በቀጥታ ወደ ዋናው ጉዳይ ግባ

በቀጥታ ወደ ርዕስ ማውጫው ሂድ

ጆርጅ ሮልስተን እና አርተር ዊሊስ የተባሉት አቅኚዎች የመኪናቸውን ራዲያተር ውኃ ሲሞሉ።—ኖርዘርን ቴሪተሪ፣ 1933

ከታሪክ ማኅደራችን

“በጣም አስቸጋሪ ወይም በጣም ረጅም የሆነ መንገድ የለም”

“በጣም አስቸጋሪ ወይም በጣም ረጅም የሆነ መንገድ የለም”

መጋቢት 26, 1937 በጉዞ የዛሉ ሁለት ሰዎች አቧራ የለበሰ መኪናቸውን በቀስታ እየነዱ ወደ ሲድኒ፣ አውስትራሊያ ደረሱ። ከሲድኒ የተነሱት ከአንድ ዓመት በፊት ሲሆን በአህጉሪቱ ውስጥ ያሉትን ርቀው የሚገኙና አስቸጋሪ የሆኑ አካባቢዎች እያቆራረጡ ከ19,300 ኪሎ ሜትር በላይ ተጉዘዋል። ሁለቱ ሰዎች አገር አሳሾች አልነበሩም። አርተር ዊሊስና ቢል ኒውላንድስ የተባሉት እነዚህ ሰዎች፣ የአምላክን መንግሥት ምሥራች በአውስትራሊያ ወደሚገኙ ራቅ ያሉ ቦታዎች ለማዳረስ የተነሱ ቀናተኛ አቅኚዎች ናቸው፤ ሌሎች በርካታ አቅኚዎችም ተመሳሳይ ሥራ አከናውነዋል።

በአውስትራሊያ የሚገኙት ጥቂት ቁጥር ያላቸው የመጽሐፍ ቅዱስ ተማሪዎች፣ * እስከ 1920ዎቹ መገባደጃ ድረስ በአብዛኛው የሚሰብኩት በባሕር ጠረፍ አካባቢ በሚገኙት ከተሞችና በአቅራቢያቸው ባሉት መንደሮች ነበር። በመሃል አገር ብዙም ሰው ያልሰፈረበት ጠፍ የሆነ ሰፊ ክልል አለ፤ ስፋቱ የኢትዮጵያን የቆዳ ስፋት አምስት እጥፍ ያህል ይሆናል። የኢየሱስ ተከታዮች ርቀው የሚገኙትን የአውስትራሊያ አካባቢዎች ጨምሮ “እስከ ምድር ዳር ድረስ” ስለ ኢየሱስ መመሥከር እንዳለባቸው ወንድሞች ተረድተው ነበር። (ሥራ 1:8) ይሁንና ይህን ታላቅ ኃላፊነት እንዴት መወጣት ይችላሉ? ይሖዋ ጥረታቸውን እንደሚባርክላቸው ሙሉ በሙሉ በመተማመን የቻሉትን ሁሉ ለማድረግ ቆርጠው ነበር።

አቅኚዎች ግንባር ቀደም ሆኑ

በ1929 በኩዊንስላንድና በዌስተርን አውስትራሊያ የሚገኙ ጉባኤዎች፣ በመሃል አገር ለመስበክ ሲሉ አስፈላጊ ቁሳቁሶች ሁሉ የተሟሉላቸው የተወሰኑ መኪኖች አዘጋጁ። መኪኖቹን የሚነዱት፣ አስቸጋሪ የሆነውን የአካባቢውን ሁኔታ መቋቋምና መኪኖቹ ሲበላሹ መጠገን የሚችሉ ጠንካራ አቅኚዎች ነበሩ። እነዚህ አቅኚዎች ከዚያ በፊት ምሥራቹ ጨርሶ ወዳልደረሰባቸው በርካታ ቦታዎች ሄደው ሰብከዋል።

