መዝሙር 84:1-12

  • የአምላክን ታላቅ የማደሪያ ድንኳን መናፈቅ

    • አንድ ሌዋዊ እንደ ወፍ ለመሆን ተመኘ (3)

    • “በቅጥር ግቢዎችህ አንዲት ቀን መዋል” (10)

    • “አምላክ ፀሐይና ጋሻ ነው” (11)

ለሙዚቀኞች ቡድን መሪ፤ በጊቲት።* የቆሬ ልጆች+ መዝሙር። ማህሌት። 84  የሠራዊት ጌታ ይሖዋ ሆይ፣ታላቁ የማደሪያ ድንኳንህ ምንኛ ያማረ* ነው!+  2  ሁለንተናዬ* የይሖዋን ቅጥር ግቢዎችእጅግ ናፈቀ፤አዎ፣ በጣም ከመጓጓቴ የተነሳ ዛልኩ።+ ልቤም ሆነ ሥጋዬ ሕያው ለሆነው አምላክ እልል ይላል።  3  ንጉሤና አምላኬ የሆንከው የሠራዊት ጌታ ይሖዋ፣ታላቁ መሠዊያህ ባለበት አቅራቢያ፣ወፍ እንኳ በዚያ ቤት ታገኛለች፤ወንጭፊትም ጫጩቶቿን የምታሳድግበት ጎጆለራሷ ትሠራለች።  4  በቤትህ የሚኖሩ ደስተኞች ናቸው!+ እነሱ ሁልጊዜ ያወድሱሃል።+ (ሴላ)  5  አንተን የብርታታቸው ምንጭ ያደረጉ፣ወደ ቤትህ የሚወስዱትን መንገዶች የሚናፍቅ ልብ ያላቸው ሰዎች ደስተኞች ናቸው።+  6  በባካ* ሸለቆ* በሚያልፉበት ጊዜ፣ስፍራውን ምንጮች የሚፈልቁበት ቦታ ያደርጉታል፤የመጀመሪያውም ዝናብ በረከት ያለብሰዋል።*  7  በብርታት ላይ ብርታት እያገኙ ይሄዳሉ፤+እያንዳንዳቸውም በጽዮን፣ በአምላክ ፊት ይቀርባሉ።  8  የሠራዊት አምላክ ይሖዋ ሆይ፣ ጸሎቴን ስማ፤የያዕቆብ አምላክ ሆይ፣ አዳምጠኝ። (ሴላ)  9  ጋሻችንና+ አምላካችን ሆይ፣ ተመልከት፤*የተቀባውን የአገልጋይህን ፊት እይ።+ 10  በሌላ ቦታ አንድ ሺህ ቀን ከመኖር በቅጥር ግቢዎችህ አንዲት ቀን መዋል ይሻላልና!+ በክፉዎች ድንኳን ከመኖር፣በአምላኬ ቤት ደጃፍ ላይ መቆም እመርጣለሁ። 11  ይሖዋ አምላክ ፀሐይና+ ጋሻ+ ነውና፤እሱ ሞገስና ክብር ይሰጣል። ንጹሕ አቋም ይዘው የሚመላለሱትንይሖዋ አንዳች መልካም ነገር አይነፍጋቸውም።+ 12  የሠራዊት ጌታ ይሖዋ ሆይ፣በአንተ የሚታመን ሰው ደስተኛ ነው።+

የግርጌ ማስታወሻዎች

ወይም “ተወዳጅ።”
ወይም “ነፍሴ።”
“ባካ” የሚለው ስም የተገኘው “ለቅሶ” የሚል ትርጉም ካለው የዕብራይስጥ ቃል ነው። የተክሉ ዓይነት በትክክል አይታወቅም።
“አስተማሪውም ራሱን በረከት ያጎናጽፋል” ማለትም ሊሆን ይችላል።
ወይም “የባካ ቁጥቋጦዎች በሚበቅሉበት ሸለቆ።”
“አምላክ ሆይ፣ ጋሻችንን ተመልከት” ማለትም ሊሆን ይችላል።