ለዕብራውያን የተጻፈ ደብዳቤ 7:1-28

  • መልከጼዴቅ፣ ልዩ የሆነ ንጉሥና ካህን (1-10)

  • የክርስቶስ ክህነት ያለው ብልጫ (11-28)

    • ክርስቶስ ሙሉ በሙሉ ሊያድን ይችላል (25)

7  አብርሃም ነገሥታትን ድል አድርጎ ሲመለስ የሳሌም ንጉሥና የልዑሉ አምላክ ካህን የሆነው ይህ መልከጼዴቅ አግኝቶት ባረከው፤+ 2  አብርሃም ደግሞ ከሁሉ ነገር አንድ አሥረኛ ሰጠው።* በመጀመሪያ ስሙ “የጽድቅ ንጉሥ” ማለት ነው፤ ደግሞም የሳሌም ንጉሥ ማለትም “የሰላም ንጉሥ” ነው። 3  አባትና እናትም ሆነ የዘር ሐረግ እንዲሁም ለዘመኑ መጀመሪያ፣ ለሕይወቱም መጨረሻ የለውም፤ ከዚህ ይልቅ የአምላክን ልጅ እንዲመስል በመደረጉ ለዘላለም ካህን ሆኖ ይኖራል።+ 4  እንግዲህ የቤተሰብ ራስ* የሆነው አብርሃም ምርጥ ከሆነው ምርኮ ላይ አንድ አሥረኛውን የሰጠው+ ይህ ሰው ምን ያህል ታላቅ እንደነበረ ተመልከቱ። 5  እርግጥ የክህነት ኃላፊነት የሚቀበሉ ከሌዊ ልጆች ወገን የሆኑት ሰዎች+ ምንም እንኳ ወንድሞቻቸው የአብርሃም ዘሮች ቢሆኑም ከሕዝቡ ማለትም ከገዛ ወንድሞቻቸው አሥራት እንዲሰበስቡ ሕጉ ያዛል።+ 6  ሆኖም ከእነሱ የትውልድ ሐረግ ያልመጣው ይህ ሰው ከአብርሃም አሥራት የተቀበለ ሲሆን የተስፋ ቃል የተሰጠውን ሰው ባርኮታል።+ 7  እንግዲህ አነስተኛ የሆነው ከእሱ በሚበልጠው እንደተባረከ ምንም ጥርጥር የለውም። 8  በአንድ በኩል አሥራት የሚቀበሉት ሟች የሆኑ ሰዎች ሲሆኑ በሌላ በኩል ግን አሥራት የሚቀበለው ሕያው ሆኖ እንደሚኖር የተመሠከረለት ሰው ነው።+ 9  እንግዲህ አሥራት የሚቀበለው ሌዊ እንኳ በአብርሃም በኩል አሥራት ከፍሏል ማለት ይቻላል፤ 10  መልከጼዴቅ አብርሃምን ባገኘው ጊዜ ሌዊ ገና በአባቱ በአብርሃም አብራክ ውስጥ* ነበርና።+ 11  እንግዲህ ፍጽምና ሊገኝ የሚችለው በሌዊ ክህነት አማካኝነት ቢሆን ኖሮ+ (ክህነቱ ለሕዝቡ የተሰጠው ሕግ አንዱ ገጽታ ስለሆነ)፣ እንደ አሮን ሥርዓት ሳይሆን እንደ መልከጼዴቅ ሥርዓት+ ያለ ተብሎ የተነገረለት ሌላ ካህን መነሳቱ ምን ያስፈልግ ነበር? 12  ክህነቱ ስለሚለወጥ ሕጉም የግድ መለወጥ ያስፈልገዋልና።+ 13  ይህ ሁሉ ነገር የተነገረለት ሰው ከሌላ ነገድ የመጣ ነውና፤ ከዚህ ነገድ ማንም ወደ መሠዊያው ቀርቦ ያገለገለ የለም።+ 14  ጌታችን ከይሁዳ ነገድ እንደወጣ የታወቀ ነውና፤+ ይሁንና ሙሴ ከዚህ ነገድ ካህናት እንደሚገኙ የተናገረው ነገር የለም። 15  ደግሞም እንደ መልከጼዴቅ ያለ ሌላ ካህን+ ሲነሳ ይህ ጉዳይ ይበልጥ ግልጽ ይሆናል፤+ 16  እሱ ካህን የሆነው በሥጋዊ ትውልድ ላይ በተመካውና ሕጉ በያዘው መሥፈርት ሳይሆን የማይጠፋ ሕይወት+ እንዲኖረው ባስቻለው ኃይል ነው። 17  “እንደ መልከጼዴቅ፣ አንተ ለዘላለም ካህን ነህ” ተብሎ ተመሥክሮለታልና።+ 18  እንግዲህ የቀድሞው ትእዛዝ ደካማና ፍሬ ቢስ በመሆኑ ተሽሯል።+ 19  ሕጉ የትኛውንም ነገር ወደ ፍጽምና አላደረሰምና፤+ ወደ አምላክ የምንቀርብበት የተሻለ ተስፋ+ መሰጠቱ ግን ይህን ማድረግ ችሏል።+ 20  በተጨማሪም ይህ ያለመሐላ እንዳልሆነ ሁሉ 21  (ያለመሐላ ካህናት የሆኑ ሰዎች አሉና፤ እሱ ግን በመሐላ ካህን ሆኗል፤ ይህም የሆነው “ይሖዋ* ‘አንተ ለዘላለም ካህን ነህ’ ብሎ ምሏል፤ ደግሞም ሐሳቡን አይለውጥም”* በማለት ስለ እሱ የተናገረው አምላክ በማለው መሐላ መሠረት ነው፤)+ 22  እንደዚሁም ኢየሱስ ለተሻለ ቃል ኪዳን ዋስትና* ሆኗል።+ 23  ከዚህም በተጨማሪ ካህናት አገልግሎታቸውን እንዳይቀጥሉ ሞት ስለሚያግዳቸው አንዱ ሌላውን እየተካ እንዲያገለግል ብዙዎች ካህናት መሆን ነበረባቸው፤+ 24  እሱ ግን ለዘላለም+ ሕያው ሆኖ ስለሚኖር ክህነቱ ተተኪ የለውም። 25  ስለሆነም ለእነሱ ለመማለድ ሁልጊዜ ሕያው ሆኖ ስለሚኖር በእሱ አማካኝነት ወደ አምላክ የሚቀርቡትን ፈጽሞ ሊያድናቸውም ይችላል።+ 26  እኛ የሚያስፈልገን ታማኝ፣ ቅን የሆነ፣ ያልረከሰ፣+ ከኃጢአተኞች የተለየና ከሰማያት በላይ ከፍ ያለ እንደዚህ ያለ ሊቀ ካህናት ነው።+ 27  እነዚያ ሊቃነ ካህናት ያደርጉ እንደነበረው፣ በመጀመሪያ ለራሱ ኃጢአት ከዚያም ለሕዝቡ ኃጢአት+ በየዕለቱ መሥዋዕት ማቅረብ አያስፈልገውም፤+ ምክንያቱም ራሱን መሥዋዕት አድርጎ ባቀረበ ጊዜ ይህን ለአንዴና ለመጨረሻ ጊዜ ፈጽሞታል።+ 28  ሕጉ ድክመት ያለባቸውን ሰዎች ሊቃነ ካህናት አድርጎ ይሾማልና፤+ ከሕጉ በኋላ የመጣው የመሐላ ቃል+ ግን ለዘላለም ፍጹም የተደረገውን ልጅ+ ይሾማል።

የግርጌ ማስታወሻዎች

ቃል በቃል “አካፈለው።”
ወይም “ፓትሪያርክ።”
ወይም “ወደፊት የሚወለድ የአባቱ የአብርሃም ዘር።”
ከተጨማሪው መረጃ ላይ ሀ5ን ተመልከት።
ወይም “አይጸጸትም።”
ወይም “እንደ መያዣ የተሰጠ።”