መክብብ 5:1-20
5 ወደ እውነተኛው አምላክ ቤት በምትሄድበት ጊዜ ሁሉ አካሄድህን ጠብቅ፤+ ሞኞች እንደሚያደርጉት መሥዋዕት ለማቅረብ ከመሄድ+ ይልቅ ለመስማት መሄድ ይሻላል፤+ እነሱ እየሠሩ ያሉት ነገር መጥፎ መሆኑን አያውቁምና።
2 በአፍህ ለመናገር አትጣደፍ፤ ልብህም በእውነተኛው አምላክ ፊት ለመናገር አይቸኩል፤+ እውነተኛው አምላክ በሰማያት፣ አንተ ግን በምድር ላይ ነህና። ስለዚህ የምትናገራቸው ቃላት ጥቂት ሊሆኑ ይገባል።+
3 ሐሳብ ሲበዛ* ለቅዠት ይዳርጋል፤+ የቃላት ብዛትም ሞኝን ሰው ለፍላፊ ያደርገዋል።+
4 ለአምላክ ስእለት በምትሳልበት ጊዜ ሁሉ ስእለትህን ለመፈጸም አትዘግይ፤+ እሱ በሞኞች አይደሰትምና።+ ስእለትህን ፈጽም።+
5 ስእለት ተስለህ ሳትፈጽም ከምትቀር ባትሳል ይሻላል።+
6 አፍህ ወደ ኃጢአት እንዲመራህ* አትፍቀድ፤+ በመልአክም* ፊት “ተሳስቼ ነው” አትበል።+ እውነተኛው አምላክ በተናገርከው ነገር ተቆጥቶ የእጅህን ሥራ ለምን ያጥፋ?+
7 ሐሳብ ሲበዛ ቅዠት እንደሚያስከትል፣+ የቃላት ብዛት ደግሞ ከንቱነትን ያስከትላልና። አንተ ግን እውነተኛውን አምላክ ፍራ።+
8 በምትኖርበት ግዛት ውስጥ በድሃ ላይ ግፍ ሲፈጸም፣ ፍትሕ ሲጓደልና ጽድቅ ወደ ጎን ገሸሽ ሲደረግ ብታይ በዚህ ጉዳይ አትገረም።+ ይህን ባለሥልጣን፣ ከእሱ ከፍ ያለ ቦታ ያለው ይመለከተዋልና፤ ከእነሱም በላይ የሆኑ ሌሎች አሉ።
9 ከምድሩ የሚገኘውን ትርፍ ሁሉም ይከፋፈሉታል፤ ንጉሡ እንኳ የሚያስፈልገውን ነገር የሚያገኘው ከእርሻው ነው።+
10 ብርን የሚወድ ብርን አይጠግብም፤ ሀብትንም የሚወድ በሚያገኘው ገቢ አይረካም።+ ይህም ቢሆን ከንቱ ነው።+
11 መልካም ነገሮች ሲበዙ፣ በላተኛውም ይበዛል።+ ታዲያ በዓይኑ ብቻ ከማየት በቀር ይህ ለባለቤቱ ምን ይጠቅመዋል?+
12 የሚበላው ጥቂትም ሆነ ብዙ፣ የሠራተኛ እንቅልፍ ጣፋጭ ነው፤ ባለጸጋ ሰው ያለው ብዙ ሀብት ግን እንቅልፍ ይነሳዋል።
13 ከፀሐይ በታች ያየሁት እጅግ አሳዛኝ የሆነ ነገር* አለ፦ ይህም ባለቤቱ በገዛ ራሱ ላይ ጉዳት ለማምጣት ያከማቸው ሀብት ነው።
14 ይህ ሰው አደገኛ ነገር* ውስጥ በመግባቱ ሀብቱን አጥቷል፤ ልጅ በሚወልድበት ጊዜም ለልጁ የሚያወርሰው ምንም ነገር አይኖረውም።+
15 ሰው ከእናቱ ማህፀን ራቁቱን እንደወጣ ሁሉ፣ ልክ እንደዚያው ተመልሶ ይሄዳል።+ ደግሞም ከደከመበት ነገር ሁሉ ሊወስደው የሚችል አንዳች ነገር የለም።+
16 ይህም ደግሞ እጅግ የሚያሳዝን ነገር* ነው፦ ሰው በዚያው በመጣበት መንገድ ተመልሶ ይሄዳል፤ ለነፋስ የሚደክም ሰው የሚያገኘው ትርፍ ምንድን ነው?+
17 ደግሞም በየቀኑ ጨለማ ውስጥ በከፍተኛ ብስጭት፣ በሕመምና በንዴት ይበላል።+
18 እኔ ያየሁት መልካምና ተገቢ የሆነ ነገር፣ ሰው እውነተኛው አምላክ በሰጠው አጭር የሕይወት ዘመን ሁሉ መብላቱና መጠጣቱ እንዲሁም ከፀሐይ በታች በደከመበትና በትጋት ባከናወነው ሥራ ሁሉ ደስታ ማግኘቱ ነው፤+ ይህ ብድራቱ* ነውና።+
19 ደግሞም እውነተኛው አምላክ ለሰው ሀብትና ቁሳዊ ንብረት+ ብሎም በእነዚህ ነገሮች የመደሰት ችሎታ ሲሰጠው ብድራቱን* ተቀብሎ በትጋት በሚያከናውነው ሥራ መደሰት ይገባዋል። ይህ የአምላክ ስጦታ ነው።+
20 እውነተኛው አምላክ ልቡን ደስ በሚያሰኙ ነገሮች እንዲጠመድ ስለሚያደርገው የሚያልፈውን የሕይወት ዘመኑን ፈጽሞ ልብ አይለውም።*+
የግርጌ ማስታወሻዎች
^ ወይም “ጭንቀት ሲበዛ።”
^ ቃል በቃል “ሥጋህን ወደ ኃጢአት እንዲመራ።”
^ ወይም “በመልእክተኛም።”
^ ወይም “ክፉ ነገር።”
^ ወይም “ሥራ።”
^ ወይም “ክፉ ነገር።”
^ ወይም “ድርሻው።”
^ ወይም “ድርሻውን።”
^ ወይም “አያስታውሰውም።”