መኪና ለመግዛት አቅማቸው ያልፈቀደላቸው አቅኚዎች ደግሞ ወደ እነዚህ ራቅ ያሉ ቦታዎች በብስክሌት ተጉዘዋል። ለምሳሌ ያህል፣ በ1932 የ23 ዓመት ወጣት የነበረው ቤነት ብሪከል ከሮክሃምፕተን፣ ኩዊንስላንድ ተነስቶ ርቆ የሚገኘውን የዚህን ግዛት ሰሜናዊ ክፍል በማቋረጥ ለአምስት ወራት ያህል እየተጓዘ ሰብኳል። በብስክሌቱ ላይ ብርድ ልብሶች፣ ልብሶች፣ ምግብና በርካታ መጻሕፍት ጭኖ ይጓዝ ነበር። የብስክሌቱ ጎማ ቢያልቅም ይሖዋ እንደሚመራው በመተማመን በድፍረት ጉዞውን ቀጥሏል። በጉዞው መጨረሻ ላይ የነበረውን 320 ኪሎ ሜትር ያጠናቀቀው ብስክሌቱን እየገፋ ነበር፤ ከዚያ ቀደም አንዳንዶች በዚህ አካባቢ ሲጓዙ በውኃ ጥም ሕይወታቸውን አጥተዋል። በቀጣዮቹ ከ30 የሚበልጡ ዓመታት ወንድም ብሪከል በመቶ ሺዎች የሚቆጠሩ ኪሎ ሜትሮችን በብስክሌት፣ በሞተር ብስክሌትና በመኪና በመጓዝ በመላው አውስትራሊያ ተዘዋውሯል። በአቦሪጂኖች ክልል ምሥራቹ እንዲሰበክ መንገድ የከፈተው እሱ ሲሆን አዳዲስ ጉባኤዎች እንዲቋቋሙ እርዳታ አበርክቷል፤ በዚህም ምክንያት በአውስትራሊያ ራቅ ያሉ አካባቢዎች በብዙዎች ዘንድ የታወቀና የተከበረ ወንድም ለመሆን ችሏል።

አስቸጋሪ ሁኔታዎችን መቋቋም

አውስትራሊያ በዓለማችን ላይ ሕዝብ ተራርቆ ከሚኖርባቸው አገሮች መካከል አንዷ ናት፤ በተለይ ራቅ ብለው የሚገኙት አካባቢዎች ሕዝብ በብዛት አልሰፈረባቸውም። በመሆኑም የይሖዋ ሕዝቦች በዚህች አህጉር ውስጥ ራቅ ባሉ አካባቢዎች የሚኖሩ ሰዎችን ለማግኘት ከፍተኛ ጥረት አድርገዋል።

ስቱዋርት ኬልቲ እና ዊልያም ቶሪንግተን እንዲህ ዓይነቱን ቁርጠኝነት አሳይተዋል። በ1933 አሊስ ስፕሪንግስ በሚባለው በአህጉሪቱ እምብርት ላይ የሚገኝ ከተማ ለመስበክ ሲሉ በአሸዋ ክምር የተሞላውን የሲምፕሰን በረሃ አቋርጠዋል። ትንሿ መኪናቸው በመበላሸቷ ምክንያት ትተዋት ለመሄድ በተገደዱ ጊዜ፣ በእንጨት በተሠራ እግር የሚጠቀመው ወንድም ኬልቲ በግመል ጉዞውን ቀጥሏል! እነዚህ አቅኚዎች ርቆ በሚገኘው ዊልያም ክሪክ የተባለ የባቡር ፌርማታ አካባቢ የአንድ ሆቴል ሥራ አስኪያጅ በማግኘታቸው ጥረታቸው ተክሷል። ቻርልስ በርንሃርት የተባለው ይህ የሆቴል ሥራ አስኪያጅ ከጊዜ በኋላ እውነትን ተቀበለ፤ ከዚያም ሆቴሉን በመሸጥ በአውስትራሊያ በጣም ርቀው በሚገኙ ጠፍ የሆኑ አካባቢዎች ለ15 ዓመታት ያህል ብቻውን በአቅኚነት አገልግሏል።

