ስለ መጽሐፍ ቅዱስ ምን አመለካከት አለህ?
መጽሐፍ ቅዱስን የምትመለከተው . . .
-
የሰው ሐሳብ እንደሆነ አድርገህ ነው?
-
አፈ ታሪክ ወይም ተረት እንደሆነ አድርገህ ነው?
-
ወይስ የአምላክ ቃል እንደሆነ አድርገህ ነው?
መጽሐፍ ቅዱስ ምን ይላል?
“ቅዱሳን መጻሕፍት ሁሉ በአምላክ መንፈስ መሪነት የተጻፉ ናቸው።”—2 ጢሞቴዎስ 3:16 አዲስ ዓለም ትርጉም
ይህን ማወቅህ ለአንተ ምን ጥቅም አለው?
በሕይወትህ ውስጥ ለሚፈጠሩ አሳሳቢ ጥያቄዎች አርኪ መልስ ታገኛለህ።—ምሳሌ 2:1-5
የዕለት ተዕለት ሕይወትህን ለመምራት የሚያስችል አስተማማኝ መመሪያ ታገኝበታለህ።—መዝሙር 119:105
አስተማማኝ የሆነ የወደፊት ተስፋ ይኖርሃል።—ሮም 15:4
መጽሐፍ ቅዱስ በሚናገረው ነገር ላይ እምነት መጣል እንችላለን?
አዎ፣ ቢያንስ ሦስት ምክንያቶችን መጥቀስ ይቻላል፦
-
እርስ በርሱ ይስማማል። መጽሐፍ ቅዱስ የተጻፈው ከ1,600 ዓመታት በላይ በሚሸፍን ጊዜ ውስጥ ሲሆን የጻፉትም 40 የሚያህሉ ሰዎች ናቸው። አብዛኞቹ የኖሩት በተለያየ ዘመን ስለሆነ ተገናኝተው እንኳ አያውቁም። ያም ሆኖ ሙሉው መጽሐፍ እርስ በርሱ ይስማማል፤ የሚያጠነጥነውም በአንድ ጭብጥ ዙሪያ ነው!
-
ጸሐፊዎቹ በሐቀኝነት ዘግበዋል። አብዛኛውን ጊዜ የዓለም ታሪክ ጸሐፊዎች የሕዝባቸውን ሽንፈት ለመሸፋፈን ይሞክራሉ። በአንጻሩ ግን የመጽሐፍ ቅዱስ ጸሐፊዎች የራሳቸውንም ሆነ የሕዝባቸውን ስህተቶች በሐቀኝነት ዘግበዋል።—2 ዜና መዋዕል 36:15, 16፤ መዝሙር 51:1-4
-
አስተማማኝ ትንቢቶችን ይዟል። መጽሐፍ ቅዱስ የጥንቷ ባቢሎን እንደምትጠፋ 200 ዓመታት ገደማ ቀደም ብሎ ትንቢት ተናግሮ ነበር። (ኢሳይያስ 13:17-22) ይህ ትንቢት ባቢሎን የምትጠፋበትን መንገድ ብቻ ሳይሆን ድል የሚያደርጋት ንጉሥ ማን እንደሚሆን በስም ጭምር ጠቅሷል!—ኢሳይያስ 45:1-3
ሌሎች በርካታ የመጽሐፍ ቅዱስ ትንቢቶችም አንድም ሳይቀር በዝርዝር ተፈጽመዋል። ታዲያ ይህ አምላክ ካስጻፈው መጽሐፍ የሚጠበቅ አይደለም?—2 ጴጥሮስ 1:21
ምን ይመስልሃል?
የአምላክ ቃል ሕይወትህን ሊያሻሽልልህ የሚችለው እንዴት ነው?
መጽሐፍ ቅዱስ ለዚህ ጥያቄ የሚሰጠው መልስ ኢሳይያስ 48:17, 18 እና 2 ጢሞቴዎስ 3:16, 17 ላይ ይገኛል።