ጥላቻ ለአንዴና ለመጨረሻ ጊዜ ይወገዳል!
ጥላቻን ከልባችን ነቅለን ብናወጣም እንኳ የሌሎችን ድርጊትና አመለካከት መቆጣጠር አንችልም። ንጹሓን ሰዎች አሁንም የጥላቻ ሰለባ እየሆኑ ነው። ታዲያ ጥላቻን ለአንዴና ለመጨረሻ ጊዜ ማስወገድ የሚችለው ማን ነው?
በዛሬው ጊዜ የምናየውን ጥላቻ ጠራርጎ ማስወገድ የሚችለው ይሖዋ አምላክ ብቻ ነው። አምላክ እንዲህ እንደሚያደርግ በመጽሐፍ ቅዱስ ላይ ቃል ገብቷል።—ምሳሌ 20:22
አምላክ የጥላቻን መንስኤዎች ያስወግዳል
-
1. ሰይጣን ዲያብሎስ። በዛሬው ጊዜ ለምናየው ጥላቻ ዋነኛው መንስኤ ዓመፀኛ መልአክ የሆነው ሰይጣን ነው። አምላክ ሰይጣንንም ሆነ የእሱን የጥላቻ ጎዳና የሚከተሉትን በሙሉ ያጠፋቸዋል።—መዝሙር 37:38፤ ሮም 16:20
-
2. በጥላቻ የተሞላው የሰይጣን ዓለም። አምላክ ጥላቻን የሚቀሰቅሱ ብልሹ ፖለቲከኞችንና የሃይማኖት መሪዎችን ጨምሮ የዚህን ዓለም ክፉ ተቋማት በሙሉ ያጠፋል። በተጨማሪም በሙስና እና በስግብግብነት የተጠላለፈውን የንግድ ሥርዓት ሙሉ በሙሉ ያጠፋል።—2 ጴጥሮስ 3:13
-
3. የሰው ልጆች አለፍጽምና። መጽሐፍ ቅዱስ ሁሉም ሰዎች አለፍጽምናን እንደወረሱ ይናገራል፤ በመሆኑም አስተሳሰባቸው፣ ስሜታቸውና ድርጊታቸው ወደ መጥፎ ያዘነበለ ነው። (ሮም 5:12) ከእነዚህ የኃጢአት ዝንባሌዎች አንዱ ጥላቻ ነው። አምላክ የሰው ልጆች የአለፍጽምና ዝንባሌያቸውን በሙሉ እንዲያሸንፉ በመርዳት ጥላቻን ሙሉ በሙሉ ያስወግዳል።—ኢሳይያስ 54:13
መጽሐፍ ቅዱስ ጥላቻ የሌለበት ዓለም እንደሚመጣ ተስፋ ይሰጣል
-
1. ማንም ሰው የፍትሕ መጓደል አያጋጥመውም። ዓለም የሚተዳደረው በአምላክ መንግሥት ይሆናል፤ የአምላክ መንግሥት በሰማይ ሆኖ የሚገዛ ፍትሐዊና ዘላለማዊ መንግሥት ነው። (ዳንኤል 2:44) አድልዎና አለመቻቻል ይወገዳል። አምላክ ሰዎች በአሁኑ ጊዜ የሚያጋጥማቸውን የፍትሕ መጓደል በሙሉ ያስተካክላል።—ሉቃስ 18:7
-
2. ሁሉም ሰው በሰላም ይኖራል። በዓመፅ ወይም በጦርነት የተነሳ መከራ የሚደርስበት ሰው አይኖርም። (መዝሙር 46:9) ምድር ሰላም ወዳድ በሆኑ ሰዎች ብቻ የተሞላች ሰላማዊ ቦታ ትሆናለች።—መዝሙር 72:7
-
3. ሁሉም ሰው ለዘላለም ተመችቶት ይኖራል። በምድር ላይ የሚኖሩ ሰዎች በሙሉ ለሌሎች እውነተኛ ፍቅር ያሳያሉ። (ማቴዎስ 22:39) ጭንቀት ሙሉ በሙሉ ይወገዳል፤ መጥፎ ሐሳብና ትዝታ እንኳ ከአእምሯችን ይጠፋል። (ኢሳይያስ 65:17) ያን ጊዜ፣ ከጥላቻ የጸዱ የሰው ልጆች “በብዙ ሰላም . . . እጅግ ደስ ይላቸዋል።”—መዝሙር 37:11
እንዲህ ባለ ዓለም ውስጥ መኖር ትፈልጋለህ? በአሁኑ ጊዜም ጭምር ብዙ ሰዎች የመጽሐፍ ቅዱስን ትምህርቶች በሥራ ላይ በማዋል ጥላቻን ማሸነፍ ችለዋል። (መዝሙር 37:8) በዓለም ዙሪያ ያሉ በሚሊዮኖች የሚቆጠሩ የይሖዋ ምሥክሮች ይህን አድርገዋል። የተለያየ ዘርና ባሕል ቢኖራቸውም እንደ አንድ ቤተሰብ ፍቅርና አንድነት አላቸው።—ኢሳይያስ 2:2-4
የይሖዋ ምሥክሮች አድልዎንና የፍትሕ መጓደልን ለመቋቋም የረዳቸው ምን እንደሆነ ሊያስተምሩህ ፈቃደኞች ናቸው። የምትማረው ነገር ጥላቻን ደረጃ በደረጃ በፍቅር ለመተካት ይረዳሃል። አመስጋኝ ያልሆኑና በጥላቻ የተሞሉ ሰዎችን ጨምሮ ሁሉንም ሰዎች በደግነት መያዝ የሚቻለው እንዴት እንደሆነ ትማራለህ። ይህም ይበልጥ ደስተኛ እንድትሆን ያደርግሃል፤ ከሌሎች ጋር ያለህ ግንኙነትም ይሻሻላል። ከሁሉ በላይ ደግሞ፣ ጥላቻ ለዘላለም በሚወገድበት የአምላክ መንግሥት አገዛዝ ሥር ለመኖር ምን ማድረግ እንደሚጠበቅብህ ትማራለህ።—መዝሙር 37:29