በቀጥታ ወደ ዋናው ጉዳይ ግባ

በቀጥታ ወደ ርዕስ ማውጫው ሂድ

ጓደኛዬ የጎዳኝ ለምንድን ነው?

ጓደኛዬ የጎዳኝ ለምንድን ነው?

ምዕራፍ 10

ጓደኛዬ የጎዳኝ ለምንድን ነው?

“ካሪ በጣም ጥሩ ጓደኛዬ ነበረች። መኪና ስላልነበራት ሁልጊዜ ከሥራ በኋላ በመኪናዬ እሸኛት ነበር። ብዙም ሳይቆይ ግን መጠቀሚያ እያደረገችኝ እንደሆነ ይሰማኝ ጀመር።

“ሁልጊዜ ወደ መኪናው ስትገባ ከሞባይል ስልኳ አትላቀቅም፤ ወይ ትደዋወላለች አሊያም መልእክት ትጻጻፋለች። በዚያ ላይ ካደረስኳት በኋላ አንድም ቀን አመስግናኝ አታውቅም፤ ለነዳጅ ታዋጣ የነበረውንም ገንዘብ መስጠቷን አቆመች። ሌሎችን ከመንቀፍ ውጪ የምታወራው ነገር አልነበረም። ይህን ያህል ጊዜ ስለታገሥኳት በራሴ በጣም ተበሳጨሁ!

“አንድ ቀን ግን ከአሁን በኋላ ከሥራ ስትወጣ ልሸኛት እንደማልችል ለካሪ በአክብሮት ነገርኳት። ከዚያ ጊዜ ወዲህ ከእኔ ጋር መሆን አትፈልግም፤ ይህም የእኔን ጓደኝነት የምትፈልገው ለጥቅሟ ስትል ብቻ እንደነበረ ይበልጥ እርግጠኛ እንድሆን አደረገኝ። በዚህ በጣም ተጎዳሁ!”​—ኒኮል

በጣም በሚዋደዱ ጓደኛሞች መካከል እንኳ እንዲህ ያለ ነገር ሊከሰት ይችላል። ፈጽሞ የማይነጣጠሉ ይመስሉ የነበሩ ጓደኛሞች መነጋገር እንኳ ሊያቆሙ ይችላሉ። ታዲያ በአንድ ወቅት ደስ የሚል ጓደኝነት የነበራቸው ሰዎች በድንገት መጣጣም የሚያቅታቸው ለምንድን ነው?

● ኤርምያስ፣ የሚወደው ጓደኛው እንደተለወጠበት የተሰማው ጓደኛው አገር አቋርጦ በሄደበት ጊዜ ነበር። “ከሄደ በኋላ ደውሎልኝ አያውቅም፤ ይህ በጣም ጎዳኝ” ብሏል።

● ካረን ለአምስት ዓመት አብራት የቆየችው የቅርብ ጓደኛዋ ባሕርይ እየተለወጠ መሆኑን ማስተዋል ጀመረች። እንዲህ ብላለች፦ “አስተሳሰቧም ሆነ አነጋገሯ ይረብሸኝ ጀመር። እኔ ትልቅ ቦታ የምሰጣቸውን ነገሮች መንቀፍና ማጣጣል አመጣች። ጉዳዩን ለመፍታት ስንሞክር ደግሞ ተመጻዳቂ እንደሆንኩና ለእሷ ታማኝ እንዳልሆንኩ በመግለጽ ወቀሰችኝ፤ ከዚህም አልፋ የእኔ ጓደኝነት ለእሷ ምንም ማለት እንዳልሆነ ተናገረች!”

● አቢጋኤል፣ ከቅርብ ጓደኛዋ ጋር የተለያየችው በድንገት ነበር፤ ጓደኝነታቸው የፈረሰው በምን ምክንያት እንደሆነ እንኳ አታውቅም። አቢጋኤል እንዲህ ብላለች፦ “መጀመሪያ ላይ በጣም የምንጣጣም ጓደኛሞች ነበርን፤ እንዲያውም እንደ እህቷ እንደምታየኝ ነግራኝ ነበር። ከዚያም ከመሬት ተነስታ ከእኔ ጋር መሆን አቆመች፤ ለዚህም ሰበብ አስባብ ትደረድር ነበር።”

● በሎራና በዳሪያ መካከል አለመግባባት የተፈጠረው ዳሪያ የሎራን የወንድ ጓደኛ በቀማቻት ጊዜ ነበር። ሎራ እንዲህ ብላለች፦ “የወንድ ጓደኛዬ መሆኑን እያወቀች ከእሱ ጋር ለሰዓታት በስልክ ታወራ ነበር። የምወዳት ጓደኛዬ ያታለለችኝ ከመሆኑም ሌላ ላገባው እችል ከነበረው ሰው ጋር በእሷ ምክንያት ተለያየሁ፤ በአንድ ጊዜ ሁለቱንም አጣሁ!”

ችግሩ ምንድን ነው?

ሁሉም ሰው ይሳሳታል። በመሆኑም ጓደኛህ የሚጎዳህ ነገር ቢያደርግ ወይም ቢናገር ያን ያህል አያስገርምም። እንደ እውነቱ ከሆነ አንተም ሌሎችን የጎዳህበት ጊዜ ይኖራል። (መክብብ 7:22) ሊሳ የተባለች ወጣት “ሁላችንም ፍጹማን ስላልሆንን አልፎ አልፎ አንዳችን ሌላውን ቅር ማሰኘታችን አይቀርም” ብላለች። አብዛኛውን ጊዜ ቀላል በሆነ አለመግባባት ምክንያት የተፈጠረን ችግር በውይይት መፍታት ይቻላል።

በሌላ በኩል ግን ጓደኝነታችሁ የሻከረው በአንድ ወቅት በተፈጠረ ችግር ምክንያት ሳይሆን ከዚህ ቀደም ታስቡት የነበረውን ያህል ተመሳሳይ ፍላጎት እንደሌላችሁ እየተገነዘባችሁ በመምጣታችሁ ሊሆን ይችላል። እያደግህ ስትሄድ ለነገሮች ያለህ አመለካከት እንደሚለወጥ ሁሉ የጓደኛህም ፍላጎት ሊለወጥ እንደሚችል አስታውስ። በአንተና በጓደኛህ መካከል ሰፊ ክፍተት እየተፈጠረ እንደሆነ ከተሰማህ ምን ማድረግ ትችላለህ?

ጓደኝነትን ማደስ የሚቻለው እንዴት ነው?

አንድ የምትወደው ልብስ ተቀዶብህ ያውቃል? ምን አደረግህ? ልብሱን ጣልከው ወይስ ጠገንከው? እርግጥ ነው፣ ይህ በአብዛኛው የተመካው ‘ልብሱ ምን ያህል ተቀዷል?’ እንዲሁም ‘ልብሱን ምን ያህል ትወደዋለህ?’ ለሚሉት ጥያቄዎች በምትሰጠው መልስ ላይ ነው። ልብሱን በጣም የምትወደው ከሆነ በሆነ መንገድ ልትጠግነው መሞከርህ አይቀርም። አብዛኛውን ጊዜ በጓደኛሞች መካከል ችግር ሲፈጠርም ተመሳሳይ ነገር ማድረግ ይቻላል። በአብዛኛው ይህ የተመካው በተፈጠረው ችግር ክብደትና ለግንኙነታችሁ በምትሰጠው ቦታ ላይ ነው። *

ለምሳሌ ያህል፣ ጓደኛህ ደግነት የጎደለው ነገር በመናገር ወይም በማድረግ ጎድቶህ ከሆነ በመዝሙር 4:4 ላይ የሚገኘውን ምክር ተግባራዊ በማድረግ የተፈጠረውን ችግር ማለፍ ትችል ይሆናል፤ ጥቅሱ “በዐልጋችሁም ላይ ሳላችሁ፣ ልባችሁን መርምሩ፤ ጸጥም በሉ” ይላል። ስለዚህ ጓደኝነታችሁን አሽቀንጥረህ ከመጣልህ በፊት ነገሩን በጥሞና አስብበት። ጓደኛህ የጎዳህ ሆን ብሎ ነው? እርግጠኛ ካልሆንክ፣ ሆን ብሎ እንዳልሆነ ማሰቡ የተሻለ ነው። “ፍቅር የኃጢአትን ብዛት ይሸፍናል” የሚለውን ምክር ተግባራዊ ማድረጉ አብዛኛውን ጊዜ ጠቃሚ ሊሆን ይችላል።​—1 ጴጥሮስ 4:8

በሌላ በኩል ደግሞ ለችግሩ መፈጠር አንተም አስተዋጽኦ አድርገህ እንደሆነ ራስህን መመርመር ትችላለህ። ለምሳሌ ያህል፣ አንድ ጓደኛህ ሚስጥርህን ስላወጣብህ አዝነሃል እንበል፤ ይሁንና መጀመሪያውኑም ቢሆን ሚስጥርህን መንገርህ ጥበብ የጎደለው እርምጃ ይሆን? ምናልባትም የነገርከው ነገር ሸክም ሆኖበት ሊሆን ይችላል። ልታስብበት የሚገባ ሌላም ነጥብ አለ፦ ብዙ የምታወራ ወይም የሞኝ ንግግር የምትናገር ከሆነ ሌሎች እንዲቀልዱብህ መንገድ የምትከፍተው ራስህ ልትሆን ትችላለህ። (ምሳሌ 15:2) በመሆኑም ‘ጓደኛዬ ይበልጥ እንዲያከብረኝ አንዳንድ ለውጦች ማድረግ ይኖርብኝ ይሆን?’ ብለህ ራስህን ጠይቅ።

“ስለተፈጠረው ነገር ብንነጋገር ደስ ይለኛል”

ይሁን እንጂ የተጎዳህበትን ነገር እንዲሁ ችላ ብለህ ማለፍ እንደማትችል ቢሰማህስ? በዚህ ጊዜ ጓደኛህን ማነጋገርህ የተሻለ ሊሆን ይችላል። ሆኖም ይህን የምታደርገው ተቆጥተህ ባለህበት ሰዓት መሆን የለበትም። መጽሐፍ ቅዱስ “ግልፍተኛ ሰው ጠብ ያነሣሣል፤ ታጋሽ ሰው ግን ጠብን ያበርዳል” ይላል። (ምሳሌ 15:18) ስለዚህ ሁኔታውን ለማስተካከል ከመሞከርህ በፊት ቁጣህ እስኪበርድልህ መቆየትህ የተሻለ ነው።

ጓደኛህን በምታነጋግርበት ጊዜ ዓላማህ “በክፉ ፋንታ ክፉ [መመለስ]” እንዳልሆነ አትዘንጋ። (ሮም 12:17) ዓላማህ ችግሩን መፍታትና ጓደኝነታችሁ እንደቀድሞው እንዲሆን ማድረግ ነው። (መዝሙር 34:14) ስለዚህ የተሰማህን ነገር ምንም ሳታድበሰብስ በግልጽ ተናገር። ለምሳሌ “እኔና አንተ ጓደኛሞች ከሆንን ቆይተናል። ጓደኝነታችንን ማጣት አልፈልግም፤ ስለተፈጠረው ነገር ብንነጋገር ደስ ይለኛል” ልትለው ትችላለህ። የችግሩን መንስኤ ማወቅ ከቻልክ ጓደኝነታችሁን ማደስ ያን ያህል አይከብድህም። ጓደኛህ ለመነጋገር ፈቃደኛ ባይሆንም እንኳ ሰላም ለመፍጠር ጥረት ስላደረግህ የሚቆረቁርህ ነገር አይኖርም።

በመጨረሻም በአንድ ነገር እርግጠኛ ሁን፦ “እርስ በርስ ከመጠፋፋት ወደኋላ የማይሉ ጓደኛሞች” እንዳሉ ሁሉ ‘ከወንድም ይበልጥ ቅርበት ያለው ጓደኛም አለ።’ (ምሳሌ 18:24 NW) እርግጥ ነው፣ በጣም በሚዋደዱ ጓደኛሞች መካከልም እንኳ አንዳንድ ጊዜ አለመግባባት ሊፈጠር ይችላል። እንዲህ ያለ ሁኔታ በሚፈጠርበት ጊዜ ጓደኝነታችሁን ለማደስ የተቻለህን ሁሉ አድርግ። በእርግጥም፣ አለመግባባቶችን ለመፍታት ፈቃደኛ መሆንህ እየጎለመስክ መሆኑን የሚጠቁም ነው።

ተጨማሪ ሐሳብ ለማግኘት የዚህን መጽሐፍ ጥራዝ 1 ምዕራፍ 8 ተመልከት

በሚቀጥለው ምዕራፍ

አንዳንድ እኩዮችህ በኢንተርኔት አማካኝነት ከሌሎች ጋር በማውራት ረጅም ሰዓት ያሳልፋሉ። ወጣቶች በዚህ መልክ ማውራት የሚመርጡት ለምንድን ነው?

[የግርጌ ማስታወሻ]

^ አን.15 አንዳንድ ሰዎችን የቅርብ ጓደኞች አለማድረጉ የተሻለ ሊሆን ይችላል። በተለይ ደግሞ ምግባራቸው ከአንድ ክርስቲያን የማይጠበቅ ዓይነት ከሆነ እንዲህ ማድረጉ የተገባ ነው።​—1 ቆሮንቶስ 5:11፤ 15:33

ቁልፍ ጥቅስ

“ከሰው ሁሉ ጋር በሰላም ለመኖር በእናንተ በኩል የተቻላችሁን ሁሉ አድርጉ።”​—ሮም 12:18

ጠቃሚ ምክር

ቸኩለህ አንድ መደምደሚያ ላይ ከመድረስህ በፊት ጓደኛህ ሐሳቡን እንዲገልጽ ዕድል ስጠው።​—ምሳሌ 18:13

ይህን ታውቅ ነበር?

ጥሩ ጓደኝነት ያላቸው ሰዎች ሁልጊዜ አብረው መሆን እንዳለባቸው አይሰማቸውም፤ ከዚህ ይልቅ አንዳቸው ለሌላው ነፃነት ይሰጣሉ። (ምሳሌ 25:17) በሌላ በኩል ግን አንድ ሰው፣ ጓደኛውን መፈናፈኛ በማሳጣት ሙሉ ጊዜውንና ትኩረቱን እንዲሰጠው የሚፈልግ ከሆነ ጓደኝነታቸው በአጭሩ ሊቀጭ ይችላል።

ላደርጋቸው ያሰብኳቸው ነገሮች

አንድ ጓደኛዬ ቢጎዳኝና ላነጋግረው እንደሚገባ ቢሰማኝ ንግግሬን እንዲህ ብዬ መጀመር እችላለሁ፦ ․․․․․

ጓደኛዬ ያደረገው ነገር ቢያበሳጨኝም እንዲህ በማድረግ ሰላም ለመፍጠር እጥራለሁ፦ ․․․․․

ከዚህ ርዕሰ ጉዳይ ጋር በተያያዘ ወላጆቼን ልጠይቃቸው የምፈልገው ነገር ․․․․․

ምን ይመስልሃል?

አንዳንድ ጊዜ ጓደኛሞች ቀስ በቀስ እየተራራቁ የሚሄዱት ለምንድን ነው?

ጓደኛህን ማነጋገር ሳያስፈልግህ በፍቅር ልታልፋቸው የምትችላቸው በደሎች የትኞቹ ናቸው? የጎዳህን ጓደኛህን ማነጋገር የሚኖርብህ በደሉ ምን ዓይነት ሲሆን ነው?

አንድ ጓደኛህ ቢጎዳህ ከተፈጠረው ሁኔታ ምን ጠቃሚ ትምህርት ማግኘት ትችላለህ?

ጓደኛህ በሚያደርገው ነገር የመጎዳትህን አጋጣሚ ለመቀነስ ምን ቅድመ ጥንቃቄዎች ማድረግ ትችላለህ?

[በገጽ 95 ላይ የሚገኝ የተቀነጨበ ሐሳብ]

እንደገና አጋጣሚውን ማግኘት ብችል ኖሮ ጓደኝነታችን ምንም እንከን የሌለው እንዲሆን አልጠብቅም ነበር። የበለጠ አዳምጠው ነበር፤ እንዲሁም በስህተቶቹ ላይ ከማተኮር ይልቅ እደግፈው ነበር። ጓደኝነት የተሳካ እንዲሆን የሚያደርገው የሚገጥሙንን ፈተናዎችና ችግሮች መወጣት መቻል መሆኑን አሁን ተገንዝቤያለሁ።”​—ኪነን

[በገጽ 94 ላይ የሚገኝ ሥዕል]

በጓደኛሞች መካከል የሚፈጠር አለመግባባት በልብስ ላይ ካለ ቀዳዳ ጋር ሊመሳሰል ይችላል፤ ሆኖም የተቀደደ ልብስ እንደሚጠገን ሁሉ ጓደኝነትንም ማደስ ይቻላል