በቀጥታ ወደ ዋናው ጉዳይ ግባ

በቀጥታ ወደ ርዕስ ማውጫው ሂድ

የዳንኤል መጽሐፍና አንተ

የዳንኤል መጽሐፍና አንተ

ምዕራፍ አንድ

የዳንኤል መጽሐፍና አንተ

1, 2. (ሀ) የመጽሐፍ ቅዱስ ክፍል በሆነው በዳንኤል መጽሐፍ ውስጥ የሰፈሩት አንዳንድ እንግዳ ነገሮች ምንድን ናቸው? (ለ) በዚህ በእኛ ዘመን የዳንኤልን መጽሐፍ በሚመለከት ምን ጥያቄዎች ይነሣሉ?

አንድ ኃያል ንጉሥ እንቆቅልሽ የሆነበትን ሕልሙን ሊፈቱለት ባለመቻላቸው ጠቢባኑን በሙሉ እንደሚፈጃቸው ዝቶ ነበር። ለአንድ ትልቅ ምስል አንሰግድም ያሉ ሦስት ወጣት ወንዶች እሳቱ በሚንቀለቀልበት እቶን ውስጥ ቢጣሉም በሕይወት ተርፈዋል። በአንድ ትልቅ ግብዣ ላይ በመቶዎች የሚቆጠሩ ሰዎች በቤተ መንግሥቱ ግድግዳ ላይ አንድ እጅ ምሥጢራዊ የሆኑ ቃላት ሲጽፍ ተመለከቱ። ክፉ ሰዎች በሸረቡት ሴራ አንድ አረጋዊ ሰው ወደ አንበሶች ጉድጓድ ቢጣልም ጭረት እንኳ ሳይነካው ሊወጣ ችሏል። አንድ የአምላክ ነቢይ አራት አራዊት በራእይ የተመለከተ ሲሆን ትንቢታዊ ተፈጻሚነቱ ከዚያ በኋላ ባሉት ብዙ ሺህ ዓመታት ሁሉ የሚዘልቅ ነበር።

2 የመጽሐፍ ቅዱስ ክፍል በሆነው በዳንኤል መጽሐፍ ውስጥ ከሚገኙት ዘገባዎች መካከል እነዚህ ጥቂቶቹ ናቸው። እነዚህን ዘገባዎች በቁም ነገር መመርመራችን ተገቢ ነውን? ዘመናት ያስቆጠረው ይህ መጽሐፍ ዛሬ ለእኛ ምን ጠቀሜታ ሊኖረው ይችላል? ከዛሬ 2,600 ዓመታት በፊት ስለተፈጸሙ ነገሮች የምንጨነቅበት ምን ምክንያት ይኖራል?

ዳንኤል—ለዘመናችን የሚሆን ጥንታዊ መጽሐፍ

3, 4. የሰው ልጅ የወደፊት ዕጣ ብዙዎችን የሚያሳስባቸው ለምንድን ነው?

3 አብዛኛው የዳንኤል መጽሐፍ ያተኮረው የዓለምን አገዛዝ በሚመለከት ጉዳይ ላይ ነው። ይህ ደግሞ በዛሬው ጊዜ እጅግ አንገብጋቢ ርዕሰ ጉዳይ ሆኗል። የምንኖርበት ጊዜ አስጨናቂ መሆኑን የሚክድ ሰው አይኖርም። በሳይንስና ቴክኖሎጂ ረገድ ድንቅ ውጤቶች ቢገኙም በየዕለቱ የምንሰማቸው የዜና ዘገባዎች የሰው ልጅ ኅብረተሰብ ውስብስብ ወደሆነ የችግር አዘቅት እየገባ መሆኑን የሚጠቁሙ ናቸው።

4 እስቲ አስበው:- የሰው ልጅ በጨረቃ ላይ መራመድ ቢችልም በገዛ ፕላኔቱ ብዙ ጎዳናዎች ላይ ግን ያለ ስጋት መሄድ ተስኖታል። ቤቶችን የዘመናዊ ቴክኖሎጂ ውጤት በሆኑ የተለያዩ የምቾት ዕቃዎች መሙላት ችሏል፤ ነገር ግን የቤተሰብን መፈራረስ መግታት አልቻለም። ከፍተኛ የመረጃ ልውውጥ ማድረግ የሚቻልበት ዘመን ላይ ቢደርስም ሰዎች እርስ በርሳቸው ተስማምተው በሰላም እንዲኖሩ ማስተማር ግን አልቻለም። የታሪክ ፕሮፌሰር የሆኑት ሀግ ቶማስ በአንድ ወቅት እንዲህ ሲሉ ጽፈው ነበር:- “የእውቀትና የትምህርት መስፋፋት የሰው ልጅ ራስን መግዛትንና በስምምነት አብሮ መኖርን እንዲማር አላደረገውም።”

5. በአብዛኛው የሰው ልጅ አገዛዝ ውጤት ምን ሆኖ ተገኝቷል?

5 ሰዎች በማኅበረሰቡ ውስጥ በተወሰነ መጠን ሥርዓት እንዲሰፍን ለማድረግ ራሳቸውን በተለያዩ ዓይነት መስተዳድሮች አዋቅረዋል። ይሁንና የትኛውም መስተዳድር ቢሆን ንጉሥ ሰሎሞን ካሰፈረው ሐቅ አይወጣም:- “ሰው ሰውን የገዛው ለጉዳቱ ነው።” (መክብብ 4:1፤ 8:9 NW) እርግጥ አንዳንድ ጥሩ አስተሳሰብ የነበራቸው ገዥዎች ነበሩ። የሆነ ሆኖ የትኛውም ንጉሥ፣ ፕሬዚዳንት ወይም አምባገነን መሪ ሕመምንና ሞትን ሊያስቀር አይችልም። ምድራችንን እንደ አምላክ ዓላማ ወደ ገነትነት ሊመልሳት የሚችል አንድም ሰው የለም።

6. ይሖዋ ፈቃዱን ከዳር ለማድረስ የሰብዓዊ ገዥዎች ትብብር የማያስፈልገው ለምንድን ነው?

6 ፈጣሪ ግን እንዲህ ያለውን ነገር ለማድረግ ፈቃደኛ ከመሆኑም በተጨማሪ ችሎታውም አለው። ዓላማውን ከዳር ለማድረስ የማንኛውንም ሰብዓዊ መስተዳድር ፈቃድ ማግኘት አያስፈልገውም። ለእርሱ “አሕዛብ በገንቦ እንዳለች ጠብታ ናቸው፣ በሚዛንም እንዳለ ትንሽ ትቢያ ተቆጥረዋል።” (ኢሳይያስ 40:15) አዎን፣ ይሖዋ የአጽናፈ ዓለሙ ሉዓላዊ ገዥ ነው። በመሆኑም ሥልጣኑ ከሰብዓዊ መስተዳድሮች ሁሉ እጅግ የላቀ ነው። ሰብዓዊ መስተዳድሮችን በመተካት ለሰው ዘር ዘላለማዊ በረከትን የሚያመጣላቸው የአምላክ መንግሥት ነው። ይህ ጉዳይ የመጽሐፍ ቅዱስ ክፍል የሆነውን የዳንኤልን መጽሐፍ ያክል በግልጽ የተብራራበት ቦታ የለም ለማለት ይቻላል።

ዳንኤል—በአምላክ እጅግ የተወደደ ሰው

7. ዳንኤል ማን ነበር? ይሖዋስ ለእርሱ ምን አመለካከት ነበረው?

7 ይሖዋ አምላክ ለብዙ ዓመታት በነቢይነት ያገለገለውን ዳንኤልን እጅግ ይወደው ነበር። የአምላክ መልአክም ቢሆን ዳንኤልን “እጅግ የተወደድህ” ሲል ጠርቶታል። (ዳንኤል 9:23) “እጅግ የተወደድህ” ተብሎ የተተረጎመው የመጀመሪያው የዕብራይስጥ ቃል “ከፍ ያለ ግምት የሚሰጠው” አልፎ ተርፎም “አብልጦ የሚወደድ” የሚል ትርጉም ሊኖረው ይችላል። ዳንኤል በአምላክ ፊት እጅግ ውድ ነበር።

8. ዳንኤል ወደ ባቢሎን ሊሄድ የቻለው እንዴት ነበር?

8 ይህ የተወደደ ነቢይ የነበረባቸውን ለየት ያሉ ሁኔታዎች በአጭሩ እንመልከት። በ618 ከዘአበ የባቢሎን ንጉሥ ናቡከደነፆር ኢየሩሳሌምን ከበበ። (ዳንኤል 1:1) ከዚያ በኋላ ብዙም ሳይቆይ ጥሩ ትምህርት የነበራቸው አንዳንድ አይሁዳውያን ወጣቶች ወደ ባቢሎን በግዞት ተወሰዱ። ከእነዚህ መካከል አንዱ ዳንኤል ነበር። በዚህ ወቅት ዕድሜው ምናልባት በአሥራዎቹ ውስጥ ሳይሆን አይቀርም።

9. ለዳንኤልና ለዕብራውያን ጓደኞቹ የተሰጣቸው ሥልጠና ምን ዓይነት ነበር?

9 ለሦስት ዓመታት ያህል ‘የከለዳውያንን ትምህርትና ቋንቋ ይማሩ ዘንድ’ ከተመረጡት ዕብራውያን መካከል ዳንኤል እንዲሁም አናንያ፣ ሚሳኤልና አዛርያ የሚባሉ ጓደኞቹ ይገኙበት ነበር። (ዳንኤል 1:3, 4) አንዳንድ ምሁራን ይህ ከቋንቋ ትምህርት የበለጠ ነገር እንደሚጨምር ይናገራሉ። ለምሳሌ ያህል ፕሮፌሰር ሲ ኤፍ ኪል “ዳንኤልና ጓደኞቹ በባቢሎን ትምህርት ቤቶች ውስጥ የሚሰጠውን የከለዳውያንን ካህናትና ምሁራን ጥበብ መማር ይጠበቅባቸው ነበር” ብለዋል። በመሆኑም ዳንኤልና ጓደኞቹ ልዩ ሥልጠና ይሰጣቸው የነበረው ለመስተዳድር ሥራ ነበር።

10, 11. ዳንኤልና ጓደኞቹ ምን ፈታኝ ሁኔታዎች ገጥመዋቸው ነበር? ይሖዋስ ምን እርዳታ አድርጎላቸዋል?

10 ይህ ለዳንኤልና ለባልንጀሮቹ ቀላል ለውጥ አልነበረም! በይሁዳ ይኖሩ የነበረው ይሖዋን በሚያመልኩ ሰዎች መካከል ነበር። አሁን ግን አፈታሪካዊ የሆኑ ወንድና ሴት አማልክትን በሚያመልኩ ሰዎች ተከብበዋል። የሆነ ሆኖ ወጣቱ ዳንኤል፣ አናንያ፣ ሚሳኤልና አዛርያ አልፈሩም። ይህን የመሰለ እምነትን የሚፈታተን ሁኔታ ቢገጥማቸውም እውነተኛውን አምልኮ አጥብቀው ለመያዝ ቆርጠው ነበር።

11 ይህ ግን ቀላል ነገር አልነበረም። ንጉሥ ናቡከደነፆር ማርዱክ የሚባለው ዋነኛ የባቢሎን ጣዖት ቀናተኛ አገልጋይ ነበር። አንዳንድ ጊዜ ንጉሡ እንዲደረጉ የሚጠይቃቸው ነገሮች ይሖዋን በሚያመልኩ ሰዎች ዘንድ ፈጽሞ ተቀባይነት የሌላቸው ነገሮች ነበሩ። (ለምሳሌ ያህል ዳንኤል 3:1-7⁠ን ተመልከት።) ይሁንና ዳንኤልና ጓደኞቹ ምንጊዜም የይሖዋን መመሪያ ያገኙ ነበር። በሦስት ዓመቱ ሥልጠና ጊዜ አምላክ “በትምህርትና በጥበብ ሁሉ እውቀትንና ማስተዋልን” በመስጠት ባርኳቸዋል። ከዚህም በተጨማሪ ዳንኤል የራእይዎችንና የሕልሞችን ትርጉም የመረዳት ችሎታ ተሰጥቶት ነበር። ከጊዜ በኋላም ንጉሡ እነዚህን አራት ወጣት ወንዶች በፈተናቸው ጊዜ “በጥበብና በማስተዋል ነገር ሁሉ በግዛቱ ሁሉ ከሚኖሩ የሕልም ተርጓሚዎችና አስማተኞች ሁሉ እነርሱ አሥር እጅ የበለጡ ሆነው” አግኝቷቸዋል።—ዳንኤል 1:17, 20

የአምላክን መልእክት ማወጅ

12. ዳንኤል ምን ልዩ ኃላፊነት ተጥሎበት ነበር?

12 ዳንኤል በባቢሎን በኖረባቸው ዓመታት በሙሉ እንደ ንጉሥ ናቡከደነፆርና ብልጣሶር ባሉት ሰዎች ዘንድ የአምላክ መልእክተኛ ሆኖ አገልግሏል። ዳንኤል የተጣለበት ኃላፊነት ከባድ ነበር። ናቡከደነፆር ኢየሩሳሌምን እንዲያጠፋ በመፍቀድ ይሖዋ እንደ መሣሪያ ተጠቅሞበታል። ከጊዜ በኋላ ራሷ ባቢሎንም መጥፋት ነበረባት። በእውነትም የዳንኤል መጽሐፍ ይሖዋ አምላክ ልዑልና ‘የሰው ልጅ መንግሥታት’ ገዥ መሆኑን በጉልህ የሚያንጸባርቅ ነው።—ዳንኤል 4:17

13, 14. ባቢሎን ከወደቀች በኋላ ዳንኤል ስለ ነበረበት ሁኔታ ምን ማለት ይቻላል?

13 ዳንኤል ባቢሎን እስከወደቀችበት ጊዜ ድረስ ለሰባት አሥርተ ዓመታት ገደማ በቤተ መንግሥት ውስጥ አገልግሏል። ምንም እንኳ መጽሐፍ ቅዱስ ዳንኤል አብሯቸው ስለ መመለሱ የሚገልጸው ነገር ባይኖርም በ537 ከዘአበ ዳንኤል ብዙ አይሁዳውያን ወደ አገራቸው ሲመለሱ ለማየት በቅቷል። ቢያንስ የፋርስን ግዛት እስካቋቋመው እስከ ንጉሥ ቂሮስ ሦስተኛ ዓመት የግዛት ዘመን ድረስ ይሠራ ነበር። በዚህ ጊዜ ዳንኤል ወደ 100 ዓመት ዕድሜ ተጠግቶ መሆን ይኖርበታል!

14 ባቢሎን ከወደቀች በኋላ ዳንኤል በሕይወቱ ውስጥ የተከናወኑትን ጉልህ ክስተቶች በጽሑፍ አስፍሯል። ይህ ዘገባው ዛሬ ድንቅ የመጽሐፍ ቅዱስ ክፍል ሆኖ የሚገኝ ሲሆን የዳንኤል መጽሐፍ በመባል ይታወቃል። ይሁን እንጂ ይህንን ጥንታዊ መጽሐፍ በጥልቀት መመርመር ያስፈለገን ለምንድን ነው?

ሁለት ዓይነት አቀራረብ፤ አንድ መልእክት

15. (ሀ) የመጽሐፍ ቅዱስ ክፍል በሆነው የዳንኤል መጽሐፍ ውስጥ የተንጸባረቁት ሁለት ዓይነት አቀራረቦች የትኞቹ ናቸው? (ለ) በትረካ መልክ የቀረበው የዳንኤል መጽሐፍ ክፍል የሚጠቅመን እንዴት ነው?

15 በዓይነቱ ልዩ በሆነው የዳንኤል መጽሐፍ ውስጥ ሁለት ፈጽሞ የተለያዩ አቀራረቦች ተንጸባርቀዋል። አንደኛው ትረካ ሲሆን ሌላኛው ደግሞ ትንቢታዊ ነው። ሁለቱም የዳንኤል መጽሐፍ ገጽታዎች እምነታችንን ሊገነቡልን ይችላሉ። እንዴት? እጅግ ግልጽ ከሆኑት የመጽሐፍ ቅዱስ ትረካዎች መካከል የሚመደቡት እነዚሁ ዘገባዎች ይሖዋ አምላክ ለእርሱ ያላቸውን የጸና አቋም ሳያላሉ የሚመላለሱትን እንደሚባርካቸውና እንደሚንከባከባቸው ይጠቁመናል። ዳንኤልና ሦስቱ ጓደኞቹ ሕይወታቸውን አደጋ ላይ የሚጥሉ ፈተናዎች ቢገጥሟቸውም ጸንተው ቆመዋል። ዛሬም ለይሖዋ ታማኝ መሆን የሚፈልጉ ሁሉ የእነዚህ ወጣቶችን ምሳሌ በጥልቀት በመመርመር ብርታት ያገኛሉ።

16. በትንቢታዊ መልክ ከቀረበው የዳንኤል መጽሐፍ ክፍል ምን ትምህርት እናገኛለን?

16 የዳንኤል መጽሐፍ ትንቢታዊ ክፍል ይሖዋ በመቶ፣ አልፎ ተርፎም በሺህ ከሚቆጠሩ ዓመታት በኋላ የሚፈጸመውን ታሪክ አስቀድሞ የሚያውቅ አምላክ መሆኑን ስለሚገልጽ እምነት የሚገነባ ነው። ለምሳሌ ያህል ዳንኤል ከጥንቷ ባቢሎን አንስቶ እስከ ‘ፍጻሜው ዘመን’ ድረስ ያሉትን የዓለም ኃያላን አነሣስና አወዳደቅ የሚመለከት ዝርዝር ሐሳብ ይዟል። (ዳንኤል 12:4) ዳንኤል፣ አምላክ በሾመው ንጉሥና በተባባሪዎቹ ‘ቅዱሳን’ የሚተዳደረው የአምላክ መንግሥት ለዘላለም ጸንቶ እንደሚቆም በመግለጽ በዚህ መንግሥት ላይ እንድናተኩር ያደርጋል። ይህ መንግሥት ይሖዋ ለምድራችን ያለውን ዓላማ ሙሉ በሙሉ በማስፈጸም አምላክን ለማገልገል ለሚፈልጉ ሁሉ በረከት ያመጣል።—ዳንኤል 2:44፤ 7:13, 14, 22

17, 18. (ሀ) የዳንኤልን መጽሐፍ በጥልቀት በመመርመራችን እምነታችን የሚጠናከረው እንዴት ነው? (ለ) ይህን ትንቢታዊ የመጽሐፍ ቅዱስ ክፍል መመርመር ከመጀመራችን በፊት ልናየው የሚገባ ጉዳይ የትኛው ነው?

17 ይሖዋ ወደፊት ስለሚከናወኑት ነገሮች ያለውን እውቀት የሚሸሽግ አምላክ ባለመሆኑ አመስጋኞች ልንሆን ይገባል። እንዲያውም ‘ምሥጢርን የሚገልጥ’ አምላክ ነው። (ዳንኤል 2:28) በዳንኤል መጽሐፍ ውስጥ ተመዝግበው የሚገኙትን ትንቢቶች ፍጻሜ በትኩረት ስንከታተል በአምላክ ተስፋዎች ላይ ያለን እምነት ይጠናከራል። አምላክ በመረጠው ትክክለኛ ጊዜና መንገድ ዓላማውን እንደሚያከናውን ይበልጥ እርግጠኞች እንሆናለን።

18 የመጽሐፍ ቅዱስ ክፍል የሆነውን የዳንኤልን መጽሐፍ በቅን ልብ የሚያጠኑ ሁሉ እምነታቸው ያድጋል። ይሁን እንጂ ይህን መጽሐፍ በጥልቀት መመርመር ከመጀመራችን በፊት መጽሐፉ በእርግጥ ትክክል መሆን አለመሆኑን ለመለየት ማስረጃዎቹን መመርመር ይኖርብናል። አንዳንድ ተቺዎች የዳንኤል ትንቢቶች የተጻፉት ፍጻሜያቸውን ካገኙ በኋላ ነው በማለት ነቀፋ ሰንዝረዋል። የእነዚህ ተጠራጣሪ ሰዎች አባባል ትክክል ነውን? የሚቀጥለው ምዕራፍ ይህንን ጉዳይ የሚዳስስ ይሆናል።

ምን አስተውለሃል?

• የዳንኤል መጽሐፍ ለዘመናችን የሚሆን መጽሐፍ ነው የምንለው ለምንድን ነው?

• ዳንኤልና ጓደኞቹ በባቢሎን የመስተዳድር ሥራ ውስጥ ሊገቡ የቻሉት እንዴት ነው?

• ዳንኤል በባቢሎን ውስጥ ምን ልዩ ኃላፊነት ተጥሎበት ነበር?

• የዳንኤልን ትንቢት በትኩረት መከታተል ያለብን ለምንድን ነው?

[የአንቀጾቹ ጥያቄዎች]

[በገጽ 4 ላይ የሚገኝ ባለሙሉ ገጽ ሥዕል]

[በገጽ 11 ላይ የሚገኝ ባለሙሉ ገጽ ሥዕል]