አርተር ዊሊስ ርቀው ወደሚገኙት የአውስትራሊያ አካባቢዎች ሄዶ ለመስበክ ሲዘጋጅ።—ፐርዝ፣ ዌስተርን አውስትራሊያ፣ 1936

እነዚህ ቀደምት አቅኚዎች የገጠሟቸውን በርካታ ችግሮች ለመቋቋም ድፍረትና ጽናት ጠይቆባቸው እንደነበር አያጠራጥርም። በመግቢያው ላይ የተጠቀሱት አርተር ዊሊስና ቢል ኒውላንድስ፣ በአውስትራሊያ በሚገኙ ራቅ ያሉ ቦታዎች ባደረጉት የስብከት ዘመቻ ላይ በአንድ ወቅት 32 ኪሎ ሜትር ለመጓዝ ሁለት ሳምንት ወስዶባቸዋል፤ ይህ የሆነው ከባድ ዝናብ ጥሎ በረሃው በጭቃ ተሸፍኖ ስለነበር ነው። አንዳንድ ጊዜ ደግሞ ትላልቅ የአሸዋ ክምሮችን ለማለፍ በጠራራው ፀሐይ ላብ በላብ ሆነው መኪናቸውን ይገፉ ነበር፤ በተጨማሪም ድንጋያማ ሸለቆዎችንና አሸዋማ ደረቅ ወንዞችን አቋርጠው ተጉዘዋል። መኪናቸው በተደጋጋሚ ይበላሽባቸው ነበር፤ እንዲህ ዓይነት ሁኔታ ሲያጋጥማቸው ለቀናት በእግራቸው ወይም በብስክሌት ተጉዘው ቅርብ ወደሆነው ከተማ ይሄዱና የመኪና መለዋወጫ እስኪመጣላቸው ለሳምንታት ይጠብቃሉ። እንዲህ ያሉ አስቸጋሪ ሁኔታዎች ቢያጋጥሟቸውም አዎንታዊ አመለካከት ነበራቸው። ከጊዜ በኋላ አርተር ዊሊስ በአንድ ወቅት ወርቃማው ዘመን (እንግሊዝኛ) በተባለው መጽሔት ላይ የወጣን ሐሳብ በመጥቀስ “ለይሖዋ ምሥክሮች በጣም አስቸጋሪ ወይም በጣም ረጅም የሆነ መንገድ የለም” ብሏል።

ለረጅም ጊዜ በአቅኚነት ያገለገለው ቻርልስ ሃሪስ፣ ራቅ ወዳሉት ቦታዎች ሲጓዝ ብቻውን መሆኑና ብዙ ውጣ ውረድ ማሳለፉ ከይሖዋ ጋር ይበልጥ እንዲቀራረብ እንደረዳው ተናግሯል። አክሎም እንዲህ ብሏል፦ “ጓዘ ቀላል መሆን የተሻለ ነው። ኢየሱስ አስፈላጊ በሆነበት ጊዜ ሜዳ ላይ ለማደር ፈቃደኛ ከሆነ እኛም አስገዳጅ ሁኔታ በሚያጋጥመን ጊዜ በደስታ እንዲህ ልናደርግ ይገባል።” ደግሞም ብዙዎቹ አቅኚዎች ይህን አድርገዋል። እነዚህ አቅኚዎች ያደረጉት ትጋት የተሞላበት ጥረት፣ ምሥራቹ በዚህች አህጉር ውስጥ ከጫፍ እስከ ጫፍ እንዲሰበክ አስተዋጽኦ አበርክቷል፤ ይህም ብዙ ሰዎች ከአምላክ መንግሥት ጎን እንዲቆሙ አስችሏል።

^ አን.4 የመጽሐፍ ቅዱስ ተማሪዎች፣ የይሖዋ ምሥክሮች በሚለው ስም መጠራት የጀመሩት በ1931 ነው።—ኢሳ. 43:10