ምዕራፍ 55
የኢየሱስ ንግግር ብዙዎችን አስደነገጠ
-
ሥጋውን መብላትና ደሙን መጠጣት
-
ብዙዎች በመሰናከላቸው እሱን መከተል አቆሙ
ኢየሱስ ከሰማይ የወረደው እውነተኛው ምግብ እሱ መሆኑን በቅፍርናሆም በሚገኝ አንድ ምኩራብ ውስጥ እያስተማረ ነው። በዚህ ወቅት የተናገረው ነገር፣ ዳቦና ዓሣ ከመገባቸውና ከገሊላ ባሕር ምሥራቃዊ ክፍል ተመልሰው ከመጡት ሰዎች ጋር ሲወያይ ከሰጠው ሐሳብ የቀጠለ እንደሆነ ከሁኔታው መረዳት ይቻላል።
ኢየሱስ ንግግሩን በመቀጠል “አባቶቻችሁ በምድረ በዳ መና በሉ፤ ይሁን እንጂ ሞቱ” አለ። ከዚህ በተቃራኒ ግን ስለ ራሱ ሲናገር እንዲህ አለ፦ “ከሰማይ የወረደው ሕያው ምግብ እኔ ነኝ። ከዚህ ምግብ የሚበላ ሁሉ ለዘላለም ይኖራል፤ ምግቡ ደግሞ ለዓለም ሕይወት ስል የምሰጠው ሥጋዬ ነው።”—ዮሐንስ 6:48-51
በ30 ዓ.ም. የጸደይ ወቅት ላይ ኢየሱስ፣ አምላክ ዓለምን እጅግ ከመውደዱ የተነሳ ልጁን አዳኝ አድርጎ እንደሰጠ ለኒቆዲሞስ ነግሮታል። አሁን ደግሞ ሥጋውን የመብላትን ይኸውም እሱ በሚያቀርበው መሥዋዕት ላይ እምነት የማሳደርን አስፈላጊነት ጎላ አድርጎ ገለጸ። የዘላለም ሕይወት ማግኘት የሚቻለው ይህን በማድረግ ነው።
ይሁን እንጂ ሕዝቡ ኢየሱስ የተናገረው ሐሳብ አልተዋጠላቸውም። “ይህ ሰው እንዴት ሥጋውን እንድንበላ ሊሰጠን ይችላል?” የሚል ጥያቄ አቀረቡ። (ዮሐንስ 6:52) ኢየሱስ፣ እየነገራቸው ያለው ነገር ቃል በቃል ሳይሆን ምሳሌያዊ እንደሆነ እንዲገነዘቡ ፈልጓል። ቀጥሎ የተናገረው ነገር ይህን ያሳያል።
“የሰውን ልጅ ሥጋ ካልበላችሁና ደሙን ካልጠጣችሁ በራሳችሁ ሕይወት የላችሁም። ሥጋዬን የሚበላና ደሜን የሚጠጣ ሁሉ የዘላለም ሕይወት አለው፤ . . . ሥጋዬ እውነተኛ ምግብ፣ ደሜም እውነተኛ መጠጥ ነውና። ሥጋዬን የሚበላና ደሜን የሚጠጣ ሁሉ ከእኔ ጋር አንድነት ይኖረዋል።”—ዮሐንስ 6:53-56
አይሁዳውያን አድማጮቹ ይህ ምን ያህል ሊዘገንናቸው እንደሚችል አስበው! ኢየሱስ፣ ቃል በቃል የሰውን ሥጋ እንዲበሉ ወይም ደም መብላትን የሚከለክለውን የአምላክ ሕግ እንዲጥሱ እየጠየቃቸው እንደሆነ ተሰምቷቸው ሊሆን ይችላል። (ዘፍጥረት 9:4፤ ዘሌዋውያን 17:10, 11) ኢየሱስ ግን ቃል በቃል ሥጋን ስለ መብላት ወይም ደምን ስለ መጠጣት እየተናገረ አይደለም። ከዚህ ይልቅ የዘላለም ሕይወት ማግኘት የሚፈልጉ ሁሉ ኢየሱስ ፍጹም ሰብዓዊ አካሉን አሳልፎ በመስጠትና ደሙን በማፍሰስ በሚያቀርበው መሥዋዕት ማመን እንዳለባቸው መግለጹ ነው። የሚገርመው ግን ከደቀ መዛሙርቱ መካከል ብዙዎቹ እንኳ ይህን ትምህርት አልተረዱም። እንዲያውም አንዳንዶች “ይህ የሚሰቀጥጥ ንግግር ነው፤ ማን ሊሰማው ይችላል?” አሉ።—ዮሐንስ 6:60
ኢየሱስ ከደቀ መዛሙርቱ መካከል አንዳንዶቹ እያጉረመረሙ መሆኑን ስለተገነዘበ እንዲህ አላቸው፦ “ይህ ያሰናክላችኋል? ታዲያ የሰው ልጅ ቀድሞ ወደነበረበት ሲወጣ ብታዩ ምን ልትሉ ነው? . . . እኔ የነገርኳችሁ ቃል መንፈስም ሕይወትም ነው። ነገር ግን ከእናንተ መካከል የማያምኑ አንዳንዶች አሉ።” ይህን ሲል በርካታ ደቀ መዛሙርት ትተውት ሄዱ፤ ከዚያን ጊዜ ጀምሮም እሱን መከተላቸውን አቆሙ።—ዮሐንስ 6:61-64
በመሆኑም ኢየሱስ 12ቱን ሐዋርያት “እናንተም መሄድ ትፈልጋላችሁ?” በማለት ጠየቃቸው። ጴጥሮስም እንዲህ ሲል መለሰለት፦ “ጌታ ሆይ፣ ወደ ማን እንሄዳለን? አንተ የዘላለም ሕይወት ቃል አለህ። አንተ የአምላክ ቅዱስ አገልጋይ እንደሆንክ አምነናል፤ ደግሞም አውቀናል።” (ዮሐንስ 6:67-69) ጴጥሮስና ሌሎቹ ሐዋርያት፣ ኢየሱስ በዚህ ወቅት የሰጠው ትምህርት ሙሉ በሙሉ ባይገባቸውም እንኳ በታማኝነት ረገድ ግሩም ምሳሌ ትተዋል!
ኢየሱስ፣ ጴጥሮስ በሰጠው መልስ ቢደሰትም እንዲህ አለ፦ “አሥራ ሁለታችሁንም የመረጥኳችሁ እኔ አይደለሁም? ይሁንና ከመካከላችሁ አንዱ ስም አጥፊ ነው።” (ዮሐንስ 6:70) ኢየሱስ ስለ አስቆሮቱ ይሁዳ መናገሩ ነው። በዚህ ጊዜ ኢየሱስ፣ ይሁዳ የተሳሳተ አካሄድ መከተል እንደጀመረ አስተውሎ መሆን አለበት።
ያም ቢሆን ጴጥሮስና ሌሎቹ ሐዋርያት፣ እሱን ከመከተልና በሚያከናውነው ሕይወት አድን ሥራ ከመካፈል ወደኋላ አለማለታቸው ኢየሱስን እንዳስደሰተው ጥርጥር የለውም።