ዘፀአት 10:1-29

  • ስምንተኛው መቅሰፍት፦ አንበጦች (1-20)

  • ዘጠነኛው መቅሰፍት፦ ድቅድቅ ጨለማ (21-29)

10  ከዚያም ይሖዋ ሙሴን እንዲህ አለው፦ “ወደ ፈርዖን ግባ፤ ምክንያቱም የእሱም ሆነ የአገልጋዮቹ ልብ እንዲደነድን እፈቅዳለሁ፤+ ይህን የማደርገውም እነዚህን ተአምራዊ ምልክቶቼን በፊቱ እንዳሳይ+ 2  እንዲሁም ግብፅን እንዴት አድርጌ እንደቀጣሁና በመካከላቸው ተአምራዊ ምልክቶቼን እንዴት እንዳሳየሁ ለልጆችህና ለልጅ ልጆችህ እንድታውጅ ነው፤+ እናንተም እኔ ይሖዋ እንደሆንኩ በእርግጥ ታውቃላችሁ።” 3  በመሆኑም ሙሴና አሮን ወደ ፈርዖን ገብተው እንዲህ አሉት፦ “የዕብራውያን አምላክ ይሖዋ እንዲህ ይላል፦ ‘ለመሆኑ ለእኔ ለመገዛት ፈቃደኛ የማትሆነው እስከ መቼ ነው?+ እንዲያገለግለኝ ሕዝቤን ልቀቅ። 4  አሁንም ሕዝቤን ለመልቀቅ ፈቃደኛ የማትሆን ከሆነ ግን በነገው ዕለት በግዛትህ ላይ አንበጦችን አመጣለሁ። 5  አንበጦቹም ምድሪቱን ይሸፍናሉ፤ መሬቱንም ማየት አይቻልም። እነሱም ከበረዶው ያመለጠውንና የቀረላችሁን ነገር ሁሉ ሙልጭ አድርገው ይበሉታል፤ በመስክ ላይ እየበቀሉ ያሉትን ዛፎቻችሁን በሙሉ ይበሏቸዋል።+ 6  አንበጦቹ አባቶችህና አያቶችህ በዚህች ምድር ላይ መኖር ከጀመሩበት ጊዜ አንስቶ እስካሁን ድረስ አይተውት በማያውቁት ሁኔታ+ ቤቶችህን፣ የአገልጋዮችህን ቤቶች ሁሉና የግብፅን ቤቶች ሁሉ ይሞላሉ።’” እሱም ይህን ከተናገረ በኋላ ፊቱን አዙሮ ከፈርዖን ፊት ወጥቶ ሄደ። 7  ከዚያም የፈርዖን አገልጋዮች ፈርዖንን እንዲህ አሉት፦ “ይህ ሰው ወጥመድ የሚሆንብን እስከ መቼ ነው? አምላካቸውን ይሖዋን እንዲያገለግሉ ሰዎቹን ልቀቃቸው። ግብፅ እየጠፋች እንደሆነ እስካሁን አልተገነዘብክም?” 8  በመሆኑም ሙሴና አሮን ወደ ፈርዖን ተመልሰው እንዲመጡ ተደረገ፤ እሱም “ሂዱ፤ አምላካችሁን ይሖዋን አገልግሉ። ይሁንና የሚሄዱት እነማን ናቸው?” አላቸው። 9  በዚህ ጊዜ ሙሴ “ለይሖዋ የምናከብረው በዓል+ ስላለን ወጣቶቻችንን፣ አዛውንቶቻችንን፣ ወንዶችና ሴቶች ልጆቻችንን እንዲሁም በጎቻችንንና ከብቶቻችንን ይዘን እንሄዳለን” አለ።+ 10  እሱም እንዲህ አላቸው፦ “እናንተንና ልጆቻችሁን ከለቀኩማ በእርግጥም ይሖዋ ከእናንተ ጋር ነው!+ መቼም የሆነ ተንኮል እንዳሰባችሁ ግልጽ ነው። 11  ይሄማ አይሆንም! ወንዶቹ ብቻ ሄደው ይሖዋን ያገልግሉ፤ ምክንያቱም የጠየቃችሁት ይህንኑ ነው።” ከዚያም ከፈርዖን ፊት እንዲወጡ ተደረገ። 12  በዚህ ጊዜ ይሖዋ ሙሴን እንዲህ አለው፦ “አንበጦች መጥተው የግብፅን ምድር እንዲወሩና ከበረዶ የተረፈውን በምድሩ ላይ ያለውን ማንኛውንም ተክል ጠራርገው እንዲበሉ በግብፅ ምድር ላይ እጅህን ዘርጋ።” 13  ሙሴም ወዲያው በግብፅ ምድር ላይ በትሩን ሰነዘረ፤ ይሖዋም በዚያን ዕለት ቀኑንና ሌሊቱን ሙሉ በምድሩ ላይ የምሥራቅ ነፋስ እንዲነፍስ አደረገ። ሲነጋም የምሥራቁ ነፋስ አንበጦችን አመጣ። 14  አንበጦቹም በመላው የግብፅ ምድር ላይ መውጣትና በግብፅ ግዛት ሁሉ ላይ መስፈር ጀመሩ።+ ሁኔታው እጅግ አስከፊ ነበር፤+ ከዚህ በፊት ያን ያህል ብዛት ያለው አንበጣ ታይቶ አያውቅም፤ ዳግመኛም ያን ያህል ብዛት ያለው አንበጣ ፈጽሞ አይከሰትም። 15  አንበጦቹም መላውን ምድር ሸፈኑት፤ ምድሪቱም በእነሱ የተነሳ ጨለመች፤ እነሱም ከበረዶው የተረፈውን በምድሩ ላይ ያለውን ተክል ሁሉ እንዲሁም በዛፎች ላይ ያለውን ፍሬ ሁሉ ጠራርገው በሉት፤ በመላው የግብፅ ምድር በዛፎችም ሆነ በመስክ ባሉ ተክሎች ላይ አንድም ለምለም ቅጠል አልተረፈም። 16  በመሆኑም ፈርዖን ሙሴንና አሮንን በአስቸኳይ ጠርቶ እንዲህ አላቸው፦ “በአምላካችሁ በይሖዋም ሆነ በእናንተ ላይ ኃጢአት ሠርቻለሁ። 17  ስለሆነም አሁን እባካችሁ ይህን ኃጢአቴን ብቻ ይቅር በሉኝ፤ ይህን ገዳይ መቅሰፍት ከእኔ ላይ እንዲያስወግድልኝም አምላካችሁን ይሖዋን ለምኑልኝ።” 18  እሱም* ከፈርዖን ፊት ወጣ፤ ይሖዋንም ለመነ።+ 19  ከዚያም ይሖዋ ነፋሱ እንዲቀየር አደረገ፤ ነፋሱም ኃይለኛ የምዕራብ ነፋስ ሆነ፤ ነፋሱም አንበጦቹን ወስዶ ቀይ ባሕር ውስጥ ከተታቸው። በመላው የግብፅ ግዛት አንድም አንበጣ አልቀረም። 20  ሆኖም ይሖዋ የፈርዖን ልብ እንዲደነድን ፈቀደ፤+ እሱም እስራኤላውያንን አለቀቀም። 21  ከዚያም ይሖዋ ሙሴን “በግብፅ ምድር ላይ ጨለማ ይኸውም የሚዳሰስ የሚመስል ድቅድቅ ጨለማ እንዲከሰት እጅህን ወደ ሰማይ ዘርጋ” አለው። 22  ሙሴም ወዲያውኑ እጁን ወደ ሰማይ ዘረጋ፤ በመላው የግብፅ ምድር ላይም ለሦስት ቀን ያህል ድቅድቅ ጨለማ ተከሰተ።+ 23  እነሱም እርስ በርስ አይተያዩም ነበር፤ ለሦስት ቀን ማናቸውም ካሉበት ቦታ ንቅንቅ ማለት አልቻሉም፤ ሆኖም እስራኤላውያን ሁሉ በሚኖሩበት ስፍራ ብርሃን ነበር።+ 24  ከዚያም ፈርዖን ሙሴን ጠርቶ እንዲህ አለው፦ “ሂዱ፣ ይሖዋን አገልግሉ።+ በጎቻችሁና ከብቶቻችሁ ብቻ እዚሁ ይቀራሉ። ልጆቻችሁም አብረዋችሁ መሄድ ይችላሉ።” 25  ሙሴ ግን እንዲህ አለው፦ “እንግዲያውስ ለመሥዋዕቶችና ለሚቃጠሉ መባዎች የሚሆኑትን እንስሳት አንተው ራስህ ትሰጠንና ለአምላካችን ለይሖዋ መሥዋዕት አድርገን እናቀርባቸዋለን።+ 26  ከብቶቻችንም አብረውን መሄድ አለባቸው። አምላካችንን ይሖዋን ስናመልክ ከእነሱ መካከል አንዳንዶቹን መሥዋዕት አድርገን ስለምናቀርብ አንድም እንስሳ* እዚህ መቅረት የለበትም፤ ደግሞም እኛ ራሳችን ለይሖዋ አምልኮ ምን መሥዋዕት ማቅረብ እንዳለብን የምናውቀው እዚያ ስንደርስ ነው።” 27  ይሖዋም የፈርዖን ልብ እንዲደነድን ፈቀደ፤ እሱም ሊለቃቸው ፈቃደኛ አልሆነም።+ 28  ስለሆነም ፈርዖን “ከፊቴ ጥፋ! ዳግመኛ ፊቴን ለማየት እንዳትሞክር፤ ፊቴን የምታይበት ቀን መሞቻህ እንደሚሆን እወቅ” አለው። 29  በዚህ ጊዜ ሙሴ “እሺ፣ እንዳልከው ይሁን፤ ዳግመኛ ፊትህን አላይም” አለው።

የግርጌ ማስታወሻዎች

ሙሴን የሚያመለክት ይመስላል።
ቃል በቃል “ሰኮና።”