መዝሙር 40:1-17

  • ተወዳዳሪ ለማይገኝለት አምላክ የቀረበ ምስጋና

    • የአምላክን ሥራዎች ዘርዝረን መጨረስ አንችልም (5)

    • “መሥዋዕትንና መባን አልፈለግክም” (6)

    • “ፈቃድህን ማድረግ ያስደስተኛል” (8)

ለሙዚቀኞች ቡድን መሪ። የዳዊት መዝሙር። ማህሌት። 40  ተስፋዬን ሙሉ በሙሉ በይሖዋ ላይ ጣልኩ፤*እሱም ጆሮውን ወደ እኔ አዘነበለ፤* ለእርዳታ ያሰማሁትንም ጩኸት ሰማ።+  2  የሚያስገመግም ድምፅ ካለበት ጉድጓድ፣ከሚያዘቅጥ ማጥም አወጣኝ። እግሮቼንም በዓለት ላይ አቆመ፤አረማመዴንም አጸና።  3  ከዚያም በአፌ ላይ አዲስ መዝሙር፣+ለአምላካችን የሚቀርብ ውዳሴ አኖረ። ብዙዎች በፍርሃት* ተውጠው ይመለከታሉ፤በይሖዋም ይታመናሉ።  4  በይሖዋ የሚታመን፣ እንቢተኛ ወደሆኑት ወይምሐሰት* ወደሆኑት ፊቱን ያላዞረ ሰው ደስተኛ ነው።  5  ይሖዋ አምላኬ ሆይ፣ያደረግካቸው ድንቅ ሥራዎች፣ለእኛ ያሰብካቸው ነገሮችም ብዙ ናቸው።+ ከአንተ ጋር ሊወዳደር የሚችል ማንም የለም፤+ስለ እነዚህ ነገሮች ላውራ፣ ልናገር ብል፣ዘርዝሬ ልጨርሳቸው አልችልም!+  6  መሥዋዕትንና መባን አልፈለግክም፤*+ከዚህ ይልቅ እንድሰማ ጆሮዎቼን ከፈትክልኝ።*+ የሚቃጠል መባና የኃጢአት መባ እንዲቀርብልህ አልጠየቅክም።+  7  በዚህ ጊዜ እንዲህ አልኩ፦ “እነሆ፣ መጥቻለሁ። ስለ እኔ በመጽሐፍ ጥቅልል ተጽፏል።+  8  አምላኬ ሆይ፣ ፈቃድህን ማድረግ ያስደስተኛል፤*+ሕግህም በልቤ ውስጥ ነው።+  9  በታላቅ ጉባኤ መካከል የጽድቅን ምሥራች አውጃለሁ።+ ይሖዋ ሆይ፣ አንተ ራስህ በሚገባ እንደምታውቀው፣እነሆ፣ ከንፈሮቼን አልከለክልም።+ 10  ጽድቅህን በልቤ ውስጥ አልሸሽግም። ታማኝነትህንና ማዳንህን አውጃለሁ። በታላቅ ጉባኤ መካከል ታማኝ ፍቅርህንና እውነትህን አልደብቅም።”+ 11  ይሖዋ ሆይ፣ ምሕረትህን አትንፈገኝ። ታማኝ ፍቅርህና እውነትህ ምንጊዜም ይጠብቁኝ።+ 12  ለመቁጠር እንኳ የሚያታክት መከራ ከቦኛል።+ የፈጸምኳቸው በርካታ ስህተቶች ስለዋጡኝ መንገዴን ማየት ተስኖኛል፤+በራሴ ላይ ካሉት ፀጉሮች እጅግ ይበዛሉ፤ደግሞም ተስፋ ቆረጥኩ። 13  ይሖዋ ሆይ፣ እኔን ለማዳን እባክህ ፈቃደኛ ሁን።+ ይሖዋ ሆይ፣ እኔን ለመርዳት ፍጠን።+ 14  ሕይወቴን* ለማጥፋት የሚሹ ሁሉ፣ኀፍረትና ውርደት ይከናነቡ። በእኔ ላይ በደረሰው ጉዳት ደስ የሚሰኙአፍረው ወደ ኋላ ይመለሱ። 15  “እሰይ! እሰይ!” የሚሉኝ በሚደርስባቸው ኀፍረት የተነሳ ክው ይበሉ። 16  አንተን የሚፈልጉ+ ግንበአንተ ይደሰቱ፤ ሐሴትም ያድርጉ።+ የማዳን ሥራህን የሚወዱ፣ ምንጊዜም “ይሖዋ ታላቅ ይሁን” ይበሉ።+ 17  እኔ ግን ምስኪንና ድሃ ነኝ፤ይሖዋ ትኩረት ይስጠኝ። አንተ ረዳቴና ታዳጊዬ ነህ፤+አምላኬ ሆይ፣ አትዘግይ።+

የግርጌ ማስታወሻዎች

ወይም “ይሖዋን በትዕግሥት ጠበቅኩት።”
ወይም “ለመስማት አጎነበሰ።”
ወይም “በአክብሮታዊ ፍርሃት።”
ወይም “ውሸታም።”
ወይም “በመሥዋዕትና በመባ ደስ አልተሰኘህም።”
አንዳንድ የሰብዓ ሊቃናት ጥንታዊ ጽሑፎች “መሥዋዕትንና መባን አልፈለግክም፤ ከዚህ ይልቅ አካል አዘጋጀህልኝ” ይላሉ። ከዕብ 10:5 ጋር አወዳድር።
ወይም “እሻለሁ።”
ወይም “ነፍሴን።”