀ) ዮሴፍ ለመጠጥ አሳላፊው የተናገረው ሐሳብ የደረሰበትን ኢፍትሐዊ ድርጊት ለማስተካከል እርምጃ እንደወሰደ የሚያሳየው እንዴት ነው? (ለ) ዮሴፍ ለመጠጥ አሳላፊው ምን ነገር ከመናገር ተቆጥቧል?
12 ዘፍጥረት 40:14, 15ን አንብብ። ዮሴፍ፣ “የመጣሁት ተገድጄ ነው” እንዳለ ልብ በል። እዚህ ላይ የገባው ቃል፣ በቀጥታ ሲተረጎም “ሰርቀው” እንዳመጡት የሚገልጽ ነው። ዮሴፍ ግፍ እንደተፈጸመበት ምንም ጥርጥር የለውም። በተጨማሪም ዮሴፍ የታሰረው ያለጥፋቱ እንደሆነ ተናግሯል። በመሆኑም ጉዳዩን ለፈርዖን እንዲነግርለት የመጠጥ አሳላፊውን ጠየቀው። ዓላማው ምን ነበር? “ከዚህ እስር ቤት እንዲያስፈታኝም ስለ እኔ ለፈርዖን ንገረው” ብሎታል።
13 ዮሴፍ ከተናገረው ነገር መመልከት እንደሚቻለው፣ ያለበትን ሁኔታ ዝም ብሎ ከመቀበል ይልቅ ሁኔታውን ለማስተካከል እርምጃ ወስዷል። ይህ ወጣት ብዙ በደል ተፈጽሞበታል። ዮሴፍ፣ የመጠጥ አሳላፊው እርዳታ ሊያደርግለት እንደሚችል ስለተሰማው የደረሰበትን በደል በግልጽ አስረድቶታል። ይሁን እንጂ ዮሴፍ፣ ወደ ባዕድ አገር የሸጡት ወንድሞቹ መሆናቸውን ለማንም ሰው ሌላው ቀርቶ ለፈርዖን እንኳ እንደተናገረ የሚገልጽ ሐሳብ በቅዱሳን ጽሑፎች ውስጥ አይገኝም። እንዲያውም የዮሴፍ ወንድሞች ወደ ግብፅ መጥተው ከዮሴፍ ጋር ከታረቁ በኋላ ፈርዖን ጥሩ አድርጎ ተቀብሏቸዋል፤ በተጨማሪም “በግብፅ ምድር ያለ ምርጥ ነገር ሁሉ የእናንተው ነው” በማለት በዚያ እንዲኖሩ ጋብዟቸዋል።—ዘፍ. 45:16-20
14. በጉባኤ ውስጥ ፍትሕ የጎደለው ድርጊት ቢፈጸምብን እንኳ ሐሜት ከማሰራጨት እንድንቆጠብ የሚረዳን ምንድን ነው?
14 በጉባኤ ውስጥ ፍትሕ የጎደለው ድርጊት እንደተፈጸመብን ከተሰማን ስለ ጉዳዩ ሐሜት ላለማሰራጨት መጠንቀቅ ይኖርብናል። እርግጥ ነው፣ አንድ የጉባኤው አባል ከባድ ኃጢአት እንደፈጸመ ካወቅን የሽማግሌዎችን እርዳታ መጠየቃችንና ስለ ጉዳዩ ለእነሱ መናገራችን ተገቢ ነው። (ዘሌ. 5:1) ይሁንና ብዙውን ጊዜ የሚያጋጥሙን ሁኔታዎች ከባድ ኃጢአት ከመፈጸም ጋር የተያያዙ አይደሉም፤ በዚህ ጊዜ ለማንም ሰው ሌላው ቀርቶ ለጉባኤ ሽማግሌዎችም እንኳ ሳንናገር ችግሩን መፍታት እንችል ይሆናል። (ማቴዎስ 5:23, 24ን እና 18:15ን አንብብ።) ከመጽሐፍ ቅዱስ መመሪያዎች ጋር በሚስማማ መንገድ ጉዳዩን በመፍታት ታማኝነት እናሳይ። አንዳንድ ጊዜ ደግሞ በደል እንደደረሰብን የተሰማን ሁኔታውን በተሳሳተ መንገድ ስለተረዳነው እንደሆነ እንገነዘብ ይሆናል። ይህን ስናውቅ፣ የእምነት ባልንጀራችንን ስም በማጥፋት ጉዳዩ እንዲባባስ ባለማድረጋችን እንደምንደሰት የታወቀ ነው! ደግሞም የተሰማን ስሜት ትክክል ሆነም አልሆነ፣ ሐሜት ማሰራጨት የተፈጠረውን ሁኔታ ለማስተካከል ሊረዳ እንደማይችል ማስታወሳችን ጠቃሚ ነው። ለይሖዋና ለወንድሞቻችን ያለን ታማኝነት እንዲህ ያለ ስህተት እንዳንሠራ ይጠብቀናል። መዝሙራዊው “ያለ ነቀፋ የሚመላለስ” ሰውን አስመልክቶ ሲናገር “በአንደበቱ ስም አያጠፋም፤ በባልንጀራው ላይ መጥፎ ነገር አይሠራም፤ የወዳጆቹንም ስም አያጎድፍም” ብሏል።—መዝ. 15:2, 3፤ ያዕ. 3:5
የላቀ ቦታ የምትሰጠውን ወዳጅነት አስታውስ
15. ዮሴፍ ከይሖዋ ጋር ያለው ግንኙነት በረከት ያስገኘለት እንዴት ነው?
15 ዮሴፍ ከይሖዋ ጋር ከነበረው ግንኙነት ትልቅ ትምህርት እናገኛለን። ዮሴፍ ለ13 ዓመታት የዘለቀ መከራ ቢደርስበትም ነገሮችን ይሖዋ በሚያይበት መንገድ እንደሚመለከት አሳይቷል። (ዘፍ. 45:5-8) በደረሱበት ችግሮች የተነሳ ፈጽሞ በይሖዋ ላይ አልተቆጣም። የተፈጸመበትን በደል ረስቶታል ማለት ባይሆንም ምሬት እንዲያድርበት አልፈቀደም። ከሁሉ በላይ ደግሞ የሌሎች አለፍጽምና እንዲሁም ያደረሱበት በደል ከይሖዋ እንዲያርቀው አልፈቀደም። ዮሴፍ ታማኝ በመሆኑ ይሖዋ ኢፍትሐዊ ድርጊቶችን ሲያስተካክል እንዲሁም እሱንም ሆነ ቤተሰቡን ሲባርክ ለመመልከት በቅቷል።
16. በጉባኤ ውስጥ ፍትሕ የጎደለው ነገር ቢፈጸምብን ምን ማድረግ ይኖርብናል?
16 እኛም ከይሖዋ ጋር የመሠረትነውን ዝምድና ከፍ አድርገን መመልከትና ዝምድናችን እንዳይበላሽ መጠንቀቅ ይኖርብናል። የወንድሞቻችን አለፍጽምና ከምንወደው አምላካችን ሊለየን እና እሱን ከማምለክ ወደኋላ እንድንል ሊያደርገን አይገባም። (ሮም 8:38, 39) እንዲያውም አንድ የእምነት አጋራችን ፍትሕ የጎደለው ድርጊት ቢፈጽምብን፣ ልክ እንደ ዮሴፍ ወደ ይሖዋ ይበልጥ ለመቅረብና እሱ ለነገሮች ያለው ዓይነት አመለካከት ለማዳበር ጥረት እናድርግ። ቅዱሳን ጽሑፎች በሚሉት መሠረት ሁኔታውን ለማስተካከል የምንችለውን ሁሉ ካደረግን በኋላ ይሖዋ ጉዳዩን በራሱ ጊዜና መንገድ እንደሚያስተካክል በመተማመን ነገሩን ለእሱ መተው ይኖርብናል።
‘በምድር ሁሉ ዳኛ’ ላይ እምነት ይኑርህ
17. “የምድር ሁሉ ዳኛ” በሆነው አምላክ እንደምንተማመን ማሳየት የምንችለው እንዴት ነው?
17 በዚህ ሥርዓት ውስጥ እስካለን ድረስ የፍትሕ መጓደል ሊያጋጥመን እንደሚችል መጠበቅ ይኖርብናል። በጉባኤ ውስጥ በአንድ የምናውቀው ሰው ወይም በራሳችን ላይ በደል እንደተፈጸመ እንዲሰማን የሚያደርግ ሁኔታ ሊፈጠር ይችላል፤ እርግጥ ይህ ብዙ ጊዜ የሚያጋጥም ነገር አይደለም። ያም ቢሆን እንዲህ ያለው ሁኔታ እንዲያደናቅፈን መፍቀድ የለብንም። (መዝ. 119:165) እንዲያውም ምንጊዜም ለአምላክ ታማኝ እንሁን፤ እንዲሁም ይሖዋ እንደሚረዳን በመተማመን ወደ እሱ እንጸልይ። በሌላ በኩል ደግሞ የተሟላ መረጃ ላይኖረን እንደሚችል በመገንዘብ ትሕትና ማሳየት ይኖርብናል። በተጨማሪም ፍጹማን ባለመሆናችን የተነሳ ሁኔታውን በተሳሳተ መንገድ ተረድተነው ሊሆን ይችላል። ከዮሴፍ ምሳሌ እንደተማርነው ሐሜት ማሰራጨት አንድን ችግር የበለጠ ከማባባስ ውጪ የሚፈይደው ነገር የለም፤ ስለዚህ ይህን ከማድረግ እንቆጠባለን። በመሆኑም ችግሩን በራሳችን መንገድ ለመፍታት ከመሞከር ይልቅ ምንጊዜም ለይሖዋ ታማኝ በመሆን እሱ ነገሮችን እስኪያስተካክል ድረስ በትዕግሥት እንጠብቅ። እንዲህ ያለውን አካሄድ መከተል ልክ እንደ ዮሴፍ የይሖዋን ሞገስና በረከት ያስገኝልናል። በእርግጥም “የምድር ሁሉ ዳኛ” የሆነው ይሖዋ “መንገዶቹ ሁሉ ፍትሕ” ስለሆኑ ምንጊዜም ትክክል የሆነውን ነገር እንደሚያደርግ መተማመን እንችላለን።—ዘፍ. 18:25፤ ዘዳ. 32:4
18. በሚቀጥለው ርዕስ ላይ ምን እንመረምራለን?
18 በሚቀጥለው ርዕስ ላይ በጥንት ዘመን የነበሩ የይሖዋ ሕዝቦች ያጋጠማቸውን ፍትሕ የጎደለው ሁኔታ የሚያሳዩ ሁለት ምሳሌዎችን እንመለከታለን። እነዚህን ዘገባዎች መመርመራችን ትሕትና እና ይቅር ባይነት፣ ይሖዋ ስለ ፍትሕ ያለውን አመለካከት ለማንጸባረቅ እንዴት እንደሚረዱን ለመገንዘብ ያስችለናል።
^ አን.7 በኅዳር 1, 1991 መጠበቂያ ግንብ ላይ “ይሖዋ የምታመንበት አምላኬ ነው” በሚል ርዕስ የወጣውን የወንድም ዊሊ ዲየል የሕይወት ታሪክ ተመልከት።