ለዕብራውያን የተጻፈ ደብዳቤ 3:1-19

  • ኢየሱስ ከሙሴ ይበልጣል (1-6)

    • ‘ሁሉን ነገር የሠራው አምላክ ነው’ (4)

  • ‘እምነት የለሽ ልብ በውስጣችሁ እንዳያቆጠቁጥ ተጠንቀቁ’ (7-19)

    • “ዛሬ ድምፁን የምትሰሙ ከሆነ” (7, 15)

3  ስለሆነም የሰማያዊው ጥሪ ተካፋዮች+ የሆናችሁ ቅዱሳን ወንድሞች፣ በእሱ እንደምናምን በይፋ የምንናገርለትን፣ ሐዋርያና ሊቀ ካህናት የሆነውን ኢየሱስን አስቡ።+ 2  ሙሴ በመላው የአምላክ ቤት ላይ ታማኝ እንደነበረ ሁሉ+ እሱም ለሾመው ታማኝ ነበር።+ 3  ቤቱን የሠራው፣ ከቤቱ የበለጠ ክብር ስላለው እሱ* ከሙሴ የበለጠ ክብር ይገባዋል።+ 4  እያንዳንዱ ቤት ሠሪ እንዳለው የታወቀ ነው፤ ሁሉን ነገር የሠራው ግን አምላክ ነው። 5  ሙሴም በመላው የአምላክ ቤት ላይ ታማኝ አገልጋይ ነበር። አገልግሎቱም ከጊዜ በኋላ ለሚነገሩ ነገሮች ምሥክር ነው። 6  ክርስቶስ ግን በአምላክ ቤት ላይ የተሾመ ታማኝ ልጅ ነበር።+ እኛም አፋችንን ሞልተን የመናገር ነፃነታችንንና የምንደሰትበትን ተስፋችንን እስከ መጨረሻው አጥብቀን ከያዝን የአምላክ ቤት ነን።+ 7  ስለዚህ መንፈስ ቅዱስ እንዲህ ይላል፦+ “ዛሬ ድምፁን የምትሰሙ ከሆነ 8  በምድረ በዳ እጅግ የሚያስቆጣ ድርጊት በተፈጸመበት በፈተና ቀን እንደሆነው ልባችሁን አታደንድኑ፤+ 9  በዚያ፣ አባቶቻችሁ ያደረግኩትን ሁሉ ለ40 ዓመት ቢያዩም እኔን በመፈተን ተገዳደሩኝ።+ 10  በዚህም ምክንያት በዚያ ትውልድ በጣም ተንገሸገሽኩ፤ እንዲህም አልኩ፦ ‘ሁልጊዜ ልባቸው ይስታል፤ መንገዴንም ሊያውቁ አልቻሉም።’ 11  በመሆኑም ‘ወደ እረፍቴ አይገቡም’ ብዬ በቁጣዬ ማልኩ።”+ 12  ወንድሞች፣ ሕያው ከሆነው አምላክ በመራቅ እምነት የለሽ የሆነ ክፉ ልብ ከእናንተ መካከል በማናችሁም ውስጥ እንዳያቆጠቁጥ ተጠንቀቁ፤+ 13  ከዚህ ይልቅ ከእናንተ መካከል አንዳችሁም ኃጢአት ባለው የማታለል ኃይል እንዳትደነድኑ “ዛሬ”+ ተብሎ የሚጠራ ጊዜ እስካለ ድረስ በየዕለቱ እርስ በርሳችሁ ተበረታቱ። 14  የክርስቶስ ተካፋዮች የምንሆነው* በመጀመሪያ የነበረንን ትምክህት እስከ መጨረሻው አጽንተን ከያዝን ብቻ ነውና።+ 15  ይህም “ዛሬ ድምፁን የምትሰሙ ከሆነ እጅግ የሚያስቆጣ ድርጊት በተፈጸመበት ጊዜ እንደሆነው ልባችሁን አታደንድኑ” እንደተባለው ነው።+ 16  ድምፁን ቢሰሙም እንኳ እጅግ ያስቆጡት እነማን ነበሩ? ይህን ያደረጉት ሙሴ እየመራቸው ከግብፅ የወጡት ሁሉ አይደሉም?+ 17  ከዚህም ሌላ ለ40 ዓመት አምላክ በእነሱ እንዲንገሸገሽ ያደረጉት እነማን ናቸው?+ እነዚያ ኃጢአት የሠሩትና ሬሳቸው በምድረ በዳ ወድቆ የቀረው አይደሉም?+ 18  ደግሞስ ወደ እረፍቴ አይገቡም ብሎ የማለው ስለ እነማን ነው? እነዚያን ያልታዘዙትን በተመለከተ አይደለም? 19  ስለዚህ ሊገቡ ያልቻሉት እምነት በማጣታቸው የተነሳ እንደሆነ እንረዳለን።+

የግርጌ ማስታወሻዎች

ኢየሱስን ያመለክታል።
ወይም “ከክርስቶስ ጋር አብረን የምንካፈለው።”