መዝሙር 80:1-19
ለሙዚቀኞች ቡድን መሪ፤ “በአበቦች” የሚዘመር። ማስታወሻ። የአሳፍ+ መዝሙር። ማህሌት።
80 ዮሴፍን እንደ መንጋ የምትመራየእስራኤል እረኛ ሆይ፣+ አዳምጥ።
ከኪሩቤል በላይ* በዙፋን የምትቀመጥ ሆይ፣+ብርሃን አብራ።*
2 በኤፍሬም፣ በቢንያምና በምናሴ ፊትኃያልነትህን አሳይ፤+መጥተህም አድነን።+
3 አምላክ ሆይ፣ ወደ ቀድሞው ሁኔታችን መልሰን፤+እንድንም ዘንድ ፊትህን በእኛ ላይ አብራ።+
4 የሠራዊት አምላክ ይሖዋ ሆይ፣ ሕዝቦችህ የሚያቀርቡትን ጸሎት የምትጠላው* እስከ መቼ ነው?+
5 እንባን እንደ ምግብ ትመግባቸዋለህ፤ደግሞም እንባ ትግታቸዋለህ።
6 ለጎረቤቶቻችን የጠብ ምክንያት አደረግከን፤ጠላቶቻችን እንዳሻቸው ያላግጡብናል።+
7 የሠራዊት አምላክ ሆይ፣ ወደ ቀድሞው ሁኔታችን መልሰን፤እንድንም ዘንድ ፊትህን በእኛ ላይ አብራ።+
8 የወይን ተክል+ ከግብፅ እንድትወጣ አደረግክ።
ብሔራትን አባረህ እሷን ተከልክ።+
9 መሬቱን መነጠርክላት፤እሷም ሥር ሰዳ በምድሪቱ ላይ ተንሰራፋች።+
10 ተራሮች በጥላዋ፣የአምላክ አርዘ ሊባኖሶችም በቅርንጫፎቿ ተሸፈኑ።
11 ቅርንጫፎቿ እስከ ባሕሩ፣ቀንበጦቿም እስከ ወንዙ* ድረስ ተዘረጉ።+
12 በዚያ የሚያልፉ ሁሉ ፍሬዋን እንዲቀጥፉ፣+የወይን እርሻዋን የድንጋይ ቅጥሮች ያፈረስከው ለምንድን ነው?+
13 ከጫካ የወጡ የዱር አሳማዎች ያወድሟታል፤በሜዳ ያሉ የዱር አራዊትም ይበሏታል።+
14 የሠራዊት አምላክ ሆይ፣ እባክህ ተመለስ።
ከሰማይ ወደ ታች እይ፤ ተመልከትም!
ይህችን የወይን ተክል ተንከባከባት፤+
15 ቀኝ እጅህ የተከላትን ግንድ*+ በእንክብካቤ ያዛት፤ለራስህ ስትል ያጠነከርከውንም ልጅ* ተመልከት።+
16 እሷ ተቆርጣ በእሳት ተቃጥላለች።+
ሕዝቡ ከተግሣጽህ* የተነሳ ይጠፋል።
17 እጅህ በቀኝህ ላለው ሰው፣ለራስህም ስትል ብርቱ ላደረግከው የሰው ልጅ ድጋፍ ትስጥ።+
18 እኛም ከአንተ አንርቅም።
ስምህን መጥራት እንድንችል በሕይወት አኑረን።
19 የሠራዊት አምላክ ይሖዋ ሆይ፣ ወደ ቀድሞው ሁኔታችን መልሰን፤እንድንም ዘንድ ፊትህን በእኛ ላይ አብራ።+
የግርጌ ማስታወሻዎች
^ “በኪሩቤል መካከል” ማለትም ሊሆን ይችላል።
^ ወይም “ብርሃንህን ግለጥ።”
^ ቃል በቃል “በሚያቀርቡት ጸሎት ቁጣህ የሚነደው።”
^ የኤፍራጥስን ወንዝ ያመለክታል።
^ ወይም “የወይን ተክል ዋና ግንድ።”
^ ወይም “ቅርንጫፍ።”
^ ቃል በቃል “ከፊትህ ተግሣጽ